ቹቹ አለባቸው
ፋኖን በተመለከተ የኔ አቋም ታውቆ ያደረ ነው። ይሄንን አቋሜን የክልሉ መንግስትም ሆነ መሪ ድርጅት ያውቁታል (እንደተለመደው በዝምታ ቢታለፍም ለሚመለከታቸው አካላት አጭር ፅሁፍ አቅርቤላቸው ነበር)።
ለሁሉም የኔን አቋም በድጋሚ ለማሰረገጥ ያክል፣ ፋኖ የአማራ ባህላዊ የፀጥታ ኃይል ነው። ትውፊታዊ ማንነቱ ነው። ግብሩ ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ መዋደቅ እስከሆነ ድረስ የበለጠ እናዘምነው የሚል አቋም ነው ያለኝ።
ባህላዊ የፀጥታ ኃይል ያልኩት ከታሪካችን የወረስነው የጀግንነት ሴንቲሜንት በመሆኑ ነው።
አሁን እናዘምነው ስል የፋኖ ግንባታና አስተሳሰቡ አገራዊ ዕይታ እንዲኖረው ተደርጎ ሊታነፅ ይገባል በሚል ነው። የክልሉ ምክር ቤትም ፋኖን እንደአንድ የአማራ ባህላዊ የፀጥታ ኃይል ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል። የክልሉ መንግስት የሚደገፈው፣ አስፈላጊ ሲሆንም የሚቆጣጠረው የተማከለ ስምሪትና አመራር እንዲኖረው ሆኖ ይገንባ የሚል አቋም ነው ያለኝ። ይህ አቋም “ሕዝበኝነት” ሳይሆን ‘ወገንተኝነት’ ነው።
መዘንጋት የሌለበት ነገር አማራ መቼም ቢሆን የማይተኙለት ደመኛ ጠላትቶች ያሉት መሆኑ ነዉ ። ረዥም ክረምት ከፊት ለፊታችን ይጠብቀናል። ፋኖ የሐምሌ ፀሐያችን ሆኖ እንዲያገለግለን ዕይታችን አድማሳዊ ሊሆን ይገባል።
ጠላቶቻችን ወታደራዊ አቅማቸዉን እያሳደጉ ባለበት ሁኔታ ፋኖን መፈረጁም ሆነ መግፋቱ ፈፅሞ ተገቢነት የለውም። ፋኖ ብረት ከትክሻው የሰቀለበት ዋነኛ ምክንያት የህልውና ስጋት ነውና የአማራና የኢትዮጵያ ህልውና እስካልተረጋገጠ ድረስ የፋኖ አስፈላጊነት ጉልህ ነው። እንደሕዝብም ሆነ እንደሀገር ህልውናችን ከተረጋገጠ ማንም ፍትህን ትክሻው ላይ በጣለው ብረት አይፈልግም። አራሽ አንደፋራሽ፤ ነጋዴና አትራፊ፤ ተማሪና ተመራማሪ፤ … መሆን የሚቻለው ህልውናችን ሲረጋገጥ ነው!
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ፋኖን በተመለከተ ውዝግቡ የሚቀጥል ከሆነ በዝርዝር ልመለስ እችላለሁ።
ለጊዜው ያለኝ ዕይታ ግን ይሄን ይመስላል። ይህ ፅሁፍ ማንንም ለማስደሰት ማንንም ለማስቆጣት ታስቦ የተፃፈ አይደለም ይልቁንስ ሦስተኛ ዙር የጦር ወረራ ሊከፈትብን ከመሆኑ ጋር ይያያዛል።
ሰላም ለሀገራችን፣ማህበረሰባዊ ዕረፍት ለአማራ ህዝብ!!