>

የዘር ፍጅትን፤  የአካል መጉደልና መፈናቀልን ያስተናገደው የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እንዴት ይፈታ...??? (በድልበቶ ደጎዬ ዋቆ)

የዘር ፍጅትን፤  የአካል መጉደልና መፈናቀልን ያስተናገደው የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እንዴት ይፈታ…???
በድልበቶ ደጎዬ ዋቆ

 

*…. ‹‹በመጀመርያ ወጣቶቹ ከወልቃይት ተጭነው ወደ ትግራይ ተወሰዱ። ከዚያም እጅና እግራቸው ታጥፎ ተሰበረ። በዚህ ሁኔታ ለሃምሳ ቀናት ራቁታቸውን አንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው በቀን አንድ ዳቦ ከብዙ ዱላ ጋር እየተሰጣቸው እንዲቆዩ ተደረገ። ሃምሳ ቀን ሙሉ ከዚያ ቤት አልወጡም። በሃምሳኛው ቀን አንድ የጭነት መኪና መጣና ወጣቶቹ ተዘግተውበት የነበረው ቤት ተከፈተ። በወቅቱ በአካባቢው የነበረውን ሽታ በቃላት ለመግለጽ አዳጋች ነው። ወጣቶቹ በጣም ከመክሳታቸው የተነሳ ወታደሮቹ በአንድ እጃቸው ፀጉራቸውን አንጠልጥለው ወደ መኪናው ይወረውሯቸው ነበር። አንደኛውን ወጣት ፀጉሩን ይዞ ሲወረውረው፣ ፀጉሩ ተነቅሎ ወደቀ። ያንን ስመለከት ሰው ሆኜ መፈጠሬን ጠላሁት።
‹‹ወጣቶቹን ጭኖ የሄደው መኪና ማታ አካባቢ ባዶውን ተመለሰ። ወጣቶቹን እንደ ገደሏቸው ባውቅም ከዚያ ሁሉ ሥቃይ መሞት እንደሚሻላቸው በመረዳቴ ደስ አለኝ። 
እኔ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጅ ስሆን፣ በ1962 ዓ.ም. ከቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁ በኋላ በመንግሥት ሠራተኛነት የተቀጠርኩት በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሥር ይተዳደር በነበረው የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ነበር። በ1963/64 ዓ.ም. የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን በመላ አገሪቱ ስናቋቋም፣ ለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚያገለግል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት የተቋቋመው በጎንደር ከተማ፣ ለትግራይ በመቀሌ፣ ለኤርትራ ደግሞ በአስመራ ከተማ እንደነበር አስታውሳለሁ። ያን ጊዜ የጠቅላይ ግዛቱ ስያሜ የበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ተብሎ ሲጠራ፣ የንጉሠ ነገሥቱ እንደራሴና ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ኮሎኔል ታምራት ይገዙ ነበሩ፡፡ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የኤርትራ ደግሞ ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ ነበሩ።
በ1963 ዓ.ም. በወልቃይት ጠገዴ በሚገኘው የሁመራ መሬት ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ በሰፊው የሚያመርትና ከዓለም ባንክ ጭምር የገንዘብ ድጎማ የሚደረግለት ‹‹የወልቃይት ጠገዴ ሁለገብ የገበሬዎች ማኅበር›› ነበር፡፡ በማኅበሩ ውስጥ አባል ሆነው ለመሰማራት የሚሹ ሁሉ ከኮሎኔል ታምራት ይገዙ ከጎንደር የድጋፍ ደብዳቤ እየተጻፈላቸው ነበር የሚመዘገቡት፡፡ አያሌ ሀብታም ባለትራክተር ግለሰቦችን ያፈራ የልማት ማኅበር ነበር። የማኅበሩ የቀን ሠራተኞች (Seasonal