>

ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ዋርካ ወደቀ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ዋርካ ወደቀ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

 

የአንኮበሩ ሰው

ውልደትና የቤተሰባቸው ዳራ

ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ፣ መጋቢት 2 ቀን 1928 ዓ.ም በአንኮበር ውስጥ በምትገኝ አፈርባይኔ በምትባል መንደር ከአባታቸው ከመምህር ራስወርቅ ወልደመስቀል ማናውቆና ከእናታቸው ከወይዘሮ አስከለ ማሪያም ገ/ ጊዮርጊስ ንጉሴ ተወለዱ። 

አባታቸው መምህር ራስ ወርቅ፣ ከአባ ወልደ መስቀል ማናውቆና ከእመት አጫወቱኝ መስከረም 14 ቀን 1879 ዓ ም በጅሩ ቆላ ሺማ ወረዳ ተወልደው በጥቅምት 7 ቀን 1954 ዓም አዲስ አበባ ላይ ያረፉ ናቸው። የማናውቆ አባት አለቃ ወልደ ሥላሴ በሽዋው ንጉስ ሳህለ ስላሴ የተመሰረተውን የአፈርባይኔ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው አስተዳዳሪ ነበሩ።

አባታቸው መምህር ራስወርቅ፣ ከእስክንድርያ ከመጡት አፄ ምኒሊክን መጀመሪያ አንኮበር ላይ በንጉሥነት፤ ከዚያም እንጦጦ ላይ በንጉሠ ነገሥትነት ከቀቡት ከአቡነ ማቲዎስ የድቁና ከዚያም የቅስና ማእረግ ተቀብለዋል።

ኢንጂነር ተረፈ የተወለዱት ውጥንቅጥና ቀውጢ ጊዜ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ረቡዕ መጋቢት 2 ቀን 1928 ዓ ም። እናታቸው አራስ ቤት ሆነው ህጻኑን ተረፈን ሲንከባከቡ በድንገት የጠላት አውሮፕላኖች አንኮበር ላይ የቦምብ ዝናብ ይጥላሉ። ባካባቢው የነበሩት የሳር ክዳን ቤቶች እንደችቦ ይቀጣጠላሉ፡፡ ሕዝቡም ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ይሯሯጣል፤ እንዳይበርድ የለ እሳቱ ይጠፋል፡፡ የተረፈውም ሰው እየፈራ እየቸረ ወደቀዬው ይመለሳል። ቁጥር ሲወሰድ ህጻኑ ተረፈና እናቱ የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ሞተዋል ተብሎ ለቅሶ ይጀመራል፡፡ መምህር ራስወርቅም ወዲያና ወዲህ ፈልጉ እያሉ ይወራጫሉ። በማግስቱ ረፈድ ሲል ሁሉም እረጭ ሲል የተረፈ እናት ተረፈን በጉያቸው አቅፈው ከተደበቁበት ዋሻ ወጥተው ወደመንደራቸው ሲመለሱ በሕይወት በመገኘታቸውን እልልታ ሆነ፡፡ መምህር ተረፈም ልጄ ተረፈልኝ ብለው እግዚአብሔርን አመስግነው ለልጃቸው ተረፈ ብለው ስም አወጡለት፡፡

ትምህርት

ኢንጂነር ሀሁ የቆጠሩት አንኮበር አባታቸው ጉያ ቁጭ ብለው ነበር። የጠላት ጦር እንደወጣ በ1933 ዓ.ም የኢንጂነር ቤተሰብ ወደአዲስ አበባ ተመለሰ። ታዳጊው ተረፈም አንድ ቄስ ትምህርት ቤት መምሬ ሞገስ ዘንድ ገባና ዳዊት ደገመ። ከዚያም ላንድ አመት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተላከና ያንደኛ ክፍሌን አጠናቅቆ ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተዛወረ። 

ታዳጊው ተረፈ ፣ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤትን በጣም ወደደው። ቤታቸውና ትምህርት ቤቱን አጥር ነበር የሚለየው። በዘመኑ በአገሩ ውስጥ ትልቅ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነበር። ካንድ ሺህ ተማሪዎች በላይ ነበሩት። የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ቅርብ ስለነበር ጃንሆይ በየጊዜው እነ ተረፈን ይጎበኙ ነበር። ይህም ዘወትራዊ ጉብኝት ተማሪዎቹንና መምህራኑን ያስደስታቸውና ያበረታታቸው ነበር።

በወቅቱ ከኢትዮጵያውያን አስተማሪዎች ጋር የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪና መምህራኖቹ ከካናዳ የመጡ ፈረንሳይ ተናጋሪ ኢየሱሳውያን የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ነበሩ። ከሶስተኛ ክፍል ጀምሮ ታዳጊ ወጣት ተረፈን የሚያሰተምሩት የውጭ አገር ተወላጅ አስተማሪዎች ነበሩ። 

