>

‹ዲሞክራሲ›› እና ‹‹ዲክታቶርሺፕ›› - ምንና ምን ናቸው? (አሳፍ ሀይሉ)

ዲሞክራሲ›› እና ‹‹ዲክታቶርሺፕ›› – ምንና ምን ናቸው?
አሳፍ ሀይሉ


(ማስጠንቀቂያ፡— ይህን ጽሑፍ ካነበብክ በኋላ፣ ከአምባገነንነት ጋር ፍቅር እንዳይዝህ ተጠንቀቅ!)
ለዛሬው ፅሑፌ መነሻ የሆነኝ፣ ይህ እጅግ ታዋቂ የሆነ የፕሮፌሰር ኖርቤርቶ ቦቢዮ (Norberto Bobbio) “Democracy and Dictatorship – The Nature and Limits of State Power” የተሰኘ ቆየት ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ ፕ/ር ኖርቤርቶ ማን ነው? በ20ኛው ክፍለዘመን ወጥ የሆነ የዓለማችንን የፖለቲካ ታሪክ ካመነጩ (ወይም በወጉ ካሰናዱ) እፍኝ የማይሞሉ ብርቅዬ የታሪክ ምሁሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የፖለቲካ ታሪክ ምሁር ብቻ ግን አይደለም፡፡ የህግ ፍልስፍና ፕሮፌሰርም ነው፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ ሊቅም ነም፡፡
በ2004 ላይ በ94 ዓመት ዕድሜው ሲሞት፣ ከታወቁ የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች 9 የክብር ዶክትሬቶች ተበርክተውለታል፡፡ የተወለደበት መቶኛ ዓመት በ2009 ላይ – ትልቅ የአውሮፓ የምሁራን ሲምፖዚየም ተዘጋጅቶለታል፡፡ በትውልዱ ኢጣልያዊ፣ በአትኩሮቱ ጥንተ ሮማ፣ በግብዓቱ ደግሞ ዓለምን ያዳረሰ ታላቅ ምሁር ነው ኖርቤርቶ፡፡ ስለሰውየው ብዙ ሀተታ ሳላበዛ፣ ሰውየው ወደተጠበበበትና ወደሚተነትነው፣ ወደ ነገረ ዲሞክራሲና – በተለይም – ወደ ነገረ ዲክታቶርሺፕ (ወይም ወደ ስነ-አምባገነን) ያማረ ስብከቱ ልሸጋገር፡፡
ይሄን ‹‹አምባገነን›› ‹‹ዲክቴተር›› የሚል ቃል መቼ ነበር ያወቅኩት? መቼ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው? እኔ እንጃ! እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምናልባት ከመንጌ ውድቀት በኋላ ይሆን? ወያኔ ይሆን ከዲሞክራሲ፣ አምባገነን፣ ምናምን ቃላት ጋር ያስተዋወቀኝ? ወይስ ኢህአፓዎች ናቸው? ብቻ ከእነዚያ ከፈረደባቸው የ60ዎቹ ትውልድ አያልፍም፡፡ የሆነው ይሁን፡፡ አሁን ‹‹ዲክታተር›› ዝነኛ ቃል ነው፡፡ በመጥፎ ጎን ሁሉንም የዓለም ቃላት የጠቀለለ – ገናና ቃል፡፡
