>
5:13 pm - Friday April 19, 0515

" አገር እንድትቀና ... !!!" (ታሪክን ወደኋላ)

” አገር እንድትቀና … !!!”

ታሪክን ወደኋላ

*…. ለወጣቱ የምኒልክ አልጋ ወራሽ ለልጅ እያሱ ምክር ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያን በልማት ጎዳና ለመውሰድ አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን እርምጃዎች ነጋድራስ ገብረህይወት ባይገከዳን በሚከተለው መልክ አስቀምጠው ነበር።
አንደኛ (፩)
ለመንግስት የሚሆን ገንዘብ እና ለንጉሡ የሚሆን ገንዘብ ይለይ። ሹማምንቱ በደሞዝ ይደሩ። ካገር የሚወጣውም ግብር ለመንግስት ይግባ። የጦርም ሰራዊት ሁሉ የንጉሡ ይሁን። ያገር ምስለኔና የጦር አለቃ በያገሩ ይለይ። መጀመሪያው ባላገሩን የሚያዝ ሁለተኛው ግን ወታደሮቹን።
የንጉሱና የመንግስት ገንዘብ የተባለው ትርጉሙ እንዲህ ነው። የንጉሥ ገንዘብ ማለት ያ ለግብር እና ለሌላ የንጉሡ ቤት ጉዳይ የሚያስፈልግ ገንዘብ ነው። የመንግስት ገንዘብ ማለት ግን ያ ለሠራዊት ደሞዝ፣ ለመንገዶች እና ለትምህርት ቤቶች ማሰሪያ የጦር መሣሪያዎችም መግዣ ለሌላ እንዲህ የመሰለውም የውጭ ጉዳይ የሚሆነው ገንዘብ ነው።
ሁለተኛ (፪)
ህዝቡ ለመንግስት የሚከፍለው ግብር እንደየሃብቱ መጠን ቁርጥ ሆኖ ይታወቅለት። የሕዝቡም ቁጥር በመዝገብ ይግባ። እንዲሁም በየዓመት የሚወለደውና የሚሞተውም የሚጋባውና የሚፋታውም በመዝገብ ይታወቅ።
ሶስተኛ (፫)
ሕዝቡም የሚከፍለው ግብር በብር እንጅ በእህል በማርም በፍሪዳም አይሁን። የመንግስት ሥራ ሁሉም በባላገር አይሠራ፤ በባለ ደሞዝ እንጅ። ባላገሩም የሚከፍለው ግብር በመላው አገር እኩል አይሁን፤ ያውራጃው ሀብት እየታየ እንጅ። አሁን ቤጌምድር፣ ሰሜን ላስታ፣ ጎጃም፣ የጁ፣ ወሎ ብዙ ብር አይገኝበትም፤ ስለዚህ እንደሃብታሞቹ ሸዋና ትግሬ ሊገብሩ አይቻላቸውም።
አራተኛ (፬)
ያማርኛ ቇንቇ ገና ሰዋስው አልተበጀለትም። ስለዚህ መንግስታችን ከያገሩ ስዋስው የሚያውቁትን ሊቃውንት ሰብስቦ የአማርኛ ቇንቇን ስዋስው ቢያስወጣ ደግ ነው። በያገሩ አውራ ከተማ እንደ አውሮጳ ስርዓት ያበሻን ፊደልና ያማርኛን ቇንቇ ማስተማሪያ ቤቶች ይከፈቱ። ባዲስ አበባ፣ በሐረርጌ፣ በጎንደር፣ በአክሱም ግን አውራ የትምህርት ቤቶች በንዲህ ያለ ስርዓት ይቁሙ። በያንዳንዱ የትምህርት ቤት አራት የኤሮጳ መምህራንና አምስት ያበሻ መምህራን ይሹሙበት። የያንዳንዱ የኤሮጳ መምህርም ሥራ እንዲህ ይሁን። አንዱ የቁጥር እና የሂሳብ አስተማሪ፣ ሁለተኛው የዓለም ታሪክና ጂኦግራፊያ አስተማሪ፣ ሶስተኛው የንግሊዝ ቇንቇ አስተማሪ፣ አራተኛው የፈረንሳዊ ቇንቇ አስተማሪ። በአክሱም ግን በአንግሊዝ ቇንቇ መምህር ፈንታ የኢጣልያ ቇንቇ አስተማሪ ቢሾም ይሻላል። ያበሾቹ መምህራን ሥራ ግን ይህ ይሁን፤ አንዱ የወንጌል አስተማሪ፣ ሁለተኛው ያማርኛን ቇንቇ አገባብ አስተማሪ፣ ሶስተኛው የመንግስታችንን ታሪክ አስተማሪ፣ አራተኛው የፍትሐ ነገስት አስተማሪ።
