>
5:14 pm - Saturday April 20, 3157

ምን እደረጋለሁ በሚል ስሜት  የሚጣል ማእቀብ ማህበረሰብን ያናጋል (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

ምን እደረጋለሁ በሚል ስሜት  የሚጣል ማእቀብ ማህበረሰብን ያናጋል

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungess@gmail.com


እንደ መግቢያ

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስለ HR 6600 ሊገነዘበው የሚገባ…!

 

የዛሬው ጽሁፌ ዋነኛ ጭብጥ ይህ ኤችአር ረቂቅ ሕግ 6600 መጽደቅ አለበት ወይም የለበትም የሚል ክርክር ለመጫር አይደለም፡፡ አላማዬ የዚህን ረቂቅ ህግ ምንነት  እና ህግ ሆኖ ከጸደቀ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በተመለከተ ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ በአሜሪካ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ኤችአር 6600 ምን ይዟል?

የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዲስ ኤችአር 6600 የተባለ ረቂቅ ሕግ አስተዋውቀዋል።

ይህ በኒውጀርሲው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖወስኪ ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዋወቀው ረቂቅ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ “በኢትዮጵያ ላይ የሚያርፈው ጠንካራ የአሜሪካ ክንድ” እንደሚሆን በአንዳንድ ምሁራን በብዙ ተጽፎለታል፣ወይም ተብሎለታል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት አጥብቀው የተቃወሙት ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንት ባይደን የሚጸድቅ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ አዲስ ማዕቀብ ትጥላለች የሚል ብርቱ ስጋት በብዙ ኢትዮጵያዊ ወንድሞች አይምሮ ውስጥ ፈጥሯል።

የዚህ ረቂቅ ሕግ ይዘት ምንድን ነው?

ይህ ረቂቅ ሕግ ለአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‘የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሕግ’ (Ethiopia Stabilization, Peace, and Democracy Act) በሚል ስያሜ ቀርቧል።

ረቂቅ ሕጉን ለምክር ቤቱ ያስተዋወቁት የኮንግረስ አባላት እና ኑሮአቸውን በተባበሩት መንግስታት ያደረጉት እንደነ አቶ ቴዎድሮስን የመሰሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥረቶችን ለመደገፍ ያስችላል ይላሉ።

ይህ ረቂቅ ሕግ ጥር 27 2014 ዓ.ም. ለውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ለሕግ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ለፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለመከላከያ አገልግሎቶች እንደተመራ ከተለያዩ የዜና አውታሮች ተሰምቷል።

ፕሬዚዳንት ባይደን በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ አንደፈረሙ በመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡

ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ መረጋጋት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዳይኖር ምክንያት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ ተጠያቂነትን ለማምጣት ፕሬዝደንት ባይደን ማዕቀብ እንዲጥሉባቸው የሚጠይቅ እንደሆነም በብዙ ኢትዮጵያዊ ምሁራንና በአንዳድ አሜሪካዊ የኮንግሬስ አባላት ሳይቀር እየተነገረ ነው።

ግለሰቦች ላይ የሚያነጣጥሩት ማዕቀቦች የንብረት እግድ እና የቪዛ ማዕቀቦችን ያጠቃልላሉ። 

በተጨማሪም፦

  • በትግራዩ ጦርነትም ሆነ በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ግጭቶች ዙሪያ የተኩስ አቁም ወይም ድርድር እንዳይደረግ እንቅፋት የሆነ ወይም ስምምነት እንዳይደረስ ጥረት ያደረገ፤

     የትግራዩ ግጭትም ወይም ሌሎች በአገሪቱ ያሉ ግጭቶች እንዲስፋፉ ምክንያት የሆነ ወይም የተባበረ፣    

  • የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸመ፣ የጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት እና ሌሎች በደሎችን የፈጸመ፤
  • የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆነ እና በሰብዓዊ እርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ጥቃት የሰነዘረ፣ ለመሰንዘር ያቀደ፣ የመራ፤
  • በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት የተሳተፈ ወይም በፋይናንስ የደገፈ፤

ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ በፕሬዝደንት ባይደን ይወሰናል። ከንብረት እግዱ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመዋል የሚባሉ ግለሰቦች የጉዞ እገዳ ይጠብቃቸዋል።

ክልከላዎቹን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች ቀድሞ በነበራቸው ቪዛ አሜሪካ መግባት አይችሉም፤ አዲስ ቪዛ አመልክተው ማግኘት አይችሉም እንዲሁም ይዘው የሚገኙት ቪዛ ይሰረዛል የሚሉ ይገኙበታል።

እግዱ በላይ በተጠቀሱት ግለሰቦች ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት፣ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት ጋር፣ ከአውሮፓ እና ከአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይተባበራሉ ይላል ረቂቅ ሕጉ።

የደኅንነት እና ፀጥታ ድጋፍ ላይ የሚጣለው ገደብ

ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንቱ ከጸደቀበት ዕለት አንስቶ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የምታደርገው የደኅንነት እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ መልሶ የሚቀጥለው አሜሪካ ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ተረጋግጦ ለሚመለከተው የኮንግረስ ኮሚቴ ከቀረበ በኋላ ነው።

አሜሪካ ካስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል፡-

የኢትዮጵያ መንግሥት በእርስ በርሱ ጦርነትም ሆነ በሌሎች ግጭቶች የማጥቃት ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሙሉ በሙሉ ሲያቆም፤

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ድርድር፤ ሕጋዊ እና ሁሉን አካታች ወደ ሆነ ብሔራዊ ምክክር ለመግባት እርምጃዎችን ሲወስድ፤

መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለመጠበቅ ጥረት ማድረጉ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መፍቀዱ ሲረጋገጥ፤ የሚሉት ቅድመ ሁኔታዎች ይገኙበታል።

ረቂቅ ሕጉ በኒው ጀርሲው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖወስኪ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተዋውቋል፡፡

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል የሚጣለው ገደብ

ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት የሚሰጡ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳይፈቀዱ አሜሪካ ተሰሚነቷን እና ድምጽ የመስጠት መብቷን ትጠቀማለች ይላል ረቂቅ ሕጉ።

ከዚህ በተጨማሪም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ለማጠናከር እና ሰላምን ለማምጣት አሜሪካ ከሌሎች ቁልፍ ድጋፍ አድራጊዎች ጋር ፖሊሲ ታበለጽጋለች።

ረቂቅ ሕጉ ይህ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን እና ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚደረጉ ድጋፎችን አይመለከትም።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፍ ክልከላ የሚቆመው በተመሳሳይ ከላይ የተጠቀሱት የአሜሪካ መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎች ሲረጋገጡ ነው።

ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚደረግ ጥረት

ረቂቅ ሕጉ በትግራዩ የእርስ በርስ ጦርነት እና በሌሎች ግጭቶች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊነት መብት ጥሰቶችን እና ለወንጀሎቹ ተጠያቂዎች ናቸው የተባሉትን ለመለየት ፕሬዝደንት ባይደን የገንዘብ፣ የፋይናንስ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ማድረግ እንዳለባቸው ይጠይቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ ሕጉ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለሚመረምሩ ተዓማኒነት ላላቸው ድርጅቶች የአሜሪካ መንግሥት መረጃ እንዲያጋራ ያስገድዳል።

ረቂቅ ሕጉ ዓላማው ምንድን ነው?