አዳዲስ ቃላት ይመጡና የቀድሞውን ፈጽሞ ያስረሱናል፡፡ ያስረሱናል ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞ በተለያዩ ስያሜዎች ይጠሩ የነበሩ ነገሮችን ሁሉ በአንድ ስም ጠቅልለው ይወስዱታል፡፡ ‹‹አምባገነን›› (ወይም ‘Dictator’) የሚለው ቃልም እንዲሁ ነው፡፡ አምባገነንነት ሲጀመር የሹመት ዓይነት ወይም የልዩ ሥልጣን ዓይነት ነበር፡፡ የብዙ ነገሮቻችን ምንጭ መሆናቸው የሚነገረን የማያልቅባቸው ሮማውያን ናቸው ይህን ‹‹ዲክቴተር›› የሚል ቃል ያመጡብን፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመተ ዓለም ላይ፣ ለአንዳንድ የሮማ ሀገረ-ገዢ ዳኞች ‹‹ዲክታቶር›› የሚል ማዕረግ መሰጠት ተጀመረ፡፡ እና ለተከታዮቹ 800 ዓመታት በማዕረጉ ሲጠቀሙበት ቆዩ፡፡ እስከ 300 ዓመተ ምህረት ድረስ፡፡ ያ ‹‹ዲክታቶር›› (ወይም ‹‹አምባገነን››) ሁለት ልዩ ሥልጣኖች የተሰጡት ሀገረ-ገዢ ማለት ነበር፡-
1ኛው ዲክታቶር) የውጪ ወረራ ለመመከት ወይም ከሌሎች ጋር ጦርነት ለመግጠም በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ ሠራዊትን ለመመልመል፣ ለማሰባሰብ፣ ለማሰልጠን፣ ለማስታጠቅ፣ ለጦሩ ሀብትና ንብረት ለማስተባበር፣ እና ከሠላማዊ ሰዎች መሐል መርጦ ለማዝመት፣ ሥልጣንን የሚያጎናፅፍ ዓይነት አምባገነንነት ነበር፡፡ ‹‹dictator rei publicae gerundae causa›› ተብሎ የሚጠራው ዲክታቶርነት ነው ይሄ፡፡
2ኛው ዲክታቶር) ወይም ሁለተኛው ዓይነት በሮማውያን ለዓለም የተበረከተው የአምባገነንነት ዓይነት ደግሞ – በሀገር ውስጥ የመንግሥቱን ሥርዓት የሚያናጋ አመጽ ሲከሰት፣ ያንን አመጽ ለመዳመጥና ንጉሡን (እና ግዛቱን) በገዛ ዜጎቹ (ሳብጀክትስ) ከመፈራረስ ለማዳን ለሀገረ-ገዢው የሚሠጠው የተለየ (ወይም የአስቸኳይ ጊዜ – እንበለው) ሥልጣን ነበር፡፡ ‹‹dictator seditionis sedandae causa›› ይሉታል ሮማውያኑ – ይሄን ሁለተኛውን ዓይነት አምባገነንነት፡፡
ሮማውያን እግዜር የሥራቸውን ይስጣቸውና – እነዚህን ሁለት ዓይነት የአምባገነን ዓይነቶች ለዓለማችን አስተዋወቁብን፡፡ እና በየግዛቱ የሚሾሙ ሀገር አስተዳዳሪዎች ሁሉ – ከመሬት እየተነሱ – በእኔ ግዛት አመጽ ሊቀጣጠልብኝ ነውና – ያሻኝን እርምጃ ለመውሰድ ፍቃድ ይሰጠኝ – እያሉ ከንጉሠ-ነገሥቱ ልዩ-ሥልጣንን መቀበል ጀመሩ፡፡
በዚህ መልኩ – እንዲህ ያለው የውጪ ጠላት ሊወርረን እየተዘጋጀ መሆኑን ደርሼበታለሁና – ወታደር መልምዬ ካለበት ሄጄ ድባቅ እንድመታው – የተለየ ሥልጣን ይሰጠኝ – እያሉ – ንጉሠ-ነገሥቱን በወራሪ እያስፈራሩ – ያሻቸውን ዓይነት ልዩ-ሥልጣን የሚቀበሉ – ትናንሽ ንጉሦች – ወይም ትናንሽ ዳኞች በየግዛቱ ተፈጠሩ፡፡
