>
5:13 pm - Tuesday April 19, 3222

ከዋናው ግብ ጀርባ ያለው መራራ ሃቅ....!!! (ህብር ራድዮ)

ከዋናው ግብ ጀርባ ያለው መራራ ሃቅ….!!!

 

የግል ምልከታ – ህብር ራድዮ


ራሱን የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ብሎ የሚጠራው የባለስልጣናት ቡድን የጀመረው  “የእብደት ዘመቻ” በከፊል ቅርፁን እና ዓላምዉን ቀይሯል።

ምን ለማለት ነው፥ ዘመቻው እንዲጀመር ፖለቲካዊ ውሳኔ የሰጠው እና ስምሪቱን ያስጀመረው አካል ዓላማው ፋኖን መበተን፣ አማራውን ድምፅ አልባ ማድረግ ከተቻለም ጣልያን በአምስቱ ዘመን ሞክሮት እንደነበረው በአማራው ላይ “ፖለቲካዊ እጥበት” መፈፀም ነዉ። ይህ ዕቅድ ይሳካ አይሳካ በግዜ ሂደት የሚታይ ነው።

ከዋናው ግብ ጀርባ ያለው መራራ ሃቅ ግን የአንድን አካባቢ ህዝብ ለማጥቃት ግዜ ሲጠብቅ የነበረ እና ተላላኪነትን መተዳደሪያው ያደረገ የአንድ ሰፈር ልሂቅ የሚፈልገውን እያደረገ መሆኑ ነው። በተለይ ባህርዳር ላይ የተሳደዱ እና የታፈኑ ነጋዴዎች (ሳሚ ማተሚያን ጨምሮ) እና ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች (ቲናን ጨምሮ) አድፍጦ የሚያጠቃው ቡድን ዒላማወች እንጅ የዋናው መንግስታዊ ቡድን ዒላማወች እንዳልነበሩ ግልፅ ነው።

ይህ ቡድን ያገኘው ወርቃማ እድል ቢኖር በታሪክ አጋጣሚ  የዘመኑ መንግስት ተቃዋሚወች እና ጠላት የሚለው ህዝብ ያበቀላቸው ኤሊቶች መመሳሰል እና ዶ/ር ይልቃል ይህንን ሴራ መረዳት አይደለም መስማት የማይችሉ ደካማ መሪ መሆናቸው ነው።

ነገሩን ለፖለቲካዊ ብሽሽቅ ወይም ለግዜያዊ ትርፍ ያነሳሁት አይደለም። ለዚህ ዘመቻ ከብሔራዊ መረጃ  የተወከለው ግለሰብ፣ የወቅቱ የአድማ ብተና አዛዥ (የእድሜ ዘመንም ይባላሉ)፣ ጠቋሚ የአብን አመራሮች እና አክቲቪስቶ አጋጣሚውን ጠብቆ እያጠቃ ያለው ቡድን አካል መሆናቸው የተረጋገጠ ሃቅ ነው።

በዚህ ኦፕሬሽን ላይ የራሱን ፍላጎት ሊያሳካ እየሞከረ ያለው ቡድን የአንድን አካባቢ ኤሊት ከአማራ ፖለቲካ የመነጠል እና የሀብት ምንጭ የሆነችውን ባህርዳርን እንደገና የመቆጣጠር ግብ ሰንቆ የሚተጋ ነው። የወቅቱ የባህርዳር አመራር  ይህን ሴራ ቢያውቅም የታዛዥነት ስነ ልቦና ይዞት ወገኑን አሳልፎ እየሰጠ ነው።

በነገራችን ላይ ከተማዋ እና ክልሉ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ባሉበት ሁኔታ እና በርካታ የከተማዋ ልጆችም እየተሳደዱ ስለመንገድ ላይ አበቦች፣ ስለኮብልስቶን ጥራት እና ስለ ኪስ አውላቂወች እየፃፉ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች ዓላማም ከቡድኑ ጋር እንደሚገናኝ መጠራጠር ጀምሬያለሁ።

የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በክልሉ ውስጥ አጥቂ እና ተጠቂ ኤሊት ፈጥሮ የአማራን ፖለቲካ በእጅጉ ሊያደበዝዘው እንዳይችል ራሱን የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት ብሎ የሚጠራው ስብስብ ቆም ብሎ ቢያስብበት መልካም ነው። ነገሩ ባለበት ከቀጠለ በአማራ ፖለቲካ ውስጥ በቀላሉ የማይጠገን ሽንቁር ሊፈጠር ይችላል። ነገ ጧት ለሚቀየር ፖለቲካ እና የኃይል አስላለፍ የማይድን ሂደቱ ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍ የአጥቂው ቡድን  የቅርብ ሰወችም ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ጥሩ ነው።

ህዝብን ማሸነፍ አይቻልም!!

ተጨማሪ ፎቶውን እኛ ለማጣቀሻነት አካተነዋል። የዛሬው የደህንነት ሹም ተመስገን ጥሩነህ ኢንሳ ሲሰራ ከአብይ አህመድ ቀጥሎ የተቋሙ ኃላፊ ከነበረው የአሸባሪው ሕወሓት ጀነራል ተብዬ ጋር ነው። እነ ተመስገን ጥሩነህ ትላንትም ዛሬም አፋኞችን ወግነው በሕዝባቸው ላይ የተነሱ መሆናቸውን ልብ ይሏል።

Filed in: Amharic