ኢንጂነር በአንድ ወቅት በልጅነታቸው ስለነበረው የቦይ ስካውት ተጠይቀው እንዲህ ብለው ነበር‹‹ ‹‹….በሕይወቴ ላይ ዘላቂ ለውጥ ያመጣው የቦይ ስካውት ተቋም ነው። የስካውትነት መሀላውን በአንክሮ ተቀብዬ በእርሱም መንፈስ የቀን ተቀን ኑሮዬ መርህ እንዲሆን አደረኩት። በጠባይና ባስተሳሰቤ ላይ ዘላቂ ለውጥ አምጥተውልኛል።በአጠቃላይም ጎበዝና ትጉህ ተማሪ ነበርኩ። በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሥራዬ ከአንድ እስከ አምስት በመውጣት በጥሩ ውጤት አልፌአለሁ።›› ብለው ነበር፡፡

በመስከረም ወር 1947 ዓ.ም ኢንጂነር ተረፈ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደጅ ረገጡ። ስማቸውን በሳይንስ ክፍል ሲያስመዘግቡ ልጁ ሁሉ አብደሃል ወይ ብሎ ታዘባቸው። ምክንያቱም ከተፈሪ መኮንን የሚመጡ ልጆች እንደሌሎቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ንጹህ ኬሚስትሪና ንጹህን ፊዚክስ በመውሰድ ፈንታ ጠቅላላ ሳይንስ ስለሚማሩ የኮሌጅ ሳይንስ ይከብዳቸዋል ይባል ስለነበረ ነው። እንደሚባለውም ብዙ የቲኤምኤስ ተማሪዎች ወደአርትስ ክፍል ይገቡና አስተማሪነት ሕግ ወዘተ መማር ይመርጡ ነበር።

እንደአጋጣሚ ሆኖ ኢንጂነር ኮሌጅ ውስጥ እንደገቡ የመጀመርያው የኬሚስትሪ ፈተና በጣም ቀላል ስለ ነበረ ውጤቱ ሲለቀቅ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ አገኙ። ይህ ውጤት ግሩም ተባለ። ወሬውም ወደ ቲኤምኤስ ተዛመተ፡፡ ወጣቱ ተረፈም፣ የእችላለሁ መንፈስ ውስጡ ስላደረ የትምህርቴን ዘመን ያለችግርና በራስ መተማመን ለማለፍ በቃ።

ኢንጂነር ተረፈ፣ ኮሌጅ ውስጥ ሳሉ በብዙ ተጓዳኝ ስራዎች ውስጥ ተካፋይ ነበሩ።የኮሌጁ የሶፍት ቦል ቲም ካፒቴን ነበሩ። እንዲሁም በጥንታዊ ባሕላዊ ማህበረ ጥናት ላይም ይካፈሉ ነበር፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በ1949 ዓ. ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ንጉሠ ነገስቱ በሚገኙበት ለአገራችን የትኛው ትምህርት ይበልጥ ይበጃል? በሚል ርእስ ኮሌጁ አንድ የአደባባይ ሙግት አዘጋጅቶ ነበር። ሙግቱም ለአገራችን በጣም የሚጠቅመው ትምህርት ሕግ ወይስ ህክምና ወይስ መሐንዲስነት ወዘተ የሚል ነበር። ኢንጂነር መሐንዲስነት ነው የሚለውን መስመር ሲይዙ ተስፋዬ ገሰሰ ሕግ ይሻላል ብሎ ተነሳ፡፡ ስብሀት ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ አስተማሪነት ይበልጣል ብሎ ተከራከረ። ኢንጂነር አንደኛው መከራከርያቸው ለመሐንዲስ ሥራ የሚያስፈልጉትን የደን ውጤቶች መንከባከብ ያስፈልጋል የሚል ሲሆን የሚገርመው ግርማዊነታቸው ተረፈ ሲናገር ማስታወሻ ይወስዱ ነበር፡፡ 

በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በሳይንስ ዘርፍ ሙሉ የዲግሪ ፕሮግራም ስላልነበረው ከ 3 አመት ትምህርት በኋላ በመንግስት ወጭ ወደ ፈረንጅ አገር ተማሪዎች ይላኩ ነበር። በዚህም መሰረት፣ ኢንጂነር ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ወደ ትሮይ ኒውዮርክ ስቴት ተላኩ።

በነበረው ልማድ መሰረት ተማሪዎች ወደውጭ አገር ሲላኩ ንጉሠ ነግሥቱ ጋር ቀርበው መሰናበትና አባታዊ ምክር ይሰጣቸው ነበር። ተሰናባች ተማሪዎች ግርማዊነታቸውን የተሰናበቱት በደብረ ዘይት ቤተ መንግስታቸው ነበር። ጃንሆይም ጥሩ አቀባበል ካደረጉ በኋላ ሀገራችሁን ተመልሳችሁ አገልግሉ ሲሉ አደራ ሰጡ፡፡ 

የሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩትት (አርፒአይ) ትምህርትና ኑሮ

በ1950 ዓም ነሐሴ ወር ኢንጂነር አዲስ አበባን ለቅቀው ወደ አሜሪካ ለመሄድ ተነሱ። 

በመጀመሪያ ኢንጂነርና ጓደኛቸው ማህዲ በኤሌክትሪክ መሐንዲስነት መማሪያ ዋና ክፍል ተመዘቡ። ትምህርቱም በጣም ከባድ ሆኖ አገኙት፡፡ 

