>

በብሔራዊ የውይይት መድረክ አመሃኝነት የዜጎች መብት እንዴት ሊከበሩ ይቻላቸዋል ? (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

በብሔራዊ የውይይት መድረክ አመሃኝነት የዜጎች መብት እንዴት ሊከበሩ ይቻላቸዋል ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


መግቢያ

 ኢትዮጵያ በርካታ ባህሎች ያሉባት ሀገር፣በርካታ ቋንቋዎች የሚናገሩባት፣ብሔራዊ ማንነት ያላትም ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዝሃው የሀገሪቷ የፖለቲካ ኤሊቶች ከአንድነት ይልቅ ወደ የሚለያያቸው አጀንዳዎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ስለሆነም ይህቺ የምንወዳት ኢትዮጵያ፣የነጻነት ቀንዲል ኢትዮጵያ አንደነቷ እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ ልዩነቱ ተቋማዊ ይመስላል፡፡ በሌላ አነጋገር መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው ህገመንግስት ልዩነት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ችሎታን መሰረት ያላደረገ ሹመት፣ የጎሳ ድንበር ወይም ጎሳን መሰረት ያደረገ የክልል መስተዳድር አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን ሳይሆን ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት የተከሰቱ መጠነ ሰፊ ግጭቶች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት የነበረው ስርአት ብሔራዊ አንድነትን ችላ ያለ ነው፡፡ የህግ የበላይነትንም ችላ ያለ ነው፡፡ በእውነቱ ለመናገር ኢትዮጵያ በየግዜው ከአደጋ አለመውጣቷ አሳዛኝ ነው፡፡ ስለሆነም ባለፉት ሰላሳ አመትም ሆነ ቢያንስ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ከገጠማት ብሔራዊ አደጋ ለመውጣት ፣ ከፖለቲካ አለመረጋጋት ለመገላገል በዚች ሀገር ላይ ብሔራዊ የውይይት መድረክ እውን መሆን አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ይህ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ደግሞ ዜግነትን መሰረት ባደረገ ህገ መንግስት ላይ የቆመ፣ ሁሉንም ዜጎች ያካተተና ነጻ መድረክ መሆን አለበት፡፡ ማናቸውም የዚች ሀገር ዜጎች ከህግ በላይ መሆን የለባቸውም፡፡ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በህግ መገዛት አለባቸው፡፡ከወንጀለኞች ጋር መተባበር፣ወንጀል ለሚፈጽሙ እኩያን ሽፋን መስጠት፣ወንጀለኞች ወንጀል ከመፈጸማቸው በፊት አለመከላከል፣ ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማያደርግ መንግስት ባለበት ብሔራዊ የውይይት መድረክ ውጤታማ አይሆንም፡፡ የአንድ ሀገር መንግስት ዋነኛ ስራ የሀገርን ደህንነት እና ሰላም ማስጠበቅ ነው፡፡

ብሔራዊ የውይይት መድረክ አንድ ሀገር ከገባችበት የፖለቲካ ማጥ ውስጥ እንድትወጣ ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች እና የሲቪል ማህበረሰቡ ተወካዮች በተገኙበት የሚካሄድ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሀገሪቱን ሊታደጋት ይቻለዋል፡፡ ይህ ግጭቶችን  ለመክላት፣ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት እንደ ጥሩ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ብሔራዊ የውይይት መድረክ የዲሞክራቲክ ሽግግርና እንደ ውሃ ወቀጣ ማለቂያ ከሌለው የግጭት አዙሪት  እንዴት መውጣት እንደሚቻል መስታወት ሆኖ የሚያሳየን ነው፡፡

በእኔ የግል አስተያየት በትክክል የተዋቀረ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ከግጭት በኋላ የፖለቲካ ልዩነትን ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡ ይህም ማለት የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ይረዳል፡፡ ስለሆነም ይህ የብሔራዊ የውይይት መድረክ ሶስት አላማዎች ይኖሩታል፡፡ እነኚህም ሰላም መገንባት፣እርቅ እና የሕገመንግስት መሻሻል ናቸው፡፡

ብሔራዊ የውይይት መድረክ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ( በተለይም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ) ሶስት ደረጃዎችን ማለፍ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እነኚህም፡-

  •  ሰላም መገንባት እና እንደገና መገንባት
  •  እውነት፣ ፍትህና እርቅ ማስፈን
  •  መሰረቱን ዜጎች ላይ ያደረገ ህገመንግስት ማርቀቅ፣ አንዲሁም ለዜጎች ነጻነትን የሚሰጥ የምርጫ ውድድር ማድረግ