በነገራችን ላይ በዚያን ዘመን ሀገረ-ገዢው፣ ህግ የሚያወጣውም ራሱ ነው፡፡ ዳኛ ሆኖ የሚፈርደውም ራሱ ነው፡፡ መንግሥት ሆኖ እንደ አስፈጻሚ ሚኒስትር ራሱ ያወጀውን ህግ የሚያስፈጽመውም ራሱ ነው፡፡ ወይም እርሱ የሾማቸው ሰዎች፡፡ እና በዚህ ሁሉ ሥልጣን ላይ – ያሻውን መግደል፣ ማሰር፣ መግረፍ፣ ማሸበር፣ መውረር፣ የመሳሰለው ሥልጣን ሲጨመርበት – ደንበኛ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ለምሳሌ፣ በክርስቶስ ዘመን (ማለትም ሮማውያን የዲክታቶርን ሀሳብ በተገበሩ በ500 ዓመታቸው)፣ በእስራኤል ላይ ያሻቸውን የሚፈጽሙ የሮማ ገዢዎች (እንደ ሄሮድስ፣ እንደ ጲላጦስ፣ ወዘተ) እንዲህ ያለ ልዩ የአምባገነንነት ሥልጣንን የተጎናፀፉ ዲክታቶሮች ነበሩ፡፡ ማለት ነው፡፡
በጣም የሚገርመኝ ነገር – ወራሪ መንግሥታት ሁሉ – አሁን በእኛ ዘመን የሚታይባቸውን ባህርይ የተላበሱትም – ከእነዚያው ከተረገሙ ሮማውያን ዘመን ጀምሮ መሆኑን ስመለከት ነው፡፡ ለምሳሌ በሮማውያኑ ዘመን – አንድ ‹‹ዲክታቶር›› ወይም አምባገነን ተደርጎ የተሾመ ሀገረ ገዢ – የተሰጠውን ልዩ ኃይል በሁሉም ላይ እንዳሻው መጠቀም አይችልም፡፡
ከሀገር ግዛቱ ውጭ የሚያካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ (አሁን ‹‹ኦፕሬሽን›› ሲባል የምንሰማው) ከሆነ፣ አምባገነኑ ያሻውን ለማድረግ ማንም ከልካይ የለበትም ነበር፡፡ ሮማውያኑ ይህንን ዓይነቱን ክልከላ የሌለው የዲክታቶርነት ሥልጣን ‹‹imperium militiae›› ይሉታል፡፡ አምባገነኑ – ከሀገሩ ግድግዳና ጣሪያ ውጭ – ያለምንም የህጎች ፍራቻ – ያሻውን ለማድረግ ነጻ ነው፡፡
ነገር ግን ዲክታቶሩ ሥልጣኑን በገዛ ሀገሩ ሰዎች ላይ (ወይም በሀገር ውስጥ) በሚጠቀምበት ጊዜ – የሀገሩን ህግ የማክበር ግዴታ ነበረበት ‹‹provacatio ad populum›› ይሉታል ይሄን ዓይነቱን በህግ የተገደበ-አምባገነንነት፡፡ ዲክታቶሩ አስፈላጊ መስሎ ሲታየው፣ ንጉሠነገሥቱን ሳያስፈቅድ፣ በውጭ ሀገሮች ላይ ያሻውን ግፍ ቢፈጽም የሚጠይቀው የለም፡፡ በሀገሩ ዜጎች ላይ ግን የሆነ የከበደ ግፍ ከፈጸመ – በንጉሡ ፊት ቀርቦ – እንደሁኔታው የእጁን ያገኛል፡፡