Workers) በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች እንደነበሩ ሳስታውስ፣ (ልክ የወንጂና የመተሃራ የስኳር ፋብሪካዎች የቀን ሠራተኞች በአብዛኛው የከምባታና የሐዲያ ተወላጆች እንደነበሩ ሁሉ) የሁመራ ከተማ ባለሆቴሎችም አብዛኞቹ ኤርትራውያን እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ወደ ሁመራ ከተማ የሱዳን ዜጎች ያላንዳች ገደብ እየገቡና እየተዝናኑ እንደሚመለሱና ኢትዮጵያውያንም በነፃነት ወደ ሱዳን እየገቡ ይነግዱና ይመላለሱ እንደነበር አስታውሳለሁ።
የወልቃይት ጠገዴ ሁለገብ የገበሬዎች ማኅበር በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ከዓለም ባንክ ብድርና ዕርዳታ የሚያገኝ እጅግ የዳበረ ጠንካራ የእርሻ ልማት ማኅበር ነበር። ምርታቸውን በተመለከተ ማሽላውን ወደ ከረንና አስመራ የሚያስጭኑ ሲሆን፣ ጥጡንና ሰሊጡን በምፅዋ ወደብ በኩል ወደ ውጭ አገሮች ነበር ኤክስፖርት የሚያደርጉት። እነዚህን ምርቶች ወደ ምፅዋ የሚጭነው የቀይ ባህር ኤርትራ የጭነት ማመላለሻ ማኅበር እንደነበር አስታውሳለሁ።
እኛም የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር (ዛሬ የትራንስፖርት ባለሥልጣን) ቡድን በ1963 ዓ.ም. ወደ ሁመራ የሄድነው ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ማኅበራት በጭነት ታሪፍ የተነሳ ስላልተስማሙ ለማስታረቅ ነበር፡፡ በአጭሩ ለመግለጽ የሁለቱን ማኅበራት መሪዎች በማወያየትና በማደራደር በኩንታል ሦስት ብር የነበረው የጭነት ታሪፍ ወደ አራት ብር በኩንታል ከፍ እንዲል በማስማማት ወደ ጎንደር እንደተመለስን አስታውሳለሁ።
ያን ጊዜ ማለትም የዛሬ 51 ዓመት ወልቃይት ጠገዴ ምንም በማያሻማና በማያወዛግብ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና ፖለቲካዊ የግዛት ይዞታ የቤጌምድርና ስሜን አካል ሲሆን፣ ነዋሪዎቹም ራሳቸውን ወልቃይቶች ብለው እንደሚጠሩ አስታውሳለሁ። ከዚያ ወዲህ በዘመናዊ የትግራይ ነፍጠኛ አቅኚዎች በኃይል ካልተያዘ በስተቀር ከትናንትናው የበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት፣ ከዛሬው የአማራ ክልል ይዞታ ውጪ የሚሆንበት ታሪክ ሊከሰት አይችልም። በወሎ በኩል ደግሞ ከአላማጣና ከራያ ቆቦ አካባቢዎች ተቦጭቀው በጊዜው ወራሪዎች የተነጠቁትን ወረዳዎች ጨምሮ  (“መሬት የሁሉም ናት ባለቤት የላትም፣ ኃይለኛው ያስገብራል እየሄደ የትም”፣ ሲል የኢጣሊያ ተወላጅ ቹሊ የተባለ ሰው በትዕቢት የተናገረውን ያስታውሷል!) የወሎ ጠቅላይ ግዛት አካል ነበሩ። የራያ አዘቦ ይዞታ ግን የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አካል እንደነበር አስታውሳለሁ።
ያን ጊዜም ሆነ አሁን የቤገምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛትና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት የድንበር ወሰን ደግሞ የማያሻማና ግልጽ የሆነ የተፈጥሮ ወሰን የተከዜ ወንዝ እንደነበርና ዛሬም እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከሁመራ የሚጫነውም ምርት ተከዜ ሰቲትን ተሻግሮ ከኦምሀጀር (ኤርትራ) ወደ ምፅዋ ወደብ ድረስ የሚጓጓዝ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምት፣ ወልቃይት ጠገዴ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923 እስከ 1966 ዓ.ም.) የቤገምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ክልል፣ በደርግ ዘመነ አገዛዝ ደግሞ (1966 እስከ 1983 ዓ.ም.) የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ክልል አካል ነበሩ። በእነዚያ የአገዛዝ ዘመናት አማራ የሚባል ክልል አልነበረም።
