>

ኢትዮጵያን እንዴት ከጥፋት እንታደጋት ? (ንጉሤ አሊ)

ኢትዮጵያን እንዴት ከጥፋት እንታደጋት ?

ንጉሤ አሊ


ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ የመፈራረስ አደጋ ላይ ነች ይህ ሟርት ሳይሆን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔት የሚያረጋግጠው ሀቅ ነው ። ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አህመድና ድርጅታቸው ብልጽግና ፓርቲ ይህንኑ ተግባር ደረጃ በደረጃ በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ ። ውድ አገርህን የምትወድ ኢትዮጵያዊ በሙሉ አጽንዖት ሰጥተህ ካየህ ጠቅላይ ሚንስትሩ አገር ወዳዱ ዜጋ መስማት የሚፈልገውን ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ እያጮሁ ድምጻቸውን አጥፍተው ግን ከሀገር አፍራሾች ጋር ተመሳጥረው ብዙ እርምጃ ወደፊት ተራምደዋል ። ከቅንነት የተነሳ አብዛኞቻችን ኢትዮጵያ አትፈርስም  እንላለን አዎን አትፍረስብን ግን ላለመፍረሷ ምንም ማረጋገጫ የለንም ስልታዊ በሆነ መንገድ የውስጥና የውጭ አፍራሽ ኃይሎች በመተባበር ብዙ አገሮችን በታትነዋል። 

ኢትዮጵያን ለመበታተን እጅግ በጣም ቀላልና ውጣ ውረድ የማያስፈልገው ነገር ነው ይሄውም ትህነግና ኦነግ ህጋዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ እንድትፈረስ የጫኑብን ህገመንግሥት አንቀጽ 39 የብሔሮች፣ብሔረሰቦች፣ መብት በሚለው ተራ ቁጥር አንድና ተራ ቁጥር 4 ሀ እንዲህ ይላል፦

„1. ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረስብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው ። „

„4. የብሔር ፣ ብሔረስብ ፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ከሥራ ላይ የሚውለው ፦ „ 

    „(ሀ) የመገንጠል ጥያቄ በብሔር ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጭ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ የድምጽ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ ፣

እዚህ ላይ አጽንዖት መስጠት የሚገባንና መምታታት የሌለብት ነገር ኢትዮጵያ ከስማኒያ ሁለት በላይ ዘውጌዎች ወይንም በእነርሱ አጠራር ብሔር ፣ ብሔረስቦችና ሕዝብ የሚኖሩባት  ሀገር ሆና እያለ ለመገነጣጠል በሁለት ሶስተኛ የመወሰን መብት የተሰጠው ለፈደሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን ለክልል ምክር ቤት ነው ። ይህንን አንቀጽ ትህነግና ኦነግ  በህገ መንግሥቱ የደነቀሩት ያለ ምንም ችግር ኢትዮጵያን ለመበታተን እንዲያመቻቸው ነው ። 

ህወኃት መራሹ መንግሥት ሁለት ፕላኖችን  ( ፕላን Aና ፕላን B) ይዞ ለሃያ ሰባት ዓመታት ተንቀሳቅሷል ። የ ፕላን A አላማ ታላቋንና  የማትነጥፈውን ኢትዮጵያ እያለቡ ትግራይን ምድረ ገነት ማድረግ ነበር ነገር ግን ያልጠበቁት ሥልጣንና ነዋይ ከነምቾቱ ሲመጣ የትግራይ ሕዝብም ሆነ ትግራ ተረስቶ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንዲሉ በፕላን A መሰረት ሳያበለጽጉና በፕላን B መሰረትም ታላቋን ትግራይ እንደ አገር ሳይመሰርቱ እንደ ጅብ ሁሉንም ሲያግበሰብሱ ነጋባቸውና አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ ።