ዘንድሮ የምናያቸውን ሀገሮች እስቲ እናስተውል፡፡ ያው ዓለማችን ከሮማውያን ዘመኑ የዲክታቶሮች ህግ ብዙም ፈቅ ያለች አትመስልም፡፡ ዛሬም ዲሞክራሲያዊ ነን የሚሉ መንግሥቶች – የራሳቸውን ህዝብ አቀማጥለው እየያዙ፣ በሌሎች ሀገሮች ላይ ግን የግፍ ወረራዎችን፣ ብዝበዛዎችን፣ ጦርነቶችን፣ ቦምቦችን ያዘንባሉ፡፡ ሌላ ጉልበተኛ ካልተነሳባቸው፣ በገዛ ሀገራቸው፣ ልክ እንደ ጥንቶቹ የሮማ አምባገነኖች፣ ጠያቂ የለባቸውም፡፡
ብቻ ግን – ድሮ በሮማውያኑ ዘመን- አንድ ትልቁ ከአምባገነንነት ሥልጣን – የሚታመንበት ጠባዩ ‹‹ጊዜያዊ›› የመሆኑ ነገር ነበር፡፡ የሆነ አደጋን ለማስቀረት፣ ወይ የሆነ ሁከትን ለመፍጠር ወይ ለመቀልበስ ነበር ያንን የዲክታቶርነት ሥልጣን ገዢዎች የሚጠቀሙበት፡፡ እና በሌላው ጊዜ – ያው የተለመደ፣ ተሰፍሮ የተሰጣቸውን ሥልጣን፣ በሀገሩ ልማድ መሠረት ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ አምባገነንነት ለአንድ ሀገር ህዝብ ያን ያህል አስፈሪ ነገር አልነበረም፡፡ (ጉድ የመጣው ኋላ ነው፡፡)
ለዚህ ነው ለምሳሌ በ1780ዎቹ እስከ 90ዎቹ የተካሄደው የፈረንሣይ የጭቁኖች አብዮት ሲቀሰቀስ፣ የአመጹ አስተባባሪዎች በይፋ ነበር የአምባገነንነት ዓላማቸውን ያስተጋቡ የነበሩት፡፡ አንዱ የፈረንሳይ አብዮት ፀሐፊ የፈረንሣይን አብዮት ዓላማ ሲያብራራ፡- ‹‹የአብዮቱ ዋና ዓላማ፣ አሁን ህዝብን እየበዘበዙ ያሉ ንጉሣዊ አምባገነኖችን ጠራርጎ፣ በምትካቸው፣ በአብርሆት የተሞሉ ጥቂትና ጠንካራ፣ ለህዝብ አሳቢ አምባገነነኖች ለመፍጠር ነው›› ብሎ ጽፎልን እናገኘዋለን፡፡
ሀቀኝነቱ ደስ ይላል፡፡ ግን የሀቀኝነት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ዲክታቶርነት እንደ ክፋት አይታይም ነበር፡፡ ሌላ ቀርቶ ሥልጣንን በማምለክ የሚታመነው ማኪያቬሊ እንኳ፣ አምባገነንነትን ለአንድ ሀገር መሪ ‹‹እጅግ አስፈላጊና ተገቢ ሥልጣን›› በማለት ነው የሚገልጸው፡፡
ማኪያቬሊ ሲያብራራ፣ ለምሳሌ፣ በሮማውያን ግዛት ‹‹የባርነትና የጭቆና ዘመን›› (Rome’s period of tyranny’ (1513-19) የተከሰተው፣ አምባገነንነትን የተላበሱ ነገሥታት በመምጣታቸው ሳይሆን፣ ያንን አምባገነንነት በቋሚነት ለማራመድ በመሻታቸው የተነሣ ነው ይለናል፡፡ አምባገነንነት ለጊዜያዊ ጥቅም እስከዋለ ድረስ – ለሀገር ጠቃሚ፣ ለሕዝብ አለምላሚ ነው – ይለዋል፡፡
ቆይ እኛ እንደ ማኪያቬሊ ከመሠለ የሥልጣን አምላኪ ጋር ምን አጨቃጨቀን? ለምን ቅዱስ የዲሞክራሲ አባት ተደርጎ ወደሚቆጠረው ወደ ሩሶ (ዣን ዣክ ሩሶ) ለምን አንመጣምና ስለ አምባገነንነት ያለውን ሀሳብ አንጠይቀውም?
