ጋሽ ታዴዎስ ታንቱን በትንሹ…
ጌጥዬ ያለው

ወያኔ የ15 ዓመታት እስር ፈርዶባቸው ለዓመታት በሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ቆይተዋል።
ታዴዎስ ታንቱ በአብዮታዊ ጦር ሃይሎች ዋና የፖለቲካ አስተዳድር ስር በነበረው ‘ታጠቅ’ ጋዜጣ ከ1975 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። ከዚህ በኋላም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ በኢትዮጲስ ጋዜጣ፣ በፍትሕ ጋዜጣ፣ በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ እና በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች በአምደኝነትና በአዘጋጅነት ለረጅም ዓመታት በነፃው አገልግለዋል። በአሁኑ ጊዜ በትርፍ ጊዜያቸው በራስ ሚዲያ በጋዜጠኝነት እያገለገሉ ሲሆን የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆነዋል።
የኅሊና እስረኛው ጋሽ ታዴዎስ ከሀቀኛ ጋዜጠኝነታቸው በተጨማሪ በመምህርነታቸው እና በታሪክ ፀሐፊነታቸው ይታወቃሉ።
በኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ ተከታታይ ቅፅ ያላቸው መፅሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል። ይህ ባለተከታታይ ቅፅ መፅሐፍ ‘ደም መላሽ’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን አንደኛውና ሁለተኛው ቅፅ ታትሞ በመነበብ ላይ ነው። ሦስተኛው ቅፅ በወረቀት ደረጃ በዝግጅት ላይ እያ ከሰምኑ በኦሕዴድ-ብልፅግና የውንብድና ቡድን ሲታፈኑ በእጃቸው ላይ ስለተገኘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል።
‘የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ’ እና ‘ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ’ ሌሎች ጋሽ ታዴዎስ ለንባብ ያበቋቸው መፅሐፍት ናቸው። ‘የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ’ በ2009 ዓ.ም. የታተመ ሲሆን የወያኔን ውድቀት አስቀድሞ የተነበየ ነበር። ‘ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ’ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ልዕልና የሚያሳይ ሲሆን ባንዳ፣ ሆድ አደር እና ባለሟል ጋዜጠኞችንም ያለ አንዳች ይሉኝታ ለይቶ ያስቀመጠ ነው። ለሐቅ ውግንና የታየበት መፅሐፍ ነው።

ጋሽ ታዴዎስ ከሁሉም በላይ ብዙዎቻችን ልቦናችን እያወቀው አንደበታችን የማይደፍረውን ሐቅ አፍርጠው በመናገር ይታወቃሉ።
በቅርቡ በተረኛው የወራሪዎች አገዛዝ “‘የአማራ ደም የእኔም ደም ነው’ ብለሀል” በሚል ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በመናድ በሀሰት ተወንጅለው ታግተው ቆይተዋል። ከሰሞኑ ደግሞ “አንድን ብሔር ለይቶ መጥላት” በሚል አስቂኝ ውንጀላ ተወንጅለው ማዕከላዊ ማጎሪያ ቤት ይገኛሉ። ተጠላ የተባለው ብሔር የተረኞቹ ወገን ኦሮሞ መሆኑ ነው። በምግባር እንጂ በማሰር መወደድ ይቻል ይሆንን?