>

በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም እንዴት ማስፈን ይቻላል ? (መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም እንዴት ማስፈን ይቻላል ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

 

መግቢያ

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ኖቬምበር 4 2021 በሰሜን እዝ ላይ ድንገት በተከፈተ ጥቃት ምክንያት ላለፉት አስራ አምስት ወራቶች የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት በታሪክ ውስጥ አንደኛው አስከፊ ደም መፋሰስ የተካሄደበት እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እና ጋዜጠኞች የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡ ከተለያዩ የዜና አውታሮች ( በተለይም አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የጦር አዋቂዎችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት እንደዘገቡት ከሆነ) በመቶሺህዎች የሚቆጠር የሰው ህይወት አልፏል፣በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀዬቸው ተፈናቅለዋል፣ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሟል፣ ዛሬም ቢሆን የወያኔ ታጣቂ ቡድን በአፋር እና አማራ አንዳንድ አካባቢዎች ጦርነት እያካሄደ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በነገራችን ላይ ሁሉም ቡድኖች በቅን ልቦና ሆነው በጠረቤዛ ዙሪያ መነጋገረቸው ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላም ድርድር እየመጡ ነው በተባለበት በአሁኑ ግዜ የወያኔ ቡድን የሚከፍተው ጦርነት አሳሳቢ ነው፡፡ ሌላ ተጨማሪ የሲቪል ዜጎች ዋይታን ይፈጥራል፡፡ ንብረትም እንዲወድም ምክንያት ይሆናል፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ለማምጣት ብሔራዊ የውይይት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን እየተሰማ ይገኛል፡፡( ውጤቱ ወደፊት የሚታወቅ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም መንግስት እና ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች በቅን ልቦና መነጋገራቸው እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡) ይህ በእንዲህ እንዳለ 11 አባላት ያሉት የምክክር መድረኩ አባላት ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና ፈተና ለመፍታት በሚደረገው ውይይት  ያለአድሎው እንዲካሄድ ሃላፊነት ወስደዋል፡፡ እንዲሁም በታሪክ ፊት ቆመዋል፡፡ እነኚሁ በታሪክ ፊት የቆሙት 11 ሰዎች የኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የትኞቹ እንደሆኑ ከለዩ በኋላ እንዴት ኢትዮጵያ ከዚህ የታሪክ ፈተና ውስጥ መውጣት እንደምትችል መንገዱን ማመቻቸትና ለሰላም በር መክፈት አለባቸው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የምክክር መድረኩ አባላት ዋና ዋና ተግባራት መሃከል ሰላም እንዳይሰፍን መሰረታዊ ሳንካ የሆኑ ተግዳሮቶችን በተመለከተ በምን ያህል ስፋት፣ደረጃ እና ውስብስብነታቸውን በቅጡ መረዳት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች ስፋት፣ደረጃ፣ውስብስብነት በተመለከተ መረዳት ዋነኛ ተግባራቸው መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለሆነም ይህ የምክክር መድረክ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ መንግስታ ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ  ሰላምን በቀበሌ(በአካባቢ) ደረጃ፣ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲሰፍን የጋራ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ያለ ሰላም ሁሉም ከንቱ ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ንግግርም ሆነ ሌሎች ነገሮች አይታሰብም፡፡ በቅድሚያ በሀገሪቱ ሰላም መሰፍኑ አማራጭ የለውም፡፡

ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ 

ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ ምንድን ነው ?

ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ ሂደት ሲሆን  አጥፊ ግጭቶችንና ረብሻዎችን በመቀነስ፣በመከላከል ወይም እንዳይኖር በማድረግ መልካም የማህበረሰብ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡

ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ ሂደት በቅጡ ከተካሄደ በመዋቅር የሚደገፍ ረብሻን፣ መልከ ብዙ ኢፍትሃዊነትና ጭቆናን መሰረታዊ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅም ይረዳል፡፡ 

ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ ሂደት እውን ሊሆን የሚቻለው ደግሞ የማህበረሰቡን ስሪት (the social fabric) ወደ ግጭት የሚወስዱ መንገዶችን በመክላት ፣ ሰላማዊ ባህል (reconstructing a culture of peace ) በማስፈን ይሆናል፡፡ ጋልተንግ እና ፊሸር የተባሉ የውጭ ሀገር ምሁራን ስለ ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ በተመለከተ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያቀረቡት ቁም ነገር ጠቃሚ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

Sustainable peacebuilding can only be materialized by dismantling violent structures within the social fabric and reconstructing a culture of peace (Galtung, 2004; Galtung & Fischer, 2013). 

ዘለቄታ ያለውን ሰላም ለመገንባት በማእከላዊነትና በመጀመሪያ ደረጃ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ፣ እና በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ ኢፍትሀዊነት ድርጊቶች መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፣ እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህ እና ሰብአዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር መንግስት፣ህዝቡ እና የግል ባለሃብቱ፣ የሲቪል ማህበረሰቡና የፖለቲካ ሃይሎች፣የሀገር ሽግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ምሁራን ፣ ጋዜጠኞች ወዘተ ወዘተ ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈን አንድ ላይ በህብረት ተባብረው መስራት አለባቸው ብዬ አስባለሁ ፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ቁምነገሮች ባሻግር ዘለቄታ ያለው የሰላም ግንባታ የሰላም ባህልን የሚያስፋፋ( ህዝቡ ሰላማዊ ባህል የዘውትር ተግባሩ እንዲሆን..) እና የሁከትን ባህል መክላት የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ተቋማት ያስፈልጉታል፡፡ ይህን ቁምነገር ገቢራዊ ለማድረግ ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማትና ወኪሎች፣ የመብት አስከባሪ ድርጅቶች አብርክቷቸው የትዬሌሌ ነው፡፡ ስለሆነም በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ በክልልና ቀበሌ ገለልተኛ እና ነጻነታቸው የተጠበቀ ተቋማት መገንባት አማራጭ የለውም፡፡

ዘለቄታ ያለው ሰላም ለመገንባት በማህበረሰቡ ውስጥ የረብሻና ግጭት መነሻ የሆኑ መልከ ብዙ ምክንያቶችን መረዳት አስፈለላጊ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ተጨማሪ የግጭት መከላከያ ስልቶችን መንደፍ አስፈላጊ ነው፡፡

እረብሻ ( ግጭት) 

እረብሻ ማለት የብዙ ሰዎች ስነ ባህሪ ሲሆን  በአንድ ቡድን ወይም ግለሰብ ላይ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ማምጣት ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የረብሻ ስነ ባህሪ ያላቸው ግለሰቦች የእድሜ ጣሪያ እረጅም ላይሆን እንደሚችል የስነ ባህሪ ምሁራን በጥናታቸው ውስጥ አስቀምተውታል፡፡ ለአብነት ያህል ሬይችለር የተሰኘ የስነ ባህሪ ምሁር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ካቀረበው የጥናት መጽሐፍ የሚከተለው ይጠቀሳል፡፡

Reychler (2001) sees violence as a condition whereby the life expectancy of the target is intentionally reduced

ሁላችንም መረዳት እንደምንችለው እረብሻ ወይም ግጭቶች በሰፈኑባቸው አካባቢዎች ግድያ፣አካላዊ ጉዳት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የስነ ልቦና ችግር እውን መሆኑ አይቀሬ መራር እውነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አውዳሚ ረብሻ ማህበራዊ ቀውስ፣ በህዝብ ፣ ንብረትና አካባቢ ላይ  ሊጠገን የማይችል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ለአብነት ያህል በቅርቡ አውሮፓዊቷ ሀገር ዩክሬን ላይ እየወረደ ያለውን መዓት ከአለም መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እየተከታተልን እንገኛለን፡፡

ስለሆነም ዘለቄታ ያለው ሰላም ለማስፈን እረብሻ ወይም ግጭት በሰውነት አካል ላይ፣ስነልቦና፣ ባህልና አካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ፡፡

