>

 የፍርድ ቤት ነጻነት  አስፈላጊነት (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

 የፍርድ ቤት ነጻነት  አስፈላጊነት (The Priority of an Independent Judiciary)

 

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

አንድ ሰው ስለ ዴሞክራሲ ጽንሰሃሳብ በሚያሰላስልበት ግዜ ወዲያውኑ ብልጭ የሚልበት ሃሳብ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እውን ስለመሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኛ የሰው ልጆች በተፈጥሮ ዴሞክራሲን ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር እኩል አድርገን እናየዋለን፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የማይነጣጠሉ መብቶች በመሆናቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲ በገቢርም በነቢብም ሃሳብን በነጻነት ማቅረብ መብት እንዲኖር ይረዳል፡፡ እኛ ስለ ዴሞክራሲ ስናስብ በመጀመሪያ ማወቅ ያለብን ቁምነገር ቢኖር የመንግስት ስርአት የህግ የበላይነት ስለማስከበሩ፣የፍርድ ቤት ነጻነትን ስላለመደፈሩ ፣ሃሳብን በነጻነት መብት ስለመከበሩ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድ መንግስት ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከለክል ከሆነ፣ወይም በራሱ መልካም ፈቃድ ብቻ ዜጎች ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ፍላጎት ካሳየ ዴሞክራቲክ መንግስት ተብሎ ሊሰየም አይቻለውም፡፡ ስለሆነም የአንድ ሀገርን መንግስት ዲሞክራቲክ ከሚያሰኙት ባህሪያት ዋነኞቹ የህግ የበላይነት እንዲከበር ማድረጉና የፍርድ ቤት ነጻነትን እውን ማድረጉ ነው፡፡

የህግ የበላይነት ምንድን ነው ? የህግ የበላይነት ማለት የጥቂቶች የበላይነት የሌለበት፣ሰዎች በህግ ጥላ ስር ሆነው የሚተዳደሩበት ስርዓት ነው፡፡ አንድ ነጻ አውጪ ነኝ ባይ እንደፈለገው ህዝብን የማይጋልብበት ስርዓት አለመኖሩን ማሳያ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ህዝብ በህግ ጥላ ስር ሆኖ፣በህግ ሲተዳደር የህግ የበላይነት መኖሩን ማሳያ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የጋራ ጥቅም እውን መሆንን የሚያሳይም ነው፡፡ በህዝብ ይሁንታና ምርጫ ስልጣን የጨበጡ ባለስልጣናት ባሉበት ሀገር የህግ የበላይነት እውን መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም፡፡

      በተመሳሳይ መልኩ ነጻ የዳኝነት አካል ማለት ስልጣኑ በህግ አውጭው ያልተያዘበት ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በህግ ተርጓሚው የስራ ሂደት ላይ ህግ አውጭውም ሆነ ህግ ተርጓሚው ጣልቃ የማይገባ ከሆነ፣አንዳንድ ሀይልና ስልጣን ያላቸው የመንግስት ሹመኞች፣እንዲሁም በገንዘብ የናጠጡ ዲታዎች ጣልቃገብነታቸው የተገደበ ከሆነ፣ የህግ ተርጓሚው ወይም የዳኝነት አካሉ ነጻነቱ የተጠበቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ፍትህ እንዲሰፍን፣ ህዝቡ ነጻነት እንዲቀዳጅ የህግ ተርጓሚው አካል ከውጭ እና ውስጣዊ ጫናዎች ሙሉበሙሉ ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የዳኝነቱ አካል ነጻነት በጽኑ መሰረት ከተጣለ ሀገሪቱ አስተማማኝ መረጋጋት ላይ ልትቆም ይችላታል ብዬ አስባለሁ፡፡( ወይም ወንጀለኞች፣የሰብአዊ መብት የሚጥሱ የተለያዩ አካላት በፍትህ አደባባይ ቆመው ፍርዳቸውን ያገኛሉ፡፡)  ስለሆነም ይህ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራት እንደ ወጌሻ የሚቆጠር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የዳኝነት አካሉ እንዲህ በአጭር ግዜ ውስጥ ነጻነቱ ሊጠበቅ አይቻለውም፡፡ ይህ ሂደት ነው፡፡ ለዚህ እውን መሆን የህግ አውጪው እገዛና መለስተኛ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም የህግ አውጭው በህዝብ ይሁንታ የተመረጠ ከሆነ የህግ ተርጓሚው ነጻነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የህግ አውጭው አካል ሚና መተኪያ የለውም፡፡ በሌላ በኩል የሕግ ባለሙያዎችና ዳኞች የሞራል ልእልና መላበሳቸው የህግ ተርጓሚው ነጻነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ልክ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ እንደሚስተዋለው  የዳኝነት ሂደቱ ነጻና ገለልተኛ ለመሆን ግማሽ ክፍለዘመን ወይም አንድ መቶ አመታት ይፈጅበታል ማለት አይደለም፡፡ በቅኝ ገዢ ታላቋ ብሪታንያ  

