ኢትዮጵያ የድል ሸማ ከተከናነበችበት የ1888ቱ የአድዋ ድል የዛሬዬቱ አፍሪካ የምትማረው ቁምነገር
ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)
Tilahungesses@gmail.com
መግቢያ
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ከሶስት ሽህ ዓመት በላይ በዘለቀው ታሪኳ ዘርፈ ብዙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፍዳ እና መከራ ተፈራርቀውባታል። ጠላቶቿ ተራራ ሳይገድባቸው፤ ውቃያኖስ ሳይገታቸው፤ ርቀት ሳያሰንፋቸው ከውጪም ከውስጥም በኢትዮጵያ ላይ ሲዘምቱባት ኖረዋል። ዛሬም ቅርጽና ይዘቱን ቀይሮ እንደሆን እንጂ የማባራት ምልክት አይታይበትም።
የጣሊያን ወረራ፤ የመሃዲስቶችና የቱርኮች ጥቃት ኢትዮጵያን ቢቻል ማጥፋት ባይቻል ደካማ ሃገር ሁና በንርሱ ቸርነትና ፈቃድ እንድትኖር ለማድረግ ብዙ ጥፋት፤ ግፍና ሰቆቃ አድርሰውባታል። በእርስበርስ ሽኩቻ በበቂ ተተራምሳለች። ከጥንትም ኢትዮጵያን በግልጽና በስውር የሚአተራምሷት ምዕራባዊያን እና ግብጽን የመሰሉ የአረብ ሀገራት እንደሆኑም እናውቃለን።
ኢትዮጵያ ከውጪም ከውስጥም የተቃጡባትን ጥቃቶች ሁሉ እንዳመጣጣቸው ተቋቁማ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደርሳለች። ፈታናዎችን ተቋቁማ እስካሁን የዘለቀችበት ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ዋናዎቹ ግን የሕዝቧ ጨዋነት፤ በራስ መተማመን፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር፤ አይበገሬነትና ለሃገር ቀናዒነት፣አንድነቷን በማጥበቋ ፈተናዎቹንና ችግሮችን ስትሻገር ቆይታለች። ዛሬም የአሜሪካንና የምዕራቡ ዓለምን ማእቀብና ጫና ፣ እንዲሁም በግብጽ አጋፋሪነት የተጋረጠባትን ከባድ እና ውስብስብ ፈተና መጋፈጥ የምትችለው ያለፉ እሴቶቿን በማጎልበት፤ ቀበቶዋን ጠበቅ አርጋ አንድነቷን አጠናክራ በሕብረ ብሄራዊነት መንፍስ ታጅባ በሕብረት ስትዘምት ብቻ ነው።
በድህነት ዓለም እየኖረች በዘመናዊ መሳሪያ ታጅቦ የወረራትን የምዕራብ ኅይል አሸንፋ በመጡበት የመለሰችው፤ ነፃነቷን ሳታስደፍርና በቅኝ ግዛት እጅ ሳትወድቅ እንድትቆይ የቻለችውም በዚሁ ምክንያት ነው። በቅኝ አገዛዝ ሲማቅቁ ለነበሩ የሶስተኛው ዓለም ህዝቦች አፍሪካን ጨምሮ የነፃነትና የአይበገሬነት ተምሳሌት ሆና የኖረች ሃገር ለያንኪ ፖለቲካ የምትበገር ትሆናልች ተብሎ አይገመትም።
ከዚህ ባሻገር የራሷ ሐይማኖት፤ ታሪክ፤ ባሕልና ትውፊት የምትመራ ሃገር በመሆኗ በምዕራቡ ዓለም በተለይም በተባበረችው አሜሪካ ተወዳጅነትና ክብርን እንዳላፈራላት ኢትዮጵያውያን ሁሉ መገንዘብ አለብን። በተለይም ሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ አድዋ ላይ የፋሺስት ጣሊያንን ወረራ በማሸነፍዋ አሁን ድረስ በምእራባውያን በተለይም በታላቋ ብሪታንያ እና በተባበረችው አሜሪካ ጥርስ ተነክሶባት ይገኛል፡፡ ለማናቸውም ኢትዮጵያ አድዋ ላይ የነጭ ትምክህተኞችን አዋርዳ ያሸነፈችው በግዜው አንድነቷን በማጥበቋ እንደሆነ አፍሪካውያንና በተለይም ኢትዮጵያውያን ልብ ልንል ይገባል፡፡
ኢትዮጵያና አድዋ
አድዋ የነጭ ትምክህተኞችና ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ያላቸውን ገዢነት ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ግዜ የሽንፈታቸው ማሳያ ነው፡፡ ወይም አድዋ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን መግዛት እንደማይችሉ ምልከት ነው፡፡ በአጼ ምኒሊክ 2ኛ ፊት አውራሪነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. የጣሊያን ፋሺስቶችን ድል የነሳቸው ኢትዮጵያ የአለምን ታሪክ ወደ አዲስ አቅጣጫ ለመቀየር አስችሏታል፡፡ በቅኝ ገዢዎች ቀንበር ስር ወድቀው ሲማቅቅ ለነበረው ቀሪው የአፍሪካ ክፍል፣ለተጨቆኑ ጥቁር ህዝቦች ደግሞ የአድዋ ድል ተስፋ ሰጪና መንፈስን የሚያድስ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አፍሪካ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከቅኝ ገዢዎች የግፍ አገዛዝ የተገላገለችው የአድዋ ድል ከተገኘ አንድ መቶ(100) አመት ግድም በኋላ ማለትም ዚምባብዌ ከአዳም ስሚዝ አገዛዝ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1980፣ደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ደግሞ ከአፓርታይድ አገዛዝ እ.ኤ.አ. 1990ዎቹ ነጻ ከወጡ በኋላ ስለመሆኑ ከታሪክ እንማራለን፡፡