ብዙዎች እንደሚያውቁት፣ ከ1965 እስከ 1970 ዓ.ም. ከአርማጭሆ አንስቶ እስከ ቃፍትያ፣ መዘጋ፣ ጠለምት ጠገዴ፣ ወዘተ. ባሉት አካባቢዎች የኢዲኅ (የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት) እና የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሠራዊት በትግራይ ክልል በኢሮብ ምድር ከነበረው የአሲምባ ዋና ማዕከል ወይም ቤዝ (Base) በተጨማሪ፣ እንደ መከላከያ ምሽጎች የሚገለገልባቸው ሥፍራዎች እንደነበሩ ይታወቃል። ነገር ግን በ1970 ዓ.ም. የኢሕአፓ ሠራዊት ከሻዕቢያ የፖለቲካ ጫና፣ እንዲሁም ከሕወሓትና ከኢዲኅ የተቃጡበትን የጦር መሣሪያ ወረራና በውስጡ የተከሰቱትን የአንጃዎች ግጭትና ጫና መቋቋም ተስኖት ሲፈረካክስና ሲበታተን ከሰቲት ሁመራ፣ ከጠለምትና ከወልቃይት ጠገዴም በሕወሓቶች የጠብመንጃ ኃይል ተገፍቶ እንዲወጣ ተገደደ። ከዚያም ብዙዎች አባላቱ በሱዳን ለተወሰኑ ወራትና ዓመታት ቆይታ አድርገው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አጋዥነት ወደ ተለያዩ አገሮች ሲሰደዱ፣ ጥቂቶች ደግሞ ኢሕዴን የሚባል የፖለቲካ ቡድን መሥርተው ወደ ሕወሓት የፀረ ደርግ ትግል ወድደውና ፈቅደው በአጋርነት ተቀላቀሉ። ሌሎች ደግሞ ለደርግ እጃቸውን ሰጥተው የኢሕአፓን ህልውና በወሳኝ መልኩ እንዲያከትም አደረጉት፡፡ ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች ኢሕአፓ አሁንም ትግሉን አላበቃም የሚሉ ግለሰቦች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። በሌላ በኩል አማራ የሚባል ክልል ቀድሞ ያልነበረ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ‘የጥምቀት‘ ስያሜ ተሰጥቶት የተዋቀረው ከ25 ዓመታት በኋላ በ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በፀደቀ ማግሥት ነው፡፡ ከሌሎች ተጨማሪ ስምንት ክልሎች ጋር እንደነበር የሚታወስ ጉዳይ ነው።
ክልሎቹም የተዋቀሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46 መሠረት ‹‹በሕዝብ አሠፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመሥረት›› ስለነበር ከ46 ዓመታት በኋላ በመሬት ላይ የተከሰቱትን አስገራሚና ሊታመኑ የማይችሉ የቋንቋ፣ የማንነት፣ የሥነ ልቦናዊና ማኅበረሰባዊ ጥንቅር (Demographic) ለውጦች እንዴት ዕውን ሊሆኑ እንደቻሉ በግምት ካልሆነ በስተቀር በበቂ ምክንያት ለማስረዳት አይቻለኝም፡፡ እነዚያ በብዙ መቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኩሩና ጀግና ወልቃይቶች ወዴት ተሰወሩ? በሙሴ መሪነት እስራኤሎች ከግብፆች ባርነት ተላቅቀው ወደ ከነአን ምድር ሲጓዙና የቀይ ባህርን በተዓምር የባህሩ ውኃ በሙሴ ትዕዛዝ ለሁለት ተከፍሎ ለመሻገር ሲችሉ፣ ከባርነት በመለቃቀቸው የተቆጨው የግብፁ ፈርኦን ወታደሮቹን አሳድደው እንዲመልሷቸው ቢያዝም፣ እነዚህ ወታደሮች ተከታትለው በመሄድ እንደ እስራኤሎቹ ለመሻገር የሚቻላቸው መስሏቸው ወደ ባህሩ ሲገቡ እዚያው ተውጠው እንደቀሩ ሁሉ፣ ወልቃይቶችም ባህር ካጠገባቸው ባይኖርም ምናልባት ወደ ተከዜ ወንዝ ተወርውረውና ተበልተው አልቀው ይሆን? ግራ የሚያጋባ እንቆቅልሽ ነው፣ አሳዛኝ የሕዝብ ወገን ታሪክ ነው።