ይህን ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የኒው ጀርሲው የኮንግረስ አባል፤ ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዲመጣ የሚደረገውን ጥረት ያጠናክራል፤ የሰብዓዊ እርዳታ እና የዲሞክራሲ ግንባታን ያጠናክራል ይላሉ።

በተጨማሪም ረቂቅ ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን፤ የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ጨምሮ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እርስ በርስ በመተባበር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና ሌሎች ግጭቶች እንዲቆሙ ስትራቴጂ ይነድፋሉ።

እነዚህ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እና ለሌሎች በደሎች ተጠያቂነትን እንዲኖር ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲያብብ፣ የሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ እና እርቅ እንዲወርድ ሌላው የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ተልዕኮ እንደሚሆን በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ ሰፍሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ አሜሪካ በግጭቱ ውስጥ ሚና አላቸው በሚባሉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለሥልጣናት እንዲሁም በአማራ ክልል እና በህወሓት መሪዎች ላይ ከዚህ በፊት የቪዛ ዕቀባ ጥላ ነበር።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው የተለያዩ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ ወገኖች ላይ ያነጣጠረ ዕቀባን ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።

ይህ በሂደት ላይ የሚገኘው ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖን ሊያስከችል እንደሚችል ይታመናል።

አፍሪካና ኢትዮጵያ

ሰርክ አዲስ የሚከተለውን ጥያቄ ለራሴ አቀርባለሁኝ፡፡ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ እውን የሆነው አለም አቀፉ ኦርደር በ21ኛው ክፍለ ዘመን በፈጣን ሁኔታ እየተለወጠች ላለችው አፍሪካ ተስማሚ ነውን ? የሚለው ጥያቄ ነው በአይምሮዬ ጓዳ የሚመላለሰው፡፡ አፍሪካ የ1.3 ቢሊዮን ህዝብ መኖሪያ ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መኖሪያ ናት፡፡ አብዛኛው የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ በወጣት የእድሜ ክልል የሚገኝ ነው፡፡ እንደ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ጥናት ውጤት ከሆነ የአፍሪካ አመታዊ የምርት እድገቷ 3 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል፡፡ Its GDP is over three trillion dollars ፡፡የአለሙ ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚፈልጋቸው ውድ ማእድናትም በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በዚች በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው አፍሪካ የጂኦግራፊ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሀገራት ገና ከድህነት አለም ውስጥ አልወጡም፡፡ ዛሬም የማህበራዊ እድገት አላመጡም፡፡ ለአብነት ያህል በአለም ላይ ካሉ ሀገራት ሁሉ በላቀ ሁኔታ በማእድን ሀብቷ እጅጉን የበለጸገችው የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ምእራባውያን በሰሩት ሸፍጥና ሴራ፣ እንዲሁም በራሷ መርገምት አምባገነን መሪዎቿ ጭካኔና ዳተኝነት ምክንያት የተነሳ ህዝቧ ለከፋ ድህነትና ስቃይ ተዳርጎ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር ለኮንጎ ህዝብ ምድራዊ ስቃይ መቀበል የምእራቡ አለም ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ለምን እንዲሆነ ብሎ መጠየቅ ግዜው አሁን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

አፍሪካ በብየነ መንግስታቱ የጸጥታው ጥበቃ ምክርቤት ውስጥ ሁነኛ ቦታ ለማግኘት ችሎታ እንደ አላት ብዙዎች የፖለቲካ ሃያስያን የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአለም መንግስታት ስነ ህንጻ በአብዛኛው በምእራባውያኑ በሚዘወረው የተባበሩት መንግስታት ስርአት ተጽእኖ ውስጥ የወደቀ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአንድም በሌላ መልኩ የምእራባውያን ሀገራት ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ከ1.3 ቢሊዮን ባላይ የሆነውን የአፍሪካ ህዝብ ፍላጎት፣ተስፋ እና ምኞት ለማሟላት ከተፈለገ በአለም ላይ ሚዛናዊ የሆነ የንግድ ስርአት መስፈን አለበት፡፡ ከዚህ ባሻግር የኮቪዲ በሽታ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት ሳይንሳዊ ዘዴ ገቢራዊ ስለመሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአፍሪካ የሚመደብ በጀት፣ ከአንደኛው የአለም ክፍል ወደ ሌላው የአለም ክፍል ለከት ያጣውን የህዝብ ፍልሰትን ወይም ስደትን ለመቀነስ ፣ በአምባገነኖች ላይ ማእቀብ መጣልን በተመለከተ፣የአየር ጸባይ ለውጥ ፖሊሲ ሲረቀቅ ወይም ሲጸድቅ፣ ወዘተ ወዘተ ለአብዝሃው አፍሪካዊ በሚጠቅም መልኩ ገቢራዊ መሆን ይገባዋል፡፡

