ቪየትናም በተገላቢጦሽ (የሩሲያና አሜሪካ ቦታ መለዋወጥ)
ሐሙስ፣ መጋቢት ፳ ፪ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. (03/30/2022)
አንዱ ዓለም ተፈራ፤
ታሪክ ራሷን ደገመች የሚሉ አሉ። ይህ እንግዲህ በተለያዩ የተራራቁ ወቅቶች፤ ተመሳሳይ የታሪክ ኩነቶች ሲመዘገቡ ያዩ ታዛቢዎች፤ ሁኔታውን የሚገልጡበት መንገድ ነው። እብሪተኞች ከታሪክ መማር ቀርቶ፤ ከፊታቸውን ያለውን የገጠጠ ሀቅ አይቀበሉም። በጭንቅላታቸው የሚሽከረከረውና ገዥው ጉዳይ፤ የሚፈልጉትን ማድረግ ብቻ ነው። ባሳለፍነው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ላይ፤ አሜሪካ፤ ቪየትናማዊያንን አንበርክኬ፣ እኔ የፈለግሁትንና ለኔ የሚታዘዙ መሪዎችን በመንግሥት ሥልጣን ላይ፤ ሳይጎን አስቀምጣለሁ ብላ፣ በአስርተ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወታደሮቿን ሕይወት አስረክባ፣ ቀንዷን እንደተመታች ላም እየተሸማቀቀች፤ እጆቿን ሰብስባ ወደ ቤቷ ተመልሳለች። አሁን ደግሞ የሩሲያው መሪ ፑትን፤ በዩክሬን ላይ የፈለግሁትን መንግሥት አቋቁማለሁ ብሎ፣ ዩክሬንያዊያንን እንደሳር በማጨድ፣ ከተሞችን ዶጋ አመድ በማድረግ፣ የራሱን ወጣት ወታደሮች በማያውቁት ጦርነት በመማገድ፣ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደ ገደል በመክተት፣ እንደ አሜሪካ ጅራቱን በግሮቹ ሥር ሰንቆ ወደ ቤቱ ሊመለስ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል። የዚህን ሁኔታ ተመሳሳይነት ማሳየት ነው የዚህ ጽሑፍ ተልዕኮ።
የሃያኛውን ምዕተ ዓመት ገላጭ ከሆኑት ከፍተኛ ጉዳዮች መካከል፤ የሶሺያሊስት መንግሥታት መፈጠር፣ በአስራዎቹ የተከሰተው የመጀመሪያው የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ጦርነት፣ ያው ተደግሞ በሰላሳዎቹና አርባዎቹ በዓለም ዙሪያ የተደረገው፤ የናዚ፣ የፋሺስትና የጃፓን ወረራና ያንን ሊመክቱ የተነሱት የኃያላን መንግሥታት ጦርነት፣ የአብዛኞች ቅኝ ግዛት አገሮች ነፃነት ማግኘትና የአሜሪካ በቪየትናም ተሸንፎ መውጣት ይገኙበታል። በርግጥ በየአገሩ የየራሳቸውን የግል ሁኔታ በመመልከት፤ ከፍተኛ በማለት ሌሎችን ሊዘረዝሩ ይችላሉ። ለሴቶች፤ የሴቶች ትግል ከፍተኛ ቦታ ይኖረዋል። ለአፍሪካዊ አሜሪካዊያን፤ የነፃነት ትግላቸው ከሁሉም ይበልጥባቸዋል። ለኢትዮጵያዊያን የፋሽስቱን ወረራና የአርበኞቻችንን ተጋድሎ የሚበልጥ የትም አይገኝም። እዚህ ላይ እኔ ለማስፈር የፈለግሁት፤ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ፤ ለዓለም ሁሉ ጉልህ የሆነውን ነው።