አካላዊ ረብሻ ምንድን ነው ? አካላዊ ረብሻ በሰው ላይ አካላዊ ጉዳት፣ ንብረት ለማውደም ግለሰብን ወይም በርካታ ሰዎችን ለመግደል ሲሉ  ሌሎች ሁከት ፈጣሪዎች የሃይል እርምጃ የሚወስዱበት እኩይ ድርጊት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ  ወይም የተደራጁ ቡድኖች ወይም ሀገራት ሁከት በመቀስቀስ( ወይም ጦርነት በመክፈት)  በሰውና ንብረት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት የታወቀ እና የሚታይ አካላዊ የረብሻ አይነት እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ጦርነትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የሰውን ልጅ ህይወት የሚቀጥፉ፣ ለንብረት መውደም እና ለአከባቢ ውድመት ምክንያት የሚሆኑ በስፋት የታወቁ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ረብሻና ግጭቶችን ማስቆም ካልተቻለ በመጪው ግዜ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ላይ ጥላውን ማጥላቱ አይቀሬ መራር እውነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በቅድሚያ ዘለቄታ ያለው ሰላም መስፈን የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

ስነ ልቦናዊ ረብሻ ምንድን ነው (Psychological violence) ? ፡- ሌላው የግጭት ወይም የረብሻ አይነት ሲሆን ዋነኛ አላማው የሰውን አይምሮ እና የስነልቦና ሁኔታ መጉዳት ነው፡፡ ከአካላዊ ረብሻ ወይም ግጭት የተለየ ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው በአይን የሚታይ አይደለም፡፡ የሰውንም ስሜት የሚጎዳ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ግዛቶች የተካሄዱ እና አሁንም የሚከሰቱ ግጭቶች በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ  አውዳሚ ጭንቀት፣የስሜት መረበሽ እና የስነልቦና ውድቀትበ የፈጠሩ ወይም  የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የስነ ልቦናን ረብሻ እና ጭንቀትን ማስቆም ወይም መቀነስ  ካልተቻለ ዘለቄታ ያለውን ሰላም ለማስፈን የሚቻል አይደለም፡፡ ( በዜጎች ላይ የስነ ልቦናን ቀውስ የሚፈጥሩ ረብሻዎችን መቀነስ ካልተቻለ ሰላም ማስፈን አይታሰብም፡፡) 

መዋቅራዊ ረብሻ ምንድን ነው (Structural violence )፡- ይህ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገነባ ፣ ሃይለኛና አውዳሚ የረብሻ አይነት እና ለማየት አስቸጋሪ የሆነ ሲሆን፣ ግለሰቦች፣ ማህበረሰቡ እና ቡድኖች ስርአታዊ በሆነ መንገድ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸው እና ክብራቸው እንዲገፈፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ( ለአብነት ያህል በአንድ የተወሰነ አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ የተጠቀሱት መብቶቹ ስርአታዊ በሆነ ዘዴ እንደሚነፈጉ ስርክአዲስ ከመገናኛ ብዙሃን የሚደመጥ አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ )

መዋቅራዊ ረብሻ ጭቆናን ይወልዳል፣ሰዎችን የበላይና የበታች (maintains social hierarchies) ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ለወደፊቱ የበለጠ የሚጨቆኑ እጅጉን የተገለሉ ማህበረሰቦችን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ( መማር ከቻለን በሩዋንዳ እና በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሄርዞጎቪኒያ ያ/ ሁሉ የዘር ፍጅት የተከሰተው  ማህበረሰብን ከፍና ዝቅ አድርጎ የመከፋፈል እኩይ ድርጊት በመፈጸሙ ነበር፡፡) 

በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት ውድቀት መሰረታዊ ምክንያቱ መዋቅራዊ ረብሻ እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣  የማህበራዊ ፖለቲካዊ  እና የባህል አውድ እድገቷን በተመለከተ ሙሉ እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡( it is important to fully understand the historical, contextual, sociopolitical, and cultural dynamics of Ethiopia )