አንድ በግልጽ መጤን ያለበት እውነታ እንደነበረ ከላይ መገለጹን አስታወሱ፡፡ ይኸውም ከ1967 እስከ 1970 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በተለይም መዘጋ፣ ቃፍትያ፣ አዲረመጥ፣ አርማጭሆና ሌሎች የሰሜን ተራራ ኮረብታማ ወረዳዎችና ዋሻዎች የኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ሠራዊት ምሽጎች እንደነበሩ ይነገር ነበር። በ1970 ዓ.ም. ሕወሓት የኢሕአፓን ድርጅት ከአሲምባ ምሽጉ በጦር ኃይል አስገድዶ ሲያስወጣና ድርጅቱ ከውስጥ አንጃዎች፣ ከውጭ ደግሞ የሕወሓትና የሻዕቢያን ዱላ ለመቋቋም ባለመቻሉ ተፍረክርኮ ሲበታተን አብዛኛዎቹ ወደ ሱዳንና ወደ ተለያዩ አገሮች ተሰደዱ፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ምሽጎቹን ለሕወሓት ታጋዮች ለቅቆ መውጣት የግዴታው ስለነበር ይህንን ስትራቴጂካዊ የሱዳን መውጫና መግቢያ በር ሕወሓቶች ፈጥነው ለመቆጣጠር እንደበቁ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን እስከሆኑ ድረስ ጥያቄና ተቃውሞ አልተሰነዘረባቸውም በዚያን ዘመን።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ የሕወሓት ሠራዊት አባላትና ደጋፊዎች የሁመራንና የአካባቢውን ለም የእርሻ መሬቶች ሁሉ ቀስ በቀስ በተወላጆቻቸው ቋሚ ይዞታ ሥር ለመጠቅለል በቅተዋል ማለት ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የወልቃይት ነባር ተወላጆችን (ወልቃይቶችን) በግድያም ሆነ በማፈናቀል ከገዛ መሬታቸው ነቅለው እንዲሰደዱ አደረጓቸው ማለት ነው። በዚህም የተነሳ ዛሬ በአንድ ወገን፣ የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የወልቃይቶች (የአማራ ክልል) ነው፣ ጥንትም ዛሬም፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ የለም የትግራይ ነው ጥንትም ሆነ ዛሬ የሚሉ እርስ በርስ የሚጣረሱ አቋሞች እየተራገቡ ናቸው። አሳዛኝ ትርክት ነው። ይህ በዚህ እንዳለ ቢሆንም፣ የኢሕአፓ ርዝራዦች የነበሩት ጓዶች ‹‹ኢሕዲን›› (በኋላ ‹‹ብአዴን›› ተብሎ የክርስትና ስያሜ በሕወሓት ተሰጥቶት) የሚል የሕወሓት ተቀጥላ ድርጅት መሥርተው እስከ ዛሬ ለመዝለቅ በቅተዋል።
ሆኖም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች መሠረት የተከናወኑት የክልሎች አከላለል ሒደቶችና አፈጻጸሞች በሰላማዊ መንገድ የተከናወኑ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ ክልሎች ደም አፋሳሽ ሁኔታዎች ተከስተዋል፣ የሰዎች ሕይወት ሳይቀጠፍና የንብረት ውድመት ሳይኖር የተከናወነ የክልል አወሳሰንና አወቃቀር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ይህ በዚህ እንዳለ ዛሬ የወልቃይቶችንም ሆነ የማንኛውንም ዘውግ ማንነት የሚወስኑት ራሳቸው ማኅበረሰቦቹ እንጂ፣ ማንም ሌላ አካል የእነሱን የዘውግ ማንነት እንደ ቦሎ አይለጥፍላቸውም፡፡ እንዲሁም ያለ ፈቃዳቸውና ያለ ፍላጎታቸው ወደ የትኛውም ክልል እንዲካለሉ መወሰን የማንም ሥልጣን አይደለም።
