>

ጦርነትና የዳቦ ዋጋ! (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

ጦርነትና የዳቦ ዋጋ!

ደረጀ መላኩ  ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

እንደ መግቢያ

በእኔ እምነት ድህነት ቤቱን የሰራባቸው አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ እና ወጣቶቿ አለም ሰላምና የተረጋጋች ስትሆን ተቃሚዎች ናቸው፡፡ በአንድ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ተከባብሮ የመኖር እሳቤ ሲያዳብሩ፣ በአለም ላይ ያሉ ሀገራት በጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ ግንኙነት ሲኖራቸው፣ተከባብረው ሲኖሩ ዘላቂ የልማት እድገት እውን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በድህነት እና ችጋር የሚታወቁት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በሰላም እጦት፣በአለመረጋጋት ምክንያት ፍዳቸውን ይቆጥራሉ፡፡ ለአብነት ያህል በከተማ ከሚኖረው ኢትዮጵዊ ወጣት መሃከል ስራ ፈት ወይም እድሜው ለስራ ያልደረሰ ነው፡፡

ወጣቱ ትውልድ እድልን ለማግኘት ምን መስራት ይጠበቅበታል ?

በጣም አጭሩና ቀላሉ መልስ አብዛኞቹ ወጣቶች እትብታቸው የተቀበረበትን ሀገር ጥለው እግራቸው ወደ መራቸው ይሰደዳሉ የሚለው ነው፡፡ ወጣቶቹ የስራ እድል ለማግኘት እግራቸው ወደ መራቸው ይነጉዳሉ፡፡ በየአመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ወደ መሃከለኛው ምስራቅ እና ቀሪው የአፍሪካ ክፍል ይሰደዳሉ፡፡ በነገራችን ላይ የኮቪዲ በሽታ ወረርሽኝ የስደተኛውን ቁጥር የቀነሰው ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የስደተኛው ቁጥር እንዲቀንስ ከተፈለገ ሁነኛው መፍትሔ ተስማሚ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መፍትሔ እውን ማድረግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ማንበር ከሆነልን ወጣቶች በሀገራቸው ምርታማ እንዲሆኑ ማድረግ ያስችላል፡፡ 

የምግብና ሌሎች መሰረታዊ ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምር፣ ተራው የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ?

ለሁለቱም አጋጣሚዎች ሁነኛው ሰራሔመፍትሔ የምጣኔ ሀብቱን ማረጋጋት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ተባበረችው አሜሪካን የመሰሉ እጅግ የበለጸጉ ሀገራት  ህዝባቸው በኢኮኖሚ ግሽበት እንዳይደቆስ በየግዜው ድጎማ እንደሚሰጡ ( ገቢራዊ እንደሚያደርጉ) ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም ግን የተባበረችው አሜሪካ ኢትዮጵን ከአጎዋ ጥቅም መሰረዟ ለኢትዮጵያ ወጣት ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡ የአጎዋ የንግድ ሰንሰለት ወጣቶችን፣ ብዙ ልጆችን ያሳድጉ የነበሩ እናቶችን ኢኮኖሚ ገቢም ያሳጠረ ነበር፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በአጎዋ የምርት ሽያጭ ተጠቃሚ በነበሩ ፋብሪካዎች ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሴቶችና ወጣቶችም ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡

ለዚህም ነው እንደ እነ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራን የመሰሉ ስመጥር ኢትዮጵዊ ምሁራን የተባበረችው አሜሪካ ኢትዮጵያን ሊያናጋ የሚችለውን H.R. 6600 ውሳኔ ገቢራዊ እንዳይሆን መወትወታቸው፡፡ ይህ ገቢራዊ ከሆነ ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጎዳት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እየወረደ ያለውን መአት ያባብሰዋል እንጂ ለኢትዮጵያ የሚበጃት አይመስለኝም፡፡ እየከሸች ያለች ሀገርን እጅጉን ያሽመደምዳታል እንጂ ለኢትዮጵያ አንድነት አይጠቅምም፡፡ ይህ ውሳኔ ሰላምን ታሳቢ ያደረገ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ለሰላም መደፈርስ መሰረታዊ ምክንያት የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ ለመክላት የታሰበ ባለመሆኑ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ገቢራዊ ከሆነ ዴሞክራሲን ያቀጭጫል፡፡ ይህ ሲባል ግን በኢትዮጵያ ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ የመጣውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ችላ ማለቴ እንዳልሆነ አንባቢውን በአክብሮት አስታውሳለሁ፡፡ ጎሳን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ይፈጸማሉ፡፡ ይህ መራሩ እና አሳዛኙ የሀገራችን ሁነት ነው፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የውጭ ጉዳይ የኢኮኖሚ ቅጣት ፖሎሲ በዋነኝነት የሚጎዳው የድሆች ድሃ የሆነውን ሕዝብ ነው ብዬ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር ኤችአር 6600 ከጸደቀ የተባበረችው አሜሪካ ፖሊሲ አውጭዎች ካሰቡት በተቃራኒው የሚጎዳው ተራው ህዝብ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ (HR 6600 does the opposite)

