>

ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ስመለከታት - ከብዙው በጥቂቱ...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ስመለከታት – ከብዙው በጥቂቱ…!!!

አሳፍ ሀይሉ


ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ልብ ብለህ ተመልከታት፦


● መንፈሳዊ ስዕሎቿ የሚሳሉት ሀገር ባፈራቻቸው ሠዓሊያን ነው፣

● መፅሐፎቿ የሚደጎሱት ሀገር ካፈራው ብራና (ሌጦ) ነው፣

● ቅዱሳት መፅሐፎቿን ቀለም አዋህደው የሚገለብጡት ሀገር ያፈራቸው፣ ቀለም የቆጠሩ ዐዋቂዎች ናቸው፣

● የምታበራቸው ጧፎች ከንብ አርቢዎች ደጃፍ የተገኙ፣ ከሸማኔ ደጅ የፈለቁ ናቸው፣

● ፀናፅሎቿን ብረት አቅልጠው፣ ነሃስ ቀጥቅጠው፣ ቅርፅ አበጅተው፣ ተጠበው የሚሠሩላት ያገር ውስጥ የያካባቢው አንጥረኞች ናቸው፣

● የካህናቶቿ፣ የምዕመኖቿ የክብረ በዓላትና የሰንበታት አለባበሶች ሁሉ በሀገር ውስጥ ሸማኔዎች የተደኸሩ፣ በሴቶች የተፈተሉ፣ የሀገር ውስጥ የጥጥ ምርቶች ናቸው፣

● የቤተመቅደስ ዕጣኖቿ ከበረሃ ዕጣን እያወጡ ለሚያቀርቡ ነጋዶች ቋሚ የእንጀራ ገመድ ነው፣

● የቤተክርስትያን ካባዎች፣ የቅዳሴ፣ የተክሊል፣ ለተለያዩ ሥርዓቶች የሚውሉ አልባሶቿ፣ ዣንጥላዏቿ፣ በሙሉ በሀገር ውስጥ ልብስ ሰፊዎች፣ ስፌት አዋቂዎች፣ ጥልፍ አዋቂዎች የሚመረቱ ናቸው፣

● ከዓመቱ አብዛኛውን ቀን በሚይዙት የቤተክርስትያኒቱ የፆም ወቅቶች ሁሉ ለመብል የሚውሉት የተለያዩ አትክልቶች፣ እህሎች፣ ጥራጥሬዎችና ፍራፍሬዎች ናቸው፣ በዚህም የተነሳ የምዕመኑ ጤናና የገንዘብ ወጭ ሲጠበቅ፣ ከጎመን እስከ ሱፍ፣ ከኑግ እስከ ስንዴና ገብስ፣ ሁሉም አምራቾችና ነጋዶች የምርት አቅርቦትና የገበያ ተራ ይደርሳቸዋል፣ እንስሳት ያርፋሉ፣ ጥጆች የተራቸውን እግዜር የለገሳቸውን እንገር ያለተቀናቃኝ ይጠጣሉ፣

● ደሞ ፆም ሲፈታ ሌሎች እንዲሁ የየራሳቸው የዕድል ተራ ይደርሳቸዋል፣ መንፈሳዊ ጎኑን እንኳ ትተን፣ ይህን የeconomic interplay ወይም livelihood dynamics ብናስተውለው፣ ቀላል ቀመር፣ ቀላል ሳይንስ አይደለም፣ እጅግ በጣም የሚያስደንቅ ማህበረሰቡን ሁሉ የሚያካትት macro economic concept ነው፣ ሀገርንና ሕዝብን በዘመናት ውስጥ ያሻገረ፣ በተግባር የተፈተነ አስገራሚ ሥሪትና ዕውቀት ነው፣

● የተዋህዶ ቤተመቅደሶች ሁሉ የመገነቡት እንደየዘመኑ የተሻለና የመጠቀ የስነ ህንፃና የአናጢነት ሙያ ባላቸው ከማህበረሰባቸው በቅለው ማህበረሰባቸውን ለማገልገል በበቁ ሰዎች አማካይነት ነው፣ ከእነዚህ ሀገር በቀል የዕጅ ሙያዎች አንዳንዶቹ አስደማሚ መራቀቅ ላይ ለመድረስ በቅተውም ነበር፣

● የተዋህዶ ቤተክርስትያናትና ገዳማት በተቆረቆሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ፣ አንድም ዛፍ እንዳይቆረጥ ህዝቡን በመገዘት እስካሁንም የሚያኮሩ የደንና የተፈጥሮ ሀብታችንን ጠባቂዎችና ተንከባካቢዎች ሆነው ዘመናትን ዘልቀዋል፣

● የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ዘመናዊ መፃህፍት ቤቶች በአፍሪካ ቀርቶ ከግብፅ በቀር) በአውሮፓ ባልታወቀባቸው ጥንታዊ ዘመናት ጀምራ፣ በርካታ መፃህፍትን ጠብቃ በማኖር፣ ዘመናትን የዘለቀች ሀገር በቀል ቤተመፃህፍት ሆና አገልግላለች፣