በእኔ የግል አሰተያየት መሰረት አንድን ሀገር አብዝሃውን ህዝብ ለመቅጣት ታልሞ ገቢራዊ የሚሆን ፣ማእቀብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡  የአንድን ሀገር የገንዘብ ሀብት መያዝ በአለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ዝውውር እንዳይኖር ማእቀብ መጣል የሚጎዳው በአብዛኛው ደሃውን እንጂ የፖለቲካ ልሂቃኑን አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ለአብነት ያህል ለአፍጋኒስታን ይሰጥ የነበረውን 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መከልከል እጅጉን የጎዳው በማእድን የበለጸገ ምግብ ያስፈልጋቸው የነበሩትን ደሃ የአፍጋኒስታን ህጻናትን ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር የህግ የበላይነት እንዳይሰፍን፣አሸባሪዎች እንዲደረጁ የረዳም ውሳኔ ነበር፡፡ ዛሬ በአንዲት የአፍጋኒስታን ድሆች ከተማ የሚኖሩ ቀን የጎደለባቸው ሰዎች ኩላሊታቸውን እስከመሸጥ እንደደረሱ የሚያሳይ አሳዛኝ ዘገባ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ካቀረበው ጥናት ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ድህነት መጥፎ ነው ያዋርዳል፡፡ ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ በዛ ግሩም እና ጣፋጭ ድምጹ እያለህ ካልሆነ ከሌለ የለህም ብሎ ገና ድሮ ነግሮናል፡፡መማር ከቻልን ማለቴ ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መጋቢት 9 2022 ገለልተኛ አቋም ያለው ጋዜጠኛ አና ጋሪሰን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹“Sanctions: a sanctimonious word for economic warfare and outright theft ›› በሚል ርእስ ባቀረበው ጽሁፍ ላይ እንዳብራራው ከሆነ የተባበረችው አሜሪካ ማእቀብ የመጣል መብቷን በመጠቀም በአንድ ሀገር ላይ አግባብ ያልሆነ ማእቀብ ስትጥል አንድ ሶስተኛ የሆነው ህዝብ ይጎዳል፡፡ አግባብ ያልሆነ ቅጣት እንደ ጦርነት ይቆጠራል፡፡ ታላቅ ስቃይንም በአለም ላይ ይፈጥራል፡፡ በሚል ነበር የገለጸው፡፡

<< ማእቀብ ›› የሚለው ቃል በመጀመሪያ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ( የተገኘው) እ.ኤ.አ. በመሃከለኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ትርጉሙም ሃይማኖታዊ አዋጅ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የምጣኔ ሀብት ጦርነት መክፈት እንደ የሞራል ድርጊት ይቆጠራል የሚል ትርጉም ይሰጠናል፡፡ በሌላ አነጋገር በአንድ ሀገር ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ የሚጥሉ ሀገራት በተለይም የምእራቡ አለም ራሳቸውን የሞራል የበላይነት እንዳላቸው ይቆጥራሉ ፡፡ የእነርሱ መከራከሪያ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የህግ የበላይነትን በአንዲት ሀገር ለማስከበር ነው ማእቀብ የምንጥለው ባዮች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል አፍጋኒስታን ተጥሎባት በነበረው ማእቀብ ምክንያት ዛሬም ድረስ በችጋር ፍዳዋን እየቆጠረች ትገኛለች፡፡ በነገራችን ላይ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለመረዳት እንደሚቻለው አፍጋኒስታን ወደ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ክምችት እንዳታንቀሳቅስ ከተባበረችው አሜሪካ መንግስት አኳያ ማእቀብ ተጥሎበታል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ዛሬም አፍጋኒስታን ዴሞክራቲክ መንግስት ማቆም እንዳልቻለች ከአለም የመገናኛ ብዙሃን ይሰማል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ አልታዘዝ ያላትን የአፍጋኒስታን ታሊባን መንግስት ለመቅጣት ስትል የያዘችው በቢሊዮን የሚቆጠር ረብጣ የአሜሪካን ዶላር በእጅጉ የጎዳው ደሃውን የአፍጋኒስታን ህዝብ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የታሊባን መንግስት አይጎዳም ማለት እንዳልሆነ አንባቢውን ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡ ጸሃፊው ለምን በታሊባን መንግስት ላይ የተባበረችው አሜሪካ ማእቀብ ጣለች የሚል ከንቱ ሰው እንዳልሆነም ማስገንዘብ ይሻል፡፡ የታሊባን አስተምህሮ ለአለም ሰላም አይበጅም፡፡ ይህ የመንግስት ስብስብ መቀጣቱ የጸሃፊው ራስ ምታት አይደለም፡፡ ጸሃፊው የአንድ ሀገር ዜጎች በአምባገነን መንግስታት ጥፋት ለምን አብረው ይቀጣሉ የሚል እምነት አለው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የአሜሪካ ኮንግሬስ ኤች አር 6600 ህግን የሚያጸድቅ ከሆነ ሁለቱም ሀገራት ከባድ ማእቀብ ይጠብቃቸዋል ብዬ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡

በነገራችን ላይ የህሊና ሚዛናቸው ያልተሰበረ እና መልካም አስተሳሰብ ያላቸው አሜሪካውያን  የተባበረችው አሜሪካ በሀገራት ላይ በምትጥለው ማእቀብ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች ማለትም  የእናቶች፣ልጆች፣አረጋውያን፣ዝቅተኛና መሃከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ስቃይ ምን እንደሆነ መረጃ እንደሌላቸው ይነገራል፡፡ በብዙ የአለም ክፍል የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንዲት ዳቦ ገዝተው ለመብላት ምን ያህል እንደቸገራቸው አያውቁም፡፡ ለአብነት ያህል በሩሲያና ዩክሬን መካከል በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት የተነሳ ጦርነቱ ገና አንድ ወር ሳይሞላው ሊባኖስ:- ከዓለማችን በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ በገጠመ የስንዴና ሌሎች የምግብ እህል እጥረት የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ መጋለጧንና  ይህቺ በፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ ፍዳዋን የምትቆጥረው ሀገር ሊባኖስ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት ሁሉ በበለጠ ሁኔታ የምግብ ዋጋ ንረት አንድ ሺ ፐርሰንት (1,000 ፐርሰንት) ያህል የጨመረባት አገር ስለመሆኗ ምን ያህሎቻችሁ ታውቃላችሁ? የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው እና ዳቦ በገፍ ለህዝቧ ታቀርብ የነበረችው ግብጽ ሳትቀር የስንዴ ግዢ አቅርቦት እየቀነሰባት በመምጣቷ ስጋት ውስጥ ወድቃለች፡፡ይሄ ሁሉ የሆነው ደግሞ እንደው ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ አይደለም፡፡ ምራባውያን በተለይም የተባበረችው አሜሪካ በሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ በጣሉት የኢኮኖሚ ማእቀብ ነው፡፡ ለግዜው ሩሲያን ማንበርከክ ቢያቅታቸው በምእራባውያንና ሩሲያ መሃከል የተጀመረው አጉል እና የማንአህሎተኝነት ፉክክር ምክንያት የተነሳ ደሃው አለም ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡

ከላይ ስሙን የጠቀስኩት ገለልተኛው ጋዜጠኛ ጋሪሰን የምጣኔ ሀብት ጠበብትን ጠቅሶ ባቀረበው ሪፖርት (Garrison reports )መሰረት የተባበረችው አሜሪካ በሩሲያ ላይ በጣለችው ማእቀብ የተነሳ በአለም ላይ  ከሚኖረው አጠቃላይ ህዝብ መሃከል ሶስት፣አራተኛው ህዝብ በኑሮ ውድነት ሊጠቃ እንደሚችል  ስጋቱን አስፍሯል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን በአለም በታወቁ መገናኛ ብዙሃን ሰርክ አዲስ የሚዘገበው ዜና በሩሲያ ላይ የተለያዩ ማእቀቦች እየተጣሉ ስለመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ማእቀቡ እጅጉን የሚጎዳው ደሃ ሀገራትን እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ምእራባውያን ሀገራትን ያስጠነቅቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሰሚ ጆሮ ያገኙ አይመስለኝም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር የካቲት ወር ጀምሮ ኤችአር 6600 እረቂቅ ህግን በኤርትራ እና ኢትዮጵያ ላይ ለመጫን እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከዚህም ባሻግር ፕሬዜዴንት ባይደን ዛሬም በፌዴራል ሪዘርቭ( ክምችት) የሚገኘውንና ከአፍጋኒስታን የተያዘውን 7ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለመልቅቅ አለመፈለጋቸውን ከአለም መገናኛ ብዙሃን በመሰማቱ አለምን አስደንግጦ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር የአፍጋኒስታን መንግስት በጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ታላቋ ብሪታኒያ እና የተባበረችው አረብ ኤሜሪትስ ማእከላዊ ባንኮች ውስጥ ያስቀመጠው ፣ከሁለት እስከ ሶስት ቢሊዮን የሚገመት የአሜሪካ ዶላር እንዳልተለቀቀላት በተለያዩ ጥናቶች ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ በአንድ ሀገር ላይ ማእቀብ ከጣለች ሌሎች ምእራባውያን ሀገራት እና የአሜሪካ ወዳጅ የሆኑ ሀገራት የተባበረችው አሜሪካን ዱካ ተከትለው ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸው በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ታይቷል፡፡ ( በሰሜን ኢትዮጵያ ተከፍቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የምእራባውያን በተለይም የተባበረችው አሜሪካ አቋም ምን እንደነበረ ልብ ይሏል 

የአለም አቀፉ የገንዘብ ስርአት መዳከም

እንዴት ነው ደሃውን ህዝብ የሚጎዳ ቀጪ ማእቀብ ትክክለኛ እና ፍትሃዊ የሚሆነው ? የራስን አላማ ለማሳካት አንድን ሀገር በወረራ መያዝ እና በአንድ ሀገር ላይ ማእቀብ በመጣል የአንድን ሀገር ሀብት መቆጣጠር መሃከል ያላቸው ልዩነት ምንድን ነው ? ( ለአብነት ያህል የተባበረችው አሜሪካ በአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ ወይም ቬትናም  ምድር ላይ የፈጸመችውን ግፍ ማስታወስ ይቻላል፡፡ በሶስቱም ሀገራት ያደረገችው ጨዋታዎች መጨረሻቸው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ )  የተባበረችው አሜሪካ አፍጋኒስታንን ጥላ ስትወጣ ሀገሪቷን ለመከራ ዳርጋ ነበር፡፡ አብዛኛው የአፍጋኒስታን ተቋማት ፈርሰዋል፣ ምጣኔ ሀብቷ ደግሞ ወድቆ ነበር፡፡ወይም ተንኮታክቷል፡፡ ከዚህ ባሻግር ድርቅና ችጋር የአፍጋኒስታን ህዝብ መለያ ሆኗል፡፡ አፍጋኒስታን የአለም አደንዛዥ እጽ መሸጫ ማእከል እና ዝውውር የሚደረግባት ሀገር ሆናለች፡፡

በነገራችን ላይ ‹‹ የሰብአዊ ቀውስ ›› በብዙ ሀገራት ከሚያስከትለው መቅሰፍት ባሻግር  ቀጪ ማእቀብ መጣል (ለአብነት ያህል  በአፍጋኒስታን፣ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ኢራቅ ፣ሶሪያ፣ የመን ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡) በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ደሃዎችን ኑሮ ያናጋል፡፡

ማነው በአፍጋኒስታን የሚጎዳው ? በኤርትራ የሚሰቃየው ማን ነው ? በኢትዮጵያ ወይም ሶሪያ የሚሰቃየው ማን ነው ? እስቲ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል ገንዘብ ዘርፈው የሚሸሹ  የፖለቲካ ኤሊቶች የሚጎዱ አይመስለኝም፡፡ ምንግዜም ቢሆን ድምጽ የሌላቸው፣ ስልጣን የሌላቸው ተራ ዜጎች፣ ዋህ ዜጎች ከባድ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡በአንድ ሀገርጦርነትም ሲከፈት በአብዝሃ ህይወቱ የሚቀጠፈው ከእኛ ኢትዮጵውያን በላይ የሚያውቅ ሀገር ነዋሪ ቢኖር  ጥቂት ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር የካቲት 14 2022 በዝነኛው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ  በቱፍተስ ዩንቨርስቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ደብሊው. ድሬዝነር በቀረበው ጽሁፍ መሰረት ‹‹ የተባበረችው አሜሪካ የአፍጋኒስታንን ገንዘብ ዘርፋለች፡፡ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ካቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ውስጥ የሚከተለውን እንደ አስረጂ ጠቅሼዋለሁ፡፡

  “After the seizure, on February 14, the Washington Post published an editorial by Tufts University professor Daniel W. Drezner, “The United States is stealing Afghanistan’s money, in which he wrote, “The United States has essentially forced everyone to witness the firepower of its fully operational machinery of coercive financial statecraft,” argues Garrison. ››

እውን ተራው የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ እና ቀሪው አለም በአሜሪካ መንግስት ካዝና ብቻ ያለው የሀብት ክምችት በትክክለኛና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ቢውል የአለምን የምጣኔ ሀብት እንደገና ሊያንሰራራ ሊረዳ እንደሚችል ያውቅ ይሆን ? የተባበረችው አሜሪካ የብዙ ሀገራትን የገንዘብ ሀብት ፍሪዝ አድርጋለች፡፡ ለአብነት ያህል የአፍጋኒስታን 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ክምችት ይጠቀሳል፡፡ ይህ እንደሌብነት አይቆጠር ይሆን ?