ትህነግ ሁለቱንም ፕላን ሳያሳካ ድንገተኛ ዶፍ ዝናብ ጥሎ ጎርፉ ቢጠራርጋቸውም ባልበላው ጭሬ እበትናለሁ የሚለውን የዶሮ ብህል ይዘው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትኖር ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር አብረው ምንም የማያውቁትን ጨቅላ የትግራይ ወጣቶችን በጦርነት እየማገዱት ነው ። 

ያሁኖቹ ተረኞች የኦህዴድ ብልጽግናዎችም ቢሆኑ ሁልት አማራጭ ፕላን ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ አንደኛው ኦሮሞን የምትመስል አዲስ አገረ መንግሥት (ኦሮሙማ) መመስረት ሲሆን ይህ ማለት የሌላውን ዘውጌ ባህል ፣ ቋንቋ ፣ እመንት ፣ ቴሪቶሪ በመውረርና በመዋጥ (assimilate) በማድረግና የኔ ከሚሉት ክልል ሌላውን በዘር ማጽዳትና ማጥፋት አስወግዶ የኦሮሞ ብቻ ማድረግ ነው ።

ኢትዮጵያን አፍርሰን በመቃብሯ ላይ ኦሮሚያን እንመሰርታለን የሚለው ኦንግ አርቅቆ ያጸደቀውን ይህንን ሕገመንግሥት ይዘነና  የታክቲክ ካልሆነ የእስትራቴጂ ልዩነት የሌለውን የኦህዴድ ብልጽግና ፓርቲን ሥልጣን ላይ አስቀምጠን ኢትዮጵያ አትፈርስም ብሎ ራስን ማታለል ብዙ አስከፍሎናል ደረጃ በደረጃ እየፈረሰች ለመታዘብም በቅተናል ። 

ኢትዮጵያን ደረጃ በደረጃ የማፍረስ ህደቶች ፦

1/ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በብሔራዊ ደረጃ የምትታወቅባቸውን ቅርሶችና ታሪካዊ እሰቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ማውደም ፦

 • የሚንልክን ቤተመንግሥት በእድሳት ስም ያለ ሕዝብ ይሁንታ ታሪካዊ ይዘቱን መለወጥና ስም መቀየር ፤
 • በዩኔስኮ የተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶችን ከአዲስ አበባ ለማስወገድ የተጀመረው ጥንታዊና ታሪካዊ ቤቶችን ማፍረስ ፤
 • 126ኛው የአደዋ የድል በዓል በሚንልክ አደባባይ እንዳይከበር መንግሥታዊ ክልከላና ትንኮሳ ፤
 • በሕዝበ ውሳኔ ያለተቀየረውን ነባርና ታሪካዊ ሰንደቅ ዓላም ሕዝቡ እንዳይዝ መከልከል ፤
 • ጥንታዊቷን የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተከርስቲያንን ለማዳከምና ለመከፋፈል እየተካሄደ ያለው ሴራ ፤
 • በቅርቡ የተጀመረው የሙስልሙን እምነት ተከታይ ለመከፋፈልና ብሎም ከኦርቶዶክ እምነት ለማጣላት የተጀመረው ሴራ ፤ 

