በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ይህ ድንቅ ክስተት ዛሬ በሰአሊተ ምሕረት ግቢ ኾኜ ሳለሁ በተመለከትኩ ጊዜ በእጅጉ ደስ ብሎኝ ፎቶ አንሥቼ ከለቀኩ በኋላ የብዙዎችን ትኩረት በመሳቡ ትንሽ ልል ወደድኩ።
እንደ እውነቱ ይህ አስደሳች ቅርጽ በሳይንስ፣ በባሕል፣ በሃማኖት በስፋት ይተነተናል፡፡ በዚህ አክሊል መታየት ዙሪያ የተለያየ እይታ እንደየባሕሉ እንደየሃይማኖቱ እንደየምልከታው ይነገራል፡፡ ሁሉንም በዚህ ላይ ለመተንተን ጊዜ ስለሌለ የተወሰነውን በዐጭሩ ስናይ በሳይንስ ይህ ክስተት አክሊለ ፀሐይ ወይም የ22 ዲግሪ አክሊል በመባል ይታወቃል፡፡
የሚከሰተውም ስድስት ማእዘን የሆኑ በከባቢ አየር ላይ ተንሳፈው የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ የበረዶ ክሪስታሎች ላይ የፀሐይ ብርሃን ሲያልፍ ቀስተ ደመና መስሎ የሚታይ በአማካይ 22 ዲግሪ ራዲየስ ላይ ሠርቶ የሚታይ ቀለበት ነው፡፡
ክብ አክሊል የሚፈጠረው ከእኛ በላይ20 ሺ ጫማ (6 km) በሚርቀው ስስ ሽፋን ባለው ሲሩስ በተባለው ደመና ነው ይላል የዘመናችን ሳይንስ፡፡ ይኸውም በብርሃን መጉበጥና መከፈል ወይም ከበረዶው ክሪስታል ብርቅርቅታ የተነሣ ነው፡፡ እያንዳንዱ የሚታየው እንደየቆመበት ቦታ ሲወሰን ቢሆንም ትኩር ብሎ መመልከት በአልትራ ባዮሌት ጨረር ምክንያት ዐይንን ሊጎዳ ይችላል ይላል ሳይንስ፡፡
የጥንት የሥነ አየር ተመራማሪዎች በጨረቃ ዙሪያ የሚፈጠር አክሊል ካለ ከፍተኛ ዝናብ ይዘንባል ይላሉ፡፡ ምክንያቱም የሲሩስ ደመና ከወጀብ በፊት የሚመጣ ስለኾነ የሚል ምልከታ ነበራቸው፡፡
ወደ ሃይማኖት ሊቃውንት ምልከታ ስንሄድ ደግሞ “ቀስተ ደመናዊ የፀሐይ ቀለበት” ይሉታል፡፡ እነዚህ ጥቃቅን የበረዶ ክሪስታል መስታወት መሰል ቅንጣቶች “በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ” በመባል በራእ 4፡6 ላይ የተጠቀሰውት ነው ይላሉ፡፡ ስሙንም “ባሕረ ማሕው” በማለት ይጠቅሱታል፡፡
አንዳንድ የሃይማኖት መምህራን ደግሞ “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል” (ሉቃ 21፡25) የሚለውን በመያዝ ምልክት በፀሐይ፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት መታየታቸው የክፉ ቀን መቃረብ መልእክት ከእግዚአብሔር ሲገለጽ ነው ይላሉ፡፡ ቢሆንም ግን የክፉ ቀን መምጫ መቃረብ የተጠቀሰው አብዛኛውን ከመጨለም ጋር ተያይዞ ያለው ነው እንጂ የፀሐይ አክሊል አይደለም ይላሉ አንዳንድ ምሁራን፡፡ በዚህ ዙሪያ ማዛሮት መጽሐፌን አንብቡ፡፡