ሩሶ የዓለም ህጎችና ህገመንግሥቶች ሁሉ መሠረት ነው በሚባልለት Social Contract መድብሉ ውስጥ፣ የአንድ ሀገር የሕዝብና-የመሪ ቃልኪዳን (ወይም ህገ-መንግሥት) የቱንም ያህል ስለወደፊቱ አርቆ-አሳቢ ቢሆን፣ ሁሉንም የወደፊቱን አደጋና ሁናቴ ሁሉ አስቀድሞ በዝርዝር ማወቅ አይችልም – ይለናል – ለአምባገነንነት ሲያመቻቸን፡፡ እና ምን ይጠበስልህ? ስንለው፣ የሩሶ መልስ ሊያስገርመን ይችላል፡፡
በሩሶ አባባል፣ አንዳንድ አስቸጋሪ የውጪና የሀገር ውስጥ መናጋትን የሚያስከትሉ ነገሮች ሲመጡበት፣ የሀገር መሪ፣ ወይም የሀገሪቱ ጠቅላይ አዛዥ፣ ለጊዜው፣ በተለመዱ ህጎች መጣስ የማይፈቀዱለትን ነገሮች ሁሉ ጥሶ፣ ያሻውን እንዲያደርግ ልዩ-ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል፡፡ በራሱ ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹by nominating a supreme chief (the dictator) who ‘silences all laws and momentarily suspends sovereign authority’ (Rousseau 1762)››፡፡
ይህቺ የሩሶ ቃል በጣም የሚጮህ ወርቅማ ነገር አላት፡- ከሀገራዊ ቀውስ ለማምለጥ – ‹‹ለጊዜው ህጎችን ፀጥ-የሚያሰኝ›› አምባገነን የግድ ያስፈልጋል ይለናል፡፡ የዲሞክራሲው አባት ሩሶ፣ ህጎችን የሚረመርም፣ የሚበጣጥስ፣ ያሻውን ህግ የሚጥስ፣ ከፈለገ ህገመንግሥቱን ከዛሬ ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ወስኛለሁ፣ የሚል፣ ያኛው ህግ ጣስከኝ፣ ይሄኛው ህግ ተላለፍከኝ፣ እያለ የማያደነቁረው፣ ህጎችን ሁሉ በጊዜያዊነት ‹‹ፀጥ የሚያሰኝ›› ሀገረ-ገዢ የሚያስፈልግበት ወቅት አለ – ይለናል ሩሶ፡፡ አወየሁ ሩሶ! አወየሁ ሩሶ! ሰው ማመኔ ጎዳኝ!
ይቺ የዲክታቶርነት ሃሳብ እንግዲህ፣ ጊዜያዊቱን ውብና ልዩ ሥልጣን፣ ለጊዜያዊ ቆይታ ብቻ ሳይሆን፣ ለዕድሜ ልካቸው ለማራዘምና በረከቷን ለመቋደስ፣ ክፉኛ ከከጀሉት የሮማ ፈላጭ-ቆራጭ ቄሳሮች ጀምሮ፣  በየዘመናቱ የብዙዎችን ቀልብ ስባ እናገኛታለን፡፡ ሌላ ቀርቶ እነ ሩሶ፣ ጊዜያዊነቷን አስምረውባት ሲያበቁ፣ ግን አስፈላጊነቷን ዘክረዋል፡፡
የፈረንሣይ አብዮት ፈንጣቂዎች ራሳቸው፣ ስለ Enlightened dictators ሊሰብኩን ሞክረዋል፡፡ ‹‹ዶማ፣ ዱልዱም›› አምባገነን እኮ አላልንም! ኖ ኖ ኖ!
‹‹የተማረ፣ የተመራመረ፣ ያወቀ፣ የነቃ፣ የህዝቡ የልብ ትርታ የሚሰማው፣ የሚፈላሰፍ፣ የህዝብን ብሶት ለማዳመጥ ልቡን ወከክ ያደረገ፣ በመጽሐፍት ፍቅር የተለከፈ፣ አርቲስቶችን እንደነፍሱ የሚወድ፣ በአብርሆት የተሞላ፣ ስለራሱ ግላዊ ጥቅም ሳይሆን፣ ‹‹ሀገር›› ስለሚባለው ረቂቅ ሀሳብ የገባው፣ ሙድ የገባው፣ Enlightened dictator ይምጣና (ወይም በቡድን ተሰባስበው ይምጡና)፣ ሕዝቡን ይምሩት!››፡፡ ብለው ነበር የጀነጀኑን የፈረንሳይ አብዮተኞች፡፡
ቦናሮቲ የአብዮቱን ጓዶች ታሪክ የዘከረበት፣ ‹‹Conspiration pour I’egalite dite de Babeuf›› የሚል መጽሐፍ፣ አቤት ሲጀነጅን በተማሩ-በተመራመሩ ሰዎች ‹‹ሤራ›› ስለሚመጣ ውብ አምባገነንነት ሲሰብክ! አቤት ማማለሉ!! ሤራ እንዲህም ያምራል እንዴ ለካ!!