2\ ሕገመንግሥቱን ተገን በማድረግ ከትህነግ የቀሩ ተግባራትን በመፈጸም ግንጠላውን እውን ማድረግ 

 • የክልሎችን ቁጥር በመጨመር መበታተኑን (  disintegration) ማፋጠን ፤
 • የክልሉ ነዋሪ የአንድ ዘውጌ አባላት ቢቻ እንዲሆኑ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲካሄድ መፍቀድ ፤
 • በመለስ ዜናዊ ግዜ ተፈርቶ እንዳይነካ የተባለውን ውህድ የዲስ አበባ ነዋሪ ዲሞግራፊ ለማስተካከል ተብሎ የሚፈጸም ግፍና እንቅፋት የሚሆኑትን በጉልበት ለማንበርከክ 50 ሺህ ፖሊስ ከአዲስ አበባ ውጭ መመልመሉ፤
 • ከኦሮሞ ክልል ውጭ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የኦሮሚያን ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘምሩ ማስገደድ ፤  
 • ለግንጠላው እንቅፋት ይሆንብናል ያሉትን የአማራን ዘውግ ስጋት እንዳይሆን በዘዴ በጦርነትና ከክልሉ መሬት እየቆረሱ ወደ ሌላ ክልል በመስጠት ማዳከም ፤
 • በአማራ ክልል ራሱን ለመከላከል የተደራጀውን ልዩ ኃይል ፋኖና ሚሊሺያ ለማፍረስና ትጥቅ ለማስፈታት እየተካሄደ ያለው ህጻን ታዋቂ ያልለየ አፈናና ዘመቻ እንዲሁም አሰልጣኙን ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞን ማባረርና ማሰር ፤ 
 • እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው የተሰጉ ነባር የክልሉን አመራሮች ከብልጽግና ፓርቲ አመራርነት ማባረር ፤

3\ በሰላምና በእርቅ ስም የሚደረግ ስውር ሴራ ፦

 • ሀ) የጦር ወንጀለኞችን ከእስር ፈቶ መልቀቅ ፤
 • ለ) ወልቃይት ጠገዴና ራያን ለትህነግ ሰጥቶ እንድትገነጠል ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ በዶክተር አብይና ዶክተር ደብረጽዮን እየተካሄደ ሲሆን ይህም የኦሮሞ ተስፋፊዎች ከአማራ ክልል አለን ለሚሉት በር ከፋች መሆኑ ፤
 • በታክቲክም ሆነ በእስትራቴጂ ልዩነት የሌላቸው የኦነግ ኦህዴድ ብልጽግናና ትህነግ የሥልጣን ጥላቸውን በእርቅ አስወግደው የጋራ እቅዳቸውን ለማሳካት በጦርነቱ የጦስ ዶሮ የሆነውን የአማራንም ሆነ የአፋርን ሕዝብ ሳያካትት በድብቅ ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ሽመልስ አብዲሳ ማካሄዳቸው ፣ 

እነዚህ ከላይ ከብዙ በጥቂቱ ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸው ደረጃ በደረጃ ኢትዮጵያን የማፍረስ ህደቶች የሚተገበሩት በትረሥልጣኑን በጨበጠው የኦህደድ ብልጽግና መንግሥት ነው ።

ከሁለ አስቀድሜ ዶክተር አብይ ያሻግሩናል ፣ ከእኔ የበለጡ ኢትዮጵያዊ ናቸው ፣ ጊዜ እንስጣቸው ፣ የሚናገሩት በሙሉ ስለ ኢትዮጵያ ነው የሚትሉ ቅንና አፍቃሬ አብይ  እህትና ወንድሞቼ ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን የሚወዱ ዜጎች መስማት የሚፈልጉትን ነገሮች እንደ ውዳሴ ማሪም ሸምድደው በበአለ ስመታቸውና ለተወሰኑ ወራቶች ሁላችንንም አታለውናል እውነትና ንጋት እያደር የጠራል እንዲሉ ውሎ ሲያድር ትክክለኛው ማንነታቸው አፍጦ ወጣና ተቀባይነታቸውም እንደ ጉም በነነ። አሁንም ዶክተር አብይነ እንደ ለውጥ ፈላጊ አድርገው የሚያዩና የሚደግፉ ቅን ኢትዮጵያውያን መደገፍ መት ቢሆንም ሀገርን ለማፍረስ ሲንደረደሩ በቃህ ሊሉ ይገባል የሚሉትንም ቢሆን መርጦ ከመስማት ሁሉንም አድምጦ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ለሀገርም ለወገንም የሚጠቅም ተግባር ነው ። 

