>
5:21 pm - Wednesday July 20, 2507

ይድረስ  ለዝናብ አዝናቢው ጠቅላይ?! (ዘምሳሌ )

ይድረስ  ለዝናብ አዝናቢው ጠቅላይ?!

 

እስኪ ልጠይቅህ

የምታዘንበው ዝናብ  ውኃ ነው  ወይ ስቃይ

በኢትዮጵያ ምድር  ጥይት  በህዝብ ላይ

ስንቱ ቤት ፈረሰ ልጆች ወላጅ አጡ

ሴቶች ተደፈሩ ቀሩ እንደወጡ

እርሱ አልበቃ ብሎ በችጋር ተቀጡ

በዘር ተለይተው ወንዶች ህይወት አጡ

ተቃዋሚዎችን እያሰርክ ስትፈታ

ያሰጉህን  ስትገል   በየሁሉ ቦታ

የህዝብ እድል ሰብረህ በሀሰት ይቅርታ

ምርጫን አጭበርብረህ  በወንጀል  ስትረታ

ሀያሰባቱ አመት አልበቃ ስላለህ

ማለያ  ቀይረህ  ብልፅግና ብለህ

ሀገር  እስኪጠፋ  ልጆቿን ከፋፍለህ

በሥልጣን መከታ  መከራ አብዝተህ

በወያኔ  ኦነግ  ሀገር  ህዝብ  ሲፈርስ

ቤተሰብ ሲበተን  በግፍም  ሰው ሲያለቅስ

አንተ በእርዳታ ብር  ዘወትር ስትደግስ

ደናቁርት ከርሳሙ  ስርህ ሲልከሰከስ

ትንሽ የማይገድህ  የሌጊዎን አዛዥ

የኢትዮጵያን ልጆች በቁማቸው ገናዥ

እንዳተ ያለውን መርዝ ንፁሀን አሳሪ

ስብእና የለሽ  አምባገነን  መሪ

በኢትዮጵያውያን ትግል ወተህ እድል ቀንቶህ

በዘረኞች ገነህ ስልጣንን ተረክበህ

የገባኸው ኪዳን ለመላው ኢትዮጵያ

ዛሬን  ስናስበው የሆንከው ማፈሪያ

ላሻግራችሁ  ስትል አደባባይ ወጥተህ

የዋሾዎች ጥበብ ተንኮልን ተመልተህ

ቀሳውስት ኢማሙን ፈጣሪ አስረስተህ

ማውገዝ ተስኖአቸው  የፊጥኝ ቀርምደህ

አንተን የደገፉ  የህሊና አይን አጥተው

እርጉማን ምሁራን በዘር ተመርዘው

ሀገሪቱን ቁልቁል ለመክተት ተቻኩለው

ሲያመልኩህ እንደጣኦት ነውራቸውን ይዘው

ቀናት ተቆጠሩ አመታት ታጀሉ

ጉድና ጅራትህ  ባገር እዳ ሞሉ

ተንኮል ምግባሮችህ ሀገር አቃጠሉ

እርሱ አልበቃ ብሎህ ስንቶች ተገደሉ

በሰሜን በደቡብ ምስራቅና ምዕራብ

ሀገሬ ነው ያለ በዘር ሲለበለብ

በእምነት  ደጃፎችም  የእሳት  ዶፍ ሲዘንብ

ገና ይቃጠላል  ስትል ስንታዘብ

እሾህ ምላስህን በመርዝህ ተብትበህ

ቂሎች ሲከተሉህ በሀሰት አታለህ

ህዝቡን አፈናቅለህ ስንቶችን አስርበህ

የሞቱት ኢትዮጵያውያን  በገዛ ተንኮልህ

መላው አባላትህ በዘር የሰከረ

ሀገር የማይገደው ለሆዱ ያደረ

ሴራ እየሸረበ ህዝብ እያሸበረ

የሚኖር ካንተጋር  ቀን እየቆጠረ

የምትመራው  ጦር ለሀገር ካልሆነ

በደርግም አይተናል ስንቱ እንደተነነ

በወያኔም  ደርሷል  አጋዚ እንደጎነ

አይቀር ትወርዳለህ  ህዝብ  ከባነነ

ላስታውስህ ይህን ቃል ለምድር ወሰማይ

በቀረ ዘመንህ  አትሁን  ዋሾ አታላይ

መውረድህ አይቀርም በዝቷል የህዝብ ስቃይ

ጊዜ እንደሁ የለህም የማትሰማ  ድንጋይ

መምራት የማትችል  የሌጊዎን ጠቅላይ

መነቀልህ አይቀርም ከኢትጵያ ምድር ላይ !!!

ዘምሳሌ 

 

Filed in: Amharic