ታላቁ የአፍሪካ የነጻነት ታጋይ ኒልሰን ማንዴላ እንደተናገሩት ‹‹ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብሔርተኝነት የተወለዳባት ሀገር ናት፡፡
As Nelson Mandela said
ታሪክ እንደሚያስተምርን የአድዋ ድል የጎሳን ማንነት፣የሃይማኖትና ቋንቋን ማንነት የሚገድቡትን ድንበር በመጣስ የአንድን ህዝብ አንድነት ማስጠበቅ እንደሚቻል ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የዲፕሎማሲ ጫናን በመቋቋም የአርበኝነት ስሜት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ሁነኛ መንገድ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ባሳለፍነው የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. 126ኛው የአድዋ ድል በአል ተከብሮ መዋሉ የቅርብ ቀናቶች ትዝታ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አፍሪካ ዛሬም ቢሆን በፖለቲካው፣ምጣኔ ሀብት፣የባህል ነጻነት ወዘተ ወዘተ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር ትገኛለች፡፡
አፍሪካ ነብሷን ለማዳን ጦርነት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ጦርነት ከማሊ እስከ ሶማሊያ፣ ከሊቢያ እስከ ሞዛምቢክ ፣ እንዲሁም በብዙ የአፍሪካ ሀገራት አኳያ የህልውና ጦርነት አለ፡፡
አሁን በአለው የኢትዮጵያ አሳሳቢ ሁኔታ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚደረጉ ጦርነቶች መሰረታዊ ምክንያት ወይም ስሩ ምእራባውያን ያላቸውን የምጣኔ ሀብትና ጂኦፖሎቲካ ስር ተመሳሳይነትን ማሳያ ነው፡፡ በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች በየግዜው የሚካሄዱ ጦርነቶች ስሩ ምእራባውያን ካላቸው የኢኮኖሚና ጂኦፖለቲካ ፍላጎትን ለማሟላት የታለመ ነው፡፡ ( ለአብነት ያህል በተለይም የተባበረችው አሜሪካ፣ታላቋ ብሪታንያ እና የአውሮፓ ህብረት ይጠቀሳሉ፡፡ )
ሆኖም ግን ይሁንና ኢትዮጵያ ጥንታዊ አባቶቿን እና እናቶቿን በአንድነት መንፈስ፣ በዲፕሎማሲና አርበኝነት ተጋድሎ አመሃኝነት ዝንተ አለም ትዘክራቸዋለች፡፡
በነገራችን ላይ የምእራቡ አለም የበዝባዥ ጥቅምን ብቻ በማስከበር ተመስርቶ የነበረውን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መልካም አጋጣሚ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ምእራባውያን ከእፍሪካውያን ጋር በመከባበር፣ ለጋራ ጥቅም ግንኙነት ለመመስረት እድል በሯን ከፍታ እየጠበቀቻቸው ትገኛለች፡፡
ለአብነት ያህል የኢትዮጵያና ጣልያን ግንኙነት ይጠቀሳል፡፡ ከአውሮፓ ሀገራት ሁሉ ጣሊያን ለኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ወዳጇ መሆኗ ይነገራል፡፡ ( ፋሺስት ጣሊያን በ1933 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው ግፍ በቂ ካሳ አለመከፍሏን በተመለከተ ግን የአሁኑ ትውልድ ታሪክን መመርመር፣መጠየቅ ታሪካዊ ሃላፊነትና የግዜው ጥያቄ መሆኑን መረዳት፣ የሰውነት ባህሪ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ አሁን ያለው የናሚቢያ ትውልድ የጀርመን ፋሺስቶች ለፈጸሙበት ግፍ ካሳ ጠይቆ፣ተገቢውን ካሳ ማግኘቱን ፣መረዳት ብልህነት ነው፡፡) በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ አንዳንድ አበረታች ውጤቶች በመሬት ላይ ይታያሉ፡፡ በቀድሞው አጠራር ሳሊኒ ኢምፔሪጌሎ፣ፔትሮ ሳሊኒ ,( Pietro Salini )ተብሎ የሚጠራው አለም አቀፍ ካምፓኒ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ሀይል ማመንጫ ግድብ ስራ ላይ ሁነኛውን ሚና እየተጫወተ መሆኑ ጣሊያንና ኢትዮጵያ ያላቸውን የጠበቀ ወዳጅነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ጣልያን በመከባበር ላይ የተመሰረተ ወዳጅነትም አላቸው፡፡ የዚህ የሃይል ማመንጫ በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ጨለማ ውስጥ ሲዳክር የነበረውንና ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነውን ህዝቧን ከጨለማ ውስጥ አውጥታ የብርሃን ሸማ ለማልበስ ያስችላትል፣ የቴክኒክ ባለሙያዎቿ ቁጥር ይጨምራል፣ጣሊያኖች የስራ እድል በኢትዮጵያ እንዲከፈት አድርገዋል፣ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ በአፍሪካው ቀንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ያስችላታል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ተርባይን ሃይል ማመንጨት በጀመረበት ግዜ በተካሄደው ስነስርአት ንግግር ያደረጉት የፔትሮ ሳሊኒ ዋና ስራ አስኪያጅ በአደረጉት ንግግር፡-