ከብዙ ሀገራት ልምድ ለመረዳት እንደሚቻለው ( ለአብነት ያህል ቱኒዚያ፣የመን፣ኮሎምቢ እና ደቡብ አፍሪካ ይጠቀሳሉ፡፡) ብሔራዊ የውይይት መድረክ ውጤታማ የሚሆነው ዋነኞቹ አክተሮች መካፈል ከቻሉ፣ ማለትም ምልአተ ህዝቡ ተሳታፊ የሆነበት፣ግልጽነት ፣ መተማመን የሰፈነበት ህብረተሰብ መፈጠር ሲቻል ወዘተ ወዘተ ሲሟሉ እንደሆነ ብዙዎች ምክረሃሳብ ያቀርባሉ፡፡

በነገራችን ላይ የጎሳ ኤሊቶች የአብዝሃ ዲሞክራሲ ውሳኔ  ያስፈራቸዋል፡፡ እነርሱ በዲሞክራሲ አካሄድ ወክለነዋል ከሚሉት ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ከሚኖርበት አካባቢ ውጭ ሄደው ፣ ወይም ሌሎች ህብረብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች በእነርሱ ክልል ውስጥ መጥተው ተፎካካሪ እንዲሆኑ ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ አብዛኛውን ግዜ ስልጣን የሚይዙት በችሎታ ሳይሆን በብሔር ተዋጽኦ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ( ይህ ማለት ግን የጎሳ ፖለቲካ ኤሊቶች እውቀት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ በፕሮፌሰር ደረጀ ላይ የሚገኙ የጎሳ ኤሊቶች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና መሰረት ( እንደ ፍልስፍና ከተቆጠረ ማለቴ ነው) የአንድ ጎሳ አባል ያልሆነ የተማረ ግለሰብ ወይም ሌላ ሙያ ያለው ሰው በሚኖርበት የጎሳ ክልል ውስጥ የስልጣን ባለቤት መሆን አይችልም፡፡ ለዚህም ነው አሁን ድረስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የውይይት መድረክ እውን ሆኖ ውጤታማ ለመሆን ያዳገተው፡፡ ( የወደፊቱን አብረን የምናየው መሆኑ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡)

የሽግግር ሂደት

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የሀገሪቱን 95 ፐርሰንት የፓርላማ ወንበር የተቆጣጠረው የብልጽግና ፓርቲ ከጥቂት ወራት በፊት አገራዊ ምክክር ጉበኤ መመስረቱን ከመገናኛ ብዙሃን የተሰማ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አገራዊ የምክክር ጉባኤ የተመሰረተው በፓርላማው እንደተመሰረተ የሚዘነጋ አይደለም፡፡( The ruling Prosperity Party, with over 95% of the seats in the lower Parliament, has recently established a national dialogue commission (NDC፣ አገራዊ ምክክር ጉባዔ) by an act of Parliament.)

ከዚህ ቁምነገር የምንማረው ቁምነገር ጉዳይ ቢኖር ሁለት የማይነጣጠሉ ሂደቶች እንዳሉ ማሳያ ነው፡፡ ይህም ማለት መንግስት ተከታዩ ብሔራዊ የምርጫ ውድድር ግዜ እስኪደርስ መንግስታዊ ሃላፊነቱን መወጣት ሲኖርበት፣ አገራዊ የምክክር ጉባኤው በበኩሉ  በገለልተኝነት አቋም፣ የታወቁ ችግሮችን፣ ምክንያቶች፣ውጤታቸውን እና ለችግሩ ደግሞ ሰራሄ መፍትሔ መፈለግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ አገራዊ የምከክር ጉባዔ የገለልተኛ አቋም መያዝ አለበት ተብሎ ሲጻፍ እንደው ለላንቲካ ወይም ወሬ ለማሳመር አይደለም፡፡ይቺ ሀገር በታላቅ የችግር አረንቋ ውስጥ ገብታ የተዘፈቀች ናት፡፡ ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲካ ፣ በርስበርስ ጦርነት ምክንያት ፍዳዋን እየቆጠረች ትገኛለች፡፡ ክልላዊ መንግስታት በገለልተኝነት መንፈስ ሰላም ማስፈን አልሆነላቸውም፡፡ ስለሆነም ይህ አገራ የምክክር ጉባኤ ገለልተኛ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡

ይሄው 11 ገለልተኛ አባላት ያለው አገራዊ ምክክር ጉባኤ ለፓርላማው ሪፖርትና ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ሶስት አመታት ሊፈጅበት እንደሚችል ይነገራል፡፡ ይህ ጉባኤ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ውይይት ይገመግማል፣ የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግር ከመረመረ በኋላ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በሀገሪቱ ሰማየሰማያት ላይ ሰፍኖ የቆየው ወይም አሁን የሚታየው የፖለቲካ አየር ተስፋ የሚሰጥ ላለመሆኑ አንዳንድ አስረጂዎችን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡( ለአብነት ያህል የሰላም ኮሚሽን የድንበርና ማንነት ኮሚሽን ስራች አመረቂ አልነበሩም፡፡) ከዚህ ባሻግር መንግስት የምክክር ጉባኤው እንዴት መስራት እንዳለበት መጠቁም ማድረጉ አይደለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የስልጣን ፍትጊያም እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ ( የስልጣን ፍትጊያው ስልጣን በያዙት ቡድኖች፣ ስልጣን በያዙትና ከስልጣን ውጭ ባሉት ሃይሎች መሃከል፣ወይም ገና ስልጣን ለመያዝ በቋመጡ ቡድኖች መሃከል ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡

 በነገራችን ላይ የሰላም ሂደቱ ደረጃ በርካታ ሂደቶችን ማለፍ ይኖርበታል፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ  ኢትዮጵያ ከ 28 አመታት በላይ የዘረኝነት አገዛዝ ወገቧ መድቀቁን መገንዘብና ከዚህ መርዘኛ ደዌ እንድትገላገል በሰለጠነ መንገድ ሰራሄ መፍትሔ መፈለግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በሁሉም ወረዳዎችና ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የማህበረሰቡ ተወካዮች በተገኙበት ነጻና ገለልተኛ ውይይት መካሄድ አለበት፡፡ ለአብነት ያህል በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ህዝባዊ ውይይት ቢካሄድ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የመገንጠል ጽንሰ ሃሳብ አደገኛ ስለመሆኑ፣ ሰላምን የሚያደፈርሱ ታጣቂ ሀይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው አብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ እንዴት ማመቻቸት እንደሚቻል፣በድንበርይገባኛል ምክንያት የሚቀሰቀሱ የርስበርስ ግጭቶችን ስለማስወገድ በተመለከተ፣ አለም አቀፍ የሰብዓዊና የሲቪል መብቶችን ስለማስከበር በተመለከተ፣የፖለቲካ እና ህሊና ታሳሪዎች ከእስር ስለሚለቀቁበት ሁኔታ፣መንግስት ጸጥታ ማስከበር እንዳለበት መወትወትን በተመለከተ ወዘተ ወዘተ ውይይት መደረግ አለበት፡፡

በሁለተኛው ደረጃ የምክክር ጉባኤው የብሔራዊ አንድነት አጀንዳ እውን እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ወይም ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ይህ ፍትህ እና እርቅን እውን ለማድረግ ይረፋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ አሁን የደረስንበትን ግዜ ጨምሮ በመንግስትና መንግስታዊ ስልጣንን ባልጨበጡ አክተሮች የተፈጸሙ ወንጀሎችን መመርመር ያለበት ይመስኛል፡፡ ቅጣቱ ምናልባትም ጥፋታቸውን ላመኑ ወንጀለኞች ይቅርታ በማድረግ፣ከባድ ወንጀል የፈጸሙትን በአለም አቀፍ ህግ አግባብ፣ እንዲሁም በሲቪልና ልማዳዊ ህጎች መሰረት መቅጣት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሶስተኛው ደረጃ ዜጎች ነጻ፣ገለልተኛና አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በሚካሄድ የምርጫ ውድድር ላይ የሚፈልጉትን ተወካያቸውን መምረጣቸውን ማረጋገጥ ይሆናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ፡-

  •  የፍርድ ቤት ነጻነት እንዲከበር፣የህገመንግስት ፍርድ ቤት እንዲመሰረት፤
  •  የመሬት ባለቤትነት ነጻነት መብት እንዲከበር፣
  • የዜጎች መብት ሙሉሄበኩልሄ በሆነ ሁኔታ እንዲከበር የራሱን ድርሻ መወጣት ያለበት ይመስለኛል፡፡

እንደ መደምደሚያ

በመጨረሻም ህገመንግስቱ የዜጎችን መብት የሚያስከብር ሰነድ እንዲሆነ ከተፈለገ የሚከተሉት ተግባራት መከናወን አለባቸው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡

  1. መዋቅራዊ ውደቀት፣መዋቅራዊ ሰራሄ መፍትሔ ያስፈልገዋል
  2. በኢትዮጵያ አሁን የፖለቲካ ስርአት መሰረት የጎሳ ፖለቲካ ነው ስለሆነም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ በውይይት በዜግነት ላይ በተመሰረተ የፖለቲካ አስተምህሮ መተካት ይኖርበታል
  3. በኢትዮጵያ ወደ ሰላም፣ፍትህ፣እኩልነትና አንድነት የሚወስድ ጎዳና በህዝቡ ስምምነት መገንባት አለበት፡፡
  4. የምክክር ጉባኤው ብሔራዊ የውይይት መድረክን በተመለከተ የአጭርና የረዥም ግዜ እቅድ እንዲወጣ ማድረግ ቢችል፣በሀገሪቱ ሰላም የሚሰፍንበት መንገድ እንዲፈለግ፣እውነት፣ፍትህና እርቅ ስለሚወርድበት ሁኔታ በተመለከተ የበኩሉን ሁነኛ ድርሻ ቢወጣ ከገባንበት የፖለቲካ ማጥ ለመውጣት የሚያስችል አንዱ መንገድ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለማናቸውም ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

 

 

Filed in: Amharic