ስላራቱም አውራ የትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉን መምህራን አስራ ስድስት የኤሮጳ ሰዎችና ሃያ አበሾች ናቸው። አንድ ደልዳላ የኤሮጳ መምህርም በሁለት ሺህ ብር ባመት ይገኛል። ያበሻውም አንድ አስተማሪ ሶስት መቶ ብር ባመት ቢያገኝ ይበቃዋል። ስለዚህ ለመምህራን የሚሆነው ደሞዝ በየዓመቱ 38 ሺህ ብር ነው። ለትምህርት ቤቶችም ሌላ ጉዳይ ሁሉ 132 ሺህ ብር ይበቃል። ስለዚህ አውራዎቹ የትምህርት ቤቶች የሚያስፈልገው ኪሳራ 500 ሺህ ብር በዓመት ብቻ ነው። ፊደልን ያላጠና ልጅም በአውሮቹ የትምህርት ቤቶች አይግባ። የፊደል ማስተማሪያ ቤት ግን ያውራዎቹ ገዦች እንዲያስባቸው መንግስት የግድ ይበላችው።
ያገራችንም ሰው ፊደልን ለመማር ቢተጋ አገራችን ቶሎ በቀናች።ፊደልንም መማር እጅግ ቀላል ነገር ነው። በሱዳን መሬት የሚኖር አንድ ትጉህ የወሎ ልጅ እድሜው 35 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ምንም አያውቅም ኖሮ አሁን አማርኛን እና ዓረብኛን አጥርቶ ይፅፋል። ብዙዎችም ያገራችን ሰዎች የዚያን ብልህ ወሎዬ መንገድ ቢከተሉ አገራችን በተጠቀመች። ደሞም የኤሮጳን ሰራተኞች አምጥተው በአዲስ አበባ፣ በጎንደርም እንዲሁም በአክሱም የእጅ ሥራ ማስተማሪያ ቤቶች ቢበጁ ማለፊያ ነበር። መንግስትም ለንደዚህ ያለ የትምህርት ቤቶች ምንም ብዙ ዋጋ ቢያጠፋ ግድ የለም ነበር። ወዲያው የሚያስፈልገውን ሥራ በነዚያ የትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሰራ ነበርና። እንደዚህ ያለ ጠቃሚ የትምህርት ቤት በካርቱም ከተማ ተነጅቷልና መንግስታችን ወደዚያ ተመልካች ይላክ።
አምስተኛ (፭)
ፍትሃ ነገስታችን ከዛሬው ያደባባይ ስርዓት ጋር አይስማማም። ስለዚህ መንግስት የሥርዓት አዋቂዎችን ሰብስቦ ከኤሮፓ ስርዓት ጋር የተስማማ ፍትሃ ነገስት ያውጣ። ይህም ሲደረግ የኤሮጳ ስርዓትን የሚያውቅ አማካሪ ያስፈልጋል። የተፃፈ ስርዓት የሌለው መንግስት ብዙ እድሜ የለውም።
ስድስተኛ (፮)
ያገራችን ሰራዊት ስርዓት የለውም። ስለዚህ የኤሮፓን መክዋንንት አምጥተው ሰልፍን ቢማር ማለፊያ ነበር። እንዲሁም የኤሮፓን መምህራን አምጥተው ባዲስ አበባ ላይ የጦር ትምህርት ቤት ይበጅ። ላገራችን የሚስማማ ማለፊያ አይነት የጦር ትምህርት ቤትም በካርቱም ከተማ ተበጅቷል። ስለዚህ መንግስታችን ወደዚያ ተመልካች ይስደድ። የሰራውትም ብዛት በልክ ይሁን። ሰራዊት ቢበዛ መንግስት ይደሄያል እንጅ አይበረታም።
ሰባተኛ (፯)
የዛሬው የመንግሥታችን ብር የተበላሸ ነው። ስርዓት ውል የለውም። ባንዱም አውራጃ በጨው በሌላው በጥይት ይገበያያል። ስለዚህ መንግስት ለመላይ ኢትዮጵያ የሚሆን የገንዘብ ስርዓት በቶሎ ያላወጣ እንደሆነ ንግድ ሊለማ አይችልም።
ስምንተኛ (፰)
ላገራችን ነጋዴ ስርዓት እስኪወጣለት ድረስ መንግስታችን አይቀናም። በሩና ቀራጩ ብዙ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት አንድ አደፋር የጎንደር ነጋዴ በመተማ ግመሎች እንደተወደዱ ሰምቶ ግመሎችን ሊገዛ ወደ ጥልጣል መሬት ወረደ። ገዝቶ ሲመላለስ ያገኘውንም መከራ እንዲህ ሲል አጫወተኝ። ከጥልጣል መሬት ግመሎችን ይዤ ተነስቼ መተማ እስክገባ ድረስ በረኞቹ ላይ ቀረጥ ከፈልሁ። በየበሩም ጉቦ እስኪቀበሉ ድረስ አናሳልፍም