ዶክተር አብይ  ሕጉን ሊያጸኑ እንጂ ሊያፈርሱ አልመምጣታቸው ፦  

የአማራ ሕዝብ ባልተሳትፈበትና በማያውቀው ሕግ መተዳደር የለብት ተብሎ ለሚቀርብ የብዙኃን ጥያቄ ዶክተር አብይ ለአንድ ክልል ተብሎ ሕግ አይቀየርም ብለዋል ። ሰሞኑን ከብልጽግና የጉባኤ ድራማ መልስ ብልጽግናም ሆነ ሌላ ሕገመንግሥቱን ማሻሻል አይችልም ቢሻሻልም በህጉ መሰረት ነው ብለዋል በሌላ አባባል ሕገመንግሥቱን መቀየር አይቻልም ማለት ነው ምክንያቱም  ሕገ መንግሥቱ  ሊሻሻል የሚችለው በአንቀጽ 105 ተራቁጥር 1 (ሀ) መሰረት ነው ።

አንቀጽ 105 

ሕገ መንግሥትን ስለ ማሻሻል ፦

1\ በዚህ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ ፣ይህ አንቀጽ ፣ እንድሁም አንቀጽ  104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኻን ብቻ ይሆንል ፦

( ሀ) ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት ፤  

ይህ ማለት ሕጉ ያለ ትህነግና ኦነግ ፈቃድ እንዳይሻሻል ሆን ብለው የደነቀሩት አንቀጽ እስካልተወገድ ወይንም የፖለቲካ ውሳኔ እስካልተሰጠ በቀር በምንም አይነት ማሻሻል እንደማይቻል እያወቁ ጠቅላይ ሚንስቴሩ አንዴ ለአንድ ክልል ተብሎ አይቀየርም ሌላ ጊዜ በህጉ መሰርት ይሻሻላል እያሉ ያላግጣሉ ። አጾንኦት መስጠት የሚገባን በኦህደድ ብልጽግናና በትህነግ ኢትዮጵያን በማፍረሱ ጽንሰ ኃሳብ ምንም ልዩነት የላቸውም ችግር የተፈጠረው ትህነግ በምሊቴር ጉልበቱን አፈርጥሞ ፤ በኢኮኖሚ ደርጅቶና የግዛት ይዞታውን አስፍቶ አቶ መለሰ ሁሌም እንደሚያስፈራሩን ለኦነግ አስረክበውን መሰሥ ሊሉ ነበር ነገር ግን የለውጡ ድንገተኝነት ያበሳጫቸው ህወኃቶች ቂማቸውን ለመወጣት ሲኦልም ቢሆን ገብተን ለዚህ እንድንበቃ ባደረገን አማራ ላይ ህሳብ እናወራርዳለን ብለው በአብይ ታዛቢነት ወረራ አካሔዱ ። ዶክተር አብይም ይህንን ሳይዋሹ ትህነግ አዲስ አበባ ቢገባ እናንተን ጠራርጎ ያጠፋችኋል እንጂ ኦሮሞን አይነካም ነበር ብለዋል ።

 

ኢትዮጵያን እንዴት ከጥፋት እንታደጋት ?

ይህ ጥያቄ የሚመለከተው ኢትዮጵያ በምትባል ሉአላዊ ሀገር የሚኖሩ በዘውጌው የሕዝብ ብዛት ቀሚሴ በቁመቴ ልክ ይሰፋልኝ በሚል ፍልስፍና ሳይሆን ሁሉም እንደዜጋ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ ተከብሮ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያውና ባህላዊ ነጻነቱ እንዲረጋገጥ የሚፈልገውን ዜጋ በሙሉ ነው ። በመሆኑ የትህነግና የኦነግ ኦህዴድ ብልጽግና ከላይ የተጠቀሱትን ፕላኖቻቸውን እውን ለማድረግ የሥልጣን ጥላቸውን ለጊዜው ወደጎን ብለው ለእርቅ በውይይት ላይ ናቸው

እዚህ ላይ እርቅ ለምን ይደረጋል እያልኩኝ አይደለም እንኳንስ በወንድማማቾች መካከል ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የተከሰተ አሸናፊ የሌለው ጦርነት ይቅርና ከውጪ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት እንኳን መቋጫው እርቅ ነው ። ጥያቄው የጦርነቱ ሰለባ ከሆነው ሕዝባችን ጀርባ በምስጢር እንዲደረግ ለምን ተፈለገ ? የእርቅ ውጤቱ ሰጥቶ መቀበል እንደመሆኑ መጠጥን ማን ምን ሰጥቶ ምንስ ለመቀበል እየተደራደረ ነው የሚለውን መንግሥት ለሕዝብ ግልጽ  ለማድረግ ለምን ፈራ ? በዚህ መልኩ በሚካሄድ ውይይት የሚደረግ ስምምነት ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ወይ ? 