‹‹ አግዛብሔር ለኢትዮጵያ ልዩ ስጦታ አበርክቶላታል፡፡ ይህ ልዩ ስጦታ ጋዝ ወይም የተፈጥሮ ዘይት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ስጦታው ውሃ ነው፡፡ እኛ ይህን ታላቅ የውሃ ግድብ ግንባታ ስናከናውን መጠነ ሰፊ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ ይህ ፕሮዤ እንዲህ በቀላሉ እውን አልሆነም፡፡ ከእኛ በተቃራኒ የቆሙ በርካታ ጠላቶች ነበሩ፡፡ ወይም አሉ፡፡ ብለዋል፡፡
እንደ መደምደሚያ
ኢትዮጵያ በአንጸባራቂና ማራኪ ድሎቿ የተነሳ ፣ ዛሬም ቢሆን ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በመተባበር ዳግማዊ አድዋን ትደግማለች ብዬ ተስፋ አድረጋለሁ፡፡ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ለመዋጋት ኢትዮጵያ ሁለት ስትራቴጂዎችን ማቀድ፣ ማስላት ትችላለች ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎችን ሴራ ለማምከን አአፍሪካውያንን ማስተባበር ይቻላታል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ በኢትዮጵያ ምድር የአድዋ ድልን በተሳሳተ ትርጉም የሚያዩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንደ አሽን ቢፈሉም በአድዋ መንፈስ ኢትዮጵያ አራቱን አጋሮች ታጠናክራለች ብዬ አስባለሁ፡፡ ( ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ፣ደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ እና አልጂሪያ ጋር የህብረት ችቦ በመለኮስ የተጠቀሱትን፣የአራቱን ሀገራት ትብብር ታጠናክራለች ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡) በነገራችን ላይ ይህ ህብረት አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራት፣ የአፍሪካ አንድነት የአውሮፓው ህብረት ከደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲቆም፣የተባበረ የውጭ ፖሊሲ ለማንበር፣እንዲሁም፣አንድ የተባበረ የምጣኔ ሀብት ህብረተሰብ ለማምጣት የሚተጋ፣የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት በሚል የሚተጋ መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ትብብራቸው በጨመረ ቁጥር የአፍሪካ ህብረት ንቁ ተሳታፊና ተጽእኖ ማሳደር የሚችል ህብረት ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻግር አፍሪካ የአንድነት ድል በመሆኑ የተነሳ፣ አፍሪካውያን በፖለቲካው፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚው አለም የገጠማቸውን ተግዳሮት ለማሸነፍ የህብረት ችቦ መለኮሱ አማራጭ የለውም፡፡ አፍሪካውያን እንደ አድዋ ጀግኖች ሁሉ በትብብር በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ አፍሪካውያን የማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንድነት ለማንበር ካልሆነላቸው ዝንተ አለም የምእራቡ እና የምስራቁ አለም መጫወቻ መሆናቸው የማይቀር ጎምዛዛ ሀቅ ነው፡፡
በመጨረሻም አፍሪካውያን ከአድዋ አኩሪ የድል ታሪክ መማር ከቻሉ አውሮፓውያን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ በተለይም ለጀርመን ገቢራዊ ያደረጉትን የማርሻል ፕላን በአፍሪካም እንዲደግሙት መወትወት፣ግዴታ ውስጥ መዶል ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህ ግን አፍሪካውያን አንድነታቸውን ማጠንከር ግዴታቸው ነው፡፡ አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት አንድነት ይበጃታል፡፡ እነ ክዋሚ ንክሩህማ፣ አጼ ሀይለስላሴ፣ጀማል አብዱልናስር፣ ሴንጎር፣ ሙዋሊሙ ኔሬሬ፣ ታላቁ ማንዴላ እድሜያቸውንሙሉ የዋጁት ለአፍሪካ አንድነት እንደነበር የአሁኑ ትውልድ በአንክሮ አለበት፡፡ ሰላም፡፡
, encourage the West to investment in Africa the level of Marshal Plans for Europe after WWII. The investment will benefit both Africa and the West through job creation, influence with business than with force, and gain respect.