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎሳና ቋንቋ ላይ መሰረቱን ያደረገው ህገመንግስት በኢትዮጵያ ምድር በየግዜው እንደ ሰደድ እሳት ለሚቀጣጠሉ ግጭቶች መሰረታዊ ምክንያት እንደሆነ በርካታ የህገመንግስትና የግጭት አጥኚዎች በጥናታቸው የደረሱበት ጉዳይ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ህገመንግስት የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ ብዙ ባህሎች የሚገኙባት ኢትዮጵያን በቋንቋና ጎሳ እንደከፋፈላት ምሁራን አበክረው የገለጹት መራር እውነት ነው፡፡ በአጭሩ ህገመንግስቱ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

እንደ እነ ዶክተር ያቆብ ሀይለማርያም፣ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሼ ክሌ ሙላት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ( የሶስቱንም አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ነፍስ ከደጋጎቹ አባቶቻችን ጎን ያሳርፍልን ) ወዘተ ወዘተ አይናቸው ደም እስኪመስል፣ እጃቸው እስኪዝል ድረስ ባቀረቡት ምክተ ሃሳብ መሰረት  በጎሳ ማንነት ላይ የቆመ መንግስት፣ ምጣኔ ሀብት፣ የትምህርና ማህበራዊ ፖሊሲ ውጤቱ አውዳሚ ነው፡፡ ብዙሃኑን ህዝብ የሚያወድምና የሚያቆረቁዝ ሲሆን ጥቂት የየጎሳው ኤሊቶችን በእጅጉ የሚጠቅም ነው፡፡

በአጭሩ መዋቅራዊ ረብሻ እንዲቆም ማድረጉ ለሰላም በር ይከፍታል፡፡ ከዚህ ባሻግር ህገመንግስቱ የሚሻሻልበት የሰለጠነ መንገድ ካልተፈለገ በቀር በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም ማስፈን በእጅጉ ክቡድ የሚሆን ይመስለኛል፡፡

የረብሻ ባህል በሰረጸበት ማህበረሰብ መዋቅራዊ ረብሻ እንዲያብብ ይረዳል፡፡ በሌላ አነጋገር የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለመጨቆን ለመበደል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ( በደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶና ሌሎች አካባቢ የሚገኙ በርካታ የፖለቲካ ተፎካካሪ ፖለቲካ አባላት ላይ የሚደርስ ግፍ መሰረቱ መዋቅራዊ ረብሻ ነው፡፡)

በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ባህለዊ የግጭት ማስወገጃ ዘዴዎችን ችላ ማለት ግጭቶች እንዲባባሱ የሚያደርግ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ጦርነት ተቀስቅሶ ንጹሃን ሲቨል ዜጎች ይሰቃያሉ፣ መከራቸውን ይቆጥራሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መልኩ የረብሻ ባህል ወደ የሰላም ባል አይነት መቀየር ዘለቄታዊ ሰላምን ለመገንባት ያስችለናል፡፡ በአጠቃላይ  በኢትዮጵያ ምድር ከላይ በዝርዝር የተሄደባቸውን ማለትም አካላዊ፣ስነልቦናዊ፣ መዋቅራዊ እና ባህላዊ የረብሻ አይነቶችን መቀነስ ከተቻለ ዘለቄታዊ የሰላም ሂደትን ለመገንባት ያስችለናል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡

ለዘለቄታዊ ሰላም  ጭቆና ምንና ምን

ለዘለቄታዊ ሰላም እውን መሆን ጭቆና እና የጭቆና  መዋቅር መከላት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ ወይም ስስ ተረከዝ (Ethiopia’s Achilles) ማለትም ኢትዮጵያን ያዳከመና ለህልውናዋ አደጋ የሆነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ በራሱ የጨቋኝነት ባህሪ የተላበሰ በመሆኑ፣ ጭቆናን ለመክላት አይበጅም፡፡

