>

ልጆቿን እዬበላች የማትጠግብ ሀገር (አገሬ አዲስ)

ልጆቿን እዬበላች የማትጠግብ ሀገር

  አገሬ አዲስ    


                           

በተለምዶ አባባል የራባት ድመት ልጇን ትበላለች ሲባል እንጂ ሃገር ልጇን ትበላለች ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም።እርሃብ ክፉ ነው፤ክፉ ነገርም ያሠራል።ምሳሌው በድመት ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሰው ልጆችም በተግባር የሚፈጸም መሆኑን በቅርቡ በአገራችን ውስጥ የልጅ ኩላሊት ወጥቶ ሲበላ አይተናል።በዚችው አገራችን የሚኖር ትኩስ ሬሳም የሚበላ ማህበረሰብም መኖሩ ምንም እንኳን በይፋ ባይወጣም የሚያውቁ ይናገራሉ።ይህ ሁሉ የሚፈልጉትን ጤነኛና ተገቢ ምግብ ከማጣትና ከመራብ፣በችግር አስገዳጅነት የተነሳ የሚፈጸም ዘግናኝ ድርጊት ነው።አድራጊው ግን ስለለመደውና ምርጫም ስለሌለው እንደ በጎ ሥራ ይመለከተዋል፤እንደ መልካም ባህልም ይቆጥረዋል። ከዚህ የአውሬ ድርጊት ለመመለስ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ጤነኛና መልካም ምግብ እንዲመገብ እንደሰው እንዲኖርና እንዲያስብ ማብቃት ተገቢ ነው።ፍላጎቱና ጥያቄው ካልተመለሰ ሰው ሰውን መብላቱ ሊቆም አይችልም።

ድርጊቱ ሰለጠነ በተባለው ዓለም የሚኖሩትንም ሰዎች ያካተተ ሆኗል።ከሃምሳ ዓመት በፊት በኦክቶበር 13 ዐን 1972 ዓም የኡራጉዋይ የረግቢ ቡድን ተጫዋቾች ለውድድር ወደ ቺሊ  የሚጓዙበት አውሮፕላን ተከስክሶ በተራራማና በበረዷማ ቦታ ሲወድቅ ብዙዎቹ ሲሞቱ ጥቂቶቹ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ከሞት ለመትረፍ ችለው ነበር።በዚህ ከግንኙነት መረብ በራቀ አስቸጋሪ ከባቢ ለተወሰነ ቀናት የቆዩት ቁስለኞች ምንም እንኳን ነፍሳቸው ባትወጣም በሞትና በመኖር መካከል ላይ ነበሩ።ሁኔታቸውን የከፋ ያደረገው ደግሞ ለቀናት ምግብ ሳይበሉ መቆየታቸው ነበር።በዚህ አስከፊ hሁኔታ ላይ እርሃብ ሲጨመርበት የገጠማቸው ፈተና  የለመዱትንና የነበራቸውን ሰብአዊ ሞራልና ስነምግባር እንዲሁም የአመጋገብ ልምድና የምግብ ምርጫ እንዲረሱትና በሚፈሩትና በሚጠዬፉት ድርጊት ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል።ያም ከሞቱት ጓደኞቻቸው የሰውነት ክፍል ቆርጠው መብላት ነበር።እርሃብን አሸንፎ ለመቆዬት ሲሉ ያደረጉት ለሰሚው የሚከብድ ድርጊት የቁስለኞቹን ህይወት አትርፎ ለመኖር እረድቷቸዋል።እንዲህ አይነቱ ድርጊት የሰውን ልጅ ገድሎ ከመብላት ከካኒባሊዝም የተለዬ ቢሆንም ለመቀበል ይከብዳል።ታሪኩን ያነሳሁት  እርሃብ ምን ያህል የሰውን ልጅ ወደ ማይፈልገው ድርጊት ሊመራው እንደሚችል  ለማሳዬት ነው።በማጣትና በመራብ የተነሳ ሰው ገሎ የመብላቱ ነገር ግን ወንጀል ከመሆኑም በላይ ማጣት የሰውን ልጅ ህሊና ነስቶ   ወደ አውሬነት ሊለውጠው እንደሚችል ያሳዬናል።

