>
5:21 pm - Saturday July 20, 6971

የእሳት ላንቃው ደጃዝማች በቀለ ወያ ...!!! (ታሪክን ወደኋላ)

የእሳት ላንቃው ደጃዝማች በቀለ ወያ …!!!

ታሪክን ወደኋላ
*…. “አላስኬድም አለኝ አርኩ (ጣልያን) በመንገዱ፤
 ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ !”
ደጃዝማች በቀለ ወያ ከአባታቸው ወያ ኦብሴና ከወይዘሮ ብርቄ ጂሎ ጎዳና ነሐሴ 21 ቀን 1902 ዓ.ም በደቡብ ሸዋ ሶዶ ውስጥ ልዩ ስሙ ጎጌቲ ሲብስቶ በሚባል መንደር ተወለዱ፡፡ የዐማርኛ ት/ትን እቤታቸው ድረስ አስተማሪ ተቀጥሮላቸው አጠናቀቁ፡፡ በቀለ በአባታቸው የሶዶ ጉራጌ (ክስታኔ) ሲሆኑ በእናታቸው ደግሞ ኦሮሞ ናቸው፡፡ በቀለ የ16 ዓመት ልጅ ሳሉ እናታቸው ከአጎታቸው ገ/ማርያም ጋሪ ዘንድ አኖሯቸው፡፡ በቀለም እንዳደጉ የአጎታቸው እልፍኝ አስከልካይ ሆኑ፡፡
ደጃዝማች ገብረማርያም ከ1923 – 1926 ዓ.ም ድረስ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሳሉ በቀለ ወያ ሻቃ የሚል የማዕረግ ስም ተሰጣቸው፡፡ በዚህም በረዳት ወታደርነትና በአስተዳደር ሥራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ በ1927 ዓ.ም ደጃዝማች ገ/ማርያም የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ተብለው ሲሾሙ አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የታንክ መስበሪያ መሣሪያ አጠቃቀምን ለማጥናት በቁ፡፡
በ 1928 ዓ.ም ፋሽስት ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ መጀመሪያ ወደ ሰሜን ፣ ቀጥሎ ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ታዘው ወደ ሲዳሞ በመሄድ በአጎታቸው ሥር ያለውን ጦር በመምራት ከፍተኛ ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ታደሰ ዘወልዴ ቀሪን ገረመው በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ከትበዋል፦ “የጠላት ታንክ ወገንን በማጥቃቱ ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ በጣም ያዝኑ ነበር፡፡ አንድ ቀን አምስት ታንኮች በመደዳ ሆነው ጦሩን እያጠቁ ሲመጡ ‘በቀለ፥ ያንተ ብልኀት ለመቼ ሊሆነን ነው ! አትለውም ወይ ! ወይኔ !’ እያሉ ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ሲያዝኑ በቀለ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር፡፡ ታንኮቹ ጠጋ ብለው በደንብ ሲታዩት በመድፍ የመጀመሪያውን አኮማተረው፤ ደግሞም የኋለኛውን ደገመው፡፡ እንደዚሁ በ5 ደቂቃ አምስቱንም ታንክ አቃጥሎ ሲነድዱ፥ ‘ደጃዝማች ! ሄደው እሳት ይሙቁ’ አላቸው፡፡”
