>

ወደ ቀልባችን ከተመለስን፤ የድህረ ጦርነት ግምገማ እና የሽግግር ወቅት ፍትህ (ያሬድ ሀይለማርያም)

ወደ ቀልባችን ከተመለስን፤ የድህረ ጦርነት ግምገማ እና የሽግግር ወቅት ፍትህ
ያሬድ ሀይለማርያም
 
“Politicla madness is the worst of all form of madness”
 
Bamigboye Olurotimi

በርዕሴ ላይ እንዳልኩት ከፖለቲካው እብደት አገግመን ወደ ቀልባችን ከተመለስን እንደ አገር አሁን ሊያስጨንቁን እና ቅድሚያ ልንሰጣቸው ከሚገቡት በርካታ ነገሮች መካከል ዋነኞቹ፤ የድህረ ጦርነት ግምገማ ወይም ምርመራ (post war assesment) እና የሽግግር ጊዜ ፍትህ  (transitional justice) ናቸው። እነዚህ ሁለት ሂደቶች አንድ በጦርነት ሲታመስ የቆየን፣ በጦርነቱ ምክንያት ብዙ ጉዳቶችን ያስተናገደን፣ ከፍተኛ የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተፈጸሙበት እና በአለም አቀፍ ወንጀሎች የሚያስጠይቁ እንደ ዘር ማጥፋት፣ ዘር ማጥራት፣ በሰው ስብዕና ላይ ያነጣጠሩ የሰቆቃ ድርጊቶች፣ የጦር ወንጀል እና ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውሶችን ያስከተሉ ድርጊቶች የተፈጸሙበት አገር ከቁስሉ ለማገገም እና ማህበረሰቡንም ወደ ተረጋጋ ሕይወት ለመመለስ እጅግ ወሳኝ ናቸው። ይሁን እንጂ የድህረ ጦርነት ግምገማ ለማካሄድም ሆነ የሽግግር ወቅት ፍትሕን ለማስፈን አገራዊ ስክነት የግድ ይላል።
አዎ፤ ለጦርነቱ ዋነኛ ምክንያት የሆኑት ፖለቲከኞቻችን ሰቀን ሊሉና ወደ ቀልባቸውም ሊመለሱ ግድ ይላል። አገራዊ ስክነት ሊመጣ የሚችለው በቂምና በጥላቻ የተሞሉ፣ በሥልጣን ጥማት የሰከሩ፣ በሙስና የተዋጡ፣ በእብሪት ያበጡ ፖለቲከኞች ወደ ቀልባቸው ሲመለሱ፤ እንዲሁም እነሱ ሲያብዱ አብሯቸው የሚከንፍ ቁጥሩ ቀላል የማይባል በግራና ቀኝ የተሰለፈ ልሂቅ ሰከን ማለት ሲችል፣ ወደ አስተውሎቱ ሲመለስ እና አገር በጦርነት (በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት) የት ልትደርስ እንደምትችል ዘግይቶም ቢሆን መረዳት ሲችል ብቻ ነው። በእኔ እምነት የገባንበት ጦርነት ምንጩ የፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ እብደት እንደሆነ ቀደም ብዮ ጽፌበታለሁ። ነገሩን የከፋ ያደረገው ግን በግራ እና በቀኝ ባሉት ፖለቲከኞች ዙሪያ እብደቱን የተቀላቀሉ እጅግ ብዙ ልሂቃን (ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች) መፈጠራቸው ነው። ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሰላም እና ዕርቅ ማውራት ያሰድብ፣ ያስወቅስ፣ ያስፈርጅም ነበር። ለእኔ ያሳለፍነው የአንድ አመት ተኩትል ጊዜ የእብደት ወቅት ነበር። ዛሬ ከዛ ዕብደት መለስ ያልን ይመስለኛል።
“Madness is rare in individuals. But in groups, political parties, nations and eras, it’s the rule” Friedrich Nietzsche
እብደት ሕግና ለማድ ሆኖ እንዳይቀጥል ከዚህ ቀውስ በሚያወጡን ወሳኝ ነገሮች ላይ ማተኮር የግድ ይላል።
+ የድህረ ጦርነት መጠነኛ ዳሰሳ