ይህንን እንደ ዋቢ አድርገን ወደተነሳሁበት ርዕስ ስመለስ አገርም ተገቢውን አገራዊ ቁመና ስታጣና የነዋሪዎቿ መብት ሲረገጥ፣የዴሞክራሲ እርሃቧ ሲጠና ለለውጥ የሚሰለፉ ልጆቿን እንክት አድርጋ እንደምትበላ ያለፉት ሃምሳ ዓመት ታሪኳና ታሪካችን ያሳያል።አገር አፍ አውጥታ የልጆቿን ሥጋ ባትበላም ብዙ ልጆቿን በመቃብር ሆድቃዋ/ዋሻዋ መዋጧን ታዝበናል። በእሷ መንፈስና ስም የራሷ ልጆች የሆኑት ሌላውን ልጆቿን ሲገሉ፣ሲያሳድዱና መከራ ሲያሳዩ በአርምሞ ተቀብላለች።ለዴሞክራሲና ለለውጥ እርሃቧ ማስታገሻ የሚሆን በብዙ አማራጮች የታጀበ የተሻለ ሥርዓት አቅርቦ ማስፈን ተስኗት በአንድ ነጠላ ፈላጭ ቆራጭ በሆነ አመለካከት ብቻ እዬተሽከረከረች ብዙዎቹ ሲሞቱባትና ሲቀበሩባት  ሃገርእንደ ድመቷ ተርባ  ልጆቿን እዬበላች መኖሯን የሚያሳይ ነው። ሃገር ስንልም ሕዝቧ ስለሆነ በሕዝቧ መካከል የሚከናወነው መልካምም ሆነ መጥፎ፣አኩሪም ሆነ አሳፋሪ ድርጊት ሃገርን ያሶድሳል ወይም ያሶቅሳል።

ለአለፉት ሃምሳ ዓመታት ተራ በተራ በትረመንግሥቱን በጨበጡ ጉልበተኞች በሰፈነ ሥርዓት ሥር ስትንከባለል የኖረችው ኢትዮጵያ የሚፈጸመው ሁሉ በስሟ ስለሆነ የምትታወቀው ስርዓቶቹ በፈጸሙት ተግባርና በደረሰባት ስብራት ወይም በሕዝቧ ኑሮና ግንኙነት ላይ በደረሰው ቀውስ ና ልዩነቶች ነው።አገር ሕዝቧንና መሪዎቿን ትመስላለችና!

የአገሪቷን ፍላጎትና እርሃብ የተረዱት ልጆቿ የሚያነሱት ጥያቄና የሚሰጡት መልስ በተግባር ካልተተረጎመ አገር ልጆቿን እዬበላችና እያባለች መኖሯ ይቀጥላል፤በይና ተበይም ይኖራል።በመጨረሻም እራሷን በልታ ማለትም ፈራርሳ ትወድቃለች።ለዚያ መንደርደሪያ የሚሆነው ላለፉት 31 ዓመታት እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ የሰፈነባት የጎሳ ስርዓት ነው።ይህንን  ስርዓት መለወጥና ማሶገድ ተገቢ ነው።አገር በህይወትና በጤና አቋም እንድትኖር የሚያስቡላት ልጆቿ የሚያቀርቡላትን የዲሞክራሲ  ምግብ መመገብ አለባት።

የምግቡ ዓይነቱና ዝርዝርም ከሃምሳ ዓመት በፊትና በዃላ ይቀርቡ የነበሩት ጥያቄዎች ናቸው።እነሱም

ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣

የዴሞክራሲ መብቶች ማለትም፣ የመጻፍና የመናገር፣የመሰብሰብ፣የመንቀፍና የመደገፍ ፣የመምረጥና የመመረጥ መብቶች ይከበሩ 

መሬት ላራሹ ማለትም መሬት ለሚጠቀምባት ዜጋ ሁሉ ትሁን፣ 

መንግሥት በምርጫ እንጂ በጠበንጃ የሚወጣና የሚወርድበት መንገድ በሕግ ይታገድ፣

ሕገመንግሥት በሕዝቡና ለሕዝቡ  ጥቅም  ይዋል፣ ከመንግሥትና ከድርጅት በላይ መሆኑ ይታወቅ፣

መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ እንጂ እንዳሻው የሚፈነጭ አዛዥና ፈላጭ ቆራጭ አይሁን፣ 