ካለው ነባራዊ ሁኔታ የምንረዳው ሁለቱ ውይይቱን የፈለጉት ሰላም ለማስፈን ሳይሆን ዓላማቸውን ከማሳካታቸው በፊት ሁለተኛው ሕዝባዊ ማእበል እንዳይነሳ ለማደናገርና እንቅፋት ይሆንብናል የሚሉትን አሁን በፋኖ ላይ እንደጀመሩት ለይተው በመምታት ለማዳከም ነው ። ግባቸው የሚሆነው ትህነግ የበላይ በነበረችበት ወቅት ከሌሎች ክልሎች የቀማቻቸውን መሬት መመለስና የትህነግን የታላቋን ትግራይ የመመስረት ቅዠት እውን ማድረግ ነው ። በዚህ ተግባር ላይ ከውጭ ጠላቶቻችን ጭምር ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ። 

ኢትዮጵያን እንደ ዶሮ ብልት ለመገነጣጠል የሚፈቅድ ህገ መንግሥት  ስላለ ቀሪውን ኦህዴድ ብልጽግና ይገባኛል የሚለውን መሬት ከክልሎችና ከከተማ መስተዳድሮች በመውሰድ የቀሩትን  ከፈለጉ በገዳ ስርአት ደንብ ገርባ ሆኖ በኦሮሙማ እንዲዋጡ ማድረግ ያልፈለገውን በህገ መንግሥቱ መሰረት የክልሎችን ቁጥር በመጨመር  አቅመ ቢስ አድርጎ እንዲገነጠሉ መፍቀድ ነው ። በእትዮጵያ መቃበር ኦሮሙማን መገንባት ማለት ይህ ነው ። 

የኦህዴ ብልጽግና በዶክተር አብይ አህመድና በአቶ ሽመልስ አብዲስ መሪነት በቅድሚያ በአማራ ሕዝብ ቀጥሎ ሌላውን ተራ በተራ በህግ መስከበር ሽፋን በኦሮሞ ልዩ ኃይልና ኮማንዶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ህጻንና አዛውንት ሳይለይ ህገወጥ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በመገንዘብ ያለ ኢትዮጵያ የሚኖር ዘውጌ (ብሔር ፣ ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ) ስለማይኖር ማንኛውም ግለሰብ ፣ ቡድንና ድርጅት የትህነግንና የኦሮሞ ድርጅቶችን ሀገር የማፍረስ ተግባር ለማስቆም አገር አቀፍ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መደረግ አለበት ።  

አገር አቀፍ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለማደረግ  አንድ የሚያረጉን የጋራ አጀንዳዎች አሉን ፦

 የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት መኖር ፤ ህገወጥ አፈናና ግዲያን ማስቆም ፤ መንግሥት ሰራሽ የኑሮ ውድነትን መቃወም ፤ የኦህዴድ ብልጽግናን አገር አቀፍ የመሬት ወረራና የኦሮሙማ ግንባታን መቃወም ፤ የኦህዴድ ብልጽግናን ተረኝነትን መቃወም  የጋራ አጀንዳ በመሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶችን ለጊዜው በመተው በአገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ  በመሆን የህንን ወቅታዊ አደጋ በጋራ ለመመከት ሕዝባዊ እምቢተኝነት የህሊውና ጉዳይ እንጂ አማራጭ አይደለም።

 

ፈጣሪ ኢትዮፕያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅልን

 

 

Filed in: Amharic