>

ቅርሶች እያሰሱ የማጥፋቱን ዘመቻ በስፋት ተይያይዘውታል .....!!!-  (ዮሀንስ መኮንን)

ቅርሶች እያሰሱ የማጥፋቱን ዘመቻ በስፋት ተይያይዘውታል …..!!!

ዮሀንስ መኮንን

*… የአንዲት ከተማ መሪ ዕቅድ (Master Plan) ሲዘጋጅ ታሪኳን እና ቅርሶቿን የሚያንጸባርቁ አደባባዮች፣ መንደሮች፣ ግብረ ሕንጻዎች እና ሀውልቶች የመሳሰሉት ለትውልድ እንዲተላለፉ የተለየ ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ያዝዛል። አዳዲስ ሕንጻዎች መገንባት የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝም የከታማዋን የታሪክ አሻራ ሳይደመስሱ መሪ ዕቅዱ በሚፈቅደው መሠረት ማልማት ይቻላል። 
ከዚህ ሳይንሳዊ እውነት በመቃረን በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ ከከተማ ልማት (Urban Development)፣ ከቅርስ ጥበቃም (Heritage Conservation) ሆነ ከአከባቢ ልማት (Local Development Plan) በተቃረነ መልኩ በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን እያደኑ የማውደም አባዜ በቸልተኝነት ወይንም በአሠራር ስህተት የመጣ ሳይሆን ይሁነኝ ተብሎ በእቅድ እየተሠራበት መሆኑን ለማመን ተገደናል።
መቼም ባለ አጭር ትውስታ (Short Memory) ካልሆንን “የብልጽግና” መንግሥት ሰዎች በትረ መንግሥት ከጨበጡ በኋላ የተቀናጀ እና የተናበበ በሚመስል መንገድ የከተማዋን ቅርሶች እያደኑ እየደመሰሷቸው መሆኑን ለአንባቢ ጥቂት ማስታወስ ይገባል።
1) 90 ዓመታት ያስቆጠረው ለገሀር ይገኝ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ቅርስ ቡፌ ዴ ላጋር ፈርሷል።
2) የደጃዝማች ዐምዴ አበራ ካሳ መኖሪያ ቤት (ከተገነባ 90 ዓመታት በላይ የኾነው በቅርስነት የተመዘገበ ቤት) ፈርሷል፤
3) ስድስት ኪሎ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ይገኝ የነበረው የደጅ አዝማጅ አስፋው ከበደ መኖሪያ የነበረው በቅርስነት የተመዘገበ እንደሆነ እየታወቀ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ “ቦታውን እፈልገዋለሁ” ብሎ አፍርሶታል፤
4) ፒያሳ ሰባራ ባቡር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ይገኝ የነበረው እና በቅርስነት የተመዘገበው የራስ ኃይሉ መኖሪያ ቤት ፈርሷል፤
5) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው እና ከተቆረቆረ 80 ዓመታትን ያለፉትን ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ሊፈርስ ሲል በብዙ ጨኸት ለጊዜው ቆሟል፤
ዛሬ ደግሞ አሳዛኝም አሳፋሪም ሌላ የቅርስ ድምሰሳ ውሳኔ (መርዶ) ተሰምቷል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለቅርንጫፍ አራት ቤቶች ኮርፖሬሽን በጻፈው ደብዳቤ ከከንቲባ ቢሮ በደረሰው ትእዛዝ መሠረት ፒያሳ የሚገኙት አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ (በቅርስነት የተመዘገቡ) ግብረ ሕንጻዎች አቶ ጀርመን አመንቴ ለተባሉ ባለሀብት የዘመናዊ ሞል መገንቢያነት በመሰጠታቸው የተከራዮች ውል እንዲቋረጥ ትእዛዝ አስተላልፏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የካቲት 4 ቀን 2013 ለአራዳ ክፍለከተማ ፕላን እና ልማት ኮሚሽን ጽ/ቤት በጻፈው ባለ 8 ገጽ ደብዳቤ በአራዳ ክፍለከተማ ውስጥ የሚገኙ እና በቅርስነት የተመዘገቡ 205 ግብረ ህንጻዎችን አሳውቆ ነበር። በዚሁ ዝርዝር በተራ ቁጥር 26 እና34 ላይ ጥንታዊው አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ ተጠቅሰዋል።
በከተማዋ መሀልም ይሁን በዳርቻዋ ሞልቶ ከተረፈ እና ካልጠፋ የግንባታ ቦታ በከተማዋ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባቸውን መካናት እያሰሱ ማፍረስ ሆን ተብሎ በተደራጀ እና በእቅድ የሚሠራ የማንነት አሽራ ድምሰሳ ተግባር በመሆኑ ይህንን ዘውገኛ የፖለቲካ አሻጥር ሀገሩን፣ ከተማውን እና ታሪኩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ሊያወግዘው እና ሊቃወመው ይገባል።
Filed in: Amharic