>
5:33 pm - Monday December 5, 1583

“ ቀጠለ…ወደ እሳቱ”  (ጌታቸው አበራ)

“ ቀጠለ…ወደ እሳቱ”

 

እንደ እሳት እራቷ – እንደ ቢራቢሮ፣

ብር… ትር… እያለ – ክንፎቹን ሰትሮ፣

ሙቀቱን ሳይለካ – ትርፍና ኪሳራ፣

ብርሃኑ መስሎት – መንገድ እሚመራ፣

እሚቋቋም መስሎት – በሰላ አንደበቱ፣

የመቅለጡን ጉዞ – ቀጠለ ወደ እሳቱ!

 

 ፩. ቁጭ ብሎ አሸልቦት- ላይ-ታቹን ሳያማትር፣

          ከጊቢው የተነሳው – ከወንበሩ እግር ስር፣

          ባውሎ-ነፋስ ፍጥነት-አገር ያዳረሰው፣

          ሰደድ-እሳት ደርሶ-ድንገት ያስወገደው፡

 ፪.ቁርጥ ቀን ሲመጣ – ድንገት ተፈናጥሮ፣

          ያመለጠ መስሎት – ባየር ተወርውሮ፣

     ከህሊናው ርቆ ሊያመልጥ ሳይሳነው፣

     በጸጸት ልዩ እሳት…፣

     ባገር ናፍቆት ነዲድ ሲቆላ እሚኖረው፤

፫.ሕዝባዊ ማዕበል – ወላፈን ለብልቦት፣

       የእሳቱን ጣጣ – መሸከም ተስኖት፣

     ሸሩን የቀመረው – ተንኮሉን ያደራው፣

     አንጎሉ ፈንድቶ – የተሰናበተው፤

፬.ሙቀት ሲያይልበት – እሳቱ ሳይበላው፣

   “በየሱስ ስም!” ብሎ- ሮጦ ያመለጠው፤

… ቢያንስ በእኛ ዕድሜ – ያየናቸው “አራቱ”፣

   ዞረው፣… ዞረው፣…ዞረው፣… ሲገቡ ከእሳቱ፣

   እንዴት እንዳልሰማ፣ እንዴት እንዳላየ ‘እንደተበለቱ’፣

   እኔስ ግራ-ገባኝ፣ እንጃኝ! “እንጃ-አባቱ”!

 

  ተው ቢሉት እሚያውቁ – እሳቱ የታያቸው፣

  እምቢኝ ብሎ ሄደ – ጎሪጥ እያያቸው፣

  የእርሱስ መጨረሻ – ክዋኔው ናፈቀኝ፣

  እንዳህያው ሥጋ..

  አልጋ ሲሉት መደብ- መረጠ መሰለኝ፤

  “ያላወቁ አለቁ”- ነበረ ተረቱ፣

   እያወቁ ማለቅ- ጉዞ ወደ እሳቱ!

 

  ጌታቸው አበራ

ሰኔ 2014 ዓ/ም

(ጁን 2022)

Filed in: Amharic