>

ገ በ ሬ ው ! ግብርናችን ወዴት ? (አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም)

ገ በ ሬ ው !

ግብርናችን ወዴት ?

አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ


ከርስት ከመሬቱ ፣ ገበሬ አፈናቅሎ 

ጎጆውን አፍርሶ ፣ግርግሙን ደምስሶ

ጎተራ / ጎምቢሣ ፣ ድብኝት ገልብጦ

አንድ ሰው ለማልማት 

ሺውን ኑሮ ማጥፋት

ዕውቀት ወይስ ጥበብ

ጥጋብ ወይስ ንቀት

ኧረ ወዴት ? እንዴት ?

ከዛሬ 156 ዓመት በፊት አብርሐም ሊንከን የተባሉት የተባበሩት አሜሪካ መንግሥቶች ፕሬዚዳንት የግብርና ልማት መምሪያቸውን ሲመሰርቱ ግብርናው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን ድርሻና 50 % የሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ የኑሮ መተዳደሪያው ስለነበር ” people’s department ” ብለው ጠሩት ። አገር ምድሩ የገበሬ ስለነበር ።

ዛሬ ግብርናቸው ዘምኖ በዚህ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሳተፈው የሰው ኃይል ቁጥር ወደ 2 % አዘቅዝቋል ። 

አንድ የአሜሪካ ገበሬ ከመቶ ሃምሳ አምስት ሰዎች በላይ ለዓመትና ከዚያም በላይ ሊመግብ የሚያስችል አቅምን አዳብሯል ።

የኛው የግብርና ልማት ሚንስትርም በአፄ ምንይልክ ጊዜ እንድተዋቀረና ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳስቆጠረ ይታወቃል ። 

ግብርና ለአገሪቷ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገርም 85 % ለሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የኑሮው መሠረቱ ነው ። ኑሯችን በመላው ፣ ላልዘመነው ግብርናችን ጥገኛ ነው ።

ግብርና በተወሳሰቡ የዕውቀት ዘርፎች የተሳሰረ ነው ። ለብቻውም የቆመና የተገተረ ሙያ ዘርፍም አይደለም ። እንዳስፈላጊነቱ ሁሉም የዕውቀት ዘርፎችን በረከት ያሻዋል ። ዐዋቂና ጥበብ የተመላበት መሪም ይሻል ። የሚበጠብጠው ሳይሆን ቅደም ተከተል እየጠበቀ የሚጓዝን ባለሙያ ይጠይቃል ።

ግብርናችን ዛሬም በርካታ የሰው ሃይል ቢሳተፍበትም በምግብ ሰብል ራሳችንን ልንችል ግን አልቻልንም ። የምግብ ዋስትናችን አቆልቁሏል ። በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል ። ገበሬው በቂ ምርት ስለማምረቱና በቂ ገቢ ኖሮት የመግዛት አቅሙ ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ ከግምት ባሻገር በጥናት የተጨበጠ መረጃ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም ።

ለመሆኑ መታሰብ የሚገባቸውን ዋና ዋና ቁልፍ ነጥቦችን አክሎ ወይም ታሳቢ አድርጎ ፣ አንድ ታታሪ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ስንት ሰዎች ለዓመት ሊቀልብ የሚችል ምግብ ማምረት ይችላል ? 

በደምሳሳው አነጋገር ኢትዮጵያ ስንት ብርቱ ገበሬዎች ቢኖራት ፣ ራሷን በምግብ ሰብል ምርትና በእንስሳት ተዋፅኦ ችላ መቀለብ ትችላለች ? 