አሜሪካ፤ በወቅቱ በነበረው የራስን የተቀባይነት ክልል የማስፋፋት ሩጫ፣ ለራሷ ጉልቻ ሆኖ የሚያገለግል መሪ በቪየትናም ጫንቃ ላይ በመጫን፣ የቪየትናም ሕዝብን ፍላጎትም ሆነ ተጨባጭ እውነታ ወደ ጎን ገፍታ ወርውራ፣ አዲስ መጥ ለሆነው የሶቪየትና የቻይና የኮሚንዝም ፍልስፍና ተቀባይነት አጥር ለማበጀት፣ ያለ የሌለ ጉልበቷን ተጠቅማ፤ ቪየትናም ላይ በጦርነት ተዘፈቀች። የቪየትናም ሕዝብ አሜሪካንን ድረሺልኝ አላለም! የአሜሪካ ጥቅም በቪየትናም ጉዳት አልደረሰበትም! እናም በገዛ አገራቸው፣ በጎጇቸውና በንብረታቸው፣ በርሻቸውና በዱራቸው የመጣባቸውን ወራሪ፤ ቪየትናማዊያን ቆርጠው ተዋጉ። ዱሩን ቤቴ ብለው፣ በገደሉና በተራራው ውስጥ እየተሽሎከለኩ፣ ረሃብና ጥማትን እያስተናገዱ፣ ለነፃነታቸው እስከመጨረሻው ታገሉ። በርግጥ ለአሜሪካ ቡችላ ሆነው ያገለገሉ፤ ለሆዳቸው ያደሩና ሥልጣን ለመያዝ የጓጉ ከአሜሪካኖች ጎን አብረው ተሰልፈው ነበር። ቆርጠው ለተዋጉት ቪየትናማዊያን፤ ከጀርባቸው ቻይናና ሶቪየት መሳሪያ በማቀበል ረድተዋቸዋል። የአሜሪካ የጦር መሳሪያ የመጉዳት ምጥቀቱና ጥራቱ ከመቼውም በላይ አደገ። ያም ሆኖ፤ ቪየትናማዊያን የሞት የሽረት ተጋድሎ በማድረግ፤ በአቸናፊነት ወጡ። የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ልቀት፤ ዋጋው ብዙ አልገፋም። በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው የአሜሪካ ወታደር፤ ለምን እንደሚዋጋ አያውቅም ነበር። ቪየትናማዊያን ግን ማወቅ ብቻ አይደለም፤ ቆርጠው ለትግሉ ሕይወታቸውን ለመሥጠት አላቅማሙም ነበር። አሜሪካዊያን ወታደሮች የሚዋጓቸውን እንኳን አያውቁም ነበር። ቪየትናማዊያን ግን ግጥም አድርገው ያውቁ ነበር። ማን እንደሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ የት እንደሚውሉና እንደሚያደሩ ሁሉ ያውቁ ነበር። ለምን እንደሚዋጉና እነሱ ሲወድቁ ተተኪ እንዳላቸው ሁሉ ያውቁ ነበር። በመጨረሻም፤ የአሜሪካ ሕዝብ ሀቁን ተረድቶ፤ የኒክሰንን መንግሥት ዘወር በል አለው። ያ የሆነው በኛ አቆጣጠር በ፲ ፱ ፷ ፮ ዓ. ም. ነበር። ያው ዓመት ለኛ ሌላ ትርጉም አለው። ሃምሳ ዓመት ሊሞላው ሁለት ፍሬ ቀርቶታል።
ዘለን ወደዛሬ ስንመለስ፤ የሩሲያ መሪ ፑትንን ዩክሬን ላይ እናገኘዋለን። ዩክሬን ውስጥ ሩሲያ ምን አስገባት? የዩክሬን ሕዝብ ጋብዟት ነው? ዩክሬን ተወርሬያለሁና ድረሱልኝ የሚል ጥሪ ልኮላት ነው? አይደለም። ሩሲያ ዩክሬን የገባችው፤ ልክ አሜሪካ በቪየትናም እንዳደረገችው ሁሉ፤ ለራሷ መሪ እብሪትና ድንፋታ፣ ለራሷ ተቀባይነት ሰፈር እንዳይጠብ በማሰብ ስትል ብቻ ነው። “የኮሚንዝም መስፋፋት እኔን ያሰጋኛል!” በሚል ሂሳብ አሜሪካ ቪየትናም እንደገባች ሁሉ፤ “የኔቶ መስፋፋት እኔን ያሰጋኛል!” ያለው