የጎሳ ፖለቲካ  ፖሊሲ ማእከላዊ ነጥብ የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ ለመግዛት የታለመ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እና የህግ ሰዎች በጥናታዊ ጽሁፎቻቸው የገለጹት ጉዳይ ነው፡፡ባለፉት ሰላሳ አመታትና ከዚያም በላይ በኢትዮጵያ ምድር የተዘራው የጎሳ ፖለቲካ ዘር ፍሬው እረብሻ፣ልዩነት ላይ ብቻ ማተኮር፣ ጭቆናና የሰውነት ክብርን መቀነስ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ዘለቄታ ያለው ሰላም ለማስፈን አልተቻለም፡፡

በኢትዮጵያ ዘለቄታ ያለው ሰላም ለማስፍን ከተፈለገ ኢትዮጵያን በጎሳ እና ቋንቋ መስፈርት እንድተከፋፈል ያደረገው ሕገመንግስት በሰለጠነ መንገድ መሻሻል እንዳለበት ህሊና የፈጠረባቸው ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ የሞከሩበት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ይህን አስቸጋሪ ግዜ ካለፈች፣ በኢትዮጵያ ሰማየ ሰማያት ላይ ሰላም ይሰፍናል፡፡

ዘለቄታዊ ሰላም፣ ብሔራዊ እርቅና ብሔራዊ ፈውስ

እርቅ ማለት አንድ ሀገር ወደ ነበረችበት መልካም ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ሂደት ነው፡፡ ሰፍኖ የነበረውን ጭቆና፣ የስነ ልቦና ጫናንም ለማከም ይረዳል፡፡ ይህም ማለት የተሰራው በደል፣ ግፍና ጭቆና ይረሳል ማለት አይደለም፡፡ እርቅ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ እና ስሜታዊ ቁስልን ለማከም የሚረዳ አንድ ደረጃ ነው፡፡ እውነተኛ እርቅ ተበዳዮች የደረሰባቸውን ግፍ ሁሉ ተደብቆ እንዳይቀር የሚረዳ ነው፡፡ ይህ ሂደት ገቢራዊ ከሆነ ግፍ ፈጻሚዎችና ተበዳዮች ( ግፍ የተፈጸመባቸው) ለወደፊቱ መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው ይረዳል፡፡ ለብዙ አመታት በተከሰተ ረብሻ ምክንያት ግፍ የተፈጸመባቸው ሰዎች ህክምና ከተሰጣቸው ዘለቄታ ያለው ሰላም ይሰፍናል፡፡ በኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ለአመታት በዘለቀ ግጭትና እረብሻ የተጎዱ ሰዎች፣ የተበደሉ ሰዎች፣ ፈውስ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የተፈጸሙ ግፎችን ወይም በደልን መደበቅ ግዜ እየጠበቀ እንደሚፈነዳ ፈንጂ ይቆጠራል

ሁላችንም መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር በደልና ስቃይ በሲቪል ዜጎች ላይ የፈጸሙ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ወይም የስነልቦና ጫና እና ጭንቀት በህብረተሰቡ ላይ እንዲደርስ ምክንያት የሆኑ ሰዎች የፈጸሙትን ግፍና በደል ማመን አለባቸው፡፡ ስለተፈጸሙ ግፍች ሁሉ እውነቱ መነገር አለበት፡፡ ለአብነት ያህል በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ክፉ ዘመን የተፈጸሙ ግፎች ሁሉ በአደባባይ በመነገሩ ቱዋንዳ ዛሬ ፈውስ አግኝታ በእድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች ትገኛለች፡፡ እውነቱ ካልተነገር ግጭቶችና ረብሻዎች እንደገና እያገረሹ አንድን ሀገር ምስቅልቅሎሽ ውስጥ እንድትዶል ምክንያት ይሆናል፡፡ 