በዚህ ምክንያት የተባበረችው አሜሪካ ኮንግረስ ኤችአር 6600 ወደ ህግ እንዳይለወጥ ማድረግ አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ እዚች ነጥብ ላይ ግን አንባቢውን ማስታወስ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር በኢትዮጵያ ምድር ዘገናኝ እና ጭካኔ የተሞለባት የሰብአዊ መብት አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች እንዳይከሰሱ ለመከላከል እንደሆነ አስታውሳለሁ፡፡ እነኚህ አረመኔዎች በፍትህ አደባባይ መጠየቅ አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ የእኔ ስጋት ኤችአር 6600 ህግ ሆኖ ከጸደቀ ድህነት ቤቱን የሰራበት የኢትዮጵያን ህዝብ እጅጉን ይጎዳል በሚል ጭንቀት እንደሆነ አንባቢውን በድጋሚ አስተውሳለሁ፡፡

እራሷን ከፍጹም አደጋ ለመከላከል በምትፍጨረጨረው ኢትዮጵያ ላይ የበለጠ ማእቀብ ለመጣል መጣደፍ ዳፋው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሚተርፍ ነው፡፡ ከኤች አር 6600 ጀርባ የዲፕሎማሲ ሴራ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህም ባሻግር የተባበረችው አሜሪካ የህውሃት አሸባሪ ቡድን የፈጸመውን የጦር ወንጀል፣የዘር ማጥፋት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል አኳያ ከመኮነን ወይም ከማውገዝ አኳያ ክሽፈት አጋጥሟታል፡፡ በምን መሰረታዊ ምክንያት ነው የተባበረችው አሜሪካ ለህውሃት አሸባሪ ቡድን የሚደማ ልብ የሚኖራት አስቲ ህሊና የፈጠረባችሁ ጠይቁ፡፡ በጓሮ በር ወያኔን በዲፕሎማሲ የሚደግፉት የአለሙ ጤና ድርጅት ፕሬዜዴንት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቢሆኑ የሚገርም አይደለም፡፡

የህውሃት አሸባሪ ቡድን የአፋርና አመሃራ ክልሎች ላይ ወረራ ፈጽሟል፣የግለሰቦችን ንብረት ዘርፏል፣በአማራና አፋር ክልሎች ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል፣በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ሰፊ ጉዳት አድርሷል፣ በሀለቱም ክልሎች የወደመው ንብረት በብዙ መቶ ቢሊዮን ብር የሚገመት እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ኦነግ ሸኔ ተብሎ የሚጠራው ቡድን ጎሳን መሰረት ያደረገ ጥቃት ስለመፈጸሙ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተዘገበ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ኦነግ ሸኔ ቡድን አባላት የአማራ ተወላጅ ወንድሞቻችን ላይ ሰፊ ጥቃት መክፈታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በየግዜው የተነገረ መራር ዜና ነው፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው በተባበረችው አሜሪካ የሚመራው የምእራቡ አለም በህውሃት አሸባሪ ቡድንና ኦነግ ሸኔ ቡድን አባላት የተፈጸሙ የሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎችን አውግዘው ፣ለፈጸሙት አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ደግሞ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለምን አለም አቀፍ ግዴታቸውን ሊወጡ አልቻሉም ? ለምንድን አውሮፓዊቷ ሀገር ዩክሬን ከጥቁር አፍሪካዊቷ ሀገር ከኢትዮጵያ በተለየ ሁኔታ ትኩረት የተሰጣት ? እስቲ በየአካባቢችሁ ተወያዩበት፡፡ ለማናቸውም ለአንዱ ሀገር በመወገን ሌላውን በማግለል ገቢራዊ የሚሆን የውጭ ዲፕሎማሲ በአለም አቀፉ ስርአት ላይ እምነትና በራስ መተማመንን የሚያዳክም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ተካሂዶ ነበረው የ15 ወራት ጦርነት የሚታወስ ነው፣ ዛሬም ጦርነቱ በአፋር ክልል ልዩ ሀይል እና በህውሃት አሸባሪ ወራሪ ሀይል መሃከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የሩሲያና ዩክሬን ተፋፍሞ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ሰሜን ኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የወረደውን መአት በተመለከተ እና በአውሮፓ ምድር ዩክሬን ላይ እየተጋጋመ በመጣው ጦርነት ላይ የተባበረችውን አሜሪካ የፖሊሲ አቋም ስንመረምር፣ወይም ስንቃኝ አለም ወረተኛ መሆኗን የምንረዳ መሰለኝ፡፡ እዚች ነጥብ ላይ የቀድሞውን የተባበረችው አሜሪካ  መንግስት ጸሃፊ ዶክተር ኪሲንጀር (former US Secretary of State Dr. Henry Kissinger )በዩክሬን ውድቀት ላይ የሰጠውን አስተያየት ማንሳት የሚገባ መሰለኝ፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መጋቢት 5 2022 በዝነኛው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ዘለግ ያለ ጽሁፍ ላይ እንደጠቀሱት ህዝባዊ ውይይት እንደሚያስፈልግ፣ አሜሪካ አራት ጦርነቶችን አይታለች፣ከአራቱ ጦርነቶች ውስጥ  እንደማያዋጣ ተገንዝባ እራሷን ከሶስቱ ጦርነቶች አግልላለች፣ጦርነትን እንጀምረዋለን እንጂ መቼ እንደምንጨርስ አናውቀውም ነበር ሲሉ የጻፉት፡፡ ኬሲንጀር የተናገሩት ስለ ሩሲያ አልነበረም ሶየው ያወሱት የሀገራቸውን አሜሪካ ፖሊሲ ነበር፡፡