ድህረ ጦርነት ማለት በግጭት ውስጥ የነበሩ ኃይሎች አንድም በእርቅ ወይም በተኩስ አቁም ስምምነት ወይም በአንደኛው አካል ሙሉ በሙሉ አሸናፊነት ማግስት የሚመጣ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ወቅት ወይም ረዘም ያለ ጊዜ ማለት ነው። ይህ ወቅት ብዙ ጊዜ ጦርነቱ ባስከተለው ቀውስ አገር እና ሕዝብ ገና ያልተረጋጉበት፣ አልፎ አልፎም ግጭቶች እና የጥይት ድምጽ የሚሰማብት፣ ተፋላሚ ወገኖች የወታደሮቻቸውን ቁስል እያከሙ ከእልህ እና ከብስጭት ያልወጡበት፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው ያልተመለሱበት፣ የተፈናቃይና ስደተኞች ካምፖች በሕጻናት እና ሴቶች የተሞሉበት፣ ጦርነት ባደቀቀው ኢኮኖሚ የኑሮ ውድነት አቅል በሚያስጥልበት፤ ባጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውጥረቶች የነገሱበት ወቅት ነው። ይህ ወቅት ብዙን ጊዜ No war, No peace በመባል ይገለጻል። ኢትዮጵያ ዛሬ በዚህ አይነቱ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው።
ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ፣ መቼ ተጀመረ፣ ለምን ተጀመረ የሚሉትን አሰልቺ ጥያቄዎች በዚህ አጭር ጽሑፍ ማንሳት አልፈልግም። ምክንያቱም እነዚህ ጥያቄዎች መልሳቸው ግልጽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚም ሲገለጹ የቆዩ ስለሆነ እነሱን በመተንተን ላሰለቻችሁ አልፈልግም። ጦርነቱ ያስከተልወ ጉዳት ግን በጣም ሰፊ የሆን ጥናት እና በበቂ ሁኔታ መረጃዎችንም ማሰባሰብን ይጠይቃል። በጦርነቱ በዋናነት ሦስቱ ክልሎች፤ ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ቢጠቁም፣ ሙሉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ሰላም እና ደህንነት ግን ክፉያ ተጎድቷል። በመሆኑም ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት በክልሎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር ደርጃ በአግባቡ ሊጤን እና ሊመረመር ይገባል። ይሕ ጦርነት አገሪቱን በምን ያህል አመታት ወደኋላ እንደመለሳት ለማወቅ የሚቻለው በቅጡ ሲጠና ነው። በተለይም እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፣
–       በጦርነቱ በሁለቱም ወገን ምን ያህል ሰው ሞተ?
–       ምን ያህል የመንግስት እና የገለሰቦች ንብረት ወደመ?
–       ምን ያህል ሰው ለቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት ተዳረገ?
–       ምን ያህል ሴቶች የወሲባዊ እና የጽዖታ ጥቃት ተፈጸመባቸው?
–       ምን ያህል ሰው ጦርነቱን ሸሽቶ ከአገር ተሰዶ በጎረቤት አገር የስደተኛ ካም ሰፈረ?
–       ምን ያህል ሰው ከቅዮው ተፈናቅሎ በየመጠለያ ካምፕ ውስጥ ይገኛል?
–       ምን ያህሉስ ከተፈናቀሉበት ወደ ቀያቸው ተመለሱ?
–       ምን ያህል ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸ እንዲርቁ ተደረግ?
