>

የጣልኩባቸውን ተስፋ ያመከኑ ፕሮፌሰሮች (አሳዬ ደርቤ)

 የጣልኩባቸውን ተስፋ ያመከኑ ፕሮፌሰሮች!!

አሳዬ ደርቤ

ፕሮፌሰር ብርሐኑ:-

ከህውሓት የሥልጣን ዘመን አንስቶ እስከ ለውጡ ማግስት ድረስ ‹‹የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች›› ሆነኝ ከሚታዩኝ ሰዎች ዋነኛው እና ቀዳሚው ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነበር፡፡

ከሥልጣን ሽግግሩ በኋላ ግን እኒያ ፕሮፌሰር ወደ ትግል ሜዳ ይዘዋቸው የሄዱትን ታጋዮች ከሜዳ ላይ በትነዋቸው ወደ ቤተ-መንግሥት ሲያመሩ ዐየኋቸው፡፡

➔ወንበር ተቀብለው አገር ሲሰጡ፣ ድርጅታዊ ትግልን በግላዊ ድል ሲለውጡ፣ የሕዝብ ፍቅርን በግለሰብ አምልኮ ሲሸጡ፣

➔በመለስ ዜናዊ ላይ ደረታቸውን የሚነፉት ሰው ለወቅቱ መሪ ሲሽቆጠቆጡ፣ የዜግነት ፖለቲካ ትግላቸው ደጋፊ ሆኖ ገንዘቡን እና ጉልበቱን ሲለግሳቸው የኖረውን ዜጋ አሽቀንጥረው ከብሔርተኞች ስር ሲርመጠመጡ፣

➔ግዙፍ ሥማቸውንና በሕዝብ ልብ ውስጥ የተቀመጠ ዙፋናቸውን ወርውረው ከቆማሪዎች ወንበር ላይ በእርካታ ሲቀመጡ…ዐየኋቸው፡፡

በህውሓት ጊዜ አገራዊ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ቀድመው የሚተነብዩት ፖለቲከኛ በብልጽግና ጊዜ የተከሰተ ችግርን መመልከት ሲሳናቸው ዐየሁ፡፡ ያለፈውን ሥርዓት ‹‹አገር የሚያወድም ካንሰር ነው›› እያሉ የሚጠሩት ጉምቱ ፖለቲከኛ ሥልጣን ላይ ያለውን ሥርዓት ‹‹አገር የሚያክም ዶክተር ነው›› እያሉ ሲያወድሱት ሰማሁ፡፡

ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ:-

እንደ ሌሎች የአብን አመራሮች በሶሻል ሚዲያ ሳይሆን በአካልም ጭምር ያገኘሁትና በእርጋታው፣ በእውቀቱ፣ በብስለቱ በተለያዩ ጊዜያት እዚህ ገፄ ላይ አድናቆቴን የቸርኩት ፕሮፌሰር በለጠ በሰለጠነ መንገድ የዶክተር ደሳለኝን ሥልጣን ተረክቦ የአብን ፕሬዝዳንት ሲሆን ‹‹የተጀመረውን ድርጅታዊ ትግል ከፍ በማድረግ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን በደል እና ግፍ እንዲቀንስ ማድረግ ይችላል›› የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ፍልስፍና ያጠና ሰው እንደመሆኑ መጠንም ከቁሳዊ እና ግላዊ ነገሮች ይልቅ ሕዝባዊ እና ሞራላዊ ጉዳዮችን ያስቀድማል የሚል ግምት ነበረኝ።

የብልጽግናን ሥልጣን በተረከበ ማግሥት ግን ይሄንን ዐየሁ!

➔የነበረውን እርጋታ ወደ መኝታ አሳድጎ በእንቅልፍ ሲስለመለም፣ የተጀመረውን ድርጅታዊ ትግል እና የተባባሰውን ሕዝባዊ በደል እርግፍ አድርጎ ትቶ ከተሰጠው ወንበር ላይ ያገኘውን ድል ሲያጣጥም፣

➔በብልጽግና ፓርቲ ተመስጦ አብንን ሲያከስም፣ ‹‹እውነት ምንድና ናት›› ለሚለው የፍልስፍና ጥያቄ ‹‹በሕዝብ ትግል የምትገኝ ግላዊ ጥቅም ናት›› የሚል መልስ ሰጥቶ ኑሮውን ሲያጣጥም፣

➔ከአርባ በላይ የአብን አመራሮች ጋር በሺህዎች የሚቆጠሩ ፋኖዎች መታፈናቸውን የሚደግፍ መግለጫ ላይ ሲፈርም… በደል ፈጻሚው እሱ ሆኖ ሳለ እንደተበዳይ ሲያልጎመጉም፣ ከተማረው ፍልስፍና በተቃራኒ ተሰልፎ በእራስ ወዳድ ስብዕና ሥልጣኑን ለማስረከብ ሲለግም ዐየሁ፡፡

የአማራን ሕዝብ ያለመሪ ድርጅት አስቀርቶ አምሳ ሚሊዮን ግለሰብ ሲያደርገውም ታዘብኩ፡፡

Filed in: Amharic