ኢንጂነር፣ በአንድ ወቅት ስለ አሜሪካ ትምህርታቸው ሲያወሱ እንዲህ ብለው ነበር‹‹…ተማሪዎቹም በወዳጅነት መፍጠር በኩል ከአስተማሪዎቹ አይሻሉም። ለምሳሌ እኔ ወይም ማህዲ አንድ 300 ሰው በሚይዝ አዳራሽ ውሰጥ ቀድመን አንዱ 15 ሰው በሚይዝ ረድፍ ላይ ቁጭ ስንል አዳራሹ ሞልቶ ከፊታችንም ከኋላችንም ያሉት ረድፎች ቢሞሉ እኛ ረድፍ ላይ አንድም ነጭ ተማሪ አይቀመጥም ነበር። ይህ ሁናቴ በጣም ያስጨንቅ ነበር።ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማህዲ ይህን ሁናቴ መቀበል ስላቃተው የኤሌክትሪክ መሐንዲስነት ትምህርት ክፍሉን ለቅቆ ወደጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ተዛወረና የበለጠ ደስተኛ ሆነ። እኔ ግን ያደረጉኝን ያርጉኝ ብዬ ጥርሴን ነክሼ ቀጠልኩ። በቀን መአት ሰአት ጥናቴ ላይ አሳልፍ ነበር። ከሁሉም የሚከፋው የቤተ- ተሞክሮ ጊዜ ሥራ ነበር። ምክንያቱም የዚህ አይነት ጥናት ሁለት በሁለት ሆኖ ተመራርጦ ነበር የሚሰራው። እኔን ግን ማን መርጦኝ? ብቻዬን ስታገል አስተማሪው ሲያየኝ በዚያን ቀን ያልመጣውን ተማሪ በሚመጣ ጊዜ ከእኔ ጋር እንዲሰራ ይመድበዋል። በተባለው ቀን ተማሪው ሲመጣ እኔ ቦታው ላይ ቆሜ ሲያገኘኝ አብሮ ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆኑን ያላንዳች አፍረት ገልጾ ጥሎ ይሄድ ነበር። በዚህም ምክንያት ብቻዬን እፍጨረጨር ነበር። ምንም ያንጊዜ ብናደድና ብራገም አሁን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳጤነው የመንፈስ ጥንካሬ ያልበገርነት ባይነት ትምህርት ሰጥቶኝ በማለፉ ተመስገን እላለሁ።›› ብለው ትዝታቸውን አውግተው ነበር፡፡

ኢንጂነር በ1952 ዓ.ም የተሰጣቸውን ክፍለ-ትምህርት ጨርሰው ዲግሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ፡፡ 

በሃያ አምስት ዓመት እድሜ ከባድ ሃላፊነት

ኢንጂኒየር የመጀመሪያ ስራቸውን ቴሌ እንደጀመሩ ሁሉንም ክፍሎች በሚገባ እንዲጎበኙ ነው የተደረገው። ከባህር ማዶም እንደመጡ በሙያቸው ከፍተኛ ተሰሚነት ነበራቸው፡፡ የነበሩትን ክፍሎች ከጎበኙ በኋላ የትራንስሚሽንና የረጅም ርቀት ስርጭት ከሚባል ክፍል በኃላፊነት ተመደቡ፡፡ የ25 ዓመት ወጣት ሳሉ ቴሌ ውስጥ ትልቅ የሚባል ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡ የእድሜ ማነስ አንድም ተጽእኖ ሳይፈጥርባቸው ሥራቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይሞክሩ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ የነበሩት ስዊድኖች አንድን ሰው የሚመዝኑት በእድሜው ሳይሆን በስራ ብቃቱና በአመለካከት ብስለቱ ነው፡፡

እርሳቸው ከውጭ መጥተው ቴሌ በሚሰሩበት ጊዜ የፋክስ ግንኙነት አልነበረም፡፡ አብዛኛው መልእክት ይተላለፍ የነበረው በቴሌግራፍ ነበር፡፡ ኢንጂኒየር ሁኔታውን ሲገልጹ “… በጣም የደነቀኝ የዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ቋንቋ የሚላክ ቴሌግራም ሁሉ በላቲን ፊደል ነበር የሚተየበው፡፡ ለምሳሌ ‘እመጣለሁ’ ለማለት ሲፈለግ emetalehu ተብሎ ነበር የሚጻፈው፡፡” “እንዴት የራሳችን ፊደል እያለን በላቲን ፊደል ይጻፋል ስል ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ለምን በራሳችን ፊደል መጻፍ አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ባነሳም አበረታች መልስ አላገኘሁም፡፡ ‘ፈጽሞ አይቻልም፤ ብዙ ሰዎች ሞክረው ትተውታል’ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር የገጠመኝ፡፡ በኋላም ኦሊቬቲ የተባለ ኩባንያ የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ለመስራት ሞክሮ አልቻለም ሲሉ ሌላ መረጃ አቀበሉኝ፡፡ እኔም ‘በኢትዮጵያ ፊደል ቴሌፕሪንተር’ ሊኖር አይችልም የሚባለውን ተስፋቢስ ዜና ልቀበለው አልቻልኩም፡፡” ይላሉ፡፡

