>

ኢትዮጵያ ውስጥ ጄኖሳይድ አልተፈጸመም” የሚባለው እውነት ነውን? (ተሻለ መንግሥቱ)

ኢትዮጵያ ውስጥ ጄኖሳይድ አልተፈጸመም” የሚባለው እውነት ነውን?

ተሻለ መንግሥቱ


በቅርቡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጂት (ጄኖሳይድ) እንዳልተካሄደ ሲናገሩ ተደምጠው ያንን ንግግራቸውን ሚዲያዎችና ግለሰቦች በክፉም በደግም ማለትም በመቃወምም በመደገፍም ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ እውነቱን ለመናገር በሤራም ሆነ በፖለቲካ ትንታኔ በቂ ዕውቀት ባይኖረኝም በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማሮች ላይ የዘር ፍጂት ወይም ጄኖሳይድ አልተካሄደም ብዬ ለማመን የማንንም ባርኮትና ይሁንታ አልጠብቅም፤ እንደዚያ ባደርግ በሰው ደምና አጥንት የተራቀቅሁና የተዘባነንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ አሟሟታቸውን በካድኩት ወገኖቼ ደምና አጥንትም እንደቀለድኩ ነው የምቆጥረው፡፡ መዋሸት ለምን ያስፈልጋል? ማንን ከኃላፊነት ለማዳን? ምንስ ትርፍ ሊገኝበት? ጄኖሳይዱን የሚያካሂደው ወገን አምኖበት “አማሮችን ከአካባቢያችን አጸዳን!” እያለ ግዳዩን በጠራራ ፀሐይ በይፋ እያስቆጠረ ሳለ ይህን ገሃድ እውነት መካድ ምን ይሉት አለቅላቂነትና አጎብዳጅነት ነው? እኔን የሚገዛኝ እውነት እንጂ ሰዎች ተሰብስበው “ይህን ወሰኑ፤ ይህን አልወሰኑም” የሚለው አይደለም፡፡ ያ ዓይነቱ የጄኔቫና የኒውዮርክ ሞልቃቃነት አንድም አማራ ከኦነግ ሠይፍና ከሾኔ ሜንጫ አላዳነም፤ አያድንምም፡፡ እነዚህ ቅንጡ ሰዎች ሼራተንና ሂልተን ቁጭ ብለው “እነሱ ስላልወሰኑ ጄኖሳይድ ተካሄደ ማለት አንችልም” ማለታቸው ራሱ ሌላ ጄኖሳይድ እየጠሩ ነውና “ቀባጭ አማት ሲሶ ብትር አላት” እንዲሉ መጽሐፉ ፊት ባይነሳኝ ኖሮ እነሱም የቀባጭ ምሣቸውን እንዲያገኙ ልመኝላቸው በወደድኩ – ግን ይቅር ግዴለም፡፡ በምንም ምክንያት የፈጠጠ እውነትን መካድ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልና ኃጢኣትም ነው፡፡ ዳንኤል በቀለን ዛሬ የፕሮፌሰሩን ንግግር ደግፎ ሲናገር ስሰማው እውነትን እየቀበሩ ሀሰትን የሚያነግሡ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸው አሳሰበኝ፡፡ ደህና ናቸው የሚባሉ ሰዎች ሲበላሹ ማየት ደግሞ ነገን የበለጠ እንድንፈራው ያደርገናል፡፡

የዘር ፍጂት በአጭሩ አንድ ነገድ ወይ ጎሣ በሌላው ጎሣ ወይም ነገድ ላይ ጥላቻንና በቀልን አሳድሮ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋው ይፈልግና ከማሰብ ጀምሮ በማቀድ፣ ያሰበውን በመሰሎቹ መሃል በመቀስቀስና በማነሳሳት፣ ያነሳሳውን ወገኑን በጠላው ነገድ ላይ እንዲዘምት በማዘጋጀት፣ የዕልቂት ቅድመ ዝግጅቶችን በማከናወን በመጨረሻም ሃሳብና ዕቅዱን ወደተግባር ለውጦ አገርን ሬሣ በሬሣ ማድረግ ማለት ነው – ልክ እንደሩዋንዳው የዘር ፍጂት፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መራቀቅንና ፍልስፍናን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአውሮፓና አሜሪካ ምሁራን ተሰብስበው በጄኖሳይድ ላይ ቢወያዩና ቢከራከሩ የሚሊዮኖች አማሮችን በትግሬና ኦሮሞ አክራሪዎች መጨፍጨፍ ሊመልሱት አይችሉም፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነውና እነዚህ “ምሁራን” የወገናቸውን ደም በማይረባ ፍልስፍና ሲለውጡት ማየት በ30 ብር ክርስቶስ ተላልፎ የተሠጠበትን በገንዘብና በርኩስ መንፈስ የመታወርን ይሁዳዊ ትርዒት ያስታውሰናል፡፡ በሰው ቁስል እንጨት መስደድ በጣም ቀላል ነው፡፡ መማር የኅሊና መሰወርን ብቻ ሳይሆን የልብ መደፈንንም ማስከተሉን በነዚህ ሰዎች ተገነዘብኩ፡፡ እንኳንስ መማር ቀረብኝ!! ከዘግናኙ ተሞክሮኣችንና ከዐይናችን በላይ ሲሆኑ ሌላ ምን ይባላል? “ሩዋንዳና ኮሶቮ ብቻ ነው የዘር ፍጂት እንደተካሄደ የሚታመነው” ብለው የፈረንጅ አሽከርነታቸውን በአደባባይ አሰጡት፡፡ ፈረንጅን ማምለካቸው መብታቸው ነው፤ በሕዝብ ደም መቀለድ ግን አይችሉም፡፡