የግብርናው ልማት ማነቆ የሆኑትን ዐበይት ምክንያቶችና ተያያዥ ጉዳዮችን አጥርተው ሳያበቁ የሚዘጋጁ ሥልቶችና ዕቅዶች ሁሉ ከግቡ አይደርሱም ። መሃል መንገድ ይቀራሉ ። ብዙ የልማት ፕሮዤዎች አመርቂ ውጤት አስመዝግበው አገሪቷን ከረሃብ አዙሪት አላወጧትም ።

ዕውን አዲሱ የግብርና ሚ/ር ከፍተኛ  የስራ ሃላፊዎች ይህንን ዓይን ያፈጠጠ ችግር ተረድተውና ኃላፊነት ተሸክመው የተሻለ የግብርና ልማት ፖሊስና ስትራቴጂ ነድፈው ግብርናውን ከለውጥ ማማ ላይ ያደርሱታል ብለን ብንጠይቅ አሸባሪ እንባል ይሆን ?

ወይስ ጠዋት አርፍደው ቢሮ ገብተው ከሰዓት ቀደም ብለው ወጥተው ልማቱን በሚገባ ይመሩት ይሆን ?

ገበሬንስ የክልል ሰው አይደለህም ተብሎ ከመሬቱ ሲፈናቀልና ጠመንጃህን ፍታ እየተባለ በጦር ሃይል  ሲሳደድ መሬቱ ጦም ማደሩን ከቁብ አልቆጠሩት ይሆን ?

ጎተራ ውስጥስ ያልገባ ምርት የተቀቀለ የሰብል ዘመን በሚሊዮኖች ኩንታል ቁጥር ሪፖርት ማነብነብ መደበኛ ስራ አድርጎ ማቅረብ ያምርብን ይሆን ?

ሼ ማሞ ! ጋሼ ማሞ !

ጋሼ ማሞ በግብርና 85% የጦቢያ ሕዝብ የሚተዳደርበትን የግብርና ሥራ አሰራሩን ለማዘመንና ኑሮውን በገቢ ምንጭ በሚያስገኙ ተክሎች ምርት ከፍ እንዲል ደፋ ቀና ከሚሉ የዛኔ የግብርና ባለሙያዎች አንዱ  እንደነበሩ አንድ በተባበረችው አሜሪካ ኑሮአቸውን ያደረጉ እና ወዳጄ ከሆኑ የግብርና ሳይንቲስት ጽሁፍ ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ።

ጋሼ ማሞ ያንዬ ኃላፊነትና ሥልጣን በተሰጠው ነገር ግን ስሙን በየፖለቲካው ሥርዓተ ማኀበር ከሚቀያይረው መ/ቤት ባልደረባ  አንዱ ነበሩ ። 

በሁሉም የነበሩ መንግሥታት ዘመን ያልሰሩባቸውና ላባቸውን በመስክ ያላፈሰሱባቸው የቀድሞው ሐረርጌ ግዛት ሥፍራዎች እንዳልነበሩ በግዜው የነበሩ ወዳጆቻቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡ 

 ሶየው ከጨርጨር እስከ ኦጋዴን  ኢትዮጵያን በቅንነት ያገለገሉ ነበሩ። 

ከጎረምሣነት ጉልበትና ዕውቀት እስከ ጎልማሣነትና ብስለት ። ሁሌም ከድሃው ገበሬ አኗኗር በጣሙን በቅርብነት  የስሩ ነበር።

ከቀጭኑና ቁመተ አጭሩ ባለሙያ ጋር ወደ ገጠር አብረው ለሥራ ከወጡ ስሙን የማይጠሩት አነስተኛ ድሃም ሆኑ የሞላላቸው ገበሬዎች እንዳልነበሩ የግብርና ሚንስቴር ሰራተኞች የነበሩ ቋሚ ምስክሮች ነበሩ ብል አልሳሳትም ።

ከመንገድ ዳር መስክ መሄጃ መሂናዋ ጥግ ከያዘች

ጋሼ ማሞ ! ጋሼ ማሞ! ከዓዋቂውም ከልጆችም በዜማ መሰል ድምፅ የአካባቢውን አየር ይሞላው እንደነበር ኑሮአቸውን በተባበረችው አሜሪካ ያደረጉት ወዳጄ የግብርና ሳይንቲስቱ አቶ ሰለሞን አውግተውኛል ። 