የተባበረችው አሜሪካ ማእቀብ የመጣል ሂደት እና የሀገራትን ገንዘብ ክምችት መያዝ አስደንጋጭ ነው፡፡ የተባበረችው አሜሪካ  ይህን ገቢራዊ የምታደርገው ያለምንም ችግር እንደሆነ በብዙ የአለም ሀገራት ላይ በተለያዩ ግዜያት ታይቷል፡፡ ለአብነት ያህል በኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግስት በ1966 ዓ.ም. የአለምንም ደም፣ እንከን አይውደም በቀና መንፈስ ኢትዮጵያ ትቅደም በሚል መፈክር ስልጣኑን በጨበጠ ማግስት( ኋላ ላይ ሀገሪቱን የደም አባላ አልብሷት ነበር) የአሜሪካ መንግስት አጼ ሀይለስላሴ ለመሳሪያ ግዢ ይሆን ዘንድ ለአሜሪካ መንግስት የሰጡትን ገንዘብ ከልክሏል፡፡ ወይም የጦር መሳሪያውን ለደርግ መንግስት ለማስረከብ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ( ያሻትን ውሳኔ ከመፈጸም ወደኋላ የማትልበት ምክንያት ) ጠንካራ ወታደራዊ ሀይል በመገንባቷ፣የአለምን የገንዘብና የፋይናንስ ስርአት በመቆጣጠሯ ( የብሪትን ዉድስ ተቋማት የሆኑትን የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅትን ይጨምራል፡፡) (including the Bretton Woods Institutions (the World Bank and the IMF))፣( ድምጽን በድምጽ የመሻር ሀይል ስላላት፣ የአለም የእውቀት ክምችት ማእከል በመሆኗ( በአለም ላይ ከሚገኙት ሀገራት በአምባገነን መሪዎች ጡጫና ግፍ የተማረሩ ታላላቅ ሰዎችና ሳይንቲስቶች መኖሪያ በመሆኗ፣ ለአብነት ያህል በአንድ የተባበረችው አሜሪካ ከተማ ብቻ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ የህክምና ስፔሻሊስቶች ሀገር ውስጥ ካለው ቁጥር ይበልጣሉ ይባላል፡፡) ወዘተ ወዘተ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ለምን ያህል ግዜ ነው የኢትዮጵያን የውስጥ ግጭት ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የወሰደችው ?

ጋሪሰን (Garrison) የተባለች ምሁር በምእራባውየን  ስለተያዘው የሊቢያ ሀብትና አሁን ድረስ ያልተመለሰውን የሊቢያ ሀብት በተመለከተ መጻፏ ትክክል ነበር፡፡ በለንደን ባንክ የተከማቸው እና ዋጋው እስከ 1.95 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣው  የቬንዙዌላ ወርቅ ክምችት ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በተባበረችው አሜሪካ የሚገኘው የቪንዙዌላ የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብቷ በማእቀብ ስም እንደተያዘ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በተለያዩ የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ አስፍረውታል፡፡ ከዚህ ባሻግር ከተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንደተሰማው አራት የኢራን ታንከሮች ነዳጅ ጭነው ወደ ቬኑዚዌላ በሚያመሩበት ግዜ በተባበረችው አሜሪካ መንግስት ውሳኔ ከተያዙ በኋላ 40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠው በሽብር ጥቃት ለተጠቁ አሜሪካውያን ገቢ ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን ከአፍጋኒስታን የተወሰደው 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሽብር ጥቃት ለደረሰባቸው አፍጋኒስታውያን አልተሰጠም፡፡ አለም የሃይለኞች መፈንጫ መሆኗን ሲታሰብ ህሊናን ያደማል፡፡

በነገራችን ላይ አፍሪካውያን ወጣቶች( በሱስ ያልነሆለሉትን፣በጥቅም ያልታወሩትን ማለቴ ነው፡፡) የምእራባውያን ሞኖፖሊ ካፒታሊስቶች የተፈጥሮ ሀብታቸውን እንደዘረፉ፣ ገበያዎቻቸውን እንደተቆጣጠሩ ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

በስትራክቸራል አጀስትመንት የኢንቨስትመንት ፕሮግራም ስም አለም አቀፍ ካምፓኒዎች ለአፍሪካ ሀገራት ያበደሩት ገንዘብ ያደረሰውን ጉዳትም የአፍሪካ ወጣቶች ይረዱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ  አውሮፓውያን ለአፍሪካውያን የሚያዘጋጁት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአፍሪካ እድገት የሚበጅ እንዳይደለ የአፍሪካውያን የእለት ከእለት ህይወት ማሳያ ነው፡፡ ለአፍሪካ በገፍ የሚቀርበው የሰብአዊና የልማት እርዳታም ቢሆን ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳላመጣ የሚታወቅ ነው፡፡ መሰረታዊ የአፍሪካውያን ችግር በቅጡ ሳይጠና ገቢራዊ የተደረገው የልማትና የሰብአዊ እርዳታ የጥቂቶችን ኑሮ ሰማየ ሰማያት ላይ ከማድረስ በቀር የአብዝሃውን አፍሪካዊ ህይወት ማሻሻል አልተቻለውም፡፡ በጀርመን ሀገር ኑሮአቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ሀብት ጠበብት ፕሮፌሰር በፍቃዱ በቀለ ባቀረቡት ጥልቅ ጥናት መሰረት አውሮፓውያን ለሃምሳ አመታት ያህል ያቀረቡት እርዳታ አፍሪካን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት አልተቻለውም፡፡ የብዙ ሚሊዮን አፍሪካውያን ህይወት በድርቅና ጠኔ ምክንያት እንዳይቀጠፍ ግን የምእራባውያን ሰብአዊ እርዳታ መተኪያ የለውም፡፡ በነገራችን ላይ ሀይለኞችና ሀብታም ሀገራት ይህን በቀላሉ ነው የሚፈጽሙት ፡፡ ምክንያቱም በሀገር ቤት ያሉ ሌቦች የእነርሱ ተባባሪዎች በመሆናቸው እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ የተደራጀ ዝርፊያ ነው፡፡