ሻቃ በቀለ የደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ጦር የመድፍ ክፍል ኃላፊ ሆነው በማገልገልና በሲዳሞ የጦር ግንባር ግንቦት 9 እና 11 ቀን 1928 ዓ.ም የደጃዝማች ገ/ማርያምን ጦር ለመውጋት የመጣውን ወራሪ ግንባር ገጥመው በመደምሰስ የጠላትን ጦር መሣሪያ ማከማቻ አውድመዋል፡፡ በዚህ ጥረታቸው ከአጎታቸው ገ/ማርያምና ከባልደረቦቻቸው ምስጋና ሲቸራቸው፥ በጦርነቱ ደግሞ ስምንት ባለ ውሃ ከባድ መትረየስና ዐሥራ አራት ቀላል ድግን አልቤን መትረየስ ሲማረክ፥ ሠላሳ የጣሊያን መኰንኖችና በቊጥራቸው የበዙ የጠላት ወታደሮች ተደባይተዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ከሰኔ 1 ቀን 1928 ዓ.ም እስከ መስከረም 23 ቀን 1929 ዓ.ም ብዙ ጦርነት ሲካሄድ፥ ከእነዚህ ዋነኛው የደባ ስሬ ጦርነት ነበር፡፡ በዚህ ጦር ደጃዝማች ገ/ማርያም ጋሪ ቢቆስሉም ሻቃ በቀለ ደግሞ ከ12 በላይ ታንኮችን በመድፋቸው በማውደም የማይረሳ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ በኅዳር ወር (13 – 19) ቀን 1929 ዓ.ም ድረስ በአለታ ወንዶ አካባቢ ተፈሪ ኬላ በተባለው ቦታ፥ ጥር 12 1929 ዓ.ም ደግሞ አርቤጎና ላይ፥ ጥር 15 ቀን 1929 ዓ.ም በደኤላ ጭሪ፥ ጥር 19 ቀን 1929 ዓ.ም በሂበኖ አሩሲ፥ የካቲት 5፥ 10 እና 11 ቀን 1929 ዓ.ም በላቂ ደንበል የፈጸሙት ድል ከቶውኑ አይረሳም፡፡
አጎታቸው ደጃዝማች ገ/ማርያም በየካቲት 13፥ 1929 ዓ.ም ጎጌቲ በነበረው ከባድ ጦርነት ሕይወታቸው አለፈ፡፡ በዚህም ሻቃ በቀለ በጣም አዘኑ፡፡ ሙሉውን ጦር በመረከብ ከአክስታቸው የወ/ሮ ቡኔ በዳኔ ልጅ ከነበሩት በዳኔ ጉደታና ከሌሎች አርበኞች በመመካከር ወታደራዊ ትጥቃቸውን አጥብቀው በትውልድ ሀገራቸው ሶዶ ጠላትን ተቋቁመዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ጦራቸውን በማደርጀት በየካቲት ወር 1930 ዓ.ም በሶዶና ሜጫ ወሰን ላይ ሁለት ባታልዮን የጠላት ጦር ገጥመው በድል ደምስሰዋል፡፡ በዚያው ጊዜ በአገምጃ ያካሄዱት ጦርነት ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ድረስ ለ10 ሰዓታት ያህል በአይሮፕላንና በመድፍ የመጣውን ጠላት ገጠሙ፡፡ በጦርነቱ ብዙ የሶዶ ጀግኖች ተረፈረፉ፡፡ ሆኖም ድሉ የርሳቸው ነበር፡፡ ይህን ጀግንነታቸውን የሰማ የሶዶ ሕዝብ በጅምላ ይጎርፍ ጀመር፡፡ በሶዶ ቶሌና በረጲ ጦርነትም የሻቃ በቀለ ጦር የጠላትን ጦር ድል እየመታ ስለቀጠለ ጣልያን ፈርቶ ለ6 ወር ያህል ርቆ ሊቆይ ተገደደ፡፡ በሶዶ አጨበር፥ ቁሻትና ኢቲኒ ላይ ለ8 ሰዓት ያህል የተፋፋመ ጦርነት ተካሂዶ ድሉ የሻቃ በቀለ ሠራዊት ነበር፡፡ በተጨማሪም በሶዶ ጫከ ደራራ፥ አገምጃ፥ በሶዶና በወለኔ ወሰን ላይ የሲ፥ ኦሞ፥ ጎደብ በተባሉ ቦታዎች አንጸባራቂ ድል ተጎናጽፈዋል፡፡ በወርኃ መስከረም 10 ቀን 1932 ዓ.ም ሶዶ ባንቱ በተባለ ቦታ ለ7 ሰዓታት ያህል ተዋግተው ድል በማድረጋቸው የሶዶ ሕዝብ በኩራት እንዲመካባቸው አስችሏል፡፡