እንደ መንግሥት ሐረሪም ብሔራዊ ክልል መንግሥት ተብሎ ከነ ተቋሞቹ ከተዋቀረ በኋላ ጋሼ ማሞም በግብርናው ቢሮ በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬው ልማት ዘርፍ በሐረር ከተማውም ዳርቻ ሆኖ በቁጥር አነስተኛ ቀበሌዎች ይዞ የሚገኘው ሥፍራ ሁሉ በተለይም እየተመናመነ የነበረውን የሐረር የቀድሞዋ የፍራፍሬ አገር ክፍልነትና መታወቂያ ስሟን ለመመለስ በአመቺ ሥፍራዎች ችግኞችን በማፍላትና ለገበሬዎቹ እንዲታደሉ ለማድረግ የተለየ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መታከታቸውን ለትንሽ ወራቶችም ቢሆን አብረው የነበሩት አቶ ሰለሞን በልበሙሉነት ብናገርለትም ያስደፍረኛል ብለው አውግተውኝ ነበር ።

ለችግኝ ጣቢያው የሚሆን የፍራፍሬ ዘሮችንና መራቢያ አካላቶችን ለመሰብሰብም ሩቅ ኪሎ ሜትሮች ድረስ መጓዝም አስገድዷቸው ነበር ። ከልብ ከሰሩ የማያሸንፉት ጉዳይ የለም ።

በበርካታ የአትክልትና ፍራፍሬና ሌሎችም ፕሮዤዎችም ከምሥረታው እስከ አፈፃፀምና ክትትል ጋሼ ማሞ እጃቸው የሌለበት አልነበረም ።

ወደ ጅጅጋ መንገድ ኤረር ከሄድንማ ወደ ቢሲዲሞ መንገድ ዳርቻ በክረምቱ እሸት በቆሎ ቀጥፈውና ጠብሰው ለዕለት ጉርሳቸው ፍጆታ የሚያግዝ ገቢ ለማግኘት የሚታገሉ ገበሬዎች ዘንድ ስንደርስ እሽት በቆሎ ይዞ የማይጠጋና ግዙኝ ! ግዙኝ ! የማይል ብርድ የጠበሰውና ተመጣጣኝ ምግብ ዓይነት ያላገኙ ለመሆናቸው ወዝ የራቃቸውና የነጣጣ ፊት የሚታይባቸው የተለመደ ነበርና ጋሼ ማሞ በሁኔታቸው በማዘኑና ውስጡ በመረበሹ ገበሬዎቹን እባካችሁ!

” ኢሲኒስ ኛዳ !” ” ኢሲኒስ ኛዳ!” 

” እናንተም ብሉ! ” “እናንተም ብሉ ! ” እያሉ ምክራቸውን ሳይለግሱ አያልፏቸውም ነበር ።

የትናንቶቹ ገበሬዎች እንደዛ ኖሩ ።

ዛሬ እነዛ የጋሼ ማሞን ስሞች ደጋግመው የሚጠሩ አንደበቶች በሕይወት ካሉ አቅማቸው መድከሙን መገመት አያዳግትም ።

የዛሬዎቹስ ?

ገበሬው

ይህ ጽሁፍ የምርምርና የጥናትም እንዲሁም የማወዳደሪያና ማነፃፀሪያም አይደለም ። 

ልዩነቱ አስቀድሞ ጎልቶ ለማንም ስለሚታይና ለንፅፅርም የሚረዳ አስፈላጊው መረጃም በቦታው ሰለሌለው እንደው የአንባቢን ዕይታ ዞር አድርጎ ግንዛቤን ለመጫር ነው ። አንባቢ ለካስ ይሄም አለ እንዴ ብሎ እንዲያስብ ብቻ ይሁን። 

ምንአልባትም ሃገራችን በዚህ በሚጠቀሰው መረጃ ዕጦትም የምትዳክር ሆኖ ከተገኘም ለሁለተኛም ሆነ ለሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ማሟያ ጽሁፍ የሚሰሩም የግብርና ምጣኔ ሃብት ተማሪዎችና ተመራማሪዎችም ካዩት ጥያቄ ያጭራልና በጥልቀት ቢገቡበትም ያደፋፍራል በሚል እሳቤ ነው።

ይሄው ነው። No more ; no less !

