>

በዛሬው የፓርላማ ውሎ የግል አስተያየቴ.... (ጌጥዬ ያለው)

በዛሬው የፓርላማ ውሎ የግል አስተያየቴ…

ጌጥዬ ያለው

ወንድሞቻችን ክርስቲያን ታደለ እና ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ለጠቅላይ ሚንስትር ተብየው ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ ነው። እውነት የተሞላበትም ነው። ነገር ግን መንግሥት ተብየው የውንብድና ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ካለው የዘር ማጽዳት ዘመቻ አንፃር በቂ አይደለም። እንዳውም የዘር ማጥፋት ወንጀለኛን “ክቡር” እያሉ በዚያ ፕሮቶኮል መጥራት በራሱ ይሸክካል። በምክር ቤት ደንብና መመሪያ አስገድዶ በእንቁ የአማራ ልጆች አንደበት እንደዚያ መጠራት በራሱ በአማራ ላይ የተፈጸመ ሌላኛው ጥቃት ሆኖ ተሰምቶኛል።
ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ታላቁ የአማራ ሕዝብ አንገቱን ከቤተ መንግግሥቱ በተላከ ሰይፍ ሲቀላ እያዩ “የመረጠን ሕዝብ ጫማው ተወስዶበት እንቅፋት እየመታው ነው። ጫማዬ ይመለስልኛል እና መንገዱ ይስተካከላል ብሎ ሲጠብቅ ጣቱን እየተቆረጠ ነው” የሚል ዓይነት ሆነው ተሰምተውኛል።
 “አሁንም አሻጋሪ ነዎት ወይ?” የሚለው የዶክተር ደሳለኝ ጥያቄ በደፈናውም ቢሆን ሚዛን የመታ ይመስለኛል። ምክንያቱም መምራት አልቻልክምና ገለል በል የሚል ትርጉም ይሰጣል። ሆኖም ገለል ማለት ብቻውንም በቂ አይደለም። ገዳይ ነውና መቀጣት አለበት። ከደመኛ ጋር በዚህ ድምፀት መነጋገርም በአማራ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀል ያቃልላል።
 በተረፈ አድናቆት አንፃራዊ ነውና ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼን ከማድነቅ ወደ ኋላ አልልም። ምክንያቱም የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነውና እዚያው ምክር ቤት ውስጥ እጁን እስኪያመው የሚያጨበጭብ ወንድምም አለኝና ነው። በሸፍጥም ይሁን በሐቅ  ተወዳድሮ በሕዝብ አለመመረጡ ከታየ በኋላ፤ በዚያ የምርጫ ክልል በድጋሜ ድምፅ ሊያሰጥ ሲዘጋጅ አካባቢው በወያኔ ቁጥጥር ስር ውሎበት ማሳካት ባለመቻሉ በሌላ ሥልጣን በመንግሥት የተሾመና የአማራን መቁንን በሃሰት የሚበላ ሌላም ወንድም አለኝ።  ከዚህ አንፃር ክርስቲያን እና ደሳለኝን ለማድነቅ እገደዳለሁ።
ሆኖም ከላይ ካነሳሁት ኃሳብ አንፃር እነኝህ ሁለት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላት ምን ያድርጉ የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ከእነርሱም ሆነ ከአንባቢ ሊነሳ ይችላል። ለዚህ እኔ መልስ የለኝም፤ ታሪክ ግን ከተሞክሮ ይመልስልናል፦
ንጉሰ ነገሥታት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዚያ ዘመን ለፓርላማቸው የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይን ሊያስወስኑ አጀንዳ አቀረቡ። ሱዳኖች የግዎይን መስመርን ተከትለን እናካልና ድንበር እንሥራ የሚል ሃሳብ ነበራቸው። ይህ መስመር እንግሊዛዊው የሱዳን ቅኝ ገዥ ሻለቃ ግዎይን ድንጋይ እየካበ ያሰመረው ነው። በዚህ ወቅት የአፍሪካ ሀገራት የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ ጃን ሆይ የመሰረቱት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አንድ መመሪያ አውጥቷል። መመሪያውም “ድንበራችን ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት ነው። ከአንዳችን ቢቀነስ፤ ከሌላኛችን ቢጨመር ለአፍሪካ ለውጥ የለውም፤ አንድ አፍሪካ ነን” የሚል ነበር። በዚህ መመሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም አባል ሀገራት ተስማምተዋል። ግርማዊነታቸው የኢትዮ ሱዳን ድንበር በግዎይን መስመር መሰረት እንዲሠራና ይህንንም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው አጀንዳ ይዘው የመጡት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ያወጣቸውን መመሪያዎች ኢትዮጵያ የድርጅቱ መሪ እንደመሆኗ ራሷ አክብራ አርዓያ መሆን አለባት ከሚል እሳቤ ነው። ሆኖም ከፊል የምክር ቤቱ አባላት አጀንዳውን አምርረው ተቃወሙት። ምክንያታቸው ደግሞ “ድርጅቱ ያወጣው መመሪያ ቅኝ ለተገዙ ሀገራት እንጂ ለእኛ አይሠራም” የሚል ነበር። ተገቢ መከራከሪያ ነው። መመሪያው ላይ በዚህ መልኩ ልዩ ምክንያት (exception) አልተቀመጠም። ሆኖም አመክንዮው ትክክል ነው።
የሆነው ሆኖ በዚህ ምክንያት ፓርላማው ለሁለት ተከፈለ። ከተለመደው ፕሮቶኮል ወጣ፤ ይባስ ብሎ እርስ በእርስ በቦክስ መናረት ሁሉ ተጀመረ።
ይህ የሆነው የምክር ቤቱ አባላት ግብረ ገብነት ጎድሏቸው አይደለም። ግብረ ገብነታቸው ምነው በዚያ ዘመን በተወለድኩ የሚያስብል እንደነበር እሙን ነው። የሀገር ሉዓላዊነት፣ የድንበር፣ የርስት ጉዳይ ቁጭ ብሎ በእጅ ብልጫ የሚወሰን የፕሮቶኮል ጉዳይ ስላልሆነ ነው በድብድብ ለመግባባት የተገደዱት። የእነዚህ ሰዎች ጉዳዩን በልኩ መቃዎም ንጉሠ ነገሥቱንም ከታሪካዊ ስህተት አድኗቸዋል።
Filed in: Amharic