አጎታቸው ከሞተ ወዲህ ሻቃ በቀለ ከጎረቤት አርበኞች ጋር ኅብረት መፍጠር ጀመሩ፡፡ በተለይም ከዘመዳቸው ገረሱ ዱኪ ጋር ተባብረው ጠላትን የመደምሰስ ዕቅድ በማውጣት ብዙ መክረዋል፡፡ በጋራም የጠላትን ጦር ይደመስሱ ነበር፡፡ ከገረሱ ዱኪ ጋር በበዳና አቄሮና ሶዶ ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ተዋግተዋል፡፡ ለዚህ ጦርነት ምክንያቱ ሙሴ ቀስተኛ የተባለ የጣልያን መልእክተኛ ነበር፡፡ ሙሴ ቀስተኛ ገረሱን ለማጥመድ የተላከ ስለነበር በገረሱ ተነቅቶበት የሞት ውሳኔ ተበይኖበታል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጠላት የሙሴ ቀስተኛን ደም ለመበቀል ከጅማ፥ ከሲዳሞ፥ ከሐረር፥ ከአርሲና ከሸዋ ጦር አሰባስቦ የገረሱን ጦር በመውጋት ከፍተኛ እልቂት አስከተለባቸው፡፡ ገረሱ ሸሽተው ከሻቃ በቀለ ጋር በመገናኘት ለሦስት ቀንና ሌሊት አርባ አራት ባታልዮን ይገመት ከነበረ ጦር ጋር  በጣም ዘግናኝ የሆነ ጦርነት ተፋልመዋል፡፡ በአይሮፕላንና መድፍ ብዙ ሠራዊት አለቀባቸው፡፡ መሣሪያቸውም በምርኮ ተወሰደ፡፡ ሻቃም ቀኝ እጃቸው ስለቆሰለ መድፍ እንደልብ ባለመተኮሳቸው ጦርነቱ ለጊዜው ቆመ፡፡ በዚህ ምክንያት ጦሩ ተበተነ፡፡ በቀለም እስኪያገግሙ ድረስ ሸዋ ቡልጋ ሄደው ከአበበ አረጋይ ጋር ተነጋግረው የጦር ስልት ነድፈዋል፡፡ መክረውም ወደ ሶዶ ተመልሰዋል፡፡
መጋቢት 17 ቀን 1932 ዓ.ም ሻቃ በቀለ ከቀኛዝማች በየነ ጉደታ ጋር ሳሉ ከጠላት ወገን ደብዳቤ ደረሳቸው፡፡ የደብዳቤውም መንፈስ እጅ ብትሰጡ ይሻላችኋልና አስቡበት የሚል ነበር፡፡ እነርሱም በደብዳቤው ድፍረት በሽቀው ትግላቸው የነጻነት መሆኑን በመድፍ መልስ ላኩላቸው፡፡ ስለዚህ መስከረም 22 1932 ዓ.ም ጦር ተከፈተ፡፡ ሶዶ ውስጥ ረጲ የተባለ ቦታ ከቀኑ 2 ሰዓት ጀምሮ ከባድ ጦርነት ተፋፋመ፡፡ ብዙ የሻቃ በቀለ ጦር እየፎከረ በጀግንነት አለቀ፡፡ ቀኛዝማች በየነ ጉደታም ቆስለው ወዲያውኑ እናታቸው ሀገር ሶዶ አገምጃ እንዲሄዱ ተደረገ፡፡
እዚያም ሳሉ የመግደል ሙከራ ገጠማቸው፡፡ ሸሽተውም ገረሱ ዱኪ ጋር መጡ፡፡ ቁስላቸውም ሲድን ወደ በቀለ ወያ ለመሄድ መንገድ ሳሉ ጠላት ከበባቸው፡፡ በዚህም ከጠላት ወገን 20 መኰንኖችና ከ30 በላይ ወታደር ገድለው መሥዋዕትነት ሆነው አለፉ፡፡ አብረዋቸው የነበሩ ስድስት አርበኞችም አለቁ፡፡ ሻቃ በቀለ ልባቸው ክፉኛ አዘነ፡፡ ልባቸው ቂም አርግዞና ውስጣቸው በበቀል ሲናጥ ውሎ ሚያዝያ 23 ቀን 1932 ዓ.ም ዝቋላ ላይ በልዩ የጦርነት ስልት የጠላትን ሬሳ አነባብረው የወንድሞቻቸውን ደም ተበቀሉ፡፡ ግንቦት 27 ቀን 1932 ዓ.ም ደግሞ ዝቋላ ወንበራ ሌላ ጦርነት አድርገው ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡ በኮሎኔል አቡ የተባለውን በጣም ከባድ የተባለውን ጦር ገጥመው 26 የፋሽስት መኰንኖችና 60 ወታደሮች ገድለዋል፡፡ ታደሰ ዘወልዴ ጦርነቱን እንዲህ ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፦