ቴሌፕሪንተርና – ወጣቱ ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ

አሁን ወጣቱ መሃንዲስ ተረፈ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ለመስራት ተነሳስቶ ምርምሩን ጀምሯል፡፡ በወቅቱ ፕሪንተሮቹ ለላቲን ፊደል ነው የተፈጠሩት የሚል ግትር መከራከሪያ ተነስቶ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የላቲን ፊደል 26 ነው፡፡ የአማርኛ ደግሞ 270 ነው፡፡ ታዲያ የመከራከሪያ ሃሳቡ ፕሪንተሩ ለ270 ፊደላት ቦታ የለውም የሚል ነበር፡፡

ኢንጂኒየር፣ ይህ ሃሳብ ሲነገረው ጊዜ ሰጥቶ ምርምሩን ቀጠለበት፡፡ እርሱ ያደረግው ዋናው ጥናትም የኢትዮጵያን ፊደሎች እንዴት ቴሌፕሪንተር ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ኢንጂኒየር ያኔ ለማስተዋል እንደሞከረው የኢትዮጵያ ፊደሎች ቅርጽና ውበት እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ በብዛት 270 ቢሆኑም፣ ቅርጻቸው ግን ከ20 አይበልጥም፡፡ ያኔ እርሱ ለማቅረብ እንደሞከረው የላቲን ፊደሎች 26 ይባሉ እንጂ “ካፒታል ሌተር፤ ስሞል ሌተር” ሲባል ወደ አርባ ይጠጋሉ፡፡ የእኛ ግን ይላሉ የያኔው ወጣት ተመራማሪ “ቅርጹ ሲታይ በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ‘ሀ’ ሲገለበጥ ‘በ’ ይሆናል፡፡ በአናቱ ላይ ዘንግ ሲደረግበት ‘ሰ’ ይሆናል፡፡ ‘ሰ’ ላይ መስመር ሲደረግበት ‘ሸ’ ይሆናል፡፡” በማለት ጥናታዊ ምርምሩን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡

እነዚህን ቅርጾች በማስተካከል ብቻ ቴሌፕሪንተሩን መስራት እንደሚቻል ወጣቱ ተመራማሪ የዛሬ 60 ዓመት አረጋገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ የዚያን ዘመን ቴሌፕሪንተር የፊደላት ድርድር (ኪቦርድ) ቅርጽ ማስተካከል ያዘ፡፡ ማሽኑ ላይ የሚቀረጹት ፊደሎች ቁመታቸውና አቀማመጣቸው ወረቀቱ ላይ የቱ ጋር እንደሚቀመጡ በደንብ ካስተካከለ በኋላ ሲጻፍ ፈጽሞ እንደማያስቸግር በሚገባ አረጋገጠ፡፡

ከዚህ በኋላ ኢንጂኒየር የሄዱበትን መንገድ በራሳቸው እንደሚከተለው ያወጉናል፡፡

የኢንጂኒየር ቴሌፕሪንተር

‹‹……የኪቦርዱን ቅርጽ ካስተካከልኩት በኋላ በዚያን ጊዜ የአዕምሯዊ ንብረት ህግ የፈጠራ ውጤቴን በይፋ አስመዘገብኩ፡፡ በኋላም፣ ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከብኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም መኪናው (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ ሀገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የስራ ተበረታችነት ተሰማኝ፡፡

ወዲያው፣ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ፡፡ በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተ-መንግስት ተደረገ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ በወቅቱ የኤርትራው ገዢ ራስ አስራተ ካሳ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲሰ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር፡፡

ይህ ቴሌፕሪንተር ምንድነው? እንዴት ነው የሚሰራው? ብያኔው ከምን የመጣነው.. የሚል ጥያቄ ግለ-ታሪክ ጸሀፊያቸው አቅርቦ ነበር፡፡.” ግለ-ታሪክ ጸሀፊው ጥያቄውን ሲደረድር ኢንጂነር በእርጋታ ሲያዳምጡት የተሰማው የነጻነት ስሜት ነበር፡፡

“ቴሌፕሪንተር በርቀት የሚያትምና የሚያሰራጭ መሳሪያ ነው” ሲሉ ብያኔውን በአጭሩ አስቀመጡለት፡፡ ቴሌፕሪንተር በዋናነት አንድን መልእክት በመተየብ ለማሰራጨትና ለመቀበል የሚያገለግል መሳሪያ ነው፡፡ ኢንጂነር ሶፍትዌሩን የፈጠሩ ሲሆኑ፤ ሲመንስ ኩባንያ ደግሞ የቴሌፕሪንተሩን ቅርፅ ያወጣው ኩባንያ ነው፡፡ ይሁንና ፊደሎቹ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸውና የቁመታቸውን መጠን በዝርዝር አጥንተው ያቀረቡት እሳቸው ናቸው፡፡ ለስራ ውጤታቸውም በወቅቱ ጠቀም ያለ የገንዘብ ክፍያ ተደርጎላቸዋል፡፡