እነዚህ እና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በአግባቡ ማጥናት እና በቁጥር አስደግፎ የደረሰውን ኪሳራ መጠን ማስላት እና መሰነድ የግድ ይላል።
ጦርነቱ እንደተጀመረ የትግራይ አማጺዎች ትልማቸው ትግራይ የምትባል እራስ ገዝ አገር መፍጠር እንደሆነ ደጋግመው ነግረውናል። ያ ሳያንሳቸው ኢትዮጵያ የምትባልን አገር ደግሞ ለማጥፋት ሲዖል ድረስ እንደሚወርዱም ነግረውናል። በፌደራል መንግስቱ በኩል ደግሞ ጦርነቱ በህውሃት አጫሪነት በመቀስቀሱ ዋና ተልዕኮው ሕግ የማስከበር እና እነዚህን አማጺዎች ወደ ፍርድ ማቅረብ፣ የኢትዮጵያን ግዛት ማስጠበቅ እና ትግራይን ከህውሃት እጅ ሙሉ በሙሉ ነጻ ማውጣት ነበር። ይህ የድህረ ጦርነት ግምገማ እነዚህ ሁለት አካላት ጦርነት ውስጥ የገቡበትን ዋነኛ ምክንያት በማጤን ዛሬ የደረሱበትን እና አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታም በቅጡ መመርመርን ይጨምራል። እንደ እኔ ጠቅላላ ዳሰሳ ኢትዮጵያ እንደ አገር በዚህ ጦርነት ከሥራለች፣ ተዋርዳለች፣ ተራቁታለች፣ ከፊል አካሏ በእሳት ተለብልቧል፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቿን አጥታለች። ባጭሩ ኢትዮጵያ እንደ አገር ተሸንፋለች። ከተፋላሚ ወገኖች አንጻር ካየነው ህውሃት የትግራይ ወጣቶችን፣ ሕጻናትን ሳይቀር አስበልቶ፣ የክልሉን ሕዝብ በርሃብ ፈጅቶ እንደ ልቡ የሚቦርቅባት ትግራይን በእጁ አስገብቷል። ለሕውሃት እነዚህ በጦርነቱ ያለቁ የትግራይ ድሃ ወጣቶች ሞቶ ቁም አይሰጠውም። የተለመውን ግን በከፊልም ቢሆን አግኝቷል። በፌደራል መንግስቱ በኩል የታለመው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በከፊል እነ አቦይ ስብሃትን በቁጥጥር ስር ከማዋል (ምንም እንኳ ድንገት ቢለቀቁም)፣ እነ ስዩም መስፍንን በሞት ከመሸኘት ባለፈ የተሳካ አይደለም። ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጋር በተጓዳኝም የታለመው የአገር አንድነትን የማስጠበቁ እና ትግራይን ከህውሃት እጅ ነጻ የማውጣቱ ህልም ውሃ የበላው ይመስላል። በተቃራኒው ግን ከትግራይ ክልልም አልፎ የአማራ እና የአፋርን ክልል ክፉኛ የጎዳና ኪሳራ ያስከተለ ጥቃትን አስተናግዷል።
ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት ከላይ እንዳልኩት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በተለይም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ክፉኛ ተጎድታለች፣ ተሸንፋለች፣ እረዘም ያለም የማገገሚያ ጊዜን ትፈልጋለች። የእያንዳንዱ ዘርፍ የደረሰውን ጉዳት ለመመርመር ግን ሰፊ ጥናት ያስፈልጋል።
+ የሽግግር ወቅት ፍትሕ  
ለአንድ በከፋ የሰበአዊ መብቶች ጥሰት ውስጥ ለቆየ፣ በፖለቲካ ሸር ለተቋሰለ፣ በተሳሳቱ ትርክቶች ወደ ጎንዮሽ ጸብ ላመራ፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ላስተናገደ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር ብቸኛ የመፈወሻው መንገድ የሽግግር ወቅት ፍትህን በአግባቡ ማካሄድ ነው።
በተባበሩት መንግስታት ሰነዶች ላይ የሽግግር ወቅት ፍትሕ ማለት፣
“Transitional justice is an approach to systematic or massive violations of human rights that both provides redress to victims and creates or enhances opportunities for the transformation of the political systems, conflicts, and other conditions that may have been at the root of the abuses.”