“በ18 ካሚዮን የነበሩትን ፋሽስቶች አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨረሷቸው፡፡ ወዲያውኑ አስክሬናቸው በፍጥነት ወደ ነበሩበት ካሚዮን እንዲሰበሰብ ከተደረገ በኋላ ናፍጣ አርከፍክፈውና በእሳት አቀጣጥለው ሌሊቱን እንደጧፍ ሲነድ አደረ፡፡”
ይህን የሰሙ ፋሽስቶች ላብ አሰመጣቸው፡፡ በጎጃም በላይ ዘለቀ የተፈራውን ያህል በሶዶ ደግሞ በቀለ ወያ በጠላት ወገን እጅግ ተፈሩ፡፡ ጣልያንም የሻቃ በቀለን ሠራዊት ላንዴ ሊደመስስ ብዙ የባንዳ ሠራዊትና ነጭ ወታደሮችን ከጅማ፥ ከሲዳሞ፥ ከናዝሬት፥ ከወሊሶ፥ ከአዲስ አበባ፥ ከአርሲ አሰባስቦ ቶሌ በተባለው ቦታ 12 ሰዓት የፈጀ ጦርነት ገጠሙ፡፡ በሁለቱም ወገን አለ የማይባል ጦር አለቀ፡፡ የጠላት ወገን ግን እንዳለመው አልተሳካለትም፡፡ ይልቁኑ የበቀለ ወያ ጦር ከገረሱ ዱኪ ጋር በመተባበር አሳድዶ እየወጋው ብዙዎቹን ማረከበት፡፡ ሻቃ በቀለ አምስቱንም ዓመት ሙሉ ለኢትዮጵያ ነጻነት ቆስለዋል፥ ተንከራተዋል፥ በጀግንነትም የጠላትን ጦር ደምስሰዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንደተመለሱ በቀለ ወያ እነዚህን ማዕረጎች አግኝተዋል፦
1. በ 1933 ዓ.ም በፊታውራሪነት ማዕረግ የሲዳሞ ጥብቅ አስተዳዳሪና የክብረ መንግሥት የወርቅ ማዕድን ኃላፊ፤
2. በ 1933 ዓ.ም የሁለተኛ ሬዥማን አዛዥ፤
3. በ 1934 ዓ.ም በወለጋ የሶዩ አውራጃ ገዥ፤
4. በ 1935 ዓ.ም የጨቦና ጉራጌ አውራጃ ገዥ፤
5. በ1936  ዓ.ም የወላይታ አገረ ገዥ፤
6. በ 1938 ዓ.ም በሐረር የጨርጨርና ኢሳ አውራጃ ገዥ በመሆን ሠርተዋል፡፡
ደጃዝማች በቀለ ወያ በሥራ ላይ እያሉ ባደረባቸው ጽኑ ሕመም ምክንያት ለሕክምና ወደ ስዊዘርላንድ በጉዞ ላይ ሳሉ ሚያዝያ 6 ቀን 1946  ዓ.ም አርፈዋል፡፡ አስክሬናቸውም ሚያዝያ 10 ቀን 1946  ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ብዙ ዘመድና አዝማድ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአርበኞች ማኅበር አባላት፣ በግልና በዝና የሚያውቃቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ በተገኘበት በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን  በደማቅ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ አርፏል፡፡
ሻቃ በቀለ ወያ መቼም የማይረሱ ጀግና በመሆናቸው ይህ ግጥም ማስታወሻቸው ሆኖ ይኖራል።
“አላስኬድም አለኝ አርኩ (ጣልያን) በመንገዱ፤
 ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ !”
Filed in: Amharic