ይድረስ ለውለታቢሶች!
ፋኖነት እውነት ነው የአምሀራ ጥላ
ከገፊዎች ሚያስጥል የሀገር ከለላ
ፋኖነት ልብ ነው የአምሀራ ትርታ
ለዘረኞች በትር በገቡበት ቦታ
ፋኖ እስትንፉስ ነው ነፃ መተንፈሻ
በሰላም ለመኖር ለኢትዮጵያ ጋሻ
ፋኖነት ረቂቅ ነው በእጅ አይጨበጥ
ከፋፋይ እብሊሱን ደርሶ ሚደፈጥጥ
ፋኖነት ጥበብ ነው በልብ የሚያጠልቁት
በጥባጮች ዘረኞች ጫፉን የማይነኩት
ፋኖነት ደራሽ ነው ከተፍ የሚል ጀግና
ለተገፉት ቋሚ በሁሉ ጎዳና
ብጣቂ ወረቀት ፅፈው ቢሳደቡ
በገንዘብ ተገዝተው ውሸት ቢዘግቡ
አምሀራ ፋኖ ነው በየሁሉ ስፍራ
ሲነኩት ታግሶ ችሎ የሚሰራ
የማይርድ ባገሩ ጠላት የሚገራ
ትንሽ ያገሳ እንደሁ ሽብር የሚዘራ
ፋኖነት እድል ነው የሚወለዱበት
ሀገር የሚያስወድድ መንፈስም ያለበት
ልነጠል የማይል ለአንድነት የቆመ
ከፋፋይ ነፃ አውጪን ሁሌም የረገመ
ፋኖነት እንዲህ ነው ለማታውቁት ስሙ
አጀንዳ ይዛአችሁ ለምትራገሙ
ክርስቲያን ሙስሊሙን በክብር ያቆየ
የኢትዮጵያ ተስፋ ዘር በዘር ያለየ
ጎዳ እየገባ ሴትን የማይደፍር
ቁጥርጥር ተሰርቶ ሀገር ማያሸብር
ሰላማዊውን ህዝብ በዘር የማይጠላ
ቤት እምነት የሚጠብቅ እርሱ ሆኖ ጥላ
እንዲህ ነው ፋኖነት ሩቅ ከፍታ አለው
ከታች የማይዘቅጥ ጠርቶ የሚኖር ነው
ስሙን ለማጠልሸት ወንጀል እየሰሩ
ፋኖ ሌባ እያሉ ጎዳና ቢዞሩ
ፋኖነት መንፈስ ነው ውግዘት የማይሽረው
እውነትን የያዘ የአምሀራ እስትንፋስ ነው
አምላኩን ተስፋ አርጎ ለሀገሩ የቆመ
በሀገር ውስጥ በውጭ ተጠልቶ የከረመ
ብቸኛው ተስፋችን መንግስትም የጠላው
ኢትዮጵያን የሚያድን የሀገር ፍቅር ያለው
ከፈጣሪ ወዲያ መመኪያ ማይፈልግ
ጀግንነቱን ይዞ ታግሶ ሚታደግ
ህፃን አዋቃውን በክብር የያዘ
ለሀገሩ ቀናኢ አዕምሮ ያልደነዘ
ሁሉን ያከበረ አትንኩኝ ሚል ጀግና
ፋኖ ነው ተስፋችን የአምሀራ ህልውና
እርማችሁን አውጡ ከእንግዲህ በኋላ
ፋኖ አምሀራነት ነው አታስቡ ሌላ
መሳሪያ አይጥልም ጉዳችሁም ይፍላ
ዘምሳሌ