ለአመታት በዘለቀ ረብሻ፣ሽብር፣ እና ግፍ የተነሳ በኢትዮጵያ ምድር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አካላዊ፣ ስነልቦናዊ እና ስሜታዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከዚህ በደል ባሻግር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዝብር ዜጎች በሀገራቸው ምድር ባይተዋር ሆነዋል፣እትብታቸው ከተቀበረበት ቀዬ ተፈናቅለዋል፡፡ ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ቢኖር በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግፎችን፣ ኢፍትሐዊነት፣ ማጣራትና መናገር በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን በእጅጉ የሚረዳ ነው፡፡ በድጋሚ ለማስታወስ ሩዋንዳም ሆነች የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ዛሬ ፈውስ አግኝተው ሰላም የሰፈነባቸው ሀገራት የሆኑት በሁለቱም ሀገራት የተፈጸሙ ግፎች ሳይደበቁ በፍትህ አደባባይ ስለተገረ ነበር፡፡ ( በዳይና ተበዳይ ፊትለፊት ተገናኝተው የተፈጸሙ ግፎች ሁሉ ላይ ተማምነው ነበር፡፡ )

በተጎጂው ህብረተሰብ እና በመንግስት አካላት፣ እንዲሁም በህብረተሰቡ መሃከል የሚደረግ እርቅ የጋራ ፈውስ ያመጣል (Collective Healing in the Vertical and Horizontal Reconciliation Proces ) 

የጋራ ፈውስ  ፣ የስነ ልቦና ጫናን ማሰወገድ ወይም መቀነስ በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈን በእጅጉ የሚበጅ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ጎንዮሽ ( ማህበረሰቡ ውስጥ) እና ወደላይ ( ከታችኛው የመንግስት መዋቅር እስከላይኛው ድረስ) የሚፈጸም እርቅ ሰላምን ለመገንባት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

በመንግስትና በህብረተሰቡ መሃከል የሚደረግ እርቅ( Vertical reconciliation) የእርቅ ሂደት ሲሆን እርቁም የሚካሄደው በመንግስት ተቋማት ሃላፊዎች ወይም ባለስልጣናት ( አካባቢ(ቀበሌ)፣ ክልልና ፌዴራል )፣ እና ተጎጂዎች ( ማለትም በመንግስት ቸልተኝነት ምክንያት በተቀሰቀሱ ግጭቶች የተጎዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ) መሃከል የሚደረግ እርቅ ሰላም ለማስፈን የሚረዳ አንደኛው ሂደት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ላይ መንግስት በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ የፈጸመው የስብአዊ መብትም ሆነ ሌሎች የመብት ጥሰቶች በግልጽ መቀመጥ ይገባዋል፡፡

የአካባቢ፣የክልል፣ የከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ እና የፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣናት ለተፈጸሙ በደሎች ሁሉ ሃላፊነቱን ከወሰዱ በኋላ ከህብረተሰቡ ጋር እርቅ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

አንደኛው ማህበረሰብ ከሌላኛው ማህበረሰብ ጋር የሚያደርገው የእርቅ ሂደት በርካታ የማህበረሰብ አካላትን አንድ ላይ ሊያሰባስብ ይቻለዋል፡፡ ይህም ማለት የተለያዩ የጎሳ አባላት፣የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችና ባህል ያላቸውን ግለሰቦችና ማህበረሰቦችን የሚያቀራርብ ነው፡፡ ሁሉም እርቅ ያወርዳሉ፣ፈውስም ያገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በሃይማኖትና ጎሳ ልዩነት ምክንያት በተለያዩ ግዜያትና በተለያዩ ስፍራዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ረብሻ ምክንያት በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በሚገኙ ማህበረሰቦች ዘንድ መቃቃር ፈጥሯል፡፡ የነበረውን መልካም ግንኙነት አሻክሮታል፡፡ ስለሆነም በህብረተሰቡ መሃከል የሚደረጉ የእርቅ ሂደቶች ዘለቄታዊ ሰላም ለማውረድ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ 