“የዛሬ 60 ዓመት ኢትዮጵያ የቴሌፕሪንተር ሶፍትዌር የሰራ የሰለጠነ ባለሙያ ነበራት” የሚል ዜና ዛሬ ላይ ቆመን ስንሰማ ውስጣችን የሚጭረው የደስታ ስሜት የላቀ ነው፡፡

ወደጋብቻ ዓለም

ኢንጂነር 60 አመት ወደ ኋላ ተመልሰው ባለቤታቸው ወይዘሮ ብርሀኔ ጋር የተዋወቁበት አጋጣሚ ሲያስረዱ ‹‹…በአይን የወደድኳት ልጅ የ4ኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዳሪ ተማሪ መሆኗን ተረዳሁ። ከዚያም ከሥራ በኋላ ማታ ማታ ብቅ እያልኩ ቡና ሻይ ማለትን ተያያዝኩት። ለሥራም ከከተማ ካልወጣሁ ቅዳሜና እሁዴ ከወይዘሪት ብርሃኔ ጋር ማሳለፍ የዘወትር ዕቅዴ ሆነ።ካንድ ስድስት ወር ትውውቅ በኋላ ነገሩ ወደዘላቂ መንገድ የሚወስድ ስለመሰለኝ መዳፈር ጀመርኩ። 

ሞጆ ከተማ ከመግባቴ በፊት ወደጎን ታጠፍኩና አንድ ውብ የሆነች ድብቅ ቦታ ላይ የወንዙ ፏፏቴ በሚያፏጭበት ስፍራ ወሰድኳትና ኮለል ያለውን ውሃ እየተመለክትን አሸዋው ላይ እግራችንን ዘርግተን ጨዋታችንን ጀመርን። ቀኑ ሞቅ ያለ፤ ሰማዩ ጥልቅ ሰማያዊ አንዳንድ ጠብ ጠብ ያሉ ነጭ ዳመናዎች የሚታዩበት ውብ ቀን ነበር። ያመጣሁበትን ጉዳይ ለመግለጽ ከየት እንደምጀምር ጠፍቶኝ የባጡን የቆጡን መቀበጣጠር ጀመርኩና አይን አይኗን ማየት ቀጠልኩ። እሷ ደግሞ ትክ ብላ እያየችኝ በጥሞና ታዳምጠኝ ነበር። ደቂቃዎቹ እጅግ ረጅም ሆነው አገኘኋቸው ልቤም ዝም ብሎ መደለቅ ቀጠለ…….

የኋላ ኋላ እጇን ግጥም አድርጌ ይዥ ብርሃኔ አስፋው፤ ተረፈ ራስ ወርቅ…. ታገቢኛለሽ ብዬ እጅግ የከበደኝን ጥያቄ አፈረጥኩት…..እርሷ ግን ዝም አለች፤ ደነገጥኩ አልሰማችኝ ይሆን? እምቢ ማለቷ ይሆን? እነኛ ሰኮንዶች ረጅም ዘመን መሰሉኝ፡ ከዚያ ከንፈሯ መነቃነቅ ሲጀምር ትክ ብዬ አይ ነበር፡ 

ለመሆኑ ይህን ሃሳብ ከመቸ ጀምሮ ነው ያጤንከው? አለችኝ ፡ ቶሉ ብዬ መጀመሪያ ካገኘሁሽ ቀን ጀምሮ ነው ስላት፤ እንግዲያውስ እሺ አለችኝ፡ ›› በማለት ትውውቃቸውን አስመልክቶ አስታውሰው ነበር፡፡

. ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅና እና ወይዘሮ ብርሀኔ አስፋው በነሐሴ 20 ቀን 1954 ተጋቡ፡፡

ኢንጂኒየር በጄኔቭ

የዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን አንድነት በ1865 ዓ.ም የተፈጠረ መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ኢንጂኒየር በሄዱበት ዘመን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ክፍል ነበር፡፡ ያኔ የህብረቱ ዋና ጸሐፊ የቱኒዚያው ሚስተር መሐመድ ሚሊ ነበሩ፡፡ ህብረቱ ሰዎችን ሊቀጥር ሲያወዳድር የአፍሪካ ክፍል ክፍት ሲሆንባቸው ለአባል ሀገሮች ሁሉ ክፍት ቦታ መኖሩን አሳወቁ፤ ኢንጂኒየርም ያኔ ነበር ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ለመሆን የበቁት፡፡ የትምህርት ሁኔታውና የሰሩት ሁሉ በሚገባ ታይቶ የህብረቱ ባልደረባ ሊሆኑ ቻሉ፡፡ ከዛም በዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት የአፍሪካ ጉዳይ ክፍል ውስጥ ማገልገል ያዙ፡፡ በጄኔቭ አንድ ብለው የጀመሩት የስራ ዘመን ለ40 ዓመታት ዘልቋል፡፡