በነገራችን ላይ እነኚህ ትላልቅ ካምፓኒዎች ለምን ሁል ግዜ የላቀ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እነማንን እንደሚያገለግሉ በስፋት አይታወቅም፡፡ አለም አቀፍ አበዳሪዎች፣ አለም አቀፍ ተቋማት ለአብነት ያህል የብይነ መንግስታቱ ወኪሎች ሞኖፖሊ ካፒታልን የሚደግፉ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር ምእራባውያን መንግስታት ሞኖፖሊ ካፒታልን የሚቆጣጠሩ ሲሆን፣ የተባበረችው አሜሪካ የምእራባውያን ተጽእኖ ፈጣሪ እና ፖሊሲያቸውን የምትመራ ናት፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ግዜ የተባበረችው አሜሪካ በደሃ ሀገራት ላይ ማእቀብ ስትጥል ተቃውሞ የሚገጥማት፡፡ የአለም አቀፍ የፋይናንስና የገንዘብ ፖሊሲ( ህግና ጨዋታው) የሚረቀቁት፣አለም አቀፍ የንግድ ስርአት፣የስደተኞች ፖሊሲ፣ በአንድ ሀገር ላይ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ቱጃሮች የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ  በአብዛኛው የሚዘጋጀው ምእራባውያን ሀገራት በሚመሩት የተባበረችው አሜሪካና ታላቋ ብሪታንያ ሀገራት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ አለምን በራሳቸው አምሳል የቀረጹት፣ የአለም ባንክና የገንዘብ ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ ብዙ ካምፓኒዎች የቦርድ አባላት በአብዛኛው በምእራባውያን ተጽእኖ ውስጥ የወደቁና የሚመሩ ናቸው፡፡

በዚህ ምክንያት ነው ቻይና፣ሩሲያ፣ኢራን እና ሌሎች ሀገራት በእድገት ወደኋላ ለቀሩ ሀገራት የሚበጅ፣ ሚዛናዊ የሆነ አማራጭ አለም አቀፍ የመንግስት ለማቆም የተስማሙት፡፡

የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር የሆኑትን ጃፓናዊው ጂን-ክላውድ ማስዋና ኢፍ ሪትሱኒከን Jean-Claude Masawana of Ritsuniekan, በመጥቀስ ኢትዮጵዊው የምጣኔ ሀብት ጠበብት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በጥናታዊ ጽሁፋው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ ‹‹ የተባበረችው አሜሪካ እና ታላቋ ብሪታንያ ለረጅም አመታት የአለሙ ንግድና ፋይናንስን አሰራር ህግ ያወጡ ናቸው፡፡›› 

እነኚህ ማለትም የምእራቡ አለም በተለይም የተባበረችው አሜሪካና ታላቋ ብሪታንያ ለራሳቸው ታላቅ ክብር( ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የቆሙ ናቸው፡፡) ይህንን ነው በገሃዱ አለም ላይ የምናየው፡፡ በዛሬው ዘመን የሩሲያ ፌዴሬሽን ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት ከአለም አቀፉ የባንክ ስርአት( ዝውውር) እንድትወጣ ማእቀብ ጥላለች፡፡ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የባንክ የገንዘብ ዝውውርም አግዳታለች፡፡

ለዚህ የምእራበውያን ማእቀብ ምላሽ በሚመስል መልኩ ሩሲያና ቻይና የፋይናንስ መረጃ ኔትወርካቸውን ወደ የላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማተዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሁለቱም ሀገራት ( ቻይና እና ሩሲያ) እቃን በእቃ በመለዋወጥ barter.”  አዲስ የንግድ ግንኙነት ጀምረዋል፡፡

ያልተቋረጠ የስልጣን ትእቢት 

ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በርእሱ ተንተርሰው የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አስፍሬዋለሁ፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1967 በተባበረችው አሜሪካ ሴናተር ፉልብራይት  ‹‹ the “Arrogance of Power ›› በሚል ርእስ የተጻፈውን መጽሐፍ አስታውሰዋለሁኝ፡፡ በግዜው ያንዬ በተባበረችው አሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የነበሩት ሰው የሀገራቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአደባባይ ተችተውት ነበር፡፡ በርግጥም ፖሊሲውን ተችተውት ነበር ምክንያቱም ራሳቸውን ገምግመው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሮጋንት ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በግዜው የተባበረችው አሜሪካ በቬትናም ላይ  ጦርነት በመክፈቷ ምክንያት የአሜሪካን ወጣቶችን ጨምሮ በአለም ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስቆጥቶ እና አንቀሳቅሶ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር አክሎግ አክለው እንደጻፉት ከሆነ ፡-

‹‹ በግዜው ማለትም ጀማሪ የኮሌጅ ተማሪ በነበርኩበት ግዜ በሴኔተር ፉልብራይት የቀረበው ትችት ማለትም የአሜሪካን ብሔራዊ አሮጋንሲ ባህሪ በሴኔቴሩ በመተቸቱ ምክንት አነቃቅቶኝ ነበር፡፡ የአለም ፖሊስ ነኝ የምትለው አሜሪካ ለቀሪው አለም እድገት ደንታ እንደሌላት ማሳያ ነው፡፡ፉልብራይት የዘር እና የጾታ እኩልነት እውን እንዲሆን፣ በቂ ክፍያ ለሰራተኞች እንዲሰጥ፣በጥቂት ሰዎች እጅ ሀብት መከማቸት እንደሌለበት፣ በቬትናም የተከፈተው ጦርነት ያስከተለው ጥፋት የአሜሪካንን ስም ማጠልሸቱን ወዘተ ወዘተ በተመለከተ ለሴኔቱ አስረድተው ነበር፡፡ ያንዬ የቀረበው ጥያቄ ዛሬ ተመልሶ ይሆን ? መልሱን በተመለከተ ተወያዩበት፡፡

ሴናተር ፉልብራይት እና በመቶ ሺዎች የሚቆጣጠሩ አሜሪካውያን በቬትናም የተከፈተው ጦርነት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ባሳደረው ከባድ ምስቅልቅሎሽ በመፍጠሩ ምክንያት የአሜሪካንን ድርጊት አውግዘውት ነበር፡፡ ይህ ስልጣንን አለአግባብ መጠቀም ሲሆን ወረራው አሁን ድረስ እንደተወገዘ ነው፡፡ ማነው ቻይናን ወይም ኢራንን ሌላ ለተለዋዋጩ የአለም ምጣኔ ሀብት የሚስማማ አማራጭ የፋይናንስ እና የገንዘብ ስርአት ቢፈልጉ የሚወቅሳቸው ?