እያሉ መከራ ሲያበሉኝ ነበር። መተማም ደርሼ ግመሎቹን ብሸጥ ስላገኘሁት መከራ የሚክስ ጥቅም አላፈራሁም። በዚህ ምክንያት ይህ አይነት ንግድ እነግዳለሁ ብዬ አይደግመኝም። ያ ሰው እውነቱን ነው። የግመሎቹም ንግድ ቢቀር የሚጎዳ እርሱ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ከሁሉ ይልቅ ያገራችን መንግስት ያገራችን የቀረጥ ስርዓት ያለው ቢሆን ብዙ ግመሎች ሲሸጡ መንግስት ገንዘብ ያገኝ ነበር። ነጋዴዎቹም በሚያገኙት ትርፍ በሬና ላም ገዝተው ወይም በሌላ አይነት ሥራ አገርን ባለሙ። ግመሎቹ አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የጥልጣልን ሜዳ ሳር ቢበሉ ግን መንግስታችን የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው?
ባንድ መንግስት ውስጥ ብዙ በር ሊበጅ አይገባም። ለመንግሥትም ትልቅ ጉዳት ነውና። ምነው ወደ ሱዳን ወይም ወደ ሐማሴን ተመልካቾች ሰደን ስርዓት አንማርም?
ዘጠነኛ (፱)
ህዝቡ ባንድ መንግስት ውስጥ መሆኑን አጥብቆ እንዲታወቀው አገሩን የሚዞሩ ተቆጣጣሪዎች ይሹሙበት። እነሱም ባገር ግዛት ከሚንስትር በታች ይሁኑ።
አስረኛ (፲)
የሃይማኖት አርነት ይታወጅ። የሃይማኖት ጥቅም መሆኑን የማያውቅ ብዙ ሰው ይኖራል። ስለዚህ የሚከተለውን ብናስተውል ደግ ነው። ያገራችን ሰው የተዋህዶ ሃይማኖት ከሁሉ ሃይማኖት ይበልጣል ብሎ ያምናል። በልጦ ግን ምን ረባን? ማንስ አወቀው? ያገራችን ካህናት መንግስት ጠበቃቸው ሆኖ ሌላ ሃይማኖት እንዳይገባ አውቀው ሃይማኖታቸውን ለሕዝቡ ለገልፁለት ሃሳብ የላቸውም። ስለዚህ ህዝቡ እንክዋን ተዋህዶ ማለት ምንድን እንደሆነ አይለይ፤ የክርስትያን የሃይማኖት አውራ መሰረት የወንጌልን ቃል አያውቅም። ስለዚህ አጉል ቀረ፤ የሃይማኖት አርነት እስኪታወጅ ድረስም አጏጉል ይቀራል። ለዚህም ነገር ምስክር በሀማሴን እናገኛለን። በድሮ ዘመን በዚያች አገር መሃይማን ይቅርና ብዙ ቄሶች ሃይማኖታቸውን ሳያውቁ ይኖሩ ነበር። ፕሮቴስታንቶች እና ካቶሊኮች ከመጡ ወዲህ ግን ትንሹም ትልቁም የወንጌልን ቃል አውቆ በትርጉሙ ይከራከራል። ካህናቱም በል አምጣ ቢበዛባቸው ያስተምሩ ጀመር። በዚህ ምክንያት የሃይማኖት አርነት ቢታወጅ ሃይማኖት ይታወቃል እንጂ አያጠፋም።
ደግሞም ባገራችን አንድ የድንቁርና ነገር አለ። ሃይማኖቱ ተዋህዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ እርኩስ ይቆጠራል። ይህም እጅግ ያስቃል። አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል።
ሃይማኖት የልብ ነገር ነው። ስለዚህ ሰማያዊው ንጉስ እንጂ የዚህ ዓለም ንጉሥ አይቆጣጠረውም። ወንጌል የቄሳርን ለቄሳር ስጡ የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር ያለውም በዚሁ ቢተረጎም ለመንግሥታችን ሳይበጅ አይቀርም።
ምንጭ:- የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ስራዎች
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ
Filed in: Amharic