>
5:26 pm - Monday September 17, 2260

ጥቂት በማይባሉ የአ.አ. አካባቢዎች ሕገ ወጥ የውኃ ሽያጭ ደርቷል (ከይኄይስ እውነቱ)

ጥቂት በማይባሉ የአ.አ. አካባቢዎች ሕገ ወጥ የውኃ ሽያጭ ደርቷል

ከይኄይስ እውነቱ


በርእሱ የተመለከተውን ጉዳይ ስታዘብ ከረምረም ብዬአለሁ፡፡ ዐቢይ ከሆነው አገራዊ ጉዳይ በተጓዳኝ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የምናነሳው የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያዳምጥ ጆሮ አለ ብለን መፍትሄ ለማግኘት ሳይሆን፣ ሁሉም ማለፉ አይቀርምና እንዲመዘገብ ነው፡፡ አንድም ኅብረተሰቡ ለዘረፋ የተሰማሩትን ‹ተረኞች› ዐውቆ ተገቢ ነው የሚለውን ርምጃ እንዲወስድ ለማሳሰብ ነው፡፡  ይህ ደግሞ ለጋራ ጥቅም በጋራ ተሰልፎ በኅብረት መብትን ማስከበር ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ በወያኔና በአሁኑ ተረኞች ዘመን የመተባበርና የመደጋገፍ እሤቶቻችን በመሸርሸራቸው ይሁን ወይም ጸጕረ ልውጦች ጣልቃ ገብተው በተረኝነት መንፈስ እየከፋፈሉት ወይም የሁለቱ ድምር ውጤት የኅብረት መንፈሱ በእጅጉ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ የውኃ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ሌሎች የጋራ አገልግሎቶች ሲቋረጡ አብዛኛው የአካባቢ ነዋሪ አድፍጦና ጥጉን ይዞ ጥቂት ግለሰቦች እንዲሯሯጡለትና ክትትል እንዲያደርጉለት ጠባቂ መሆኑ የተለመደ አሳፋሪ ጠባይ ሆኗል፡፡ 

ይህን ርእሰ ጉዳይ ያነሳሁት ሕዝብ የሚያውቀውንና ፀሐይ የሞቀውን በአ.አ. ውኃ በፈረቃ መታደሉ ዓመታትን ያስቈጠረ ክስተት መሆኑን ለማርዳት አይደለም፡፡ ይልቁንም ‹‹የመጠጥ›› ውኃውን አገልግሎት የሚሰጠው መንግሥታዊ ድርጅት (በ‹ተረኞቹ› ቊጥጥር ሥር በመሆኑ) አገር እያመሱ ካሉ ተረኞች ጋር በመመሳጠር በአንዳንድ አካባቢዎች በፈረቃ የሚሰጠውን አገልግሎትም እስከነአካቴው አቋርጦ ተገልጋዩን ማኅበረሰብ ለቀን ጅቦች ሲሳይ ማድረጉን ስንሰማ ባንደነቅም ምድራችን አልጠገብ ባይ ከርሳሞችን በፈረቃ ማስተናገዷ ያስገርመናል፡፡

ከተገልጋዩ ማኅበረሰብ እና ከተቋሙ ሠራተኞች ባገኘነው መረጃ መሠረት ‹ተረኞቹ› የመክፈል አቅሙ አላቸው ብለው በገመቱባቸው አካባቢዎች በፈረቃ የሚሰጠው የውኃ አገልግሎት እንዲቋረጥ በማድረግ ውኃ በተለምዶ ቦቲ በምንላቸው (በርሜል በተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች) ውኃ በሽያጭ አቅራቢዎች ሆነዋል፡፡ እነዚህ ተረኞች አገራዊ ተቋም ተክተው ያልተፈቀደላቸውን አገልግሎት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመስጠት ኅብረተሰቡን እየዘረፉ ይገኛሉ፡፡ 

እኔ ለሬከርድ እንደጫርኹት ሁሉ፣ ኅብረተሰቡም ‹አቤት› ከማለት ጀምሮ በመፍትሄው ላይ እንዲመክር ለማሳሰብ የታዘብሁትን እነሆ ብዬአለሁ፡፡

Filed in: Amharic