ወደፊት መመልከት

ዘላቂ ሰላም እውን ሊሆን የሚችል ስትራቴጂ ያስፈልገዋል፡፡ ( መሬት ላይ የሚውል ስትራቴጂ ያስፈልገዋል፡፡) ከዚህ አኳያ ገቢራዊ ሊሆን የሚችል የግጭት ማስወገጃ ስትራቴጂ ግጭትን ለመፍታት ጤናማ መንገድ ይፈጥራል፡፡ በነገራችን ላይ  በኢትዮጵያ ገቢራዊ የሆኑት የግጭት መፍቻ ስትራቴጂዎች ውጤታማ እንዳልነበሩ በርካታ የመስኩ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያ ግጭቶችን ለመፍታት ገቢራዊ የሆኑ ስልቶች ውጤታማ አልነበሩም፡፡

ስለሆነም በኢትዮጵያ እውነተኛ ሰላም ለማስፈን በቅድሚያ የሽግግር ፍትህ ገቢራዊ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የኢትዮጵያ ህዝብ ወደፊት ማየት አለበት እላለሁ፡፡ ወደፊት ለመመልከት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ፈውስ ማግኘት አለበት፡፡ ፈውስ ለማግኘት ደግሞ ሰፊ እርቅ(በታሪክ አጋጣሚ፣በፖለቲካና ኢኮኖሚዊ ምክንያቶች  በህብረተሰቡና በመንግስት፣በህብረተሰቡ መሃከል የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማከም  እርቅ መውረድ አለበት) ይህም ማለት የተፈጸሙ በደሎች ሁሉ በግልጽ እና እውነት መሰረት ላይ መነገር አለባቸው፡፡ በዳይና ተበዳይ ፊትለፊት ተገናኝተው ይቅር ለእግዛብሔር መባባል አለባቸው፡፡ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከአመታት የተፈጸሙ በደሎች ሁሉ መነገር አለባቸው፡፡ እዚህ በዚች አጭር ጽሁፍ ይህን ለመዳሰስ አስቸጋሪ እንደሆነ አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡

ለአብነት ያህል ለአለፉት በርካታ አስርተ አመታት በሀገራችን በሰፈነው ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ፣ እና ታሪካዊ ሁነት ላይ በብዙዎች ዘንድ እጅጉን የተራራቅ ልዩነት አለ፡፡ ለአብነት ያህል በብዙዎች የፖለቲካ ልሂቃን አኳያ በኢትዮጵያ ታሪክ አረዳድ ላይ እጅጉን የሰፋ ልዩነት አለ፡፡ በአጭሩ ያላቸው ልዩነት  ዋልታ ረገጥ ነው፡፡ ላለመስማማት መስማማት እንኳን አልቻሉም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢትዮጵውያን ወደፊት በመመልከት በኢትዮጵያ ምድር ዘላቂ ሰላም ስለሚሰፍንበት መንገድ በየሰፈራቸው እንዲወያዩ ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡

ምክረሃሳብ  (Recommendations )

ገቢራዊ ሊሆን የሚችል የግጭት መፍቻ ስትራቴጂ መንደፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ይበጃል፡፡ ስለሆነም የሚከተሉት ነጥቦች ገቢራዊ ከሆኑ ዘላቂ ሰላም ያሰፍናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