ይህንን የመወሰን መብት የራሳቸው የወልቃይቶች የማይገሰስ መብት ነውና። በሌላ በኩል፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48 መሠረት፣ ‹‹የአከላለል ለውጥ ወይም የክልል ወሰን የመደንገግ ወይም የመለወጥ/የማሻሻል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ ጉዳዩ በማኅበረሰቡና በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት መፈጸም ይኖርበታል። እነዚህ ለመስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብ አሠፋፈርንና ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ›› በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ራሱ ደርግን የገረሰሱት የአሸናፊዎቹ የሕወሓት ትሪክት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰፊ ጊዜ ወስዶና በበቂ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ያሳለፈውን ስምምነትና ውሳኔ እንዳልነበር በጊዜው የነበርን የቅርብ ተሳታፊዎችና ታዛቢዎች በትክክል የምንመሰክረው እውነታ ነው።
ልክ እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥቱ የ1923 እና የ1948 ዓ.ም. ሁለት ሕገ መንግሥቶችና እንደ ደርጉ የ1979 ዓ.ም. የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት፣ የወያኔ/ኢሕአዴግ የ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ‹‹ለሚወዱትና ለሚወዳቸው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፤›› ወድደውና ፈቅደው የሰጡት ስጦታ ነው። በዚህም የተነሳ ሰጪዎቹ ባለፉት 27 ዓመታት ሕገ መንግሥቱን እንዳሻቸው ሲጥሱ በመቀጠላቸው ሰነዱ የወረቀት ላይ ነፃነት ብቻ ሆኖ ቀርቷል።
ለማንኛውም የወልቃይት ጠገዴ፣ የጠለምት፣ የሰቲት ሁመራ፣ አላማጣ ራያ ቆቦ የማንነትም ሆነ የአከላለል ጥያቄ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ምላሽ የሚያገኝ ውስብስብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዛሬው ዘመን የትግራይ ነፍጠኛ ወራሪዎችና ጉልበተኞች በ1984 ዓ.ም. በጠብመንጃ ኃይል በቅኝነት ተይዞ የቆየ የአማራ ክልል ይዞታ ስለሆነ፣ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታና ማካካሻ ለአማራ ክልል መንግሥት በአስቸኳይ መመለስ የግዴታ ይሆናል፡፡ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የሁለቱም ክልሎች የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን አሁንም በአግባቡ ለመወጣት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ለወልቃይት ጠገዴም ሆነ ከወሎ ጠቅላይ ግዛት ተቆርሰው የተወሰዱትን የአላማጣ፣ የኮረምና የራያ ቆቦ የአማራ ይዞታ የነበሩትን መሬቶችንም በተመለከተ፣ የፌዴራል መንግሥት ብዙ ጊዜ ሳይወስድ የማያዳግም የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጠውና የአካባቢው ሰላም እንዲከበር ሊያደርገው ይገባል፣ ይቻላልም።
