በነውጥ ጎዳና ላይ የምናደርገው ጉዞ የት ያደርሰን ይኾን?! …
(ዘከሪያ መሀመድ)
አራት የከሸፉ ዓመታት! …
* …. በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን በጥልቀት እና በእርጋታ ፣ ጣትን ሌሎች ላይ ከመቀሰር ይልቅ ራስን መፈተሽን እና በብስለት ተመካክሮ ሁነኛ መፍትኄ ማመንጨትን በሚጠይቁ፣ … በመሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በሚፈለገው መጠን ያጤነ መላ ካልተገኘላቸው፣ ሀገርን ከምንጊዜውም የከፋ የሁከት አዙሪት ውስጥ ሊከትቱ በሚችሉ … ትልልቅ ፈተናዎች ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች።
የዛሬ አራት ዓመት፣ ኢሕአዴግ ዐቢይ አሕመድን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመርጥ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ “ከእንግዲህ ሀገራችን በተሻለ የለውጥ ጎዳና ላይ ትጓዛለች” የሚል እምነት አሳድሮ፣ ትልቅ ተስፋም አድርጎ ነበር።
… ሁላችንም እንደምናስታውሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን ላይ ሲወጡ፣ በታሪክ የትኛውም የኢትዮጵያ መሪ አግኝቶት የማያውቀውን መጠነ ሰፊ ድጋፍ አግኝተው ነበር። … ከመጋቢት 2010 በኋላ በነበሩት ወራት፣ የሀገሩን ወደተሻለ ደረጃ መድረስ ከልብ በመመኘት እርሳቸውን ለማገዝ ያልተነሳሳ ምሁር ለማግኘት ያስቸግር ነበር። … (በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ አብዮት አደባባይ ድረስ የዐብይ እና የለማ ምስል የታተመበትን ከነቲራ ለብሼ መሰለፌንስ ማን ይዘነጋዋል?!)
ታዲያ፣ (“ጽድቁ ቀርቶ፣ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ) እንደዚያ ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ ለውጥ እውን መኾኑ ቀርቶ፣ ሀገራችን ዛሬ እንደዚህ በነውጥ ጎዳና ላይ ለመጓዝ የበቃችው ለምንድን ነው?! … ብሎ መጠየቅና ትክክለኛ መልስ መሻት እጅግ አስፈላጊ እንደኾነ ይሰማኛል። …
ይህን ጥያቄ ከማንም በላይ ከ2007 ጀምሮ በኦሮሚያ የተካሄደውን የሕዝባዊ አመጽ ግፊት በመታከክ፣ በኦሕዴድ እርካብ ላይ ተፈናጥጠው መንበረ ሥልጣን ከጨበጡ አራተኛ ዓመታቸውን የደፈኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአንክሮ ሊጠይቁ የሚገባ ይመስለኛል። የዚህም ምክንያት፣ ትናንት ተስፋ የጣልንበት ሀገራዊ ለውጥ እውን ካለመኾኑ እጅግ በበለጠ፣ አሁን ብዙዎቻችንን እያስጨነቀን ያለው፣ ዛሬ ሀገሪቱ የምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ምስቅልቅል እና ትርምስምስ መጨረሻው ምን ሊኾን ይችላል? የሚል እውነተኛ የሀገራዊ ኅልውና ጥያቄ በመኾኑ ነው። …
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚያደርጉት ጥረት፣ ራሳቸውን በመከላከልና ሌሎችን በመውቀስ ላይ ካተኮሩ፣ #የእርሳቸው_አመራር ባለፉት አራት ዓመታት የሠራቸውንና ዛሬ ለምንገኝበት እጅግ አደገኛና አሳሳቢ ሁኔታ አስተዋጽዖ ያደረጉ “ስህተቶችን” ለመግደፍ ስለሚዳረጉ፣ ሀገራችን ከገባችበት ቀውስ ልትወጣ የምትችልበትን ሁነኛ መላ ለማግኘት ይቸገራሉ ብዬ እሰጋለሁ። …
እኛ ከውጭ ያለነው አቃቂር ማውጣትና ጉድፍ መፈልፈል እንደሚቀልለን ሁሉ፣ እርሳቸውም ጣታቸውን ሌሎች ላይ መቀሰር ይከብዳቸዋል ብዬ አልጠረጥርም። እንደዚያ ማድረጉ ግን ሀገራችንን ከገጠማት ፈተና አያወጣትም። …
ከዚያ ይልቅ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር …
ከዚያ ይልቅ፣ እኛ ዝም ብንል እና እርስዎ ራስዎ፣ [በአመራር እና በውሳኔ አሰጣጥ ዘይቤዎ ላይ በማተኮር] ሀገራችን ለገባችበት ከባድ ፈተና የሚመጥን እውነተኛ ግለ-ሒስ ቢያደርጉ፣ ባለፉት አራት ዓመታት የእርስዎ አመራር የት ጋ ስህተት እንደሠራ ሊደርሱበት፣ ያሉትን ማናቸውም መልካም ዕድሎች ተጠቅመው የተሠሩ ስህተቶችን ሊያርሙ እና ሀገርን ከገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅልና የግጭት አዙሪት ለማውጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ሊያሳልፉ፣ አስፈላጊ የማስተካከያ እርምጃዎችንም ሊወስዱ ይችላሉ ብዬ … ያው … ተስፋ አደርጋለሁ። … ተስፋ ከማድረግ ውጪ ምን አማራጭ አለኝና!! …
መልካም የግለ-ሒስ ጊዜ እንዲኾንልዎ ከልቤ እመኛለሁ።