>
5:13 pm - Thursday April 18, 4233

ከሁሉም በፊት ጥቅማ ጥቅማችን ይከበርልን ሆዳችን ይሞላ ሲሉ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጠየቁ ...!!! (ቆንጅት ስጦታው)

ከሁሉም በፊት ጥቅማ ጥቅማችን ይከበርልን ሆዳችን ይሞላ ሲሉ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጠየቁ …!!! 

ቆንጅት ስጦታው

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ከተጣለባቸው አገራዊ ኃላፊነት አንፃር የሚከፈላቸው ጥቅማ ጥቅም በቂ ባለመሆኑ፣ ፓርላማው ማስተካከያ እንዲያደርግ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አረዓያ (ፕሮፌሰር) ጠየቁ፡፡

ኮሚሽኑ በፓርላማው ከተቋቋመበት የካቲት አጋማሽ አንስቶ እያከናወናቸው ያሉና በቀጣይ ሊሠራቸው ያሰባቸውን ተግባራት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ፣ እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስትሩና የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትሩ በተገኙበት ማክሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ በዕለቱ አንድ ሰዓት በወሰደው አጠቃላይ የዝግጅት ሒደት ገለጻቸው፣ በየካቲት 2014 ዓ.ም. አጋማሽ በፓርላማው ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደ ሥራ የገቡት፣ አብዛኛዎቹ ኮሚሽነሮች ድሮ ከነበራቸው የተሻለ ሥራና ኃላፊነት ለቀው አገራዊ ኃላፊነት የተረከቡ በመሆናቸው፣ በዚህ ኃላፊነት ውስጥ ሊሟሉላቸው የሚገቡ መብቶች በሚገባ መከበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽነሮቹ የሚሰጣቸው የቤት አበልና የሚያገኙት ደመወዝ ተደማምሮ 28 ሺሕ ብር እንደሚደርስ፣ በዚህም አንዳንዶቹ ለተከራዩበት ቤት ክፍያ መክፈል እንደማይችሉ ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

በኮሚሽነሮች የሚነሱ የመብት ጥያቄዎችን የመጠየቅ ግዴታ እንዳለባቸው የገለጹት መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ የሚከፈላቸው ደመወዝና የቤት ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነሮቹ ምንም እንኳ በሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙ ቢሆንም ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሚኒስትር ስላልሆኑ፣ ሥራ ሥሩ ተብሎ ኃላፊነትና ግዴታ ሲጣል ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚጋበ ዋና ኮሚሽነሩ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከተመሠረተ ጀምሮ እያከናወናቸው ያሉና በቀጣይ ሊተገበሩ የታሰቡ ተግባራትን በምዕራፍ በምዕራፍ በማድረግ ያቀረቡት መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ ባለፉት ሁለት ወራት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ዙሪያና አጠቃላይ ተቋማዊ አደረጃጀት ላይ የተከናወኑ ሥራዎችን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከኅብረተሰቡ ጋር በቀጥታ ስለሚደረጉ የውይይትና የምክክር ሒደቶች ሌሎች ጉዳዮች ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ይሁን እንጂ በምክር ቤቱ ከተሳተፉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች መካከል፣ ኮሚሽኑ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሊያከናውናቸው ስላሰባቸው ተግባራት የሚያሳይ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ ማቅረብ እንደነበረበት ጠይቀዋል፡፡

የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ፣ የኮሚሽኑ ሥራ የፕሮጀክት መልክ እንዳለው በመጥቀስ ለዚህ ፕሮጀክት ጠንካራ የሆነ ስትራቴጂ እንዲቀረፅ ጠይቀዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሊፈጸሙ የታሰቡ የሥራ ድልድሎች፣ እነ ማን ተዋናይ እንደሚሆኑ ሊያስረዳ የሚችል ደንብና መመሪያ መዘጋጀት እንዳለበት፣ አጀንዳ እንዴት ሊለይ እንደሚችል፣ ከማን እንደሚሰበሰብ፣ መቼ እንደሚሰበሰብ፣ እንዴት እንደሚሰበሰብና አወያዮችና አመቻቾች እንዴትና በምን መሥፈርት ሊመለመሉ እንደታሰበ ሊያሳይ የሚችል መመርያና ስተራቴጂ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረብ እንደነበረበት ለኮሚሽኑን ጥያቄ አቅርበዋል፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ የዝግጅት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ መቼ ምን ሊፈጽም እንዳሰበና አጠቃላይ ዕቅዱን ማቅረብ እንደነበረበት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ገና ከጅምሩ የአገራዊ ምክክሩን የፖለቲካ ፉክክር እስኪመስል ድረስ ገዥው ፓርቲ የበለጠ ተቆርቆሪ እንደሆነ የታየበት፣ ሌሎች በተለይ ደግሞ አንደንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሒደቱን የማጥላላትና ጣልቃ ገብነት የሚመስሉ ሒደቶችና የማይመቹ የቃላት አጠቃቀሞች መስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ በቀጣይ ሥራውን በሚገባ እንዲያከናውኑ የአስፈጻሚ አካላት የአገራዊ ምክክሩን ሒደት በሚመለከት በሚዲያ እየወጡ የሚሰጧቸው አስተያየቶችና ንግግሮች ጥንቃቄ የተሞላባቸው፣ የኮሚሽኑን ገለልተኝነት ተጠያቂነት ውስጥ የማያስገቡ እንዲሆኑ ለማድረግ መሠራት እንዳለበት ለፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፖለቲካው ለአገሪቱ በሽታ ስለፈጠረ፣ በምክክርና በውይይት ለማከም የታሰበ በመሆኑ፣ በዚህ ሒደት ውስጥ የአገራዊ የምክክሩ ጉዳይ ፖለቲካዊ መሆኑን መዘንጋት እንደሌለበት አቶ ክርስቲያን አክለው ገልጸዋል፡፡

በውይይት ጊዜ ብዙኃን ማኅበራት ይሳተፋሉ ተብሎ የቀረበውን ጉዳይ፣ ‹‹እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና እንደ አንድ የምክር ቤት አባል እነዚህ ብዙኃን የሚባሉ የወጣት ማኅበራት፣ የሴቶችና የወጣቶች ሊግ ዓይነት ማኅበራት በዚህ አገራዊ ምክክር ሒደት ላይ መሳተፍ ቢኖርባቸውም፣ የፖለቲካ ነፃነታቸውና ገለልተኝነታው ላይ ጥያቄ ይኖርባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ማኅበራት ሁሉንም አካል ይወክላሉ? አይወክሉም? የሚለውን በደንብ ማየት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

ጠቅለል ያሉ ይዘቶችን የያዘ በመሆኑ በአዋጁ ላይ በዝርዝር ያልተጠቀሱ ጉዳዮችንና አዋጁን ለማስፈጸም የሚያግዝ ደንብና መመርያ በፍጥነት መውጣት እንዳለበት፣ በአዋጁ መሠረት አወያዮችና አመቻቾች መረጣን ለማስፈጸም የሚረዱ ዝርዝር የአፈጻጸም መመርያ ማውጣት እንደሚገባ የጠቀሱት፣ የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ናቸው፡፡

‹‹በተለያዩ አገሮች ተጀምረው ሳይሳኩ የቀሩ ሙከራዎች ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንዲገጥመን አንፈልግም፤›› ያሉት ወ/ሮ ሸዊት፣ እዚህም እዚያም ሐሳብ መወራወር የጀመሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን፣ ‹‹ሁላችንም ከኢትዮጵያ በታች ነን፣ አገራችን ስትኖር ነው እኛ የምንኖረው፡፡ ስለዚህ የረዥም ጊዜ የአገራችን ህልም እንዲሳካ ሁላችንም ሰከን ብለን፣ ስሜቶችንን ተቆጣጥረን በዚህ አገር ለረዥም ዓመታት ተቀምጦ የኖረ ችግር ምላሽ የሚያገኝበት የአገራዊ ምክክር እንዲሆን ሁሉም አካላት ትኩረት ይስጡበት፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Filed in: Amharic