አሁን አሁን መማር ማለት ከመሰልጠን ይልቅ ወደ መሰይጠን ይቀርባል መሰለኝ፡፡ ኢትዮጵያችን እየተሰቃየች ያለችው የታወጀበትን የጎሣና የነገድ አጥር በጣጥሶ አሁንም እርስ በርስ እየተጋባና እየተዋለደ አብሮና ተባብሮ በሚኖረው ባላገር ሳይሆን ሥልጣንንና ሀብትን በአቋራጭ ለመቀራመት የሃይማኖት ልዩነትን በሚያጦዘውና የጎሣ ፖለቲካን በሚያራምደው ልሂቅ (ኤሊት) ተብዬው ነው፡፡ ይህ የገረፍ ገረፍ ወይም የለብ ለብ ሸፋፋ የትምህርት ሥርዓት ውጤት የሆነ አንካሣ ትውልድ ሀገሪቷን ጨርሶ ሳያነዳት አንዳች መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ ካለፉት ጥቂት የማይባሉ አሠርት ዓመታት ወዲህ ከየትምህርት ማዕከላት እንደአሸን የሚፈልቀውን ምሁር ተብዬ ጥርብ ማይም ስንታዘብ የዘመኑ መማር ለዕልቂትና ለድህነት የሚዳርግ እንጂ እውነተኛ ዕድገትንና ብልጽግናን የሚያመጣ አልሆነም፡፡ ከመማር የሚመነጭ ድንቁርና ደግሞ ካለመማር ከሚመጣ ድንቁርና የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ ከዶክተር ዳንኤል በቀለና ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ተረድቻለሁ፡፡ መማር አንዳንዴ ብልቃጥ ውስጥ የሚቀረቅር ይመስለኛል፡፡ እጅግ ብዙ መማር በብልቃጥ ውኃ ውስጥ የሚገኙ የዓሣ ዝርያዎችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ይጠራ ሳያስብል አይቀርም፡፡ እውነት ነው የምላችሁ መማር እንደዚህ የሚያደነቁር ከሆነ ማይምነታችን ተፈልጎ የማይገኝ ወርቅ ነው፡፡ በመተከል፣ በወለጋ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአሰቦት፣ በአጣዬ፣ በከሚሴ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በቤንሻንጉል፣ በባሌ፣ በሐረር፣ አሁን ደግሞ በምንጃርና በመላው ሸዋ ውስጥ … በአማራነታቸው ምክንያት የተገደሉና እየተገደሉ ያሉ ዜጎች ደምና ዐፅም በገዳዮች ብቻ ሳይሆን የግድያውን ዓይነት በሚክዱ ሰዎች የእንቅልፍ ሰዓት እየመጣ ዕረፍት ይንሳቸው፡፡ ሁለተኛ ግድያ እኮ ነው!!

የት ሆስፒታል እንደሆነ አላውቅም፡፡ አንድ ታማሚ በህክምናው ዓለም የሀኪሞች ቋንቋ “ኢክስፓየር” ያደርግና ወደ ሬሣ ክፍል ይላካል፡፡ በተላከ በማግሥቱ የሬሣ ክፍል ሠራተኛው ያን በድን ከፍኖ ቤተሰብ ወዳመጣው ሣጥን ሊከተው ሲል ሟቹ ድንገት ከሞት ይነቃል፡፡ እንደነቃም በድንጋጤ “ምንድን ነው? ምን እያደረግኸኝ ነው?” በማለት ከፋኙን ይጠይቀዋል፡፡ ከፋኙም ሥራውን ሳያቋርጥ “ሞተህ ነዋ! እየገነዝኩህ ነው ወንድም” ይለዋል፡፡ ከሞት የነቃው ሰውዬም “አሃ! አሁንማ ከሞት ተመለስኩ አይደል እንዴ? ተወኝ እንጂ!” በማለት ሊከራከረው ይሞክራል – በደከመ አንደበቱ፡፡ ሬሣ ገናዡም “ወይ ሞኞ! አሁን አንተ ከዶክተሩ ልትበልጥ ነው? በል ሞተሃል ተብለሃል አርፈህ ተገነዝ?” አለው ይባላል፡፡ 