እርሳቸው እንደሚያስረዱት የክፍሉ ሥራ አፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ ዕድገት እንድታመጣ ማስቻል ነው፡፡ በህብረቱ ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት የአፍሪካን የቴሌኮም ዕድገት ዕውን ለማድረግ የአቅማቸውን ያህል ሞክረዋል፡፡ የመጀመሪያው የህብረቱ ቀዳሚ ተግባር የቴሌኮምኒኬሽን ማሰልጠኛዎች በየሀገሩ መመስረት ነው፡፡

ሌላው በኢንጂኒየር አመራር ጊዜ የተለወጠው የተለመደው የቅኝ ግዛት የስልክ መስመር መሰበሩ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ነፃም ከወጡ ወዲያ፣ የቴሌፎን የመገናኛ መስመራቸው ከድሮ ቅኝ ገዢያቸው ጋር ስለነበረ በዛ ላይ መስመሩን የሚያስተላልፉት በብራስልስ፣ በፓሪስ፣ በለንደንና በሮም በኩል ስለነበር ቅኝ ገዢዎቹ መረጃውንም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ፓትሪስ ሉሙምባ የተገደለው የስልክ መስመር ተጠልፎ ነው፡፡ የኢንጂኒየር ትልቁ ስኬት የነበረውን የቅኝ ግዛት መስመር መስበር መቻላቸው ነው፡፡

በዚህ መስሪያ ቤት በነበራቸው ቆይታ የበርካታ ሀገራትን የቴሌኮም የዕድገት ደረጃ ለመለየት ችለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል በዚያን ዘመን (በ1981 ዓ.ም ግድም ማለታቸው ነው) የቻይና ቴሌኮምኒኬሽን ከኢትዮጵያም ያነሰ እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በቴሌው ዘርፍ ብዙ መሠራቱን ያምኑበታል፡፡ ሆኖም ግን የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር የብዙ ሰው መነጋገሪያ መሆኑን አግባብነት ይረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል የአገልግሎት ለውጥና፤ የተጠቃሚ መበራከት በአንድ ላይ ሲከሰት እንዲህ አይነት የኔትወርክ መጨናነቅ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ጉዳዮ የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሰጥቶ፤ ተግቶ ጊዜው የሚጠይቀውን አገልግሎት በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት ይጠብቅበታል ይላሉ፡

የአንኮበር ቤተ መንግሥት ሎጅን መሥራት

ኢንጂነር የአንኮበር ሎጅን ለመስራት የወሰኑበትን አጋጣሚ በአንድ ወቅት እንዲህ ተርከው ነበር››

‹‹…..የአንኮበርን ታሪካዊነት በመገንዘብ እፊታችን ደግሞ የወደመውን የታላቁን የንጉሥ ምኒልክን ቤተ መንግሥት ስመለከት ያለፉት መንግሥታት መልሰው ባይሰሩትም እኔ ራሴ እንደገና አሰርቼ ላገሬው ሥራ መፍጠር የቀድሞውንም ታሪክ በመዘከር የጎብኝዎች መስህብ እንዲሆን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ወሰንኩ። አንኮበር ከአዲስ አበባ እምብዛም ስለማትርቅ፤ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ብዙ ያገር ውስጥና የውጭ አገር ነዋሪዎች መናኸሪያ በመሆኗ ለእንግዶች የሚስማማ የመስተንግዶ ቤት (ሎጅ) ቢሰራ አዋጭ ይሆናል ብዬ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ።

ከዶክተር ኃይለ ገብርኤል ዳኜ ጋር ሽርክና በመግባት አምባ ኤኮቱሪዝም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቋቁመን ከመንግስት በሊዝ ውል የቀድሞውን ቤተ መንግሥት ይዞታ ተረክበን ፋሽስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ያወደሙትን የአፄ ምኒልክ የነበረውን አዳራሽ በማስመሰል በባሕላዊ መንገድ እንደገና እንዲሰራ ሆኖ፤ ትልቁ አዳራሽ እንደግብር ቤትና እንደመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲያገለግል በዙሪያው የነበሩትን የሹማምንቱን መኖሪያ መሰል ቤቶችን በጥንቱ አሰራር እንደገና ገንብተን የእንግዶች መኝታ ቤቶች እንዲሆኑ አቀድን።

የቀድሞውን ቤተ መንግሥት በ 1928 ዓ ም ጠላት ሲያወድመው የቀረው ነገር ከላይ የሚታየው ከቤቱ ፊት ለፊት ያለው የድንጋይ ግንብ ብቻ ነው።›› በማለት ገልጸው ነበር፡፡

ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅን አጣን

በሀገራችን የመጀመርያውን ቴሌ ፕሪንተር በ1950ዎቹ ፈጥረው ፓተንት ያገኘኑትና ፤ በአለም አቀፉ የቴሌኮሚኪኔሽን ህብረት የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊ የነበሩት ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ሚያዝያ 30 2014 በድንገት ማለፋቸው ተሰማ፡፡