  1. በሀገራችን በአሁኑ ግዜ የሚከሰቱና የሚታዩ ግጭቶች መወገድ አለባቸው፡፡ በርግጥ ሰላማዊ በሆነ ዘዴ ግጭቶችን መፍታት ይመከራል፡፡ ለበርካታ ግዜያት ግን ሰላማዊ የግጭት አፈታት ዘዴ በኢትዮጵያ ውጤታማ ሲሆን አይታይም፡፡ ለአብነት ያህል በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትና በማእከላዊው መንግስት መሃከል ለአለፉት 15 ወራቶች ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ሁለቱም ሀይሎች በመሃከላቸው የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት የተጠቀሙት ጉልበትና ጡንቻቸውን ነበር፡፡ በጉልበት ግን አሁን ድረስ እውነተኛ ሰላም አልሰፈነም፡፡ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን በበኩሉ ግጭት በመፍጠር ይታወቃል፡፡ ለማናቸውም በኢትዮጵ ምድር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ በጠረቤዛ ዙሪያ ውይይት አስፈላጊ ነው፡፡
  2. አማጺ ሀይሎችን ትጥቅ ማስፈታት እና ሰላማዊ ኑሮ እንዲጀምሩ የሚጨበጥ ተግባር ማከናወን፣በጦርነትና ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሲቪል ዜጎችን መልሶ ማቋቋም፣ወደ ቀደመው ኑሮአቸው መመለስ ለሰላም ይበጃል
  3. በማህበረሰቡ መሃከል የተሰበሩ ግንኙነቶችን መልሶ መጠገን፣ በህብረተሰቡ መሃከል እምነትን ያሳድራል፡፡ ለአብነት ያህል በሰሜን ኢትዮጵያ የአማራና የትግራይ ወንድሞቻችን  ማህበራዊ ግንኙነት ወደ ነበረው እንደ ጥንቱ፣ እንደጠዋቱ የሚመለስበት መንገድ እንዴት እንደሆነ ባለሙያዎች በጥልቀት ማጥናት አለባቸው፡፡
  4. በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮችን ለአብነት ያህል ዩንቨርስቲዎችን፣ተምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማት፣ መንገዶች፣ድልድዮች፣ እና የሲቪል ዜጎች መኖሪ ቤቶች ተመልሰው መገንባት አለባቸው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የመንግስትና የግለሰቦች ንብረቶች ተመልሰው ከተገነቡ ህብረተሰቡ በራስ መተማመን ያድርበታል፣ለሰላምም የሚጠቅም ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የፍትሕ ስርአቱን ማሻሻል የህግ የበላይነት እንዲከበር ይረዳል፡፡ ፍትህ መስፈኑ ረብሻና ግጭት እንዳይኖሩ በመከላከል ለሰላም መስፈን በእጅጉ ይረዳል፡፡
  5. በግጭት ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ በሲቪል ዜጎች ላይ ስለሚፈጸሙ ግፎች፣በደሎች፣ እንዲሁም በአካላቸው ላይ፣ስነ ልቦናቸው ላይ የደረሰባቸውን ጉዳት መለየት፣ ለሰላም መስፈን ይረዳል፡፡ ስትራቴጂክ እቅድ ማውጣትና ገቢራዊ ማድረግም ለዘለቄታው ሰላም ይረዳል፡፡
  6. የህግ የበላይነት፣ ፍትህ፣ትምህርት፣ ሰብአዊ መብት፣ እንዲከበሩ የሚያስተምሩ ከፍተኛ ተቋማትና የመብት አስከባሪ ድርጅቶችን ማጠናከርና ነጻነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መስራቱ ተገቢ ነው፡፡
  7. ለዘለቄታዊ ሰላም መስፈን ከአለም አቀፍ የውጭ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረገም ጠቃሚ ነው፡፡

በመጨረሻም ይቅር ለእግዜአብሔር ለመባባል፣ፈውስ ለማግኘት፣ የግጭት አዙሪትን ለመስበር፣ መንፈሰ ጠንካራ በመሆን ወደፊት ማየት አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ አለበለዚያ ውሃ ወቃጣ አይነት ከሆነው የግጭት አዙሪት በጭራሽ መውጣት አንችልም፡፡ ይህ የግጭት አዙሪት ሁላችንንም ይበላናል፡፡ በተለይም በሃይማኖት አኳያ ወደ ግጭት ውስጥ መግባት ለማንም አይበጅም፡፡ ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ አመታት በሃይማኖት ተቻችላ የኖረች ሀገር ናት፡፡ ይህ በጣም አስጊ እና አደገኛ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቁጭ ብለነ በሰከነ መንፈስ መነጋገር አለብን፡፡ ድህነቱ ይበቃናል፡፡ ሰላም፡፡

we need to realize that somehow, we must find ways to be brave, bold, forgiving, heal, break the cycle of violence, and move forward collectively. Otherwise, the vicious violent cycle we inflict on one another will consume all of us. 

Filed in: Amharic