>
5:31 pm - Monday November 12, 2266

አምባሳደርና ጋዜጠኛ አሐዱ ሳቡሬ...!!! (ታሪክን ወደኋላ)

አምባሳደርና ጋዜጠኛ አሐዱ ሳቡሬ…!!!

ታሪክን ወደኋላ

‹‹አሀዱ ሳቡሬ›› የሚባል ስም ሲነሳ ‹‹አጠገበኝ ወሬ›› የሚል ሐረግ ይከተላል። ይህ ስያሜ ሰውየውን በሚያውቋቸውም ሆነ በማያውቋቸው ዘንድ የተለመደ ነው። በአስተርጓሟነት ጀምረው፤ ጋዜጠኝነትን ተረማምደውበታል፤ ዝነኛም ሆነውበታል። በጸሐፊነት አሟሽተው እስከ አምባሳደርነት ድረስ ዘልቀዋል። በ 1940ዎቹ እና 50ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት በጋዜጠኝነት ተደናቂና ተወዳጅ የነበሩት የምሥራቁ ፀሐይ … አሀዱ ሳቡሬ!
አሀዱ የተወለደው መስከረም አንድ ቀን 1917 ዓ.ም በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ነው። በሦስት ዓመቱ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ የኔታ መንግሥቱ ከሚባሉ መምህር ዘንድ ፊደል ቆጠረ፤ ዳዊት ደገመ። በመቀጠልም የፈረንሳይ ትምህርት ቤት (አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሲስ ትምህርት ቤት) በመግባት ዘመናዊ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ። በልጅነቱ አባቱን በሞት የተነጠቀው አሀዱ፤ ‹‹ሳቡሬ›› የተባሉ ፈረንሳዊ ግለሰብ እገዛ ያደርጉለት ስለነበር በእርሳቸው ስም መጠራቱ ተለምዶ ‹‹አሀዱ ሳቡሬ›› ተባለ። በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ምክንያት ትምህርቱን አቋርጦ የጣሊያኖች ትምህርት ቤት ገብቶ ለሁለት ዓመታት ያህል ከተማረ በኋላ በ13 ዓመቱ አስተርጓሚ ሆኖ መሥራት ጀመረ። እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ በዚህ ሥራው ቆይቷል።
ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላም የድሬዳዋ ማዘጋጃ ቤት በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሲቋቋም የታክስ ክፍል ሠራተኛ ሆኖ ተቀጠረ። በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የነበሩ አውራጃዎችን እየተዘዋወረ የሚቆጣጠር ክፍል (ኢንስፔክሽን ክፍል) በተቋቋመበት ወቅት የክፍሉ ጸሐፊ ሆነ።
አሀዱ የሕይወት ጉዞውን ቀጥሎ በ1936 ዓ.ም በጅቡቲ በነበረው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በጸሐፊነት ተመድቦ መሥራት ጀመረ። የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ያሳለፈውም በጅቡቲ ነበር። የጅቡቲ ቆይታው የፈረንሳይኛ ችሎታውን ለማሻሻል፣ ለማንበብና ከፈንሳዮች ጋር የነበረው ግንኙነት ለማሻሻል ጠቅሞታል። በቆንስላ ጽሐፈት ቤቱም ለስድስት ዓመታት ያህል አገልግሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። አሀዱ በጅቡቲ ሳለ ጽሑፎችን እያዘጋጀ ለጋዜጦች ይልክ ነበር። ለአብነት ያህል ‹‹አዲሱ ሥራችን›› በሚል ርዕስ ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላ ኢትዮጵያውያን ማድረግ በሚገባቸው ነገሮች ላይ ያኮሩ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ ለጋዜጦቹ መላኩ መነሻ ሆኖት በ1942 ዓ.ም የጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤትን ተቀላቀለ።
አሀዱ በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት ሥራ የጀመረው በጋዜጠኝነት (በጋዜጣ ጽሑፍ አዘጋጅነትና በሬዲዮ ተናጋሪነት) ነበር። በወቅቱ የ‹‹አዲስ ዘመን›› እና የ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ የነበሩት የብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ረዳት ሆኖ መሥራት የጀመረው አሀዱ፤ በሬዲዮው ዘርፍም የዜናና ሐተታ አንባቢና አዘጋጅ ሆኖ ይሠራ ነበር። አቶ አሀዱ ኑሯቸውን በአሜሪካ ካደረጉ በኋላ ስለጋዜጠኝነት ሥራ አጀማመርና ጉዟቸው ሲናገሩ …
