>

እውነቱን ተቀበል....!!!  (ሀብታሙ አያሌው)

እውነቱን ተቀበል….!!! 

ሀብታሙ አያሌው
       
 የግንቦት ፩ ቀጠሮ !! 
*…. ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋ አራቱም ዞኖች  የሚገናኙበት ብቸኛ ማዕከል  Intersection  ሲሆን ቦታው የዓለም አቀፍ የጥንተ ስልጣኔ  መመዘኛ መስፈርቶች ተሟልተው የሚገኙበት መሆኑ በእጅጉ አነጋጋሪ ሆኗል… እንዴት እና በማን ተዳፍኖ ኖረ ??   እንጠይቅ  የተዳፈነውን እንግለጥ !!
1. ሃይማኖት … የኦሪት መስዋዕት ይሰዋበት የነበረ በዘመነ
    ክርስትና  የሐዲስ ኪዳን ማዕከል ሆኖ የቀጠለ።
2. ቋንቋ…አማርኛ ቋንቋ የተፈጠረበት ምድር መሆኑ።
3. ዜማ … የዘመነ ብሉይ የአምልኮ መፈፀሚያ ዜማ
     የነበረበት ፣  በዘመነ ሐዲስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
     የሰዓታት ዜማ የደረሱበት።
4. ፍልስፍና … ዮሐንስ ገብላዊ ቅኔ ደርሶ ያመለከተበት፤
5. ትምህርት … በጽሑፍ ቋንቋ የአብነት ትምህርት ይሰጥበት
     የነበረ።
6. የመንግሥት አስተዳደር … እንደ ክብረ ነገስት ያለ   የሥርዓተ መንግሥት መምሪያ ቦታና  መዋቅር  የነበረበት።
7 . የሐይማኖት እና የፍልስፍና ፣ የኪነ ጥበብና የስነ ጥበብ ድርሰቶች ያሉበት።
8 . የግዕዝ፣ የአረማይክ፣ የአማርኛ ጽሑፎች  በብራና እና በድጋይ ላይ ታትመው የሚገኙበት።
9. የጥንት ዘመን የጦር መሳሪያዎች እና የግብርና መሳሪያዎች  የእንስሳት እርባታና የሰብል ማምረቻ
     ጥንታዊ  መገልገያዎች  የሚገኙበት።
10. ስነ-ህንጻ … ከክርስቶስ ልደት በፊት የጥንት የስነ ህንፃ አሻራዎች፣ የአምልኮ መሰዊያ ቦታዎች፣  ሌዋውያን
       በእስራኤል ይሰሯቸው የነበሩ የሰቀላ ቤት አምሳያዎች…
ወ.ዘ.ተ … መሆኑ  የጥንት ፐርሺያ፣  ቻይና፣ ግብፅ እና ግሪክ የመሳሰሉት በስልጣኔ የተለኩበት በአገራችን የአክሱም ስልጣኔ  የተገለጠበት ሁሉ ሳይጓደል ተሟልቶ የሚገኝበት ግን እስከ ዛሬ  ታሪኩ ተዳፍኖ የኖረ ስፍራ ነው።
አምሃራ ሳይንት (ቤተ አምሃራ) 
       —————-
በዚህ አስገራሚ ስፍራ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በአምሐራ ሳይንት ወረዳ የምትገኘው ጥንታዊቷ  ርእሰ አድባራት ወገዳማት ተደባበ ማርያም የተመሰረተችው በዘመነ
ብሉይ በቃዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት
በ982 ዓመተ ዓለም ነው፡፡
በመፅሐፈ ሱባኤ ዘአማኑኤል ካልዕ ገጽ 2  ላይ እንደተጻፈው “ሌዋዊያን ካህናት ከእስራኤል በአዛሪያስ መሪነት የጁን አልፈው ከዛሪዋ አምሐራ ሳይንት ደረሱ”
ሌዋውያኑ አምሐራ ሳይንት እንደደረሱ 12 የተፈጥሮ በር ያለው ዙሪያው ገደል የሆነ የተለየ የተመረጠ ተራራ አግኝተው  ለእግዚብሔር ቤተ መቅደስ ከሰሩ በኋላ ግማሾቹ ደብር ደባብ እንበላት ሲሉ  አዛርያስ እና የዳዊት የወንድም
ልጆች ሳቤቅ ደግሞ “ይህቺማ የኢየሩሳሌም የዳዊት መታሰቢያ ከተማ ትሆን ዘንድ ተድባበ ጽዮን እንበላት” ብለው እንደሰየሟት ድርሳናት ያትታሉ፡፡
በብሉይ ዘመን መስዋዕተ ኦሪት ከተሰዋባቸው
መካከል አክሱም ጽዮን፣ ተድባበ ጽዮን (የዛሬዋ ተድባበ
ማርያም)፣ መርጡ ለማርያም፣ ጣና ቂርቆስ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