ይህንን ከተለያዩ ጽሁፎች በምንጭነት ያገኘሁትን መረጃ ልጥቀሰው። 

ልብ በሉ ! ዝርዝር ሃተታ ውስጥ አልገባም። 

ውዠንብርም አልፈጥርም። 

ነገር ግን ዘርዘር ብሎ የተገኘ መረጃ ለሥራው ዕቅድ ታሳቢነትና እንዲሁም ለፍሬያማነትና ለልፋቱ ውጤት ሰጭነት ዋስትና ለመሆኑ ግን አያጠያይቅም ወይም አያከራክርም ። 

ድፍን ዱባ ይንከባለላል እንጂ ካልቆራረጡት ወይም ከልበጠረቁት ውስጡ ምን እንዳለው መመልከት አይቻልም ። የግብርና ልማት ስራንም ዘርዘር አድርገውና አገላብጠው ካላዩት በስተቀር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በብድር በማደልና በኋላ ላይ ገበሬውን የፊጢኝ አስሮ ገንዘቡን አለውቅቱ ማስመለስ ኪሳራ ነው። 

ልማት ሳይሆን ጥፋትን ማበራከትና የገበሬውንም ሕልውና መዳፈር ነው ።

ለመሆኑ አንድ አሜሪካዊ ገበሬ ስንት የአገሪቱን ዜጎች ይቀልባል ወይም ደግሞ ለስንት ሰዎች ለአንድ ዓመት የሚበቃ የምግብ እህል ያመርታል ? 

ጥያቄው ውስብስብ ነው ? 

አመላካች እንጂ መቶ በመቶ የጥያቄው መልስ ይሄ ነው ለማለትም አይደለም። 

ለምን ? 

ገበሬ የተለያየ ዓይነት አዝርዕትን ያመርታል። 

ሁሉም የግብርና ልማት ምርቶች ለሰው ልጅ የምግብ ፍጆታ ይውላሉ ተብለው አይታሰቡም ። 

አንዳንዱ ለሰው ልጅ ምግብ ሲውል ሌላ ጊዜ ደግሞ ለእንስሳት መኖ ፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በጥሬ ሃብትነት የሚውሉና ለውጭ አገር ኤክስፖርት ሰብልና ከድንበሩም ተሻግሮ ሌሎችንም አገር ሰዎችም ለምግብነት የሚውለውንም ምርት ስለሚያመርትና በሌሎችም ነጥቦች ስለሚለያይ ነው ። 

በተጨማሪም በመስክ የተመረተው ምርት በድኀረ ምርት አጠባበቅ ጉድለት ለጥፋትና ብክነትም ጭምር ስለሚጋለጥ ነው ። 

አንዳንዴም በምርት ዋጋ መውደቅም ምክንያት ምርቱ ሳይሰበሰብም በመስክ ላይ ይባክናል ። 

ግብርናውን ዓይነቱን የሚያውቀው ሁሉ ያውቀዋልና በዝርዝር አልገባም።

እ አ አ በ1930ዎቹ አንድ አሜሪካዊ ገበሬ ( የቤተሰብ እርሻ ) ለራሱና ሦስት ሰዎችን በድምሩ ለ4ት ሰዎች ለአንድ ዓመት መቀለብ የሚያስችል የምግብ ምርት ማምረት ይችል እንደነበር ተዘግቧል። 

ከ40 ዓመቶች ( በ1970 ዎቹ) በኋላ ግን ይህ ቁጥር በማሻቀብ ከፍ ብሎ ወደ 73 ሰዎች ደረሰ ተብሎ ተገመተ ወይም ሂሳብ ስሌት ተሰራለት ። 

ነገር ግን በ2010ቹ ደግሞ ግብርናው በሥነ ሕይወት ሳይንስ ዕውቀትና የተለያዩ አሰራራ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ በመሆኑ ወደ 155 ሰዎች ሊቀልብ የሚያስችል ምግብ ያመርታል ተብሎ በቀመር ተሰላ ። 