ዩክሬን ወደ ምስራቅ ወይም ወደ ምእራብ ልታዘነብል ትችላለች፣ ሆኖም ግን ይሁንና ዩክሬን መኖር አለባት፡፡ የምስራቁ አለምም ሆነ፣የምእራቡ አለም ጦርነቱን ማጋጋም የለበትም፡፡ በተለይም የምእራቡ አለም የሶስተኛው አለም ጦርነት እንዲቀሰቀስ የካታሊስት መርህ መከተል የለበትም፡፡(cataclysmic ) የምእራባውያን የዜና አውታሮች እንደሚዘግቡት ሳይሆን ሩሲያውያንና ዩክሬናውያን ከሚያለያያቸው ይልቅ፣ የሚያቀራርባቸው ግንኙነቶች ይበዛሉ፡፡ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላም ቢሆን እንደ ጥሩ ጎረቤት አብረው መኖር አለባቸው፡፡

የሁለቱንም ሀገራት ታሪክ በቅጡ የሚረዳው ዶክተር ኬሲንጀር እላይ ከጠቀሰው ቁምነገር ባሻግር ሚዛናዊ አስተያየት መስጠት ይገባው ነበር፡፡ ምእራባውያን ሩሲያንና ዩክሬንን እንደውጭ ሀገር መቁጠር የለባቸውም፡፡ የሩሲያ ታሪክ የሚጀምረው ኪዬቭ ( Kievan-Rus.) መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ የሩሲያ ሃይማኖት መገኛም ኪዬቭ ናት፡፡ ዩክሬን ለብዙ ክፍለዘመናት የሩሲያ አንዷ አካል እንደነበረች ከታሪክ እንማራለን፡፡ ሁለቱም ሀገራት ለብዙ ክፍለዘመናት የቆየ የህዝብ መደበላለቅ ነበራቸው፡፡ በሃይማኖት፣ባህል፣ጋብቻ፣ቋንቋ መወራረስ አላቸው፡፡ ሩሲያ ነጻነቷን ለመጎናጸፍ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1709 በዩክሬን አፈር የፖልታቫ ጦርነት (the Battle of Poltava in 1709) አድርጋ እንደነበር መታወቅ አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ሩሲያ ሜድትራኒያን ባህር ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን በጥቁር ባህር ዳርቻ የምትገኘውን ክሬሚያን መቆጣጠሯ ስትራቴጂካዊ እንደሆነ አንባቢው መረዳት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አሌክሳነድር እና ጆሴፍ( Aleksandr Solzhenitsyn and Joseph Brodsky) ተብለው የሚታወቁ ታዋቂ ሰዎች ዩክሬን አንደ የሩሲያ ሉአላዊ ግዛት ናት በማለት ይከራከራሉ፡፡

በመጨረሻው ቀን ዩክሬናውያንና ሩሳዊያን ጥሩ ጎረቤት ሀገር ሆነው መኖራቸው አይቀርም፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙት የትግራይ ክልል ነዋሪዎችም ቢሆኑ በመጪው ግዜ( በመጨረሻው ቀን) በተመሳሳይ በጥሩ ጉርብትና መኖራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡

ዩክሬን ሉአላዊና ነጻ ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም ሩሲያ ይህን መራር ሁነት መቀበል አለባት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አንዳንድ ጫፍ የረገጡ ዩክሬናውያን ለምን ይሆን ዩክሬን የኔቶ አባል ሀገር እንድትሆን የፈለጉት ወይም የሚጠይቁት ? እዚህ ላይ የኬሲንጀር ፐሮፖዛል ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ዩክሬን በአውሮፓና ሩሲያ መሃከል እንደ ድልድይ ሆና የምታገለግል ሀገር መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሆኖም ግን የምእራባውያን ወይም ሩሲያ ሳተላይት ( አሻንጉሊት) መሆን የለባትም የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡

እዚህ ሀገር ቤት በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ ገለልተኛ ተመልካቾች እንደሚሰማቸው( እንደሚያምኑት) ከሆነ የተባበረችው አሜሪካ ሰልፏ ከህውሃት ቡድን ፊትአውራሪዎች ጋር እንደሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ቻይና በኢትዮጵያ የመዋእለ ንዋይ ግንባታ እና የኢንዱስተሪ ልማት ላይ ሁነኛ ሚና እየተጫወተች በመሆኗ ነበር ( ነው) ፡፡ ይህ ግን ምክንያታዊ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ የቻይና እና ኢትዮጵያ ግንኙነት የሚጀምረው አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ስልጣን ከመያዙ እረጅም አመታት በፊት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር ሊኖራት የሚገባው ግንኙነት በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ  ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዋነኛ እና የመጀመሪያ ሃላፊነት የራሷን ብሔራዊ ፍላጎት መከላከል ፣ዳርድንበሯን ማስጠበቅና ሉአላዊነቷን ማስጠበቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 2020 የወያኔ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ጦር ከሰበቀ ወዲህ በተባበረችው አሜሪካ አጋፋሪነት የሚመራው የምእራቡ አለም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኤችአር 6600 የተሰኘው የህግ እረቂቅ ገቢራዊ ከደረገ ደግሞ ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ የአደጋ ደረጃ ላይ ያደርሰዋል፡፡ ይህ ቀጪ የህግ እረቂቅ ገቢራዊ እንዲሆን ግፊት ማድረጉ ከ118 አመት በፊት የተጀመረውን የኢጥዮጵያና የተባበረችውን  የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ችላ ማለቱን ማሳያ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ሃያሳያን የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1950ዎቹ ላይ ኢትዮጵያን በይፋ ጎብኝተው የነበሩት  ያንዬ የተባበረችው አሜሪካ ምክትል ፕሬዜዴንት ሪቻርድ ኒክሰን (Richard Nixon ) የሚከተለውን ታሪካዊ ንግግር አሰምተው ነበር፡፡

‹‹ ኢትዮጵያ ታማኝና የረጅም ዘመን አጋር ሀገር ናት ›› ነበር ያሉት፡፡ ኤችአር 6600 ህግ ሆኖ የሚወጣ ከሆነ ይህን በጽኑ አለት ላይ ተጽፎ የነበረውን ለሁለቱም ሀገራት ብሔራዊ ፍላጎት ይጠቅም የነበረውን  ግንኙነት ችላ እንዳለ ይቆጠራል፡፡ 

 በእኔ ማእከላዊ አርግዩመንት (My core argument) መሰረት ከአንድ ሀገር ተጻራሪ የሆነ ቀጪ ማእቀብ ገቢራዊ መሆኑ ለኢትዮጵያ፣ ወይም ቀሪው የአፍሪካ ክፍል፣መሃከለኛው ምስራቅ፣ ወይም ለአውሮፓም ጭምር ሰላምን አያመጣም፡፡ለአለምም ሰላም ስጋት ነው፡፡ ከባድ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ማእቀብ በአንድ ሀገር ላይ መጣል ሰላምና መረጋጋትን  ችላ ያለ ውሳኔ ነው፡፡ ( በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ከዳቦ አቅም ለሁሉም ዜጎቻቸው በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዳገት ለሆነባቸው ደሃ ሀገራት መዘዙ ብዙ ነው፡፡) ኢትዮጵን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ውስጥ አሸባሪዎችና አክራሪዎች እንደፈለጉት መርመስመስ ያስችላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በዩክሬን  ለተከሰተው ግጭት የሰለጠነና ሰብአዊነት የተላበሰ ዘዴ ሁነኛ መፍትሔ ያስገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ግጭት፣በሩሲያና ዩክሬን መሃከል የተከፈተውን ጦርነት በማርገብ ሰላም እንዲሰፍን መርዳት ዋነኛ አላማ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከተሳነው የተባበሩት መንግስታት፣ የጸጥታው ጥበቃ ካውንስል ጭምር የሰብአዊነት ስሜታቸውን ያጣሉ፡፡ ያልተቋጨው ጦርነት ( በተለይም በአፋር ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት) የኢኮኖሚ ድቀትን ያስከትላል፣ ዜጎችንም ተስፋ ያስቆጥራል፡፡ለአብነት ያህል  አንድ ጡረታ የወጣ ኢትዮጵያዊ ወርሃዊ ደሞዝ ከ1000 እስከ 3000 ብር እንደሚደርስ ጥናት ያደረጉና አንቱ የተባሉ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የመሰሉ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ከጻፉት ጥናት እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ በዚች ደሞዝ ቤተሰቡ ለመመገብ ሲል የምግብ ማጣፈጫ ዘይት፣ጥራጥሬ ለመግዛት አትበቃውም፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡አንገትንም ያስደፋል፡፡ የሰለጠነው አለም ከምግብ አልፎ ሌሎች ፍላጎቱን ለማሟላት በሚጣደፍበት በዚህ ዘመን እኛ ካለፉት ስልሳ አመት ጀምሮ በየምክንያቱ የዳቦ ፍላጎት አልተሟላም ብለን ዛሬም ስንጽፍ በእውነቱ ህሊናን ያደማል፡፡ ፖለቲከኞቻችን አለም ወደ ታሪክ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ አሽቀንጥሮ የጣለውን፣አፋጀሺን የዘር ፖለቲካን ትታችሁ ህብረተሰቡ በአንድነት ገመድ አስተሳስራችሁ የአይምሮ፣መንፈሳዊ እና አካላዊ ሀይሉን በመጠቀም ወደ እድገት ጎዳና ትወስዱት ዘንድ በታሪክ ፊት ቆማችኋል፡፡ ምርጫው ግን የራሳችሁ ነው፡፡