እነዚህ “ምሁራንም” (ብርሃኑና ዳንኤል) ስንትና ስንት አማሮች ወደውና ፈቅደው ባልተፈጠሩበት ማንነታቸው ምክንያት አንገታቸው ተቆራርጦ፣ ጭንቅላታቸው ተፈልጦ፣ ወገባቸው ተጎማምዶ የዐውሬ ሲሣይ ሆነው መቅረታቸውን፣ እንደየእምነታቸው የጸሎት ፍትሃት በክብር እንኳን እንዳይቀበሩ እንደአልባሌ ቆሻሻ በግሬደር በአንድ ጉድጓድ ውስጥ መቀበራቸውን ልቦናቸው እያወቀ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነውና እነሱና የነሱ የሆነ ስላልሞተ ብቻ ይህን መሳይ ወራዳ መልስ ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” እንደሚባለው ሆነ ነገሩ፡፡

የኛ የብዙዎቻችን ችግር የሌሎችን ችግር መረዳት አለመቻላችን ነው፡፡ አማሮች የተገደሉት በአማራነታቸው እንጂ በሰውነታቸው አይደለም፡፡ ይህንን እውነታ መካድ መማር ሳይሆን መደደብ ከዚያም ባለፈ ለጥቅም ወይም ለዓላማ አንድነት ሲባል የሚዘፈቁበት ኅሊናን በመሸጥ አሻሮ ይዞ ወዳለው የመጠጋት ፍላጎት የሚፈጥረው ቅሌት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጅት በአማራ ላይ መታወጁንና ብዙ አማራ ማለቁን ለመረዳት የብርሃኑ ወይም የዳንኤል ወይም እነሱ የሚያመልኩት የጄኔቭ ጉባኤን ቡራኬ አይጠይቅም፤ ምን አገባቸውና? የዘር ፍጅትን ካላወቁ ከኛ ይማሩ፡፡ ምንም ምርምር አይሻም – “ነፍጠኛን (አማራን) አጥፍተን በኦሮሙማ የገዳ ሥርዓት የሚመራ ታላቁን አባት ሀገር ኦሮምያን እንገነባለን!” ብሎ በመነሳት በየቦታው የሚገኝን አማራ የሚያርድና የሚያሳርድ አክራሪ ኦሮሞ ሊያውም በቤተ መንግሥት ውስጥ መሽጎ ሁሉን ነገር መቆጣጠሩ ለጄኖሳይድ መኖር ዋናው መገለጫ ነው፤ ከተፈለገም ራሱን በኦሮሙማ ተክቶ ለጊዜው ዘወር ያለውን ፀረ-አማራ የሕወሓት ማኒፌስቶ መጨመርም ይቻላል፡፡ ከዚህ በተረፈ በሰው ደም የሚቀልድ ከዚህ የጎመዘዘ ቀልድ ቢወጣ ይሻለዋል፡፡ ችግራችን የፍልስፍና ሳይሆን የኅልውና ነው፡፡ አጓጉል ለመሰልጠኑ የቄሱ ሚስት ትበቃናለች፡፡ የርሷ መሰልጠንስ በመጽሐፍ ማጠብ ብቻ ነውና ቀላል ነው፡፡ የነዚህ ግን በላኪዎቻቸው አስገዳጅነት ዓላማቸው በሰው ደምና አጥንት መቆመር በመሆኑ ከሁሉም ወንጀሎች ይከፋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1968 ጀምሮ በዐዋጅ የፀና የዘር ፍጂት አለ – ሊያውም በ40 እና 50 ሚሊዮን በሚገመት ሕዝብ ላይ፡፡ ስለዚህ ምሁሮቻችን ሆይ! እባካችሁን ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፤ ደግሞም ስለምንም ምንነት ይበልጥ ለማወቅ አንብቡ – ብዙ ቢፈትንም በማንበብና በመመራመር ወደኅሊና መመለስ ይቻላል፡፡ እናንተ ራሳችሁ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ትሉ የለም? እርግጥ ነው ማንበባችሁም ከተዘፈቃችሁበት የሞራል ዝቅጠትና የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ሊመልሳችሁ አይችል ይሆናል፤ ለምን ቢባል አሁንም ቢሆን እውነታውን አጥታችሁት ሳይሆን አውቆ የተደበቀ ቢጠሩት እንደማይሰማ ሁሉ እናንተም የያዘ ይዟችሁ ከእውነቱ አፈንግጣችኋልና፡፡ እንጂ መላው ኢትዮጵያዊ በእሥር ቤት የተሰቃየችውን ስቃይ አብሮ በስሜት የተሰቃየላትና እጅግ ይወዳት የነበረችዋ ደፋር እንስት የህግ ምሁር አሁን ከልጓም ዘር ስቦ፣ ትንሽ ሥጋም እንደመርፌ ወግቶ፣ ምናልባት በ“የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” ልክፍት የተያዘች ልጃችን ዛሬ ተለውጣ እየሆነች ያለችውን እያየን ነው፡፡ ከሀገር አገልጋይነት ይልቅ ለአንድ አምባገነን ተንበርክካ ከራሷም ከሀገርም ሳትሆን ክፉ ቀን እየገፋች ትገኛለች – በዚህ ደግሞ ደስተኛ እምትሆን አትመስለኝም – ይሉኝታ መጥፎ ነው፤ የቃላት ሽንገላም እንዲሁ መጥፎ ነው፤ ካለቦታ ያውላል፡፡ አዝንላታለሁ፡፡ 