‹‹…በሙያው ተሰማርቼ ሥራ የጀመርኩት ጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት ከገባሁ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ግን በሌላ የመንግሥት ሥራ ላይ ሆኜ በ‹‹አዲስ ዘመን›› እና በ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› ጋዜጦች ላይ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን እጽፍ ነበር። ወደ ጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት እንድዛወር ያስቻለኝም ይኸው ነው ማለት እችላለሁ። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውሬ ወደ ጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት የገባሁት በ 1942 ዓ.ም ነው። መስሪያ ቤቱ ከ 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ‹‹ማስታወቂያ ሚኒስቴር›› ተብሎ ተሰይሟል። የወቅቱ የመስሪያ ቤቱ መሪ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ ነበሩ። ለጥቂት ጊዜያት ያህል የ‹‹አዲስ ዘመን›› እና የ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› ጋዜጦች ረዳት አዘጋጅ ሆኜ ሠራሁ። በኋላ ‹‹ኑሮ በዘዴ›› የሚባል በየ15 ቀኑ በአማርኛና በፈረንሳይኛ የሚወጣ ትንሽ ሕትመት እንዲቀርና ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ዘርፎች የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ጎላ ባለ መልኩ የሚያቀርብ ጋዜጣ እንዲጀመር ታሰበ። ስያሜውም ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ተባለና በ1944 ዓ.ም በአማርኛና በፈረንሳይኛ ሥራው ተጀመረ። የአማርኛው ክፍል ኃላፊ/ዋና አዘጋጅ እኔ ሆንኩኝ። ጋዜጣው በየሳምቱ ዓርብ የሚታም ነበር … ጋዜጣው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ወሬዎች እንዲሁም ሌሎቹ ጋዜጦች ደፍረው የማይሸፍኗቸውን ጉዳዮችን ይዞ ይወጣ ስለነበር ተወዳጅ ሆነ። በዚያው ልክም የሹማምንት ነቀፌታና ቅሬታም ነበር … በጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት ለ11 ዓመታት ያህል ቆይቻለሁ … ›› በማለት ተናግረው ነበር።
‹‹አሀዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ›› የሚለው አገላለፅ በብዙዎች ዘንድ የታወቀና የተለመደ ነው። የስያሜው መነሻ እንዲህ ነው።
‹‹አሀዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ›› የሚለውን ስያሜ /አገላለፅ/ የሰጡት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥታት ስመ ጥርና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ናቸው። የእነ አሀዱ አለቃ የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተወልድ ታመው አዳማ ይገኙ ነበር። አቶ መኮንንም ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስንና አሀዱን ወደ አዳማ አስጠርተዋቸው ነበርና ወደ አዳማ ሄደው ሆቴል ውስጥ ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ጋር ተገናኙ። ብላታ ወልደጊዮርጊስም ‹‹ … ሁላችንንም የሚያስንቀው አሀዱ ሳቡሬ የሚባለው ወጣት ጋዜጠኛ ይህ ነው … ምናልባት ጽሑፎቹን በጋዜጣ ላይ ሳይመለከቱና ድምፁንም በሬዲዮ ሳይሰሙት አይቀሩም … አሁን ደግሞ በአካል ላስተዋውቅዎ …›› በማለት ለነጋድራስ ተሰማ ይነግሯቸዋል። ነጋድራስ ተሰማም ‹‹ … እርሱንማ አውቀዋለሁ! አሀዱ ሳቡሬ … አሀዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ …›› የሚል ምላሽ ሰጡ። የነጋድራስ ተሰማ አገላለፅም በሕዝቡ ዘንድ ተሰራጭቶ በስፋት ታወቀ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ‹‹አሀዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ›› የሚለው ስያሜ /አገላለፅ/ የተለመደ ሆኖ ‹‹አሀዱ ሳቡሬ›› የሚባለው ስም ሲነሳ ‹‹አጠገበኝ ወሬ›› የሚለው ቅጥያ ይከተላል።