ፕሮፌሰር ማስዋና ኦፓይንስ (Jean-Claude Maswana’s)  በበኩላቸው አሜሪካ ስልጣኗን አለአግባብ በመጠቀሟ ምክንያት መልሶ እራሷን አናዷታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቻይና ቀደም ብላ ከአሜሪካ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር በመቆሟ ነበር፡፡ ቻይና አሁን ድረስ የአለምን ኢኮኖሚ ለመለወጥ የሚያስችል የፋይናንስና የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ላይ ገና አልደረሰችም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ምልክቶች አሉ፡፡ ምልክቶቹ እውን ይሆኑ ዘንድ አፍሪካ የፍትህና እኩልነት ሰልፍ ውስጥ መግባት አለባት፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ የመሰሉ ስመጥር የምጣኔ ሀብት ተጠባቢዎች ፕሮፌሰር ጂን-ክላውድ ማስዋና ለጋሪሰን በሰጠው መልስ ላይ እንደሚስማሙ በጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረውት ይገኛል፡፡ ( ፕሮፌሰር ጂንክላውድ ቻይና የንግድ ትርፍ እንዳለት፣ ይህም ማለት ትርፍ የአሜሪካን ዶላር እንዳከማቸች መጥቀሳቸውን ልብ ይሏል፡፡) ቻይና ከአለም ባንክም ይሁን ከአለም ገንዘብ ድርጅት ብድር ከመበደር ይልቅ ያከማቸችውን የአሜሪካ ዶላር በተባበረችው አሜሪካ ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ትርፍ እንዳስገኘላት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የጥናት ውጤት ከሆነ ሁለቱንም ሃያል ሀገራት ተጠቃሚ ያደረገ የንግድ ትርፍ ግንኙነት እረዥም ግዜ ሊቆይ ይችላልን የሚለው ጥያቄ አወያይ ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ መልስ በሩሲያና ዩክሬን መሃከል የተከፈተው ጦርነት የማብቂያ ግዜ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን፣ ማለትም የሁለቱ ሀገራት ጦርነት በሰላም ቢጠናቀቅም የአሜሪካ ዶላር ሃያልነትን የማዳከም ሂደት የሚቆም አይመስልም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ያለው ስርአት አፍሪካን የሚጎዳ ነው፡፡ ስለሆነም አፍሪካውያን መልካም አማራጭን ይሻሉ፡፡

ይህ እኔን  ህግ ሆኖ በተባበረችው አሜሪካ ኮንግሬስ አባላት ( በተወካዮች ምክርቤቱ) ከጸደቀ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ወደ ኤችአር 6600 (HR 6600  ) ይወስደኛል፡፡ ይህ ህግ የሚዘጋጀው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ደሃዎች በሚኖሩባቸው  ኤርትራና ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል ነው፡፡

ጥያቄው ይህ ቢል የተባበረችው አሜሪካ የኢትዮጵያንና ኤርትራን ሀብት እንድትይዝ ያስችላታልን ? የሚለው ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ጥናት ከሆነ ህግ ሆኖ ከወጣ ለአሜሪካን ስልጣን ይሰጣታል፡፡ በያዝነው የአውሮፓውያን አመት መጀመሪያ ላይ የተባበረችው አሜሪካ በኤርትራና ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ በተባበረችው አሜሪካ የተወካዮች መድረክ ላይ ሌላ በጣም የባሰ ማእቀብ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ሰለሆነም እንደ አፍጋኒስታን 7 ቢሊዮን ዶላር ሁሉ በአሜሪካን ሊያዝ የሚችል የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ገንዘብ ወይም ሀብት ካለ ያስደንቀኛል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የጥናት ውጤት ከሆነ ኤርትራ በአሜሪካ አስተዳደደር ሊያዝ የሚችል ገንዘብ የላትም፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን ለጥቃቱ ተጋላጭ እንደማትሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በነገራችን  ላይ እንደ የምጣኔ ሀብት ተጠባቢዎች ጥናት ከሆነ ሁሉም ሀገራት ካላቸው አለም አቀፍ የገንዘብ ክምችት ላይ የተባበረችው አሜሪካ ልትይዝባቸው የምትችለው ገንዘብ አላቸው፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያና ኤርትራ አለም አቀፍ ግብይት የሚፈጽሙት በአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ ስለሆነም ልክ አፍጋኒስታን ላይ እንዳደረገችው ሁሉ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ከመፈጸም የሚያግዳት አይኖርም ማት ነው፡፡ በሌላ አነጋገገር ለኢትዮጵያና ኤርትራ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ማስቆም ትችላለች ማለት ነው፡፡ ለአብነት ያህል በልዩ ሁኔታ ለታሊባን መንግስት ሊሰጥ የነበረውን 390 ሚሊዮን ዶላር እንዳይደርስ በረጅም እጇ አግዳለች፡፡

የአለም የንግድ አገዛዝ በተባበረችው አሜሪካ ተጽእኖ ውሰጥ የወደቀ ነው

እንደነ ፕሮፌሰር አክሎግን የመሰሉ ስመጥር የምጣኔ ሀብት ጠበብት በጥናታቸው እንደረሱበት ከሆነ ማእቀብ የሚያገለግለው ለሀይለኞች ነው፡፡ ሀገራት የንግድ ግንኙነት አላቸው፡፡ የንግድ ግንኙነታቸው የሚሳለጠው ደግሞ በአሜሪካን ዶላር መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሀገራት ንግድ ለማካሄድ ከፈለጉ በሌሎች ሀገራት ባንክ ውስጥ የገንዘብ ክምችት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበረችው አሜሪካ ፈለገችውን ሀገር ለማጥቃት ከፈለገች በአለም አቀፍ የንግድ ግንኙነት ላይ  ያቺን ሀገር  ተሳትፎ ማድረግ እንዳትችል ተጽእኗዋ ከባድ ነው፡፡ ይህቺ ሀገር ማኝኛውንም ባንክ ሀገር ከሀገሯ ውጭ ገንዘባቸውን ጥቅም ላይ እንዳያውሉ ማገድ ትችላለች፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያም ሆነች ባንኳ ከኢትዮጵያ ውጭ መገበያየት እንዳይችሉ ማገድ ትችላለች ማለት ነው፡፡ ወደ አፍጋኒስታን ጉዳይ ስንመለስ አፍጋኒስታን በራሷም ገንዘብ ሆነ በአሜሪካን ዶላር እንዳትገበያይ  አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከልክለዋታል፡፡ ይህ ደግሞ የተባበረችው አሜሪካ በጣለችባት ማእቀብ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ስለሆነም የረቀቀው ቢል የህግ ሰውነት ካገኘ በኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ የኢትዮጵያን ገበሬዎች ጨምሮ ተራ ዜጋውን ይጎዳል፡፡

የተባበረችው አሜሪካ ማእቀብ ገቢራዊ ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ ምን ያመጣል ?