ለማንኛውም እንደ እስስት የምትለዋወጡ ወገኖቻችንና “ምሁሮቻችን” ፈጣሪ ይሁናችሁ፡፡ የኛ የተራ ዜጎች ጉዳይ ቀላል ነው፤ አልነበርንም – መጣን – እንሄድማለን፡፡ ከመቃብር በላይ የሚቀር መጥፎ ስም አንተውም፡፡ ምንም እንደነበርን ምንም እንሆናለን፡፡ እናንት ምሁራንና የ”ሕዝብ ሰዎች” ግን ስማችሁንና ምግባራችሁን ወረቀት ይይዘውና “በእንዲህ ያለ ዘመን ዶክተር ማንትስ አሰፋ የሚባል አካዳሚሺያን፣ ፕሮፌሰር ማንትስ ነጋ የሚባል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምሁር፣ ዶክተር ማንትስ ደግፌ የተባለ ኢኮኖሚስት ….” እየተባለ እንደየሥራችሁ የትውልድ መዘባበቻ ወይንም የትውልድ መነቃቂያና አርአያ ትሆናላችሁ፡፡ ምርጫው የራሳችሁ ነው፡፡ መረዳት ያለባችሁ ግን በምድር ላይ የሰው ልጅ ዕድሜ ቅጽበታዊ እንደመሆኑ በዚህች አጭር ዕድሜ ክፉ ከመሥራት ይልቅ መልካም ነገርን ሠርቶ ማለፍ ለገዛ ቀጣይ ትውልድም ጠቃሚ መሆኑን ነው – አንገቱን የሚደፋ የልጅ ልጅ ሳይሆን ባባቶቹና በቅድመ አያቶቹ አኩሪ ታሪክ ደረቱን ነፍቶ የሚራመድ የዘር ሐረግ የምንተካው በሆዳምነትና በአድርባይነት ሳይሆን ሃቅን ተናገሮ እንዳስፈላጊነቱ በመሞትም ጭምር ነው፡፡ እማሆይ ተሬዛንና ማኅተመ ጋንዲን እንዲሁም ኔልሰን ማንዴላን የመሆን ወይም በተቃራኒው አዶልፍ ሂትለርንና ቤኒቶ ሙሶሊኒን እንዲሁም ጆሴፍ እስታሊንን የመሆን ምርጫ በየእጃችን አለ፡፡ (ፈገግ በል አስኪ! አንዲት ያገሬ ሴት እንጨት ይሁን ውኃ ተሸክማ የገጠር መኪና መንገድ እያቋረጠች ነው፡፡ መኪና መምጣቱን ሳታውቅ ወደአውራ ጎዳናው ዘው ብላ ገባች፡፡ አንዱን የኤንትሬ መኪና ዘዋሪም ቀልቡን ገፈፈችውና ድንገት ዚታ መኪናውን ሲጢጢጢጢጥ … አድርጎ እንዲያቆም አስገደደችው – ያኔ ሹፌሩ ተናዶ አጠገቧ የነበረችዋን አህያ እያመለከታት “ካንቺስ አህያዋ ትሻላለች” ይላታል፡፡ እሷም መልሳ “የሚሻልዎትን እርስዎ ነዎት የሚያውቁት…” በማለት በንዴትና በብስጭት ጨፍግጎ የነበረውን ድባብ በሣቅና በፈገግታ ለውጣ መጨረሻው እንደመጀመሪያው ሣይሆን በሰላም ተለያዩ፡፡ በነገራችን ላይ አህያ መንገድ ስታቋርጥ ቀጥ ብላ የምትራመድ በመሆንዋ እንደሰው አታወላውልምና የመገጨት ዕድሏ አነስተኛ ነው፡፡ ለማንኛውም ብዙ ምርጫዎች አሉንና ደግ ደጉን እንዲያመላክተን ፈጣሪን እንለምነው፡፡)

Filed in: Amharic