በግርድፍ ትርጉም የሽግግር ወቅት ፍትሕ ማለት ባለፉ አመታት የተፈጸፉ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአግባቡ ተመርምረው ለተጎጂዎች ፍትሕ እና ማካካሻ የሚሰጥበት፤ እንዲሁም የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ግጭቶችን ለዘለቄታው ለማስወገድ እና ለመብት ጥሰቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ለማድረግ የሚያስችል የፍትሕ እና እውነት ማፈላለጊያ፣ ተጠያቂነትን ማስፈኛ እና ሰላምን ማጽኛ መንገድ ነው።
ኢትዮጵያ በየጊዜው በሚመጡ ለውጦች ማግስት ልታሳካው ያልቻለችው አንድ ወሳኝ ጉዳይ ቢኖር ይህ የሽግግር ጊዜ ፍትሕን ነው። የበደል ክምሮች ሳይናዱ በላያቸው ላይ ሌላ በደል ይቆለላል። ተጎጂዎች ሳይካሱ ሌላ አዲስ በደል እና ግፍ የጸናባቸዋል። አጥፊዎችን ከመከሰስ፣ ከመወቀስና ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ አንድም ከአግር ይሸሻሉ፣ አለያም ፍትሕን ያላማከለ የአሸናፊ ወገን የበቀል እርምጃ ሰለባ ይሆናል ወይም ይሾማሉ። በፍትሕ እና በይቅርታ ያልታከመ ግፍ ያመረቅዛል። ሌላ ቂም እና ሌላ ግፍ ይወልዳል። ኢትዮጵያ ለዘመናት ያልታከሙ ግፎች በሚያመረቅዙት መርዝ ተበክላለች። ለዛም ነው ከትላንት ዛሬ እየከፋባት፣ የዛሬዎቹ ግፎች የትላንቱን የሚያስንቁ እየሆኑባት የደም ምድር ሆና የቀጠለችው።
የዶ/ር አብይ አስተዳደር ለኢትዮጵያ አንድ ትልው ውለታ ውሎ፣ ስሙንም በታሪክ መዝብ አኑሮ ሊያልፍ ከሚችልባቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ እና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ይሕ የሽግግር ወቅት ፍትሕን ማስፈን ሲችል ነው። ፍትሕ የተነፈገው ሕዝብ፣ ግፍ ባናት ባናቱ የተደራረበበት ሕዝብ፣ በገዢዎቹና በሊህቃኑ የተራከሰ፣ የተዋረደ እና የተካደ ሕዝብ ምንም አይነት አብረቅራቂ ነገር ከደጁ ቢያነጥፉለት ከቁብ ላይቆጥረው ይችላል። የተገነባውም ይፈርሳል፣ ያብረቀረቀ የመሰለውም መልሶ በደም ይጨቀያል። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ስለዚህ መንግስት፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ምሁራን ማስመሰሉን አቁመው አገሪቱ እና ሕዝቡ ከገባበት እጅግ አስፈሪ እና አደገኛ ቅርቃር እንዲወጣ በእውነት እና ፍትሕ ላይ የተመሰረተ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ፣ በቅን ልቦና ላይ የተመሰረተ አገራዊ ውይይት እና መግባባት፣ ከልብ በመነጨ እርቅ እና ይቅርታ መጠያየቅ የመጣውን አደቃ መቀልበስ ይኖርባቸዋል።
ለፍትሕ፣ ለእውነት፣ ለይቅርታ፣ ለካሳ፣ ለአገራዊ መግባቢያ ውይይት እና ለሰላም መቼም አይዘገይም። ዛሬም ቢጀመር ነገን ማዳን እንችላለን።
የእግዚያብሔር ኢትዮጽያን ይባርክ!!
Filed in: Amharic