የሕዝቡ እኩልነት ይከበር፣የጾታ፣የሃይማኖትና የጎሳ  ልዩነት አይኑር፣ 

ሕዝብ የአገሩ ባለቤት፣የተፈጥሮ ሃብቱና ንብረቱ ጌታ መሆኑ ይከበር፣ በፈለገውና በመረጠው ቦታ ሄዶ ሰርቶ የመኖር መብቱ ይታወቅ፣

የጎሳ ፖለቲካና የጎሰኞች ሥርዓት ይወገድ፣

አገር እንደ ቀድሞው በተሻሻለ መልክ በክፍለሃገር ደረጃ ይዋቀር፣ የክልል ጎሰኛ አስተዳደር ይፍረስ፣ 

የኢትዮጵያ አንድነትና ዳር ድንበር ይከበር፣

መከላከያ የአገር ዳር ድንበር አስከባሪ፣  እንጂ የድርጅትና የግለሰብ ዘበኛ አይሁን፣

በአገርና በሕዝብ ላይ ወንጀል የፈጸሙ ለሕግ ይቅረቡ፣

እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ሰላምና እድገት ለተራበችው አገራችን የሚረዱ የዴሞክራሲ ምግቦች ናቸው እላለሁ።ለእነዚህም ዴሞክራሲያዊ ያገር ምግቦች አያሌ ወጣቶች የህይወት ዋጋ ከፍለውበታል።, በምክክር ኮሚቴው ማድቤት ውስጥ ተሸክነው ለፍጆታ ቢቀርቡ ኢትዮጵያ ልጆቿን እዬበላች ከመኖር ድና እያበላች ለማኖር ትችላለች ብዬ አምናለሁ።የሕዝቡ ጥያቄ እነዚህ እንጂ እንደ አውሬ አንዱ ሌላውን ለመብላት አሁን እንደሚታዬው በጎሳ ተከፋፍሎ የመገዳደልና  በጠላትነት መተያዬት አይደለም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።ሕዝቡ ከስርዓቱ ጋር እንጂ የእርስ በርስ ጥላቻና ግጭት አልነበረውም ፣አሁንም የለውም።ጎሳና ሃይማኖት ሳይለዬው በአንድ አገር ዜግነት ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ ሕዝብ ነው።እዬኖረም ነው።ክፍለሃገር ጠፍቶ በጎሳ አጥር ውስጥ ብቻዬን  በክልል በረት ውስጥ ልኑር ብሎም የጠዬቀበት አንድም ወቅት የለም።የሚለያዩት ክፉዎች ከጠፉለት  ለወደፊቱም በአንድነትና በሰላም  ለመኖር አያዳግተውም።እንዳይኖር የሚያደርጉት እራስ ወዳዶችና  በደካማ ጎኑ እዬገቡ በመቀስቀስ አንድነቱ እንዲላላና ለሃገሩ እንዳይቆም በማድረግ  አገራችንን ለባዕዳን አሳልፈው ለመስጠት የተሰለፉ ባንዳዎች ናቸው።

የሕዝቡን የዓላማና የፍላጎት ትስስር የሚያሳዬን የታሪክ ምስክር  ከላይ የዘረዘርኳቸው የዬካቲቱ 1966 አገር አቀፍ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የቀረቡትና አሁንም በመቅረብ ላይ ያሉ  ጥያቄዎች ናቸው። እኔም በተሳተፍኩበት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋናቸው ፊት ቀርበን የተነበበውና የተሰጣቸው በእኔ የተጻፈ  11 ጥያቄዎችን የያዘ ደብዳቤ እነዚህኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ያካተተ ነበር። የሰነዱም ኮፒ በእጄ ይገኛል።ላለፉት አርባ ስምንት ዓመቶች አብሮኝ ሲንከራተት የኖረው ይህ ሰነድ የሕዝቡ እውነተኛ ጥያቄ ምን  እንደነበር  ያረጋግጣል፤ለአሁኑም መፍትሔ ፍለጋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ።ለታሪክ ትምህርትም ይረዳል እላለሁ።ፊትም ሆነ አሁን የሕዝቡ ጥያቄዎች አንድ አይነት ናቸው፤መልስ ይፈልጋሉ።የተጨመረው ቢኖር ከሰላሳ ዓመት ወዲህ የሰፈነውን የጎሰኞች ስርዓት የሚመለከተው ጥያቄ ብቻ ነው።ጥያቄዎቹ መልስ ካላገኙ በተያዘው የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ጉዞ ስንኳትን ከኖርን፣አጥፍቶ በመጥፋትና በመበላላት አባዜ ውስጥ እንደተነከርን እንኖራለን። አገራችንም የደስታ ኑሮ የሚኖሩባት ሳትሆን በግፍ የሚገደሉትን፣በርሃብና ቸነፈር የሚያልቁትን ልጆቿን እዬዋጠች የማትጠግብ የብዙዎች ከርሰመቃብር ሆና ትቀጥላለች። 

አገራችንን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት እንተባበር፣የዬካቲቱን መንፈስ እንላበስ!

ጎሰኝነትና የጎሳ ስርዓት ይወገድ፤ሕዝባዊ ና ፍትሃዊ ሥርዓት ይስፈን!!

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!

 

Filed in: Amharic