በነገራችን ላይ በሩሲያና ዩክሬን መሃከል የተከፈተው ጦርነት ዘለግ ያለ ግዜ ከቆየ በአፍሪካ ምድር እና በመሃከለኛው ምስራቅ የኑሮ ውድነቱን ያባብሰዋል፡፡ ዛሬ በአለም ላይ እየጋመ የመጣው የኑሮ ውድነት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 2018 የፈነዳውን የአረቡን የጸደይ አብዮት ያስታውሰኛል፡፡  ሁላችሁም እንደምታስታውሱት በዳቦ ውድነት ተስፋ የቆረጠው ቱኒዚያዊ ወጣት ራሱን በእሳት በማቃጠሉ ምክንያት የሰብአዊ ስሜት ያላቸውን ሰዎች ሁሉ በእጅጉ አሳዝኖ ነበር፡፡ ስለሆነም በሩሲያና ዩክሬን መሃከል የሚደረገው ጦርነት፣ የትግራይ ወያኔ አሸባሪ ቡድን የጦርነት ዝግጅቱን ካላቆመ የኢኮኖሚ ድቀት ይባባሳል፣ ተራ ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ የወያኔ ኢህአዲግ በታሪክ፣በባህል፣ቅቡልነት የሌለው ጥያቄ ሰላምን አያመጣም፣ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ነው እንዲሉ የአፋርና ጎንደርን ለም መሬት ለብቻው ለመውሰድ የሚያደባው ወያኔ በህግም፣በታሪክም ተቀባይነት የሚያገኝ አይደለም፡፡ መፍትሔው የጎንደርም ሆነ የአፋር ለም መሬት በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ስር እንዲሆኑ መነጋገገር ነው፡፡ የራስ ፍላጎትን ብቻ ለማሟላት ጦር መምዘዝ የትም አያደርስም፡፡ እባካችሁ ይሄ ምዝብር ህዝብ በሰላም ሰርቶ የሚያድርበትን መንገድ ፈልጉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመዘዋወር መብቱ ከተጠበቀለት ራሱን መቻል አያቅተውም፡፡ ትልቁ የኢኮኖሚ ተግዳሮት ፖለቲካው ነው፡፡ በተለይም የጎሳ ፖለቲካ ለአተቃላይ የህዝቡ የኑሮ እድገት እንቅፋት ነው፡፡

የአለም የገንዘብ ድርጅት ሚዛናዊ ግምገማ

ጦርነቱ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበራዊ ህይወት ላይ ያደረሰውን ተጽኖ የመረመረው የአለም የገንዘብ ድርጅት የዩክሬንን ስእል ሚዛናዊ በሆነ ስእል አውጥቶታል፡፡

እንደ የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጥናት መሰረት የሰው ህይወት ከመጥፋቱ ባሻግር፣ የምጣኔ ሀብቱ ውድመት ከፍተኛ ነው፡፡ የባህር ወደቦችና የአየር ማረፊያዎች ተዘግተዋል፡፡( ወድመዋል፡፡) በተርካታ ድልድዮችና መንገዶች ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል፡፡ በዚህ ደረጃ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገና አልታወቀም፡፡ ሆኖም ግን  ይሁንና ግልጽ የሆነው ጉዳይ ዩክሬን ወደፊት የወደሙባትን የልማት አውታሮና የመኖሪያ ስፍራዎች መልሳ ለመጠገን እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚህ በተመሳሰለ መልኩ በወያኔ አሸባሪ ቡድን የተጀመረው የርስበርስ ጦርነት ዛሬም ከአስራ አምስት ወራት በኋላ መቋጫ ስላልተበጀለት ጥፋቱ መጠነ ሰፊ ነው፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ዛሬም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአፋር ዜጎችና የትግራይ ሰላማዊ ዜጎች እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡ 