ኢትዮጵያ ከጃፓን ላስገባቸው የኢንዱስትሪ ምርት በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ብር ( ከጃፓኑ የመገበያያ ገንዘብ የን እኩል የሆነ ) ለመክፈል ብትፈልግ የአሜሪካ ውሳኔ ምን የሚሆን ይመስላችኋል እውን አሜሪካ ተጨማሪ የገንዘብ ዝውውር በዶላር እንዳይካሄድ የምትከለክል ይመስላችኋል፡፡ መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ አሜሪካ ዝም ብላ አትቀመጥም የዶላር ዝውውር እንዳይኖር ታግዳለች፡፡ ስለሆነም የጃፓን ባንኮች በእንዲህ አይነት የገንዘብ ልውውጥ ላይ እጁን አያስገባም፡፡ጃፓን  የተባበረችው አሜሪካ የንግድ ሸሪክ ከሆነው አውሮፓ ህብረት  ጋር ያላት የንግድ ልውወጥ ሊጎዳም ስለሚችል ማእቀብ ከተጣለባት ሀገር ጋር የንግድ ግንኙነት ማድረግ ፍላጎቷ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ የአሜሪካ እጅ ምን ያህል እረዥም መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ጎበዝ የሩሲያ ፌዴሬሽንን በኢኮኖሚ ለማዳከም የተሄደውን መንገድ ላስተዋለ፣ አፈርድሜ የጋጠ ኢኮኖሚ ላላት ሀገር ኢትዮጵያ ላይ ማእቀቡ ከተጣለ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ መረዳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ በሩሲያ ላይ የጣሉት ማእቀብ ዩክሬንን ብቻ ለማዳን አይመስለኝም፡፡ ዋነኛ አላማቸው የሩሲያን ክንድ ለመስበር ነው፡፡

እውን በአፍጋኒስታን የተገበሩትን በኤርትራና ኢትዮጵያ ላይ ገቢራዊ ማድረግ አለባቸውን ? እስቲ ቤአካባቢችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል ለግዜው የምለው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ተባበረችው አሜሪካ የውጭ ፖሊሲዋን ለመከላከል የሞራል፣ስነምግባር፣ እና የፖለቲካ ምክንያት ማቅረብ አለባት ብዬ አስባለሁ፡፡

 ሰፊው የአፍሪካው ስእል በአይምሯችን ጓዳ መቀመጥ አለበት፡፡ የፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ( Anglophone and Francophone )የአፍሪካ ሀገራት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠረው ሀብታቸው የተከማቸው በታላቋ ብሪታንያ፣ፈረንሳይ እና የተባበረችው አሜሪካ ማእከላዊ ባንክ እንደሆነ የሚያሳዩ ጽሁፎችን እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ይህ የሚያደርጉት ደግሞ ለጥንቃቄ እና ጸጥታው አስተማማኝ ነው በሚል የራሳቸው ምክንያት ገንዘባቸውን   ማስቀመጣቸው የታወቀ ቢሆንም የአፍሪካ ሀገራት ይህን ሲያደርጉ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የተከማቸው ገንዘብ ሀገራት ስህተት ሰሩ በተባለ ግዜ አደጋ ላይ የሚወድቅ ነው፡፡( በሌላ በኩል በስልጣን ዘመናቸው የሀገራቸውን ገንዘብ ዘርፈው በምእራቡ አለም በተለይም በሲዊዝ ባንክ ገንዘብ ያከማቹ( የሚያከማቹ) አምባገነኖች ሞለተው መትረፋቸውን ልብ ይሏል፡፡) 

ይህም ብቻ አይደለም በተባበረችው አሜሪካና ምእራባውያን ተጽእኖ ስር የወደቁት አለም አቀፍ ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ መቀልበስ አይቻልም፡፡በአጠቃላይ የአፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ ተጽእኖ ስር ብቻ የወደቁ ሳይሆኑ  በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ተጽእኖም ውስጥ ናቸው፡፡ ምእራባውያን በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ውስጥ ቀርቦ እንዲቀጣ የሚፈልጉትን መሪ ከማቅረብ ወደኋላ አይሉም፡፡ በሩዋንዳ እና ላይቤሪያ የዘር ፍጅት ፈጻሚ መሃንዲሶች ላይ ገቢራዊ አድርገውት ነበር

ለማናቸውም እንደ የተባበረችው አሜሪካን የመሰሉ ሀያል ሀገራት  በራሳቸው ውሳኔ እየቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱ ከእነርሱ በላይ ሀይል ያለውና በእነርሱ ላይ ቀጪ የሆነ ማእቀብ መጣል የሚችል ሀገር ባለመነሳቱ ነው፡፡ ( በሩሲያ ወይም በቻይና፣አራንና ሰሜን ኮሪያ የሚሰጠው የኢኮኖሚ ማእቀብ ምላሽ አብዛኛውን የምእራቡን አለም ክፉኛ የመጉዳት ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በሩሲያና ዩክሬን መሃከል በተከፈተው ጦርነት ምክንያት የምእራቡ አለም በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በገጠሙት የቴክኖሎጂ፣ኢኮኖሚ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ የበላይነት ለማግኘት ግብግብ ገጥመዋል፡፡ ሆኖም ግን ዝሆኖቹ በሚያደርጉት ፉክክር በመጀመሪያ የዩክሬን ህዝብ ተጎጂ ሲሆን ፣ገና ሁለት ወር ሳይሞላ  የአብዛኛው አፍሪካ ህዝብ በተለይም በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል፡፡)

በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ የሩሲያን ክንድ ለመስበር የተባበረችው አሜሪካ በሩሲያ ላይ ያልመዘዘችው የኢኮኖሚ ሰይፍ የለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ቢያንስ አሁን ድረስ ሩሲያን አንገት ለማስደፋት አልሆነላትም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ አሳዛኙ ሁነት ማለትም ኤች አር 6600 ወደ ህግ ከተለወጠ በአፍሪካው ቀንድ የሚገኙት ሁለቱ የድሆች ደሃ የሆኑ ሀገራት፣አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎቻቸው የበለጠ ተጎጂ መሆናቸው አይቀሬ መራር እውነት ነው፡፡ ለማናቸውም ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

ማስታወሻ፡- ይህን ጹሁፍ ለማዘጋጀት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያዘጋጁትን ጽሁፍ በዋቢነት ተጠቅሜአለሁ

Filed in: Amharic