ፍዳዋን ትቆጥር የነበረው ጎረቤት ሀገር ኬንያ ዛሬ ከእኛ የተሻለ የህግ ተርጓሚ አካል እንዴት ልታነበር ቻለች ብሎ መጠየቁ ብልህነት ነው፡፡

በነገራችን ላይ የፍትህ አካሉ ነጻ የሚሆንበት ሂደት ከአድሎው አሰራር ነጻ መሆን ፣ ግልጽና ከህግ አውጪው ተጽእኖ መውጣት አለበት ፡፡ (The process by which it is constituted must be fair transparent and with minimal intervention from the executive )  

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የፍትህ አካል በተማሩ እና እውቀት ባላቸው የህግ ባለሙያዎች መሞላቱ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በለብለብ የህግ ትምህርት የተጠመቁ የህግ ሰው ተብዬዎች ነጻነታቸውን ለመቀዳጀት ይቸገራሉ፡፡ እስቲ የኢትዮጵያን የህግ ተርጓሚ አካል ታሪክ በወፍ በረር ላስቃኛችሁ፡፡ በቅድሚያ ግን ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ አመታት በፍትሃነገስት የህግ ስርአት ስትመራ እንደቆየች ለአሁኑ ትውልድ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 በአጼ ምኒልክ 2ኛ ዘመነ መንግስት የነበሩት የህግ ሰውነት ያላቸው በሰለሞን ስርወ መንግስት ተጽእኖ ስር ውስጥ የወደቁ ነበሩ፡፡ ስለሆነም በግዜው የህግ ተርጓሚው በህግ አውጪው ተጽእኖ ስር የወደቀ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ኬ.አይ.ቪብሁት በጥናት መጽሃፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ‹‹ ንጉሱ የፍትህ ፋፏቴ ነበሩ፡፡›› ፍትህ በእርሳቸው ስም ይሰጥ ነበር፡፡ ፍትህ መስጠትም መንሳትም ይችሉ ነበር፡፡ እንዲህ ተብሎ ሲጻፍ ግን አጼ ምኒሊክ ጸረ ፍትህ ነበሩ ማለት አይደለም፡፡ አጼ ምኒሊክ ለፍትህ የሚደማ ልብ ነበራቸው፡፡ ለዚህም ነበር ‹‹ እምዬ ምኒሊክ ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው የነበረው፡፡ ዛሬ በጸረ ኢትዮጵያ አስተምህሮ የተቀኙት የአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ዘመኑ በዋጀው መሰረት ባህላዊ የፍትህ ስርዓት ስለነበረው የህግ አውጪው በህግ ተርጓሚው ስራ ጣልቃ አይገባም ነበር ብሎ መደምደም ስህተት ቢሆንም፡፡ ፈሪሃ እግዛብሔር ግን ነበር፡፡

. Under the imperial regime of Atse Menelik II, there dominated a kind of “Solomonic” perception of the emperor as both legislator and ultimate judge. Thus, the judiciary was seen as being part and parcel of the executive. As Professor K.I. Vibhute put it poetically “[the] King was the fountain of justice”. Justice indeed was sought in the name of his majesty. It was in the name of the emperor that the people sought adjudication. 