ይህን ዓይነቱን አምባገነን በቁማቸው እያለሙ እያሉ ነበር፣ ለፈረንሣዮች፣ ፈጣሪ፣ ናፖሊዮን ቦናፓርትን፣ በአምባገነን አምሳል፣ ፈረንሣዮችንም አውሮፓንም፣ ግብጽንም፣ ሁሉንም ቀጥቅጠህ ግዛ ብሎ፣ ማራኪ የጄነራል ልብስ አልብሶ፣ የጀግና ማዕረግ አልብሶ፣ መልክና ቁመናውን አሳምሮ፣ ከጀርባው የጥበብ ሰዎችንና ተራማጅ የሚባሉ ምሁራንን አሰልፎ፣ ዱብ ያደረገላቸው፡፡
የምትመኘውን ተጠንቀቅ! ምክንያቱም እግዜሩን አታውቀውም! የሚል አባባል አለ፡፡ የተመኘኸውን ሊሰጥህ ይችላላ እግዜሩ ምን ጎድሎበት ደስ ካለው! ፈረንሣዮች ተመኙ! እና በአምባገነን እጅ አጨዱ፡፡ መከራቸውንም፡፡ ፍንደቃቸውንም፡፡
ከዚያ ይቺ የ‹‹ዲክታቶር›› መቋደሻ፣ ከሰል ላይ ተጥዳ ስትጠበስ፣ ስትገላበጥ፣ ስትጨስ፣ ድንገት ድንበር ተሻግራ፣ ጀርመን ሀገር በካርል ማርክስ ጆሮ ጥልቅ አለች፡፡ ‹‹አምባገነንነት››!! እንዴ! ለካ እንዲህም ያለ በረከት ከፊታችን አለልን!! ካርል ማርክስ ጊዜ አላባከነም፡፡ አሁን በየሀገሩ የሰፈነው ‹‹የጥቂት ከበርቴዎች አምባገነን›› መንግሥት ነው አለ፡፡ በጣም የሚቆጠሩ ንጉሡና ጭፍሮቹ፣ የተቀረውን ህዝብ ጋጥ አድርገው የሚበሉበት ‹‹በጥቂቶች አምባገነንነት›› የሚዘወር ሥርዓት ነው በየሀገሩ ያለው – አለ ማርክስ፡፡ እና ምን ይጠበስልህ? እንኳን!! (ብትለው ይጣላሃል – ማርያምን!)
እና ማርክስ አስቦ አስቦ ሲያበቃ በመጨረሻ፡- ‹‹የብዙሃኑን አምባገነን መንግሥት›› ‹‹የጭቁኑን የሠራተኛ መደብ አምባገነን አገዛዝ አሰፍናለሁ!›› ብሎ አወጀ፡፡ ‹‹Dictatorship of the proletariat!››፡፡ ጥቂት በላያችን ላይ ተጣብቀው፣ ደማችንን የሚመጡ፣ የከበርቴ መደቦችን ከላያችን ላይ ነቅለን ጥለን፣ በእነርሱ መቃብር ላይ፣ የብዙሃኑን የጭቁኖች፣ በላባቸው የሚያድሩ የላብ-አደሮች አምባገነን መንግሥት እናቋቁም – ብሎ ለዓለም ወዛደሮች ጥሪ አቀረበ ካርል ማርክስ፡፡
እውነተኛው ዲሞክራሲም ይሄው የብዙሃን የሥልጣን ባለቤት መሆን ነው አለ፡፡ ታሪክን እንቀይራለን አለ፡፡ ህዝብ ንጉሥ ይሆናል፡፡ ሀገር ይገዛል፡፡ ያሻውን ይፈጽማል፡፡ ሕዝብ አምባገነንነቱን በላቡና በደሙ፣ በትግሉና በጉልበቱ ያስከብራል፡፡  ኧረ ጉድ፣ ኧረ ጉድ! ፈላ! – መባል የነበረበት ያኔ ነበር፡፡ የአምባገነንነት ሀሳብ ዲሞክራሲያዊ መልክ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ሕዝብ አሸናፊ ይሆናል! ሕዝብ ያልተገደበ የመብቶች ባለቤት ነው! ህዝብ የሀገሩ ባለቤት ነው! ሕዝብ ንጉሥ ነው! ህዝብ አምባገነን ነው!
