መስከረም አበራ
ትምህርት ሚኒስትር በአማራ ክልል የተገኘውን አነጋጋሪ የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት አስመልክቶ መፍትሄ መሰል ሁለት ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡ አንደኛው ዩኒርሲቲዎች ተጨማሪ ቅበላ እንዲያደርጉ በማስቻል ይህን የተጨማሪ ቅበላ ኮታ “በጦርነት ላይ ለቆዩ” ላላቸው አካባቢዎች ተማሪዎች ሰጥቻለሁ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው በጦርነት ላይ በነበሩ አካባቢዎች የተፈተኑና መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ደግመው እንዲፈተኑ የሚል ነው፡፡ ሁለቱም መፍትሄ የተባለ ነገር የሚያወራው በጦርነት ውስጥ ከነበሩ አካባቢዎች ስለተፈተኑ ተማሪዎች ነው፡፡ ጥያቄ እናንሳ
1. “በጦርነት የቆዩ አካባቢዎች” ማለት ምን ማለት ነው? የትኛውን የአማራ ክልል ቦታ ይዞ የትኛውን ቦታ የሚተው ነው? እንደሚታወቀው የአማራ ክልል “እድሜህ የደረሰ ሁሉ ለጦርነት ክተት” ተብሎ እንደ ክልል ክተት መታወጁ ይታወሳል(እነሱ ቢረሱት እኛ አንረሳውም)፡፡ ይህ ክተት ሲታወጅ እንደ ክልል ከመሆኑ አኳያ፣ወጣቱ ደግሞ ለዚህ ጥሪ ከሚታሰበው በላይ መልስ የሰጠ ከመሆኑ አንፃር የትኛው የአማራ ክልል ቦታ ነው በጦርነት ውስጥ ያልነበረና የነበረ ተብሎ የሚከፈለው? ከሁሉም በላይ የክተት አዋጁ እድሜህ የደረሰ ሁሉ ብሎ ሲጠራ የ12 ክፍል ተፈታኞችንም ያካተተ ነበርና ትምህርት ሚኒስትር መፍትሄ ብሎ ያመጣው ነገር “በጦርነት ውስጥ የነበሩ ቦታዎች” በሚል ሀሳብ መከበቡ እውነት መፍትሄ ለመስጠት ነው ወይስ “የሆነ ነገር ብያለሁ” ለማለት ነው? የክልሉ ትምህርት ቢሮ የዘባረቀውን ማንሳት ተቋሙን አስፈላጊ አድርጎ ማየት ይሆንብኛልና ምንም አልልም፡፡
2. የአማራ ክልል ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ውጤት መበላሸትን ተከትሎ ትምህርት ሚኒስትር ራሱ “በጦርነት ውስጥ የነበሩ ቦታዎች በጦርነት ውስጥ ካልነበሩ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት አምጥተዋል” ሲል ጦርነት እንዴት የፈተና ውጤትን የማሳደግ “በጎ ተፅዕኖ” እንዳለው ሊያፈላስፈን ሞክሮ ነበር፡፡ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ዛሬ መፍትሄ ብሎ ባስቀመጣቸው ሁለት እርምጃዎች ያወሳው ደግሞ በጦርነት ቦታ ስለተፈተኑና “የተሻለ ውጤት” አስመዘገቡ ስለተባሉ ተማሪዎች ብቻ ነው፡፡ መፍትሄ የሚቀመጠው የተሻለ ውጤት ላመጣ ነው የባሰ ውጤት ላስመዘገበ ነው???