አጼ ኃይለስላሴ ለዘመናዊነት የሚደማ ልብ ስለነበራቸው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1931 እና 1955 ህግ ተርጓሚው በህግ አስፈጻሚው ስራ ላይ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክል፣ሆኖም ህግ አውጭው በህግ ተርጓሚው ላይ ጣልቃ እንዳይገባ የማይከላከሉ ሁለት ህገመንግስቶች እንዲጻፉ ፈቅደው ነበር፡፡

አጼ ሀይለስላሴ ከረዥም ግዜ የውጭ ሀገር ( አውሮፓ) ጉብኝት በኋላ ወደ ሀገር ቤት በተመለሱ አጭር ቀናት ውስጥ እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 1942 በአዋጅ ቁጥር 2 መሰረት አራት በደረጃ የተቀመጡ የፍርድ ቤት ስርዓት እንዲመሰረት አድርገዋል፡፡ እነኚህም ከላይ ወደታች፡-

  • አፈንጉስ( የንጉሱ ድምጽ) (literally the “mouth of the king) በህግ መንግስቱ መሰረት ይህ ከፍተኛው የፍርድ ቤት አካል ነው፡፡ የክፍለሀገርና የማህበረሰብ ፍርድ ቤቶች ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ነበሩ፡፡
  • ዙፋን ችሎት፡- ( literally, the Throne’s Court, often translated in English as the Crown’s Court) ይህ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ላይ ጉዳያቸውን አቅርበው ፍትህ ያጡ ግለሰቦች ንጉሱ ዘንድ በመቅረብ የፍትህ ያለ በማለት ከጠየቁ በኋላ ፍትህ የሚሰጥበት የንጉሱ ዙፋን ነው፡፡ ሰዎች ለንጉሱ የፍትህ ጥያቄ ያቀርቡ የነበረው በቀጥታ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ነበር፡፡

ምንም እንኳን ይሁንና አጼ ኃይለስላሴ ያቆሙት የፍርድ ቤት ስርዓት ምሉሄነኩልሄ የነበረ ባይሆንም አጼ ሀይለስላሴ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፍርድ ቤት ስርዓት ለመጀመሪያ ግዜ እንዲመሰረት ያደረጉ ንጉስ ነበሩ፡፡ አጼው የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር የሚጠይቅ ህግ ቢኖራቸውም የህግ ተርጓሚው ነጻ አልነበረም፡፡ 

በደርግ ወታደራዊ ዘመን ቢሆንም የፍትህ አካላት ነጻነት በየግዜው ይጣስ ነበር፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት ያለፍርድ የተገደሉ፣የታሰሩ፣በእግረሙቅ የተሰቃዩ ኢትዮጵያውያን በብዙ ሺህዎች ይቆጠሩ ነበር፡፡ ህጋዊ ከለላ በመገፈፉ ምክንያት ብዙዎች ሀገራቸውን ጥለው ተሰደው ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከደርግ የ17 አመታት አገዛዝ ውስጥ ኢትዮጵያ ለ15 አመታት ያህል ህገመንግስት አልነበራትም፡፡ የተገዛችው በአዋጆች  ነበር ፡፡ በአጭሩ የሕግ አውጭው፣በሕግ አስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው ስራ ላይ ጣልቃ ይገባ ነበር፡፡ህግ አስፈጻሚው በፈለገ ግዜ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ፣ወንጀል መፈጸማቸው፣አለመፈጸማቸው ሳይጣራ ሰዎችን ከመንገድ እያፈሰ፣ግለሰቦችን እየለቀመ ደብዛ ያጠፋ ነበር፡፡ በታወቁ የወህኒ አምባዎች ( ቤቶች ) አስሮ ያማቅቅ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የደርግ ስርአት እንደ ወያኔ ኢህአዲግ ዘመነ መንግስት ሹመኞች በቀጥታ በፍርድ ቤት ስራዎች ላይ ጣልቃ ሲገባ አይታይም ነበር፡፡ ደርግ ግፍም ሆነ እስር ይፈጽም የነበረው በግልጽ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቶችን የግፍ መፈጸሚያ መሳሪያ አላደረገም ነበር፡፡ 

አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1995 ላይ ከወጣው ህገመንግስት መሰረት በፌዴራልና ክልላዊ መንግስት ደረጃ ባለሶስት ጎማ የህግ ስርዓት ቆሟል እነኚህም የፌዴራል የጀመሪያ ፍርድ ቤት፣የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣የፌዴራል ሱፕሪም ፍርድ ቤት ናቸው፡፡ (the Federal First Instance Courts, the Federal High Court and the Federal Supreme Court,) በወረቀት ላይ እንደተቀመጠው ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ትከተላለች፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ወይም በህገመንግስቱ አንቀጽ 78(1)፣79(2)፣79(3)፣ እና 79(4) በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም የዳኞች አሰያየም አጠያያቂ ነው፡፡ ዳኞች የሚሾሙት ስልጣኑን በጨበጠው ፓርቲ የህግ አስፈጻሚዎች ይሁንታ ነው፡፡ ዳኞች የሚመረጡት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ፓርቲ በተቆጣጠረው ገዢው ቡድን ይሁንታ ነው፡፡ በህግ ተቋማት ውስጥ የፖለቲካ ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት በየግዜው እንደሚታይ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሌላው የፍርድ ቤቶች ምሉሄ በኩልሄ የሆነ ነጻነት እንዳይኖራቸው ካደረጉት ምክንቶች አንዱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገመንግስት ክርክር ላይ ለሚነሱ ክሶች የመተርጎም ስልጣን ስለተሰጠው ነው፡፡ እንደ ኬኒያ ባሉ ሀገራት የሚገኙ ከፍተኛ የፍርድ ቤቶች ህገመንግስት የመተርጎም ስልጣን ስለተሰጠው ከኢትዮጵያ የፍትህ አካላት የተሻለ ነጻነት አላቸው፡፡

በነገራችን ላይ አሁን ባለው የህግ ስርዓት ላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ በዛሬው ዘመን ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ጉዳዮች ወይም ክርክሮች እንደሚካሄዱባቸው መድረኮች እየተቆጠሩ ይገኛሉ፡፡ ህብረተሰቡ ፍትህን ለማግኘት ብዙ ወጣውረዶች አሉበት፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ማወቅ ወይም መገንዘብ ያለብን ቁምነገር ቢኖር የህግ አውጭው የሚቆጣጠረው ወይም ጣልቃ የሚገባበት የፍርድ ስርአት ነጻነቱ የተጠበቀ አይሆንም፡፡ በእንዲህ አይነት የፍትህ ስርዓት ማለትም የህግ አውጭው ጣልቃ ገብነት ያልተለየው ፍትህ እንዲያሰፍን መጠበቅ ተላላነት ነው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ፣ነጻነቱ የተጠበቀ፣ከሙስና ባህል የጸዱና የሞራል ስብእና በተላበሱ ዳኞች የተሞላ የፍርድ ስርዓት እውን መሆን አለበት፡፡

እርግጥ ነው ይገባኛል ዴሞክራሲ በአንድ ሀገር ላይ ሙልሄበክሉሄ በሆነ ሁኔታ እውን እንዲሆን ከተፈለገ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የህግ የበላይነት፣የግለሰብና ሲቪል መብቶች፣ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ወዘተ መከበር አለባቸው፡፡ እነኚህን መብቶቻችንን ማስከበር ከሆነልን የፍትህ አካላቱን ነጻነቱን ለማስጠበቅ በሚደረገው ሂደት ሁነኛ ሚና እንጫወታለን፡፡ በሌላ በኩል ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እውን ሊሆን የሚቻለው የህግ የበላይነት ሲከበር ነው፡፡ በአጠቃላይ የፍትህ ስርአቱ ነጻነት አስፈላጊነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዴሞክራሲ እንዲጎመራ የሚረዳ በመሆኑ ግዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡

Filed in: Amharic