ያ ቀደም ባሉት ዘመናት የብዙ ነገሥታትን ልብ ያሸፈተው፣ ያማለለው ‹‹አምባገነንነት›› (ዲክታቶርሺፕ) – እነሆ በመጨረሻ የዓለም ጭቁኖችን ልብ ለሥልጣን አሻፈደ! (አሸፈተ!)፡፡ እና የዓለም ጭቁኖች በየሀገሩ ሥልጣንን ከገዢዎቻቸው ለመረከብ፣ ዓለምን በአመጽና ብጥብጥ አቀጣጠሏት! በአፍሪካ፣ በአሜረካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በሶቭየት ራሺያ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በምስራቅ አውሮፓ፣ በኢትዮጵያ፣ በሁሉም ሥፍራ – ጭቁኑ የተባለው ሕዝብ፣ አምባገነንነቱን ለማረጋገጥ፣ ሆ..! ብሎ ተነስቶ፣ ‹‹ጥቂት ከበርቴ ገዢዎች›› የተባሉትን መሪዎች ቅርጥፍ አድርጎ በላ!
የሚገርመው የሠራተኛውን መደብ አምባገነንነት ለማረጋገጥ የታወጀው የዓለም የሶሻሊስት አመጽ የበላው ገዢዎቹን ብቻ አይደለም፣ በአምባገነኒቱ ሥልጣን ተከይፈው፣ ሊሰፍሩባት የሚሻሙ ተፎካካሪ ጭቁኖችም እርስ በእርስ ለወንበሯ ተበላሉ! ለነገሩ የዲክታቶርነት ፍቅር፣ ገዢዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ተፎካካሪ ጭቁኖቹንም መብላት የጀመረችው ገና በፈረንሳዮቹ የሪቮሉሽነሪ ዲክታቶርሺፕ ዘመን ነበር፡፡
ቀደም ብሎ፡፡ ‹‹The revolution devours its own children›› – ‹‹አብዮት ልጆቿን በላች!›› -ያሉትም ራሳቸው ፈረንሳዮቹ ነበሩ፡፡ በሁሉም ሀገር ዲክታቶርሺፕ – ወይም የአምባገነንነት ፍቅር – የብዙዎችን ልብ አማልላ – ብዙዎችን በልታለች! እኛ ሀገር የነበረውን መበላላት ልተወው፡፡ ጊዜ የለኝም፡፡ ብዙ ጽፌያለሁ፡፡ ይህንንም ለጤና ያርግልን፡፡ ግን አንዲት የድሮ አንድ ብር ነበረችኝ፡፡ እሷን ተናግሬ ላብቃ፡፡
የጃንሆይ አንድ ብር ነች፡፡ በአንድ ብሯ ላይ የጃንሆይ ፎቶ አለ፡፡ ወርቀዘቦ የተጠለፈ ውብ ካባቸውን አድርገው፡፡ ውብ ፊታቸው በብሯ ላይ አለ፡፡ በጀርባው ደግሞ የይሁዳ አምበሳ አለ፡፡ ሥልጣነ መንግሥታቸውን በአናቱ ይዞ፣ በክርኑ ደቁሶ፣ ጉብ ብሎ፡፡ በአንድ ብር ላይ፡፡
ልብ በል፡፡ ይቺ አንዲት ብር በየሰዉ ሁሉ ዘንድ በስፋት እንደምትዳረስ አስብ፡፡ መቶ ብር ላይ ቢሆን ኖሮ፣ መቶ ብር በህይወቱም ሙሉ አይቶ የማያውቅ ህዝብ ይበዛ ነበር፡፡ ስለዚህ እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቁጠራት ብሯን፡፡ የጃንሆይንና የአንበሣቸውን ፎቶግራፍ ይዛ በየሰዉ ሁሉ ኪስ፣ በየጣራው ሥር እየገባች ታድራለች፡፡ ጥሩ ፕሮሞሽን ነበረች፡፡