አሀዱ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስም በጋዜጣና ማስታወቂያ መስሪያ ቤት ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በ1953 ዓ.ም የፖለቲካ ታዛቢ ሆኖ የእርስ በእርስ ግጭት ወደነበረባትና ኢትዮጵያም ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደላከችባት ወደ ኮንጎ አመራ። በ1953 ዓ.ም የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ በቀዳማቂ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ተይዘው ለፍርድ ቀረቡ። አሀዱም የፍርድ ሂደቱን እየተከተለ ፍርዱ ሕግን የተከተለ ብቻ መሆኑን በጋዜጣና በሬዲዮ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያሳውቅ በመታዘዙ ከኮንጎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ለአንድ ሳምንት ያህል የፍርዱን ሂደት እየተከታተለ በዝርዝር አቀረበ። ሕዝቡም የፍርዱ ሂደት ይወጣባት የነበረችውን ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ እየተሻማ ገዝቶ አነበበ። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ሹማምንቱን ባለማስደሰቱ አሀዱ ‹‹ወደ ፍርድ ቤት ድርሽ እንዳትል!›› ተባለ። በግዞትም ወደ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ተልኮ ለአምስት ወራት ያህል በቁም እስረኛነት ተቀመጠ። አቶ አሀዱ ምህረት ተደረገለትና የግዞት እስረኛነቱ ተፈፀመ።
ከዚያም በመጀመሪያ በሶማሊያ ቀጥሎም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ሆነው እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ አገለገሉ። በየካቲት 1966 ዓ.ም የጸሐፌ ትዕዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ ተሰናብቶ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔ ሲያዋቅሩ አምባሳደር አሀዱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።
አቶ አሀዱ ሹመቱን የተቀበሉት በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት እንደታወጅና የማስታወቂያ መስሪያ ቤቱ አሠራርም እንደሚሻሻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን ቃል አስገብተው ነበር። ልጅ እንዳልካቸው ስለሹመቱ ለአምባሳደር አሀዱ በነገሯቸው ወቅት አምባሳደር አሀዱ ‹‹…ሹመቱን የምቀበለው በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት የሚታወጅ ከሆነና ምንም አላንቀሳቅስ ብሎ ያስቸገረው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚሻሻል ከሆነ ብቻ ነው፤ አለበለዚያ ሹመቱን አልቀበልም …›› በማለት ሹመቱን ለመቀበል ጠንካራና አገራዊ ፋይዳ ያለው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነበር። የኦክስፎርድ ምሩቅ የነበሩት ልጅ እንዳልካቸውም ‹‹ … የተማርኩት የጋዜጣ ነፃነት ባለበት አገር ነው። የፕሬስ ነፃነት ለአንዲት አገር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተማርኩበት አገር አይቻለሁ … እርስዎ ያሉት ነገር ይፈፀማል … ›› ብለው ሹመቱን እንዲቀበሉ አግባቧቸው።
አምባሳደር አሀዱም የጋዜጣ መስሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን ሰብስበው ሕዝባዊ ቁጣው እየበረታ ስለመጣ በተለመደው መንገድ መጓዝ እንደማይበጅና በዘርፉ ያሉትን ችግሮች መለየት እንደሚያስፈልግ በመንገር ሥራቸውን ጀመሩ። ይሁን እንጂ ሹማምንቱ በተለመደው መንገድ ከመጓዝ ውጭ ለሌላ ሃሳብ ቦታ ባለመስጠታቸውና በልጅ እንዳልካቸው የተገባላቸው ቃል ሊፈፀምላቸው ስላልቻለ አምባሳደር አሀዱ ኃላፊነታቸውን ለቀው ወደ ጅቡቲ ተመለሱ።
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ያቋቋሙት ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ›› መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውርዶ አገር መግዛት ሲጀምር የደርጉ የመጀመሪያ ሊቀ መንበር የነበሩት ሌተናንት ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አምባሳደር አሀዱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና ሽግግሩን እንዲያግዙ በጠየቋቸው መሠረት አምባሳደር አሀዱ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የሐረርጌ ክፍለ ሐገር ዋና አስተዳዳሪ ሆኑ። ከ11 ወራት የአስተዳዳሪነት አገልግሎታቸው በኋላ እርሳቸውም ‹‹በማላውቀው ምክንያት›› ብለው በገለፁት ሁኔታ በነሐሴ 1967 ዓ.ም ታሰሩ።
ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከተገደሉት (‹‹60ዎቹ››) የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ባለሥልጣናትና የጦር መሪዎች ከተረፉት ሹማምንት ጋር ታስረው የቆዩት አምባሳደር አሀዱ፤ ከሰባት ዓመታት እሥራት በኋላ መስከረም አንድ ቀን 1975 ዓ.ም ከእሥራት ተፈቱ። ከእሥራት ከተፈቱ በኋላም ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው ቆይተዋል።
አምባሳደር አሀዱ ከጋዜጠኝነቱና ከዲፕሎማሲው ባሻገር ‹‹የዓለም መስታወት›› እና ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፍፃሜና የደርግ አነሳስ›› የተሰኙ መጽሐፍትን ጽፈዋል።
ሀብታሙ ግርማ ደምሴ ‹‹የሥነ ጽሁፍ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው፡ ልቦለድ፣ የተውኔት ድርስት እና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ (1850-1960ዎቹ) በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ … በኢትዮጵያ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ታሪክ ታላቅ ቦታ የሚሰጣቸው አሀዱ ሳቡሬ ‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ› ጋዜጣ ስትመሰረት የጋዜጣዋ የመጀመሪያው ዋና አዘጋጅ ነበሩ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮም ለዓመታት ሠርተዋል፤ አሀዱ ሳቡሬ የሚለው ስም በተለይ በ1950ዎቹ እጅግ የገነነ እንደነበር ይነገራል፤ ለጋዜጠኝነት መርሆዎች በመገዛት ጥራት ያላቸውን የጋዜጣና የራዲዮ ፕሮግራሞች ያዘጋጁ መሆናቸው በህዝብ ዘንድ አድናቆትና እውቅና እንዲያገኙ አስችሏቸዋል …
አሀዱ ሳቡሬ ጋዜጠኝነት የራሱ የሆነ መርሆች እንዳሉት፣ ጋዜጠኞችም ለመርሆቹ ተገዥ መሆን እንዳለባቸውና ሙያው በዕውቀትና በትምህርት የተደገፈ መሆን እንዳለበት ያስገነዘቡ በሳል ጋዜጠኛ ናቸው፤ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በእጅጉ የተገደበ በነበረበት የአፄ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ አገዛዝ ወቅት ስለ ፕሬስ ነፃነት አስፈላጊነት በአደባባይ ይናገሩ ነበር፤ ለዚህ ተፈፃሚነትም የሚችሉትን አድርገዋል…
ብስለት በተመላበት ዘገባዎቻቸው በህዝብ የተደነቁ ጋዜጠኛ የነበሩት አሀዱ ሳቡሬ፤ ዘገባዎች እውነታን ሳይደፈጥጡ፣ ነገር ግን ከአገር ጥቅምና ክብር እንዲሁም ሉአላዊነት አንፃር የተቃኙ መሆን አለባቸው የሚል መርህ ነበራቸው…›› በማለት ስለአንጋፋው ጋዜጠኛና ዲፕሎማት አብራርተዋል።
በሎስ አንጀለስ ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዘውትረው ይታደሙና መንፈሳዊ ጉባዔዎች ሲዘጋጁም በአውደ ምኅረቱ ይገኙ የነበሩት አንጋፋው ዲፕሎማትና ጋዜጠኛ፤ ‹‹…በውጭ አገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንድ ቀን ወደ አገሩ፣ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል። በአዲስ እውቀት፣ በአዲስ ጉልበትና በአዲስ ችሎታ አገሩን ይገነባል። በዚህ አምናለሁ… ሁልጊዜም የምንፀልየው ስለኢትዮጵያ ነው…›› በማለት ሁልጊዜም ስለሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደሚፀልዩና እንደሚያስቡ በ2008 ዓ.ም በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።
አንጋፋው ጋዜጠኛ አሐዱ ሳቡሬ በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ለረጅም ጊዜ ሲኖሩ ቆይተው በወርሃ ህዳር/2012 ዓ.ም በተወለዱ በ 94 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
Filed in: Amharic