ለሀገራቸው እና ለታሪክ ታላቅ ፍቅር የነበራቸው ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ከ100 አመት አስቀድሞ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በቤተመንግስትነት ይጠቀሙበት የነበረውን የአንኮበር ቤተ-መንግስትን ፣አንኮበር ሎጅ ብለው የቀድሞ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ አሳድሰው ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ያኖሩ ናቸው፡፡ ይህም የበርካታ ቱሪስቶች መስህብ መሆን የቻለ ነው፡፡

በአሜሪካን ሀገር የኤሌክትሪክ ምህንድስና ያጠኑት ኢንጂነር ተረፈ፣ በ1980ዎቹ መጀመርያ ለአለም አቀፉ የቴሌኮሚኒኬሽህ ህብረት ዳይሬክተርነት ለመወዳደር በእጩነት የቀረቡ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይ ሀገራችን በቴሌኮም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ልምድና እውቀታቸውን ሲያካፍሉ፤ ምክር ሲለግሱ የነበሩ ናቸው፡፡ 

ኢንጂነር ተረፈ፣ ከኢትዮጵያ ባለፈ በአለም አቀፍ የቴሌኮም ባለሙያዎች ዘንድም የሚከበሩ ከመሆናቸው ባለፈ ያሳለፉትንም ህይወት ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጂኒቫ›› ብለው በመጽሀፍ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ የህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥም ላይ ከእነ መላ ቤተሰባቸው ቀዳሚ በመሆን ለሀገራቸው ያላቸውን አጋርነት የገለጹ ናቸው፡፡ 

እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ በተወለዱ በ86 አመታቸው ባለፈው እሁድ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የቀብር ስነ ስርአታቸውም ሀሙስ ግንቦት 4 2014 በመንበረ ጸባኦት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን ከቀኑ 8 ሰአት ይፈጸማል፡፡ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ በ1954 ከወይዘሮ ብርሀኔ አስፋው ጋር ጋብቻ መስርተው 3 ልጆችን እንዲሁም የልጅ ልጆችን አፍርትዋል፡፡ ኢንጂነር ተረፈ አንድነት ተረፈ ፤ ኢዛና ተረፈ እና መላዬ ተረፈ የሚባሉ 3 ልጆች አሏቸው፡፡ ሶስቱንም ለቁምነገር አብቅተዋል ፡፡

  ኢንጂነር በአሜሪካን ሀገር የሬንስለር  ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ( አርፒአይ) ምሩቅ ሲሆኑ በብዙ አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ሀገራቸውን ወክለው የተካፈሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊም ነበሩ፡፡

ዓለም አቀፋዊ ሙያዊ ሥራና ተልዕኮ

ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ በሚከተሉት አለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀጥረው አገልግለዋል

  • በአለም አቀፉ ቴሌኮሚኒኬሽን የአፍሪካ ክፍል ዋና ሃላፊ ባገለገሉበት ግዜያት የቴሌኮሚኒኬሽን የስልጠና ማእከላት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሌሴቶ፣ ስዋዚላንድ፣ ዛምቢያ፣ ሴኒጋል፣ ግብጽ፣ ማሊና ካሜሮን ውስጥ ማሰልጠኛ ለሌላቸው እንዳስጀመሩ ራሳቸው ካዘጋጁት መጽሃፍ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያና ግብጽ ላሉት ደግሞ የማስፋፋት እርዳታ እንዲሰጥ አድርገው ነበር፡፡ 
  • ፓን አፍቴል ( PANAFTEL) 

ይህን በአፍሪካ አገሮች  መሃከል የቀጥታ ግንኙነት መስመር ይፈጠር  ሲባል፣ ኃያላኑ መንግስታት አጥብቀው ይቃወሙ ስለነበር ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የፖለቲካውን ተቋም የአፍሪካ አንድነትን ድርጅት በዝርዝር በማስረዳትና የመሪዎችን ንቃተ ህሊና በመቆስቆስ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አስፈላጊውን የገንዘብ እርዳታ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ደግሞ የኢኮኖሚክና ማህበራ ጥቅማጥቅሞችን አሰባሰቦ አፍሪካ ዘመናዊ የቴሌኮሚኒኬሽን ስርዓት እንዲኖራት በእጅጉ የደከሙ ሰው ነበሩ፡፡

  • የአፍሪካ አህጉራዊ ሳተላይት መገናኛ መረብ ( ራስኮም ) ( RASCOM )