በመጨረሻም የፌዴራል አባላት ክልሎችን ወሰን በተመለከተ በየጊዜው መከለስና ለሕዝቦች መስተጋብር በሚያመች ሁኔታ ጂኦግራፊን፣ የኢኮኖሚ አዋጪነት፣ የማኅበረሰብ አሠፋፈር፣ የሚመለከታቸው ወገኖች ፍላጎት፣ የክልሎች እኩልነት ወይም ተመጣጣኝነት፣ ወዘተ. መሥፈርቶች በመጠቀም ማካለል አዲስ ክስተት አይደለም። ከናይጄሪያ እስከ ህንድ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካናዳ፣ ከስዊዘርላንድ እስከ አውስትራሊያ ያሉት የፌዴራል አገሮች በየጊዜው የአባል ክልሎቻቸውን ወሰኖች ይከልሳሉ፣ ያሻሽላሉ፣ ይለውጣሉ። የኢትዮጵያ መንግሥትም የወልቃይት ጠገዴ፣ የሰቲት ሁመራ፣ የጠለምትን፣ የአላማጣ ራያ ቆቦንም ሆነ ሌሎች የፌዴራል ክልሎችን በተመለከተ በየጊዜው የሚነሱትን ጥያቄዎች እየመረመረና እያስጠና በተመሳሳይ አካሄድ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲቋጩ ማድረግ ይኖርበታል። በእንዲህ ዓይነት የማንነትና የአከላለል ጥያቄዎች የተነሳ አስፈለጊና ተገቢ ያልሆኑ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶች ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ክስተቶችን ማስከተል በፍፁም አይኖርባቸውም።
ከዚህ ውጪ በማወቅም ሆነ ከግንዛቤ ዕጦት በመነጨ አጉል እንቅስቃሴ የሁለቱን ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች ወደ የማያባራ ግጭትና ጠላትነት የሚያስገባ እንቅስቃሴ ሁሉ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ አጥብቀን እንጠይቃለን። በዚህ ረገድ የሚደረገው አሉታዊ እንቅስቃሴ ወይም ሴራ ሁሉ በፅኑ መወገዝ አለበት፡፡ የሕዝብ እውነት ምንጊዜም አሸናፊ ነው። እግዚአብሔር ሰላማዊ አብሮነታችን፣ የእርስ በርስ መተጋገዛችንና ወንድማማችነታችንን ለዘለዓለም ይጠብቅልን።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቆቃ!
ደበሌ ከተማ የሚባል ሰው፣ ‹‹ወልቃይት በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል ሲከለል ለምን ይሆናል…›› ያሉና የተቃወሙ ወጣቶች ላይ የደረሰውን ግፍ አንድ ወታደር እንደሚከተለው ተናግሮ ነበር ይለናል፡፡ ‹‹በመጀመርያ ወጣቶቹ ከወልቃይት ተጭነው ወደ ትግራይ ተወሰዱ። ከዚያም እጅና እግራቸው ታጥፎ ተሰበረ። በዚህ ሁኔታ ለሃምሳ ቀናት ራቁታቸውን አንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው በቀን አንድ ዳቦ ከብዙ ዱላ ጋር እየተሰጣቸው እንዲቆዩ ተደረገ። ሃምሳ ቀን ሙሉ ከዚያ ቤት አልወጡም። በሃምሳኛው ቀን አንድ የጭነት መኪና መጣና ወጣቶቹ ተዘግተውበት የነበረው ቤት ተከፈተ። በወቅቱ በአካባቢው የነበረውን ሽታ በቃላት ለመግለጽ አዳጋች ነው። ወጣቶቹ በጣም ከመክሳታቸው የተነሳ ወታደሮቹ በአንድ እጃቸው ፀጉራቸውን አንጠልጥለው ወደ መኪናው ይወረውሯቸው ነበር። አንደኛውን ወጣት ፀጉሩን ይዞ ሲወረውረው፣ ፀጉሩ ተነቅሎ ወደቀ። ያንን ስመለከት ሰው ሆኜ መፈጠሬን ጠላሁት።
‹‹ወጣቶቹን ጭኖ የሄደው መኪና ማታ አካባቢ ባዶውን ተመለሰ። ወጣቶቹን እንደ ገደሏቸው ባውቅም ከዚያ ሁሉ ሥቃይ መሞት እንደሚሻላቸው በመረዳቴ ደስ አለኝ። ቢሆንም ግን ይህ ድርጊት በአዕምሮዬ እየተመላለሰ ስለረበሸኝ ከሥራዬ ልለቅ ችያለሁ። በወቅቱ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው በትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት በገብሩ አሥራት ቀጥተኛ ትዕዛዝ ነበር፤›› ሲል ነው ምስክርነቱን የሰጠው፡፡
Filed in: Amharic