ቀዳማዊ ምኒሊክ ከአባቱ ከንጉሡ ከሰሎሞን መንግስት ተቀብሎ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ 4 መናብርት ጽዮን ይዞ እንደመጣ ታሪክ ይናገራል። እንደ ኦሪቱ ስርዓት መናብርቱን ሲያፀናም፣
1. የአክሱም ጽዮን  (ንቡረ እድ)
2. የተድባበ ማርያም (ፓትርያርክ)
3. የመርጡለ ማርያም (ርዕሰ ርኡሳን)
4. የጣና ቂርቆስ (ሊቀ ካህናት)  ተብለው ተሰየሙ።
ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ጃንሆይ ዘመነ መንግስት ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ   ንጉስ ቀብተው የሚያነግሱ እነዚህ አራቱ መናብርተ ጽዮን ነበሩ።
የአክሱሙ ንቡረ እድ … ዘውድ ይጭናል
የተድባበ ማርያሙ ፓትርያርክ … ቅንአተ ሰይፍ አስታጥቆ  በትረ መንግሥቱን ያስጨብጠዋል
የመርጡ ለማርያሙ ርዕሰ ርኡሳን… ልብሰ ንግሥናውን   ያለብሳል የጣና ቂርቆሱ ሊቀ ካህን… ቅብአ ንግሥናውን ይቀባል
የመናብርተ ጽዮኑ ስያሜም 3ስቱ በእመቤታችን ምሳሌ በጽዮን ስም አራተኛው የሊቀ ካህናቱ ታቦት ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ከእነዚህ ጋር ቀዳማዊ ምኒልክን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 12.000 መሣፍንትና መኳንንት ወይዛዝርት 1.500 በተግባረ ዕድ የሰለጠኑ የወርቅና የብር፣ የብረትና የመዳብ፣ እንዲሁም የነሐስ አንጥረኞች አዋቂዎች ጠቢባን ፀበርተ ዕፀውና ወቀርተ አዕባን ናቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያ ገብተው በየክፍለ ሀገሩ ሥራቸውን ሲጀምሩ አክሱም ጽዮን ትግራይ ላይ ስትቀር የዳዊት የወንድም ልጅ ሳቤቅ የሰሎሞን አጎት ከመጀመሪያው ፓትርያርክ አዛሪያስ ጋር ተከዜን ተሻግሮ አምሐራ ሳይንት ደረሰ፡፡
የአሁኗ ተድባበ ማርያም ካለችበት አምባ
ላይ ሲደርስ ቤተ እግዚአብሔር መሥራት ጀመረ፡፡ ቦታዋንም በሀገሩ ስም ገሊላ ብሎ ጠራት፡፡ ፓትርያርክ አዛሪያስ ደስ አለውና ስሙን በቡራኬ አፀደቀለት፡፡ ለዚህችውም ተድባበ ጽዮን ቤተ መቅደሱን ሰርቶ ሲጨርስ ከሌዋውያኑም ከካህናቱም ከፍሎ መስዋተ ኦሪት የሚሰው ካህናትና ሌዋውያንንም ሾመ፡፡
መስፍኑ ሳቤቅ ቤተልሄማዊም በገፀ ንጉስ በወርቅ ወንበር የሚቀመጥ ነበር፡፡ ከዚህ ላይ ገሊላ ብሎ ከሰየመ በኋላ አገሮቹን አሻግሮ እያየ በሀገሩ ምሳሌ ይሰማቸው ጀመር፡፡ ደብረ ዘይት፣ ኬብሮን አሁን ከቀን ብዛት የተነሳ ህዝቡ ኬብሮንን ከሚኖር ይለዋል ይኽውም ከተድባበ ማርያም አምባ በር ወደ ምስራቅ ያለውን መግቢያ ነው፡፡
ወደ ቀኝ በኩል ተመልከተና እያሪኮ ትባል አለ ከቀን ብዛት ግን ሕዝቡ እያሪኮን አራሆ ይሏታል ቀጥሎ ኢየሩሳሌም ቀጥሎ ሎዛ ከዚህ ከሎዛ በላይ ታቦር አለው ይኸውም በአፄ በዕደ ማርያም ዘመን መግስት የተነሱት የቅኔ ፈጣሪዎች እነ ዮሐንስ ገብላአዊ፣ እነ ሠምራ አብ፣ እነ ወልደ ገብርኤል እነ ደቅ እስጢፋ የነበሩበት ነው፡፡
ከታቦር ቀጥሎ   ሊባኖስ፣ ደማስቆ፣ አርሞንኤም፣ ደብር ፋራን፣ ደብረሲና አሁን ቦረና በመባል የሚጠራው::
በስተ ሰሜን በኩል ኮሬብ፣ ቃዴስ ደብረ ፍጌህ፣  ቂሣርያ፣ ቢታኒያ& ጋዛ ፣ ጎልጎታ፣  ፌልስጥኤም ወዘተ ተብለው ተሰይመዋል፡፡ ይኸውም መታሰቢያነቱ ለ12 ነገደ እስራኤል እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሥርዓተ በዓላት በተድባበ ማርያም