የፑትን መንግሥት፤ ዩክሬን ገባ። በስውር አሜሪካ ስትረዳው የነበረችው የፈረንሳይ መንግሥት፤ ዲየን ቢየን ፉ ላይ መጋቢት ፲ ፱ ፵ ፮ ዓመተ ምህረት አፈር በልታ አንገቷን መድፋቷና መውጣቷ፤ “አሳስቦኛል!” ብላ ዘላ የገባችው አሜሪካ፤ እዚያ ለመግባቷና ለመዋጋቷ ብዙ ምክንያቶች ደርድራለች። ውሎ አድሮ ግን የአሜሪካ ሕዝብ አልተቀበለውም። አንድ ጊዜ፤ “በዩክሬን የሚኖሩ የሩሲያ ዝርያ ያላቸው ዩክሬናዊያን ተበድለዋል!” ሌላ ጊዜ፤ “የዩክሬን መንግሥት የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ መንግሥት ነው!” ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ “የዩክሬን መንግሥት መሪዎች ናዚዎች ናቸው!” እና የመሳሰሉትን የምክንያት ድሪቶዎች የፑትን መንግሥት ደርድሯል። እንደ ቪየትናማዊያን ሁሉ፤ ዩክሬናዊያን ለአገራቸው፣ ለንብረታቸውና ለኑሯቸው እየተዋደቁ ነው። ከተሞቻቸው ዶጋ አመድ ሆነዋል። በረሃብና በጥማት መንገድ ቤቶቻቸው ተዘግቶባቸው እየተንገላቱ ነው። ስደትም የማይገኝ ብርቅ ሆኖ፤ ታግተው በያሉበት ወድቀዋል። አዎ! ኔቶ ዩክሬናዊያንን እየረዳ ነው። ወሳኙ ግን የዩክሬናዊያን ተጋድሎ ነው።
ያኔ አሜሪካ፣ ዛሬ ደግሞ ሩሲያ እብሪተኛ መሪ ነው ያሏቸው። ኒክሰንና ፑትን ተመሳሳይ ናቸው፤ ኒክሰን ወረራውን ባይጀምረውም! ቪየትናማዊያንን ከመጤፍ ባለመቁጠር በገፍ ፈጅቷቸዋል። በናፓልም ቦምብ እርሻዎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና ዱሮቻቸውን አጋይቷል። ዛሬ ፑትን እንደሚያደርገው ሁሉ፤ የራሱን ፍላጎት ብቻ ነበር የገፋው። ቪየትናማዊያን የሚፈልጉት አልተቆጠረላቸውም። የአሜሪካ መሪዎች ፍላጎት ብቻ ነበርና የስሌቱ ሁሉ ማሽከርከሪያ! ዛሬም የፑትንና የኔቶ ፍላጎት ብቻ ሆኗል የፖለቲካ ስሌቱ ሁሉ ማሽከርከሪያ። መሪዎችና ፍላጎታቸው፤ ዕድሜው የአጭር ጊዜ ማኅተም አለበት። ጊዜ ይሽራቸዋል። አገራትና የሕዝብ ስብስብ ግን፤ ዘመናትን የሚሻገር ረዥም ዕድሜ ነው ያለው። መሪዎችና ፍላጎታቸውን በሚመለከት፤ ማሳያ የሆነ ላቅርብላችሁ። የኒክሰን ቀጥተኛ ወራሽ የሆነው ዶናልድ ትራምፕ፤ የግል ሥልጣኑን ብቻ በሚመለከት፤ በዛሬው ዕለት ድጋፉን ለፑትን በመወርወር፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከፑትን ጋር በተፋጠጡበት ወቅት፤ በባይደን ላይ ዘመቻውን አጠናክሯል። ትራምፕ፤ ግብፅ ኢትዮጵያ ላይ ቦምብ እንድትጥል የገፋ መሪ ነው። ባሁኑ ሰዓት፤ ኢትዮጵያዊያን ለአሜሪካ ያለን ጥላቻ፤ ከፍ ያለ ነው። ይሄ ግን፤ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ሩሲያ የምታደርገውን ወረራ እንድንደግፍ ሊያደርገን አይገባም።