ከዚያ ድንገት በዲክታቶርሺፕ ሀሳብ የተከየፈው የጭቁኖች አብዮት ተቀጣጠለ፡፡ እና ብሯን በላት፡፡ ብዙሃኑ አምባገነኖች፣ ጥቂቶቹን ንጉሣውያን አምባገነኖች ከሥልጣነ መንበራቸው አባርረው፣ ዙፋኑን ሲይዙ፣ የጃንሆይ አንድ ብር ተቀየረች፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ አንድ ብር ታተመ፡፡ በብሩ ላይ፣ በጃንሆይ ፎቶ ፋንታ፣ የአንድ እረኛ ፎቶ፡፡ በጃንሆይ የይሁዳ አንበሣ ፋንታ፣ የአንድ የኦጋዴን አንበሣና የፎገራ ላሞች ፎቶ ተተካበት፡፡ ሣንቲሙም እንደዚያው፡፡ ሁሉነገርም እንደዚያው፡፡
የጭቁኖች አብዮት፣ አንበሦችን በከብቶች፣ ንጉሦችን በእረኞች ተክቶ፣ ተጠናቀቀ፡፡ ዛሬ ላይ ያ ስንቱ ያበደለት አምባገነንነት፡፡ ያ ሮማውያን ለዓለም ያወረሱት ልዩ ሥልጣን፡፡ ያ በእየሱስ ላይ ስቅላት ያስፈረደ ሥልጣን፡፡ ያ የቄሳሮች ሥልጣን፡፡ ያ ፈረንሳዮችን ያማለለ፣ አሜሪካኖችን ያነሆለለ፣ ራሺያኖችን የፈነቀለ፣ ኢትዮጵያኖችን የነቀነቀ፣ ኩባውያንን የፈነቀለ፣ ዓለምን ያነቃነቀ አምባገነንነት – በመጨረሻ – ግብሩ ባይቀርም – ስሙ ተቀይሮ – መልኩ ጠልሽቶ – አሁን በዓለም ላይ – የግፈኞች ሁሉ የጋራ መጠሪያ ስም ለመሆን በቃ!
ዛሬ ላይ – ያ ብዙ ውብ ገጽታው የተራገበለት አምባገነንነት – ብዙ በዓለም ላይ የተወገዙና የተጠሉ የሥርዓት ዓይነቶችን ሁሉ መጠሪያ ጠቅልሎ – የሁሉም ክፉ ነገር መጠሪያ ሆነ፡፡ ድሮ “Autocracy”፣ “Tyranny”፣ “Despotism”፣ “Slavery”፣ “Monarch”፣ ወዘተ የሚባሉት ሁሉ፣ በዛሬ ዘመን ላይ፣ ልዩነታቸውና ትርጉማቸው ገደል ገብቶ፣ የሁሉም የጅምላ መጠሪያ “Dictatorship” የሚል ሆኗል፡፡
እና በጣም የሚያስቀው፣ ከጥንታዊ ግሪኮች መንግሥታዊ ከተሞች የአገዛዝ ዓይነት ማለትም ከ“Democracy” የተሻለ ጥቅም ያስገኛል ተብሎ ለዓለም የተበረከተው ዲክታቶርሺፕ ጥንብ-እርኩሱ ሲወጣ፣ ወንዝ አያሻግርም የተባለው ‹‹ዲሞክራሲ›› የተሰኘው ሥርዓት ደግሞ በዓለም ነገሠ!! አሁን ራሱን በራሱ ‹‹አምባገነን›› ነኝ፡፡ ወይም ‹‹አምባገነንነትን ለማምጣት ነው የቆምኩት›› የሚል መንግሥት በየትም ሥፍራ የለም፡፡
አሁን በዓለማችን ያለው መንግሥት ሁሉ ራሱን የሚጠራው “Democratic” የሚል ቅጽል ከስሙ ፊት እየጨመረ ነው፡፡ ኮንጎም ዲሞክራቲክ ነች፡፡ ኢትዮጵያም፡፡ አሜሪካም፡፡ ኩባም፡፡ ኮርያም፡፡ ኢራንም፡፡ ሌላ ቀርቶ፣ ከምድራዊ መንግሥታት አልፎ፣ የሠማዩን መንግሥት ራሱ “Democratic” ገጽታ አላብሰነዋል፡፡ እግዜርን የምታመልከው በምርጫህ ነው፡፡ ምርጫው ያንተ ነው፡፡ “Democratic”ኩ እግዜር አያስገድድህም፡፡ ጌታ አምባገነን አይደለም፡፡ የምታመልከውን ዛሬውኑ ምረጥ፡፡
Filed in: Amharic