>

የመድረኩ ንጉስ ፣ ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ...!!! (ታሪክን ወደሗላ)

የመድረኩ ንጉስ ፣ ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ…!!!

ታሪክ ን ወደሗላ

ወጋየሁ ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም አዲስ አበባ ቀበና ነው የተወለደው። ወላጅ አባቱ አቶ ንጋቱ ብዙነህ፣ ወላጅ እናቱ ወ/ሮ አምሳለ በየነ ይባላሉ። አባትና እናቱን ያጣው ገና በልጅነቱ ነበር፣ ወንድምና እህትም አልነበረውም። ብቸኛ ልጅ ነበር ወጋየሁ ለቤተሰቦቹ። የስለት ልጅ!
ወጋየሁ በ1942 ዓ.ም አካባቢ አቃቂ በሚገኘው የስዊድን ወንጌላዊት ሚሲዮን ት/ቤት ትምህርቱን ጀመረ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በዳግማዊ ምኒልክ እና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተከታተለ፡፡ ወጋየሁ በት/ቤት ቆይታው በአንዳንድ የተለዩ አጋጣሚዎች የተሰጥኦ ትርዒት ያቀርብ ነበር፡፡ ከተሰጥኦ ትርዒቶቹ ዋናው የልዩ ልዩ እንስሳትን ድምፅ አስመስሎ ያወጣው የነበረው ይጠቀሳል።
በ1955 ዓ.ም. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አቋቁሞት በነበረው “ኪነ ጥበብ ወትያቲር” ይባል ወደነበረው የአሁኑ የባህል ማዕከል በመግባት ከጓደኞቹ ከአባተ መኩሪያ እና ደበበ እሸቱ ጋር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ:: በወቅቱ የማዕከሉ ኃላፊ በነበሩት ፍሊፕ ካፕላን አማካኝነትም የትወናን፣ የዝግጅትንና የፅህፈተ-ተውኔትን መሠረታዊ እውቀት ተማረ።
➻ ወጋየሁና የጥበብ አበርክቶው
ወጋየሁ ትያትርን የኖራት፣ ያከበራትና ያስከበራት ድንቅ ልጇ ነበር። በነጋሽ ገብረማርያም “የድል አጥቢያ አርበኛ” እና “የአዛውንቶች ክበብ” ፤ በመንግስቱ ለማ “ፀረ ኮሎኒያሊስት” ፣ በፀጋዬ ገብረ መድህን “እናት ዓለም ጠኑ” እና “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ፣ በመላኩ አሻግሬ “አንድ ጡት” ፣ በማሞ ውድነህ “አሉላ አባነጋ” ፣ በተስፋዬ ገሠሠ “ፍርዱ ለእናንተ” ወዘተ. ቴያትሮች ውስጥ መልኩን እየለዋወጠ በተጫወታቸው ገፀባሕሪያት ወጋየሁ ነፍሱና ስጋው ለትያትር ጥበብ መፈጠሯን ማስመስቀር የቻለ የትያትር እንቁ ነበር።
ዘነበ አብርሃ “የመድረኩ ኮከብ” በተሰኘ ርዕስ ስለ ወጋየሁ ንጋቱ ሲጽፍ “ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁትም ቀልቤን የወሰደውም የታዋቂውን ባለቅኔ የፀጋዬ ገ/መድህንን “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ቴያትር ሲሰራ ነው። ወጣትነቱም አይሎ ነው መሰል ዕንባዬን መግታት ተሳነኝ። ደግነቱ አዳራሹን የሞላው ታዳሚ ሁሉ ይነፈርቃል” በማለት ወጋየሁ በአቡነ ጴጥሮስ ተመስሎ ሲጫወት የፈጠረበትን ስሜት ይገልጻል። ወጋየሁ እንደዚህ ነው! መስሎ ሳይሆን ሆኖ ነው የሚሰራው። የሱን ትያትሮች በመድረክ ላይ የመታደም እድል ያገኙ የትያትር ተመልካቾች በአንድ ድምጽ የሚመሰክሩትም እውነት ይሄው ነው። ወጋየሁ መሆን እንጂ መምሰልን፣ ማስመሰልን አያውቅበትም።
ወጋየሁ ንጋቱ እንዴት የተዋጣለት ተዋናይ ሊሆን እንደቻለ “ዜና ቱሪዝም” በአንድ ወቅት ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “… የስቴጅ ዓይኔን የከፈተው … ተስፋዬ ገሠሠ ነበር። የድራማ መምህሬ፤ የተውኔት አባቴ እርሱ ነው” ሲል መልሷል። ይህን ውለታዉንም ሳይረሳ እሱም ያለውን እውቀትና ክህሎት ለሌሎች ተተኪ ባለሞያዎች በማስተማር እና በማካፈል የወጣት ባለሞያዎችን የስቴጅ ዓይን በመክፈት መልሷል። ወጋየሁ በ1967፣ በ1969 እና በ1970 ዓ.ም. ብሔራዊ ቴያትር በሰጠው የተዋንያን ሥልጠና አስተማሪ በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከተማሪዎቹ ውስጥ እነሲራክ ታደሰ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ተክሌ ደስታ፣ መዓዛ ብሩ፣ ዓለምፀሐይ በቀለ፣ ዓይናለም ተስፋዬ፣ ኃይሉ ብሩና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ወጋየሁ የቲያትር ሙያ እውቀቱን ለማጉልበትም ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። በ1959 ዓ.ም. ከደበበ እሸቱ ጋር ወደ ሀንጋሪ ቡዳፔስት ተልኮ የሥነ-ተውኔት ሙያን ለሁለት ዓመታት አጥንቶ ተመለሰ። ከሀንጋሪ እንደተመለሰ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አጫጭር ተውኔቶችን ማቅረብ ቀጠለ። በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች እንግዳ የሆኑ አስማተኛው፣ ቁንጫ፣ አባሉን፣ ቀለም ቀቢው፣ የተዘጋ በር እና የመሳሰሉ ድምፅ አልባ (ማይም ተውኔቶችን ማቅረብ በመጀመሩ ተደናቂነትን እያተረፈ መጣ፡፡ በ1962 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተቀጠረ። የቲያትር ክፍሉ ኃላፊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይና እንዲሁም በሙያው ለመስራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በማስተማር ሁለገብ አገልግሎትን ሰጥቷል።
ከዚህ በኋላ ወደኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዛወረና ለመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት ሲሰራ ቆየ። በዚህ ሥራ ለአራት ዓመታት አገልግሎ በብሄራዊ ቲያትር ቤት ተቀጠረ፡፡ በብሄራዊ ቲያትር ቤት ከተቀጠረበት ጊዜ አንስቶም ቀጥሎ በተዘረዘሩት ተውኔቶች አብይ ሚናዎች እየወከለ ተጫ ውቷል፡፡
Filed in: Amharic