በነገራችን ላይ  የሩሲያን ደህንነት ወይም ደህና መሆን ግንዛቤ ውስጥ ሳይከት  ጦርነቱ የሚፈጥረውን( የሚያስከትለውን) ጣጣ እና ውድቀት መመርመር ትርጉም አልባ ይመስለኛል፡፡ ይህም ማለት የጦርነቱ ዳፋ ዩክሬን ላይ ብቻ የሚደርስ ነው ብሎ መናገር ወይም የዜና ሽፋን መስጠት ሚዛናዊ አይደለም፡፡ ከአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኖች እንደተሰማው ከሆነ በሩሲያ ፌዴሬሽን ማእከላዊ ባንክ ላይ ምእራባውያን በተለይም በተባበረችው አሜሪካ ማእቀብ መደረጉ ይነገራል፡፡ ይህ ማእቀብ የሚያስከትለው ጉዳት በአለም አቀፉ የፋይናንስ ስርአት ላይ ያለውን የገንዘብ ክምችት ይቀንሳል፡፡

በሩሲያ የባንክ ስርአት ላይ አለም አቀፍ መደረጉ፣ በርካታ የባንክ ተቋማት ከሩሲያ ምድር ነቅለው መውጣታቸው፣ ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን ሸቀጣሸቀጦች ክፍያ ለማግኘት ወይም ለመቀበል ይቸግራታል፡፡ ወደ ሀገሯ የምታስገባቸውን ጠቃሚ ሸቀጣሸቀጦች ለመግዛትም ትቸገራለች፣በሀገሯ ግዛት  ውስጥም ሆነ ድንበሯን አልፎ   የሚካሄደው የፋይናንስ ዝውውር የተሳለጠ አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ምእራባውያን፣ በተለይም የተባበረችው አሜሪካ በሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ የጣሉት የፋይናንስ ማእቀብ የሚያደርሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለመናገር ግዜው ገና ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራን የመሰሉ ስመጥር የኢኮኖሚ ጠበብት በጥናታቸው በደረሱበት ድምዳሜ መሰረት የሩሲያ ብሔራዊ ገንዘብ ሩብል (the ruble exchange rate).”የመግዛት አቅም እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ምንም እንኳን ይሁንና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ባልሆንም፣ ከአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንደተከታተልኩት ከሆነ፣ከአንዳንድ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ለመረዳት እንደቻልኩት ከሆነ ቀሪው አለም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዳፋ ምክንያት መጎዳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአብዛኛው የአለም ክፍል የተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት፣የስንዴና በቆሎ ዋጋ ገና ከጠዋቱ እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ የተትረፈረፈ የስንዴና በቆሎ ምርት ባላት የተባበረችው አሜሪካ ሳይቀር ዋጋ ጨምሯል፡፡ የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ አለማችን በገበያ ትሰስር፣በህዝብ እንቅስቃሴ እርስበርስ የተሳሰረ ነው፡፡ በዚች አለም የሚገኙት ሀገራት ከመቼውም ግዜ በላይ ግንኙነታቸው ጨምሯል፡፡ ዩክሬን ላይ የስንዴ ምርት ከቀነሰ ወይም ዋጋው ከጨመረ እነ ሸምሱና ሸዋ ዳቦ ቤቶች ዋጋቸው ይጨምራል፡፡ በነገራችን ላይ የዳቦ ወይም የስንዴ ዋጋ፣ የምግብ ዘይት ከመጨመሩ በላይ እኔን በእጅጉ የሚያሳስበኝ የተፈጥሮ ነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው፡፡ 