የዓለም ቴክኖሎጂ እየተለወጠ ሲሄድ አዲሱን የሳተላይት ቴክኖሎጂ የአፍሪካ አገሮች በጋራ እንዲጠቀሙበት ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመጣመር  ጥናት ጀምረው ነበር፡፡ ይሀውም በተለይ ያገር ውስጥና የገጠሩን  መገናኛ አነስተኛ  ፍላጎትና የከተማዎችን ከፍ ያለ ፍላጎት አስተባብሮ በተጨማሪም በአፍሪካ አገሮች መሃከል ለትምሕርት፣ ለንግድ፣ ለምርምር ወዘተ አጣምሮ ለገበያ በማምጠቅ ወይም ሳተላይት ከሚያመርቱት ድርጅቶች በመግዛት ተስማሚ ውድ ያልሆነ አገልግሎት ለህዝባቸው ለማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን በጥናት አረጋግጠው ለአፍሪካ መንግስታት  ውሳኔ አቅርበው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ተወዳዳሪ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ኢንቴልሳት፣ አረብሳትና ዩቴልሳት ያሉ ድርጅቶች ትብብር ለማድረግ ፈቃደኞች ስላልሆኑ አፍሪካውያን ሀገሮች  በጋራ ይህን ቴክኖሊጂ ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ የሆነ ሆኖ የእነ ኢንጂነር ጥናት ለአገሮቹ  ቴሌኮሙኒኬሽን መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ መስጠቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

  • የአይቲዩ ዋናው  ጸሐፊ  ልዩ የፖሊሲ አማካሪ መሆን 
  • የቴሌኮሚኒኬሽን ልማት ቢሮ ( ቢዲቲ) ዲሬክተርነት እጩ ሆነው ለመወዳደር የነበራቸው ውጥን በግዜው የኢትዮጵያ ፕሬዜዴንት አቶ መለስ ዜናዊ ችላ ባይነት  ህልማቸው አልተሳካም፡፡  በነገራችን ላይ  ብዙ ሙያና ችሎታ ያላቸው ሰዎች በእጩነት ቀርበው ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ለምሳሌ በአጼ ሐይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ክቡር እንዳልካቸው መኮንን ለተባበሩት መስግስታት የዋና ጸሐፊነት ቦታ ወድድር ቀርበው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ እንዲሁም የፕላን ሚኒስትር የነበሩትና፣  በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥም በምክትል ፕሬዚደንትነት ያገለግሉ የነበሩት ክቡር አቶ ተካልኝ ገዳሙ ለባንኩ ፕሬዜዴንትነት ቀርበው የኢትዮጵያን መንግስትን ድጋፍ  ባለማግኘታቸው ትልቁን ቦታ ለመረከብ ሳይችሉ  ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይ አምባሳደር ይልማ ታደሰ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምክትል ዋና ጸሐፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው ለድጋሚ ሲቀርቡ እጩነታቸው በራሳቸው መንግስት ሳይደገፍ በመቅረቱ  ያሉበትን ቦታ  ተነጥቀው  ለሌላ አገር ሰው  ለሱማሊያ ተሰጥቷል፡፡ እንደ ኢንጂነር  ተረፈ ራስ ወርቅና በሌሎች እውቅ ኢትዮጵያውያን ላይ ወያኔ ሸርቦት በነበረው አሻጥር ምክንያት በአለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ያለውን የሃላፊነት ድርሻ መውሰድ እንዳልቻሉ  የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል፡፡
  • የአይቲዩ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ መሆን

በሥራው  ዓለም ስለአከናወኗቸው ድርጊቶች

  • ከአርሳቸው ዘመን በፊት ስልክ ( ቴሌኮሙኒኬሽን ) አገራችን ያስገቡት አጼ  ምኒሊክ ነበሩ፡፡ ( ታሪኩም እንደሚነግረን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ 1882 ዓ.ም ልዑል ራስ መኮንን ( የቀዳማዊ ኃይለስላሴ  አባት ) ለሥራ ጉብኝት ወደ ጣሊያን አገር  ደርሰው ሲመለሱ  የስልክ እቃ  ይዘው ይመጡና ለሸዋው ንጉስ  ምኒሊክ አንኮበር  ቤተ መንግስታቸው ወስደው ሰጥተዋቸዋል፡፡ ያንን እቃ  ስቲቨነን የሚባል የፈረንሳይ  ተወላጅ ከአንኮበር  ቤተመንግስታቸው  እስከ ግምጃ ቤቱ ድረስ አያይዞ ለመነጋገገር ቻሉ፡፡ ይህም አጋጣሚ የሚጠቁመው  ስልክ ኢትዮጵያ ውስጥ  መጀመሪያ የገባው ( የተወለደው ) እንደ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ አንኮበር ላይ ነው፡፡
  • በኢትዮጵያ ፊደል  የሚጽፍ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር  በመፈልስፍ ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ አድርገዋል

እንደ መደምደሚያ

ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ከኢትዮጵያ ምድር አንኮበር ተነስተው አለም አቀፍ ስምና ዝና ያተረፉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ኢንጂነሩ በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪክ ስፍራውን አይነሳቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ አልፈው በመላው አፍሪካ የቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ ጥለው ያለፉ ሰው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ዛሬ የደረሰበት እድገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው እንደነ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ወደር የሌለው ተግባር ፈጽመው ስላለፉ እንደሆነ የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ ለማናቸውም ለኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ሲሉ የሕይወት ዘመናቸውን ሙሉ ለዋጁት ለእኚህ ታላቅ የቴሌኮሙኒኬሽን ሰው ሀውልት ሊቆምላቸው ይገባል በማለት እሰናበታለሁ፡፡ ሰላም፡፡

Filed in: Amharic