እንግዲህ ከላይ በታሳቢነት የተቀመጡት ሁሉ ወደ ምግብ ምርትነት ቢለወጡ ደግሞ የአኅዙ ስሌት ቁጥር በሁለትና ሦስት እጥፍ ዘሎ ፤ የዘመነው የአሜሪካ ግብርና አንድ ገበሬ ወደ ሦስትና አራት መቶ ሰዎችን ለመቀለብ ማሻቀብ ይችል ነበር።

የዚህን ቀመር ስሌት በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት በግብርናው ምጣኔ ሃብት የሙያ ዘርፍና ተያያዠነት ሙያ ያላቸው የዕውቀቱና የክህሎቱ ባለሙያዎች ቢሆኑም ስሌቱን ለመስራት ግን በርካታ መለኪያና አመላካች ነጥቦችም በታሳቢነት ይቀመጣሉ። 

ዝርዝር ነጥቦቹ ውስጥ አልዘልቅም ። 

ግን አንድ ነገር ማለት ግን ፈለግሁኝ። 

ይኽውም ማነው ገበሬ ? የሚባለውን እንደ የአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። 

በይዞታውም መጠን ( በሚያለማው ማሳ ስፋትና በሚያመርተው የሰብል ዓይነትና እንስሳት ርባታ ) ይሁን ከይዞታው ያገኘውን ምርት ወደ ገበያ ዋጋ ለውጦ መሃለቅ የሰራውን ሁሉ ዝቅተኛ መጠኑን ማስቀመጥና ሌሎችንም ። 

ይህንን ስሌት ቀመር ምን አልባት ጥሩ የግብርና ልማት አማካሪ ካላቸው ጠ/ሚንስትሩ  በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። 

የግብርና ኤከስቴንሽን ባለሙያዎች በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉት  ግን በቀላሉ የሚገባቸው አይመስለኝም። 

ቢገባቸውማ ኖሮ የግብርናው ልማት ጉዳይ በዝርዝር አንገብግቧቸው ሌት ተቀን የኢትዮጵያን ገበሬ ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል ሥልት ላይ ባተኮሩና ገጽታውን ለውጠው በተገኙ ነበር ። 

አገር የሚለማው ገበሬ ሲያድግና ሲለማ እንጂ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ባለሃብት ተብዬዎችን በምሽት ቢሊየነር ብር ጌታ በማድረግ አይደለም ። 

ራሱን፤ ቤተሰቡንና ዜጎቹን መቀለብ የማይችል ድሃ ገበሬ በበዛበትና አብዛኛውን የምግብ ሰብል ምርቶችን በማምረት ለወገኖቹ ለፍጆታ ለማቅረብ ያልቻለ አምራች ባለበት ምን አይነት ብልጽግና እንደምንመኝ ? 

ከቶውኑ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ጠቢብ መሆን የሚያስፈልገን አይመስለኝም ። 

ሌሎችን ዘርፎች መናቄና ዋጋ ማሳጣቴም አይደለም ። 

መሬቱ ለምልሞ አብቦ የምናየው

የገበሬው ድካም የሥራው ውጤት ነው

ይሄ ዜማ በ1968 ዓም  ጋሼ መሐሙድ አሕመድ በሸክላ ካሳተማቸው ዘመን አይሽሬ ዜማዎቹ መሐል አንዱ ነበር ። ጋሼ መሐሙድ አህመድ ይህን ጥኡም ዜማ ልብን የሚመስጥ ዜማውን ሲያንቆረቁር እኔ ያንዬ የ 4 አመት እምቦቀቅላ ነበርኩኝ፡፡ ዜማውን ማጣጣም የጀመርኩት በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ነበር፡፡  