ችግሩ መተላለፉ አይቀሬ እውነት ነው

በዩክሬን አየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት አለምን ወደ ከፋ ድቀት የሚወስዳት ነው፡፡ በአጭሩ አውዳሚ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የአለምን የምጣኔ ሀብት እድገትንም ይገተዋል፡፡ የአለም ባንክ ፕሬዜዴንት ዴቪድ ማልፐስ ,( the President of the World Bank, David Malpas) በቅርቡ ለእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት ‹‹ በዩክሬን ምድር ላይ የተከፈተው ጦርነት የተከሰተው በአለም ላይ መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ ወቅት ነው፣ ምክንያቱም ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የዋጋ ንረት ሰማይ ነክቷል፡፡ በአለም ባንክ ፕሬዜዴንት አስተያየት እስማማለሁ፡፡ በአለሙ የገንዘብ ድርጅት ለአመታት ያገለገሉት የምጣኔ ሀብት ምሁር ፐሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የቀድሞው ቀጣሪ ድርጅታቸውን ጠቅሰው በአንድ ጥናታዊ ወረቀታቸው ላይ እንዳሰፈሩት በጦርነት ምክንያት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሰው ህይወት አልፏል፣ ዛሬም እየተቀጠፈ ነው፡፡ ወደፊት የሰው ህይወት ያልፋል፡፡ ስለሆነም የሚያዋጣው ሰላም ነው፡፡ ስለሆነም የሚያዋጣው ሰላም ነው፡፡ በሩሲያና ዩክሬን መሃከል የተከፈተውን ጦርነት ለግዜው ብንረሳው እንኳን በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለአመታት በወንጀለኞች ይገደላሉ፡፡ ዛሬም ይህን አስተያየት በምጽፍበት ግዜ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ንጹሃን በነብሰ በላዎች እንደሚገደሉ ከተለያዩ የዜና አውታሮች ሲነገር አድምጫለሁ፡፡ ለአብነት ያህል በመተሃራ ከተማ ንጹሃን ዜጎች ለግዜው ባልታወቁ ወንጀለኞች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአለምን ዜና በአብዛኛው የሸፈነው የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ነው፡፡ ለማናቸውም የሁለቱም ጦርነቶች በኢኮኖሚና ፋይናንስ ላይ የሚያሳድረው ዳፋ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ሚስተር ማልፕስ በግልጽ እንዳስቀመጡት የዩክሬን ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ድንበር ተሻጋሪ ነው፡፡ በተለይም በአለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም በደሃ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ወይም የደሃ ሀገራት ህዝቦች ኑሮ( እንደ ኑሮ ከተቆጠረ ማለቴ ነው) ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል፡፡

ይህ ጦርነት ምግብና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ የበለጠ እንዲወደዱና ከገበያ እንዲጠፉም ሊያደርግ ይችላል፡፡ የዳቦ ዋጋ እጅጉን በጨመረ ቁጥር በአንድ ሀገር ላይ ያለመረጋጋት፣አመጽና እረብሻ እንዲከሰት ምክንያትም ይሆናል፡፡ለአብነት ያህል በሱዳን የነዳጅ እና ዳቦ ዋጋ መጨመር ምክንያት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመጽ ልብ ይሏል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መጋቢት ወር/ 2022  መጀመሪያ ላይ አለም አቀፉ የዜና አውታር ቢቢሲ ባስተላለፈው ዜና መሰረት 30 ፐርሰንቱ የአለማችንን አለም አቀፍ የስንዴ ምርት ሽያጭ የሚሸፍነቱ ሩሲያና ዩክሬን ናቸው፡፡ አብዛኛው የስንዴ ምርት የሚላከው ወደ አውሮፓ ሳይሆን በጥቁር ባህር አድርጎ ወደ አፍሪካ እና መሃከለኛው ምስራቅ ሀገራት ነው፡፡ ስለሆነም በአፍሪካም ሆነ በመሃከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ተራ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከፍተኛ ወጪ ያወጣሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የስንዴ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ሸክሙ ለተራው ዜጋ ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የአለም የምግብ ዋጋ ጦርነቱ ከመከፈቱ በፊት ጨምሯል፡፡ የአለም ምግብ ዋጋ እየጨመረ የመጣው ደግሞ  በኮቪዲ በሽታ ወረርሽኝ፣በአየር ጸባይ ለውጥ፣ በሰሜን አሜሪካ የተከሰተው ከፍተኛ የጸሃይ ግለት፣በደቡብ አሚሪካ ከፊል ድርቅ መከሰቱ፣ ወዘተ ወዘተ የምግብ እጥረትና የዋጋ መናር ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ እንደተለመደው በአብዛኛው የሚደቁሰው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ ሀገራት ናቸው፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ በስኮትላንድ እና ማሊዢያ እርሻ ላይ እየመጡ ይሰሩ የነበሩ ስደተኞች ቁጥር መቀነስ ለምግብ ዋጋ መጨመር ሌሎች ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር የአለም ዋነኛ የምግብ አቅራቢዎች የሆኑት ሩሲያና ዩክሬን በጦርነት በመዘፈቃቸው ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሚኖሩ ወደ 21 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለረሃብ እንደተጋለጡ ኦክስፋም መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ለአለም እረጂዎች ስጋቱን አስታውቋል፡፡በነገራችን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት 90 ፐርሰንቱን የስንዴ ፍጆታቸውን የሚሸምቱት ከሩሲያና ዩክሬን ነው፡፡በኢትዮጵያ  የበጋ መስኖ የስንዴ ምርት ፕሮፓጋንዳ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ የከፋ ችግር የሚደርስ አይመስልም፡፡