● ቤተክርስትያን የተለያዩ የዕደጥበብ ባለሙያዎችን በመጠቀም ፅላቶቿን፣ ፀናፅሎቿን፣ መርገፎቿን፣ መቋሚያዏቿን፣ መቅረዞቿን፣ ሌሎችም ብዙ የማናውቃቸውን ሀገር ያፈራቸው ቅርሶች ከዘመናት ጥፋቶች ጠብቃ፣ ለትውልድ ያቆየች መካነ ቅርስ፣ የዘመናት ቤተመዘክር፣ የዘመናት ሙዝየም ሆና አገልግላለች፣

● የቤተክርስትያን የቅዳሴና የዜማ መሣሪያዎች ሁሉ (ከበሮዎቿ፣ መሰንቆና ክራሮቿ፣ ዋሽንቶቿ፣ ነጋሪቶቿ፣ በገናዎቿ፣ ፀናፅሎቿ፣…) ሙሉ በሙሉ  የሚሠሩት በሀገር ውስጥ የዕደጥበብ ባለሙያዎች መሆኑ ብቻ አይደለም፣ ዓለም የሙዚቃ ኖታን ምንነት ሳያውቅ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዜማን፣ ቅኔን፣ ድጓን፣ አቋቋምን ሁሉን ጥበባዊ ልሳናት ቀርፃ፣ ባለሙያዎችን አፍርታ፣ በቃልና በፅሑፍ ሀገር ያበቀላቸውን የራሳችንን ትውልዶች እያስጠናች ለዚህ ዘመን ያደረሰች ድንቅ ዕፁብ ድንቅ የጥበብ መፍለቂያ ነች፣

● ቤተክርስትያን ከጥምቀት እስከ ፍታት ባሉ የተለያዩ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶቿ ሁሉ፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን፣ ሀገር በቀል ምርቶችን፣ ከዚሁ ከሀገር የፈለቁ ፊደላትን፣ ከሀገራችን የበቀሉ ሊቆችን አፍርታለች፣ አበረታታለች፣ ለሁሉም የተዳረሰ የመተዳደሪያና የምጣኔ ሀብት ምንጭ ሆናለች ለዘመናት እስካሁንም፣

● ቤተክርስትያን በብዙ የታሪክ ድርሳናት በማስረጃ ተመዝግቦ እንደምናገኘው የሕዝባችን ሠላም፣ የእርቅ፣ የመቻቻል፣ የይቅርታ፣ የመልካምነት ህይወትን ስትሰብክ፣ የኖረች የብዙ ሥልጡን እሴቶቻችን ምንጭ (moral agent) ሆና አገልግላለች፣

● ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የሀገራችንን ሕዝብ የምታበለፅግ፣ ከራሳችን ቆርሰን ለራሳችን ማዋልን፣ የራሳችንን መጠቀምን፣ ራሳችንን ችለን መቆምን፣ በአንጡረ ሀብታችን አጠቃቀም የማንም የውጪ ኃይል ጥገኛ አለመሆንን ያስተማረች፣ በተግባር የተረጎመች፣ ረዥም ሥሮቿን በምድሯ በሀገሯ ሥረመሠረት ላይ የተከለች፣ ብትገፋ የማትወድቅ፣ ቅድስት ምርኩዛችን ነች፣

● ባጠቃላይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ከቅብዓቅዱሶቿ እስከ ቁርባኖቿ፣ ከከበሮዎቿ እስከ ፅላቶቿ፣ ከአልባሳቷ እስከ ቅዱሳት መፅሐፍቷና ንዋየ ቅድሳቷ፣ በአጠቃላይ እንቅስቃሴዎቿ በሙሉ ከሀገራችን፣ ከምድራችን የበቀለች፣ ሀገራችንን ለመሸርሸርና ቦርቡረው ለመጣል የሙ ሚሹ ሁሉ በጠላትነት ፈርጀው ለዘመናት ሲደራጁባትና ሲዘምቱባት የኖረች፣ ታላቅ የሀገር ኩራት የሆነች ተቋም ነች፣

● በራሱ አፈር ላይ ያልበቀለ አይፀናም፣ ሥሮቹ ጠልቀው ምድሩን ያልረገጠ ዛፍ ይወድቃል! ለዚህ ነው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሠይጣን ቢቀናባትም፣ ገፊዋ ቢበዛባትም፣ ምን ያዘመመች ቤት ብትመስልም፣ በፍፁም አትወድቅም የምንለው!

“አቡነ ዘበሰማያት ይትቀደስ ስምከ፣ ትምጻዕ መንግሥትከ፣ ወይኩን ፈቃድከ፣ በከመ በሰማይ፣ ከማሁ በምድር፣ ሲሣየነ፣ ዘለለ ዕለትነ፣ ሃበነ ዮም።…. ”

ጥልቅ ፍቅርና ክብር ለበረከተ-ብዙዋ፣ ለታላቋ፣ ጥንታዊት ተዋህዶ ቤተክርስትያን፣ ለካህናቷና ለምዕመኗ ይድረሳቸው ዘንድ ከልብ ተመኘሁ!

የጥበብ መፍለቂያ እናታችን – ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር!

Filed in: Amharic