    ********
በዘመነ አራት የቂጣ በዓል የአይሁድ ፋሲካ ይከበር ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ታቦተ ጽዮንን ተከትለው ከመጡት አስራ ሁለት ሺህ ነገደ እስራል ሁለት ሺህ አመስት መቶዎቹ ተድባበ ማርያም እንደገቡ ይነገራል፡፡
በዘመነ ክርስትና አብረሃ ወአጽብሃ ተድባበ ማርያምን
አንጽው ካበቁ በኋላ ጥር 21 ቀን በአሏን ለማክበር ደንግገው
ነበር፡፡ ይህም የበአል አከባበር እስከ ዐፄ ገላውዴዎስ ከቆየ በኋላ ዐፄ ገላውዴዎስ ግራኝ አህመድን ድል አድርጎ ሲመለስ ግንቦት ፩ ቀን ተድባበ ማርያም በመግባቱ የገባሁት በልደቷ (እለቱ የእመቤታችን ልደቷ ነው) በማለት የልደታን ጽላት አሰገብቶ የተድባበ ማርያምን በአል ግንቦት ፩ ቀን እንዲሆን አዋጅ አስነገረ፡፡ ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ግንቦት አንድ ቀን በደማቆ ሁኔታ ይከበራል፡፡
በማግስቱ ግንቦት ሁለት የገላውዴዎስ ልደት
በመሆን ተከብሮ ይውላል፡፡ ዋዜማው ከጧቱ ሦስት ሰአት ተጀምሮ ከቀኑ አስር ሰአት ያልቃል ማህሌቱ ማታ ሁለት ሰአት ተጀምሮ እስከ ቅዳሴ መግቢያ ይቀጥላል። በማህሌት ሰርዓቱ ላይ የሚቆመው እንደሌላ ቦታ መልክዓ ማርያም ሳይሆን የራሷ ሊቃውንት የደረሱት መልከዓ ልደታ ነው፡፡
ለአብነት ያህል… ሰላም ለህንብርትኪ ዘአርያሁ ሰሌዳ ወለ ማህጸንኪ ቤቴል ማህደረ ክርስቶስ እንግዳ በእንቲአኪ ይብሉ ማርያም ሠራዊተ ንጉስ ይሁዳ ዳዊት ዘመዳ ኤያቄም ወለዳ ኤያቄም ወለዳ ዳዊት ዘመዳ፡፡ እያሉ የራሷን ድርሰት ይቆማሉ ፡፡ ይህም በሌላ ቦታ አይባልም፡፡
ከክብረ በአሏ በተጨማሪ ከዓመት እስከ ዓመት ሰብሀተ ነግህና ሠዓታት ቅዳሴና መዓልት ሰዓታት አይቋረጥባትም፡፡ አሁን በሌላው ደብር ዓመት እስከ ዓመት ይቀድስ ነበር፣ ሰብሀተ ነግህ ይቆምበት ነበር ተብሎ ይነገርበታል እንጀ ሲሆን አይታይም ተድባበ ማርያም ግን እስከ አሁን ድረስ ቅዳሴና ስብሐተ ነግህ ሰዓታትና መዓልት ሰዓታት ዓመት እስከ ዓመት አይቋረጥም፡፡
ርእስ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም የሐዲስ ኪዳን የስርዓት መነሻ የቅኔ ምንጭ የደጓ ምልክት ነቅ ደጓ ከጠፋ በኋላ የድጓን ምልክት በመፍጠር ለትወልድ ያሰተላልፉ አዛዥ ጌራንና አዛዥ ዘራጉኤልን ያፈራች ዙሪያዋን በታላቅ ገዳማት እና አድባራት የተከበበች የአማርኛ ቋንቋ መገኛ እንደሆነች የሚነገርላት የጎንደር የጎጃምና የሽዋ እንዲሁም የወሎ መገናኛ ማእከል የሆነች ለስነ ልሳን ተመራማሪዎች ትልቅ የቅርስ ስፍራ የሆነችው ርእስ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርይም የታቦር ተራራ የቅኔ መገኛ ሰማንያ ጋሻ መሬት የሸፈነ የደንቆር ብሔራዊ ፓርክ ክልል የሚገኝባት ስትሆን ለኢትዮጵያ ታላቅ የታሪክ ማህደር ናት፡፡
*********
ግንቦት ፩ ቀን (ግንቦት ልደታ)  ቀጠሯችሁን የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ወዳላት ተድባበ ጽዮን (ተድባበ ማርያም) ታደርጉ ዘንድ  በትህትና ተጋብዛችኋል።
“ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት
ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን
ጥበብ በምስጢር እንናገራለን፡፡”
 1 ቆሮ 2፣6
Filed in: Amharic