እኩሌቶቹ ደግሞ “ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ” (ራእ 10፡1) የሚለውን በመያዝ የመገለጥ ትርጕምን ይሰጡታል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ በሕልምም በውንም የምናየው የአክሊሉን ቀለም የሚከበንን መንፈሳዊ ኀይልን ጠቋሚ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ይኸውም በጣም ሰፊ ሲሆን በዐጭሩ ለመግለጽ ብሩህ አክሊል በፀሐይ ዙሪያ ከኾነ ንጽሕናንና ከአምላክ ጋር መገናኘትን ይገልጻል ይላሉ፡፡ ሰማያዊ አክሊል ፍቅርን መጠበቅን ወካይ ሲሆን በመላእክት መከበብን ያሳያል ይላሉ፡፡ ቀይ አክሊልን ከቁጣ ጋር፤ ጨለማዊ አክሊልን ከባዶነት ከመንፈሳዊነት መራቆት ጋር ጋር የሚያይዙ አሉ፡፡
በዚህ ዙሪያ ከግሪክ እነ አሪስቶትል (Meteorology III.2, 372a14) በሚል ሥራው።
ከሮማ ፈላስፎች በ2ኛው ክፍለ ዘመን አፑሊዩስ Apologia XV ሥራው።
ሉይስ ሴኔካ Naturales Quaestiones. መጽሐፉ፤ ጸሐፊው ካህኑ ፑሊቸር በ12ኛው ክፍለ ዘመን ላይ Historia Hierosolymitana (1127) መጽሐፉ።
የዮርኩ ኮማንደር ኤድዋርድ ከጦርነት ታሪክና ድል ጋር አያይዞ።
በሮም በ1629 ድጋሚ በ1630 ላይ በታየው የፀሐይ አክሊል ዙሪያ ክሪቶፍ ሼነር Parhelia በሚል መጽሐፉ ብዙ አስገራሚ ነገራትን ጽፈዋል፡፡
በ1661 ላይ ጆርጅ ፌላው “7 ክፍል ያለው የፀሐይ ተአምር” በሚለው በበራሪ ጽሑፉ ላይ ዘርዝሮ የጊዜውን የፀሐይ አክሊል ክስተት ሲጽፍ በቀጣዩ ዓመት ላይ ዮሀኔስ ሄቬሉስ Mercurius in Sole visus Gedani በሚል መጽሐፉ ላይ አስፍሮታል፡፡
በ1790 በተከሰተው በሴንት ፕተርስበርግ ሩሲያ በተከሰተው ጆሀን ቶቢያስ ጽፏል፡፡
በ1843 በኒው ፋውንድ ላንድ በተከሰተው፤ በ1876-77 በነበረው ጦርነት ጊዜ በተከሰተው የፀሐይ አክሊል፤
በ2020 ፌቡሯሪ 14 በኢነር ሞንጎሊያ ቻይና በተከሰተው ብዙ ተጽፈዋል፡፡
ሁሉንም ለመጻፍ ጊዜ ስለሌለ ነባር የአሜሪካ ሕዝቦችና ሕንዳውያን የሚሉትን ብቻ ላስቀምጥ፡፡ እነዚህ ጥንታውያን ሕዝቦች ይህንን “የለውጥ ምልክት” “ጥምዝ ቀስተ ደመና” ይሉታል፡፡ ይህንን አክሊል ቅርጽ አስመልክቶ የጥንት አሜሪካና ሕንዳውያን ትንቢት ነበራቸው ይህም “Ancient American Indian Prophecy” በመባል ሲታወቅ ታላቅ ለውጥ በምድር ላይ ለመምጣቱ ምልክት ይላሉ፤ በጥቂቱ ስናየው “ኹሉም ነገዶች፣ ሕዝቦች ያላቸውን ልዪነት በመተው ምድርንና ነዋሪዎቿን ለመፈወስ በሕብረት ለአንድነት የሚቆሙበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ሰላምን ለማምጣት እንደ ክብ ቀስተ ደመና በምድር ሁሉ ይመላለሳሉ፡፡ ሁሉም እኩል የሚሆኑበት፣ ሕፃናት የሚጠበቁበት፣ አረጋውያን የሚከበሩበት፣ ጦርነት በሽታ የሚያበቃትን የምድር መፈወሻ ጊዜ የጥበብ ጊዜ መቃረብን ያመለክታል፡፡” ይላሉ፡፡ በቡዲዝም እይታ አክሊል የመልካም ዕድል ምልክት ይሉታል፡፡
በመሆኑም ክቡራን ተመልካቾቻችን ይህን ያህል በዐጭሩ ከሳይንሱም፣ ከባህልም ይህን ያህል ካሰፈርኩ በዝርዝር ስለ ሥነ ፈለክ ለማወቅ አንድሮሜዳና ማዛሮት መጽሐፍን ያንብቡ፡፡
በሙሉ የጸደይ ጨረቃ በ8ኛ ወር ሚያዝያ በ8ኛው ቀን 8 ሰዓት ስለ ሰማይ ምስጢር የሚተነትነው ማዛሮት መጽሐፌን ለመመረቅ በዕለቱ ተገኝተው ብዙ ያልተሰሙ ምስጢራትን ይስሙ።