ብልፅግና በራሱ ብልግና ከህዉሀት ጫማ ስር ወድቋል …
አርቲስት ዝናብዙ ፀጋዬ
*…. ብልፅግና ኢትዮጵያን ለመምራት በህዝብ የተሰጠዉን አደራ ትቶ ተራ የጎሳ ቅርጫት ዉስጥ ወድቋል። ዛሬ ብልፅግና የዘር ልክፍተኞች የክፋት ቅርሻታቸዉን የሚተፉበት ገንዳ ነዉ።
አብይ አህመድ ወደስልጣን ሲመጣ ከህዉሀት ጋር የነበረዉ ንፅፅር የዝሆንና የእንቁራሪት ያክል የተራራቀ ነበር፣ ህወሓት በዛን ግዜ ዝሆንን ለማከል የምትንጠራራ እንቁራሪት ነበረች።የዛሬዉን አያደርገዉና በዛን ግዜ የህወሓት መሪዎች ከመርከብ እስከ ፋብሪካ ከ መሬት እስከ ግድብ መዋጮ ቀርጥፈዉ የበሉ ሌቦች ነበሩ።
በተቃራኒዉ የጅማዉ ጎልማሳ አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ፀበኛ ሀገሮችን ያስተቃቀፈ፣ ሌቦችን ባደባባይ ጅብ ብሎ ያዋረደ ፣ስለ ምስኪን ኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ደፍሮ የተናገረ ፤የበደልንዉ እኛ ነበርን ብሎ ህዝብን ባደባባይ ይቅርታ የጠየቀ ሙሉ ሰዉ ነበረ፣ ህወሃት በወቅቱ የሰራዉ የ 27 ዓመት ነዉር ከቁንጫ አሳንሰሶት አንድ ሆቴል ዉሰጥ የተወሸቀ የወንጀለኛ ስብስብ ሲሆን አብይ አህመድ ባንፃሩ ከመስቀል አደባባይ ታሪካዊ ሰልፍ እስከ ኖርዌይ ኦስሎ የኖቬል ሸልማት የክብር ካባ የደረበ ብርቅዬ መሪ ነበረ።
ግን ምን ያደርጋል በክብር ላይ ክብር በአጭር ግዜ ደርቦ አስገርሞን ሳናበቃ ከነበረበት የክብር ማማ ራሱን ወደ ነዉረኞች የቆሻሻ ቅርጫት ጥሎ አስደመመንና አረፈዉ እንጂ።
በፓለቲካ አቋማቸዉና ብሄራቸዉ ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ጥፍራቸዉ ተነቅሎ ተሰቃይተዋል ፣ሴቶች በባለዬ መርማሪዎቾ ተደፍረዋል፣ ወንዶች በብልታቸዉ ለይ ሀላንድ ተንጠልጥሎ ተበድለዋል፣ እናቶች በጨለማ ቤት ስለታሰሩት ዉድ ልጆቻቸዉ አመታትን አንብተዋል በማለት አዝኖ ባሳዘነን ማግስት እናትን ባደባባይ በልጆቿ ፊት የሚደፍር ፣ከተማን ሙሉ በሙሉ የሚያቃጥል፣ ክቡሩን የሰዉ ልጅ ዘቅዝቆ የሚሰቅል ፣ተማሪ ልጃገረዶችን አግቶ የሚሸልል የ 21ኛዉ ክፍለዘመን ሰዉ መሰል አዉሬ አዝምቶ ልባችንን ሰበረዉ እንጂ።
አሁን ብልፅግናም ሆነ ህዉሀት እኩል ናቸዉ።አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ ብልፅግናን ደግፎ ህወሃትን የሚነቅፍበት አንዳች ምክንያት የለም ። ህዉሀት የትግራይ ህዝብን ነፃ ለማዉጣት የሚሮጥ ፈረስ ነዉ።ብልፅግናም የኦሮሞ የበላይነትን ለመጫን የሚሸመጥጥ ጋሪ ነዉ።ሁለቱም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ትዉዉቅ የላቸዉም፣ የሁለቱ ፀብ የስልጣን እንጂ የግብር ልዩነት አይደም።
ብልፅግና ኢትዮጵያን ለመምራት በህዝብ የተሰጠዉን አደራ ትቶ ተራ የጎሳ ቅርጫት ዉስጥ ወድቋል። ዛሬ ብልፅግና የዘር ልክፍተኞች የክፋት ቅርሻታቸዉን የሚተፉበት ገንዳ ነዉ።
የዛሬው ብልፅግና ሽመልስ አንዴ ሰበርናቸዉ ሌላ ግዜ ቁማር በላናቸዉ እያለ የሚያላዝንበት፣ አንድ የአንቦ ዘረኛ ካድሬ የአዲስ አበባን 90ሺ ኮንዶሚኒየም እንደ ዝክር ዳቦ ለወገኖቹ የሚያድልበት ፣ ሰዉ ሲታረድ ገጀራ አቀባይ ፓሊስ የተፈጠረበት ከህወሓትም የባሰ ዘረኛ ድርጅት ነዉ።
ለዚህ ደግሞ ዋና ተጠያቂዉ ከትላልቅ ሀገራዊ እሳቤ ወደ መንደር ቁማርተኝነት ራሳቸዉን የጣሉት የብልፅግና ጥሬ ፓለቲከኞች መሆናቸዉ ሊታወቅ ይገባል።