>
5:13 pm - Friday April 19, 1393

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥር በማውጣት...!!!” ተከሰሰ...!!! (ይድነቃቸው ከበደ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥር በማውጣት…!!!” ተከሰሰ…!!!

ይድነቃቸው ከበደ

“ስራዬና ሞቴ በሀገሬ ላይ ነው….!!!”

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

***

ለለፉት 33 ቀናት በእስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ፤ በዛሬው ዕለት ፣ ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረበ።

ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት ባቀረበው ክስ ፤ ሦስት የተለያዩ ክሶችን በተደራራቢነት ያቀረበ ሲሆን ፤ 1ኛ. በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 44(1) (2) እና 336(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ፤ 2ኛ. በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 44(1) (2) እና 337(1) ፤ 3ኛ. በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 44 (1) 2) እና 257 (ሠ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ፡ ወንጀል ክስ የቀረበበት ሲሆን ፤ አጠቃላይ ክሶቹ ” ምስጢራዊ ወታደራዊ መረጃዎችን በማውጣት ፣ የሐሰት ወይም የሚያደናግራ ወታደራዊ መረጃ በማውጣት እንዲሁም ህዝብ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ በተከታታይ እትሞች ለህዝብ እንዲሰራጭ በማድረጉ በፈፀመው መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ ማሰናዳት ተግባር ወንጀል ተከሷል” የሚል ነው።

 

በጋዜጠኛ ተመስገን ዳሳለኝ ላይ የቀረበውን ክስ ተከትሎ ፤በዋስትና ጉዳይ በግራና ቀኝ ክርክር ተካሂዷል ።ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ፤ የደንበኛቸው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ በተከሰሱበት ወንጅል ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ለፍ/ቤቱ ጠይቋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ፤ የዋስትና መብት ውድቅ እንዲሆን እና ጋዜጠኛ ተመስገን ጉዳዩን በእስር ቤት ሆኖ እንዲከታተል የጠየቀ ሲሆን ፤ በምክንያትነት የዘረዘረው ” የክሱ ብዛት ፣ ተደራራቢነት እና የወንጅሉ ሁኔታ እንዲሁም 1ኛ እና 3ኛ ክሱ እስከ 10 ዓመት የሚያስቀጣ በመሆኑ ፣ በተጨማሪ 2ኛ ክስ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ” በመሆኑ የዋስትና መብት ሊጠበቅ አይገባም በማለት ዐቃቤ ሕግ ተከራክሯል።

ለዐቃቤ ሕግ ክርክር ምላሽ የሰጡት ጠበቃ ሔኖክ ፤ ” ጋዜጠኛ ተመስገን ሀሳብን ከመግለጽና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ከመጻፍ ባለፈ ምንም ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅ ለችሎቱ”  አስረድቷል፡፡  ከዚህ በፊት በነበረው የመንግስት ሥርዓት ታስሮ ዋስትና ተፈቅዶለት፤ ለሶስት ዓመታት ሕግን አክብሮ እየተመላለሰ ፍርድ ቤት ይቀርብ እንደነበርም  ጠበቃው አቶ ሄኖክ አንስተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፤ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ አንቀጽ  67/ሀ እና  በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 6 መሰረት የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት ጠይቀዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ጋዜጠኛው ሕግን አክብሮ ወደ ፍርድ ቤት ይመጣ እንደነበርም ጠበቃው ጠቅሰዋል፡፡  ጋዜጠኛ ተመስገን ከሀገር እንዲወጣ በተለያዩ አካላትና መንግስታት ሳይቀር ግፊት ቢደረግበትም ጋዜጠኛው ግን “ስራዬና ሞቴ በሀገሬ ላይ ነው” ብሎ ከሀገር ሳይወጣ መቅረቱን  ጠበቃው ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ቋሚ አድራሻ ያለውና ህግን የሚያከብር በመሆኑፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲፈቅድለት ጠበቃው ጠይቀዋል፡፡ ዐቃቢህግ ግን ጋዜጠኛው በተደራራቢ ክስ በመከሰሱና በልዩ ሁኔታ ዋስትና ሊያስከለክል  እንደሚችልና የሰበር ውሳኔ ድንጋጌዎች ዋስትናን ሊያስከለክል እንደሚችል ጠቅሶ ዋስትና ሊሰጥ አይገባም ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዋስትናው  ላይ ብይን ለመስጠት ለአርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።

Filed in: Amharic