ኢትዮጵያውያን የምግብ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ምክንያት ቅሬታ እንዳደረባቸው በየግዜው ይሰማል፡፡ይህ ደግሞ በአለም አቀፉ ገበያ ላይ የምግብ ዘይት በመጨመሩ ነበር፡፡ ሁመራን የሚያህል እጅግ ሰፊና ለኑግና ሰሊጥ ምርት ተስማሚ መሬት ያላት ሀገር በምግብ ዘይት እጥረት እየተደቆሰች ነው መባሉ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡

 ፕሮፌሰር አክሎግ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት ላይ እንዳነበብኩት ከሆነ የአለምን 80 ፐርሰንት ከአረንጓዴ ተክሎች( ጎመን፣ቆስጣ ወዘተ ወዘተ)  የሚገኘውን የምግብ ዘይት የምታመርተው  ሩሲያ ፌዴሬሽ ናት፡ ስለሆነም  በአንድ ወር ብቻ የአለም የገበያ ዋጋ 8.5 ፐርሰንት ዋጋ ጨምሯል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአለም ቁጥር አንድ ሀብታም ሀገር በሆነችው የተባበረችው አሜሪካ የሚኖሩ ዜጎች የምግብ ዘይት ዋጋ 7.9 ፐርሰንት ጭማሪ በማሳየቱ ምክንያት ቅሬታቸውን ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይህ እውነት በታላቋ ብሪታኒያም ታይቷል፡፡

እንደ መደምደሚያ

በጣም ጠቃሚው መደምደሚያ መልእክቴ የሚከተለው ይሆናል፡-

  • የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የምግብ፣የምግብ ዘይትና ሌሎች ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ሰብሎች ላይ ከግዜ ወደ ግዜ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል
  • የአለም ደሃ ሀገራት በተለይም በመሃከለኛው ምስራቅ፣በአፍሪካ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ደሃ ማህበረሰቦች ህመም ከባድ ይሆናል ( ኢኮኖሚውን ለመሸከም አይችሉም ማለቴ ነው፡፡)
  • የየሀገሩ መንግስታት የሚከሰተውን ከፍተኛ የኑሮ ጫና እና የምግብ መወደድ ለመክላት እውነተኛ ስትራቴጂ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፣ ይህ ደግሞ በኑሮ ውድነት ምክንያት በየሀገሮቻቸው ህዝባዊ ቁጣ እንዳይቀሰቀስ ሊረዳቸው ይችላል
  • የምግብ ዋጋ የጨመረው በአለም ላይ የምግብ ዋጋ ስለጨመረ ነው በማለት ችግሩን ውጫዊ ምክንያት መስጠት የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ እንደ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ኢንጂነር ታደሰ ሀይለስላሴ ( የበርታ ኮንስትራክሽ መስራች ነበሩ) ( የሁለቱንም ጎምቱ ኢትዮጵያዊ ነፍስ ከደጋጎቹ አባቶቻችን ጎን ያኑርልን፡፡) እንዲሁም ፕሮፌሰር ደሳለኝ ራህመቶ በብዙ መንገድ ኢትዮጵያ ከድህነትና ችጋር እንድትወጣ ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበር ሆኖም ግን ሰሚ አላገኙም፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ በምግብ አቅርቦት ራሷን አልቻለችም፡፡ ስለሆነም መንግስት የህዝቡን ምግብ ፍላጎት የማሟላት ግዴታውን መወጣት አለበት ፡፡
  • በመጨረሻም ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ ለአለም የገንዘብ ድርጅት ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ መሰረት ከሩሲያና ዩክሬን ጋር የጠበቀ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸውና ከአውሮፓ ጋር አነስተኛ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው ወይም ምንም አይነት የኢኮኖሚ ግንኙነት የሌላቸው ሀገራት፣ ከዩክሬንና ሩሲያ ሀገራት አብዛኛውን የምግብ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ስንዴ የሚገዙ ሀገራት በከፍተኛ የምግብ ዋጋ መጨመር ሊተቁ ይቻላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር እንደ አውሮፓ ህብረትና የተባበረችው አሜሪካ አፍሪካ የመግዛት አቅም ስለሌላት እጅጉን መጎዳቷ አይቀሬ ነው፡፡
  • ግራም ነፈሰ ቀኝ በዲፕሎማቲክ አንግልም ሆነ በጸጥታ ጉዳይ፣ እንዲሁም  በምጣኔ ሀብት መነጽር ስንመረምረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መዘዙ የከፋ ነው፡፡ በሌላ አነጋገገር የአለምን ዲፕሎማሲ፣ጸጥታ እና ምጣኔ ሀብት የሚጎዳ ነው፡፡ ሰላም ለአለማችን

ማስታወሻ፡- ጽሁፉን ለማዘጋጀት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ  በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያዘጋጁትን ጥናታዊ ጽሁፍ በዋቢነት ተጠቅሜአለሁ

Filed in: Amharic