አሜሪካ ቪየትናምን በወረረችበት ወቅት የነበርን ሁሉ፤ ቅኝታችን ወይ በሶሺያሊስት ወገን አለያም በአሜሪካ ፍላጎት ዙሪያ ብቻ የተወጠረ ነበር። ዛሬም የምንመለከተው፤ አንዱ ወገን በአሜሪካና ኔቶ ጥላቻ የተበረዘ፤ ሌላው ደግሞ በሩሲያ ጥላቻ የተበከለ ሆኗል። በመካከል ድሮ የቪየትናምን ሕዝብ፣ ዛሬ ደግሞ የዩክሬንን ሕዝብ ፍላጎትና ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ቦታ የሠጠው የለም። ለምን የሁለት ሰፈሮች አመለካከት ብቻ እንደነገሠ ማወቁ፤ አስቸጋሪ አይደለም። የዓለምን መንግሥታት ግንኙነት የገዛው፤ የጉልበተኞች የበላይነት ነውና! ታዲያ ቀደምቶቻችን እንዳሉት፤ ዝሆኖች ሲታገሉ ሳሩ ይደቃል ነው። ሀቁ፤ ዴሞክራሲን ሁሉ የሚተረጉመው፤ ለራሱ በሚጠቅም መንገድ ብቻ መሆኑ ነው። ድሮም ግሪኮች ዴሞክራሲ ሲሉ፤ በሥራቸው የነበሩትን ሌሎች ትተው፤ ለራሳቸው መሪዎችና ወገኖች ብቻ ነበር። ያኔ ከዴሞክራሲው ውጪ የሆኑ ሌሎች በክልሉ ነዋሪ የሆኑ እንደነበሩ ሁሉ፤ ዛሬም የጉልበተኛ አገሮች ፍላጎትና ጥቅም ብቻ ገዥ ሆኖ፤ የሌሎች አገሮች ፍላጎትና ጥቅም ተደቁሶ ነው፤ የ “ዴሞክራሲ!” ትርጉምና ሂደት! ለሩሲያ መሪ ዴሞክራሲ! ለአሜሪካ መሪዎች ዴሞክራሲ! ለቪያትናም ዕልቂት! ለዩክሬን ዕልቂት! ይሄ ነው የየዘመናችን የገዥዎች ዘፈን!
በነገራችን ላይ ይሄ ዜማ ከሞላ ጎደል ሁለንተናዊነትን የተቀባ ይመስላል። መቼም ሄደን ሄደን ይሄንን የፖለቲካ ግንዛቤያችንን ከአገራችን የፖለቲካ ሀቅ ጋር ማገናዘባችን አይቀሬ ነው። በኛ አገር ትናንት፤ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ይሄ ነበር ገዥ የፖለቲካ ስሌቱ። “እኔ ጉልበተኛ ነኝ! እኔ ገዥ መንግሥት ነኝ! እኔ የፈለግሁት ብቻ ይሆናል! ታሪክን በፈለግሁት መንገድ እጽፈዋለሁ!” እና “ሁሉም ወደደም ጠላም የምለውን ይቀበላታል!” ነበር። በዚህ ቀመር አገራችንን ለሃያ ሰባት ዓመታት ነግሦባታል። ዛሬ ደግሞ ባለተረኞች ሥልጣኑን ተቆጣጥረው፤ በዚሁ ሂሳብ እየገፉበት ነው። ይሄንን ተገንዝቦ መፍትሄ ለማግኘት፤ በራስ ጥቅም ከመታሰር ውጪ ሆኖ ማሰብን ይጠይቃል! የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበናል ከምንለው መካከል፤ ስንቶቻችን በዚህ እንገዛለን! ስንቶቻችን ከራሳችን በላይ አገርንና ወገንን እናስቀድማለን! በዩክሬን ደሴት የነበረ ወታደር፤ ከሩሲያ ወራሪ የወታደር አዛዥ ለተወረወረለት፤ “እጅህን ሥጥ!” ትዕዛዝ የሠጠው መልስ፤ ይሄንን ከራስ በላይ ወገንን እና አገርን ማስቀደምን ያስገነዝባል። ተወጥሮ በተያዘበት በዚያች ወቅት፣ ማምለጫ በሌለውና ዙሪያውን በተከበበበት ደሴት፤ በኔ አገርኛ ቋንቋ፤ “ሂድና ራስክህን ላስ!” ነው ያለው። ስንቶቻችን ይሄንን ለማለት ቆራጥነቱ አለን!