በነገራችን ላይ በዚያ ዓመት ( በ1968 ዓ.ም. ) በሸክላው ላይ የተቀረፁት ዜማዎቹ በመላው ይሄ ነው የሚባል እንከን የላቸውም ነበር ብሎ መደምደም ወደ ስህተት ይወስድ ይሆን? አይመስለኝም ። ሁሉም ፍቅር ናቸው ። ግጥሞቹም ዜማዎቹም መልእክታቸው የአመታት መቆጠር አያደበዝዛቸውም፡፡ ዛሬም ቢሆን መንፈስን ያድሳሉ፡፡ ነብስን በሀሴት ያለመልማሉ፡፡

እኔ አዲስ አበባ የወለድኩ በመሆኔ መሰል የ1960ወ0ቹ የሸክላ ዜማዎች እጅጉን ይማርኩኛል፡፡  

ከልጅነት አሁን ድረስ አዲስ አበባ አለሁ ። ጓዳጎድጓዳዋ ለእኔ ልዩ ስሜት ይሰጡኛል በተለይም የቀድሞዎቹ ሰፈሮች ውቤበረሃ፣አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ሰንጋተራ፣ቶሎሳ ሰፈር፣ መርካቶ፣አዲስ ከተማ ከፍተኛ 7 ቀበሌ 34፣ከፍተኛ 1 ቀበሌ 05፣ ገዳምሰፈር፣ ጣሊያን ሰፈር፣ ጃንሆይ ሜዳ፣ቀበና ወዘተ ወዘተ አይዘነጉኝም፡፡

በእናቴ ጀርባና ከዳዴ ብድግ ስልም እምዬ እጄን ይዛም አዲስ አበባንና ባቡር መጓዜንም ትነግረኝ ነበር ።

ታዲያ የያኔ ወጣት በተለይ መርካቶ አካባቢ፣አንበሳ ግቢ የወጣቶች ሻይቤት፣ ውቤ በረሃ ዝንቦ ካፍቴሪያ፣ ዶሮ ማነቂያ ረዲ ሻይቤትና ጃኪ ሻይ ቤት፣ቴዎድሮስ አደባባይ መደሰቻ ሻይ ቤት፣ ጣሊያን ሰፈር ሚፍታህ ሻይ ቤት ወዘተ ወዘተ ሌሎች  በርካታ ሻይ ቤቶች ነበሩና ከአንዱ ወደ ሌላ ሻይ ቤትና ኬክ ቤቶች ስትንሸራሸር፣ እንዲሁም ፒያሳ ከሲኒማ ኢትዮጵያ እልፍ ብሎ ኤሊያስ ፓፓሲኖስ ህንጻ ሻገር ብሎ ይገኝ በነበረው የመሃሙድ ሙዚቃ ቤት በር ላይ፣ አያሌው ሙዚቃ ቤት  መሐሙድን ከነአይጠገቤው ዜማዎቹ ታዳምጠዋለህ ። በቃ የዕለት መዋያህ ነበር ።

ት/ቤት ለተሜ ወታደራዊውን መንግሥት መቃወሚያ ሜዳ ነበረችና በአዋጅ ደርጉ ዘግቷት ነበር ። 

ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም !

ገበሬ በሰብል ማምረቱ ሥራው በዓይነት ድካሙ ብዙ ነው ።

በተለይ ሰብል ማምረቱ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች ቀስ በቀስ ካልታገዘ ልፋቱ ብዙ ነው ።

የሰብል ማምረት ልትቆጣጠረው እንደምትችለው የፋብሪካ ምርት ሥራ ዓይነት አይደለም ።

ሰብል ማምረት ከቁጥጥራችን ውጪ በሆኑ የአካባቢ ፋክተሮች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ነው ።

የአየር ንብረቱ ከነዓይነቶቹና ጠባዮቹ ፣ የአፈርና ውኃ ፊዚካልና ኬሚካል ጠባያት ፣ ሥነ ሕይወታዊ ምክንያቶች ( ነፍሳት ተባዮች ፣አረሞች ፣ በዓይን የማይታዩቱ ረቂቅ የሰብል በሽታ አምጭ ሕዋሳቶች ) ፣ ሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በምንጠብቀው የምርት ውጤት ላይ የማይናቁ ፈተናዎች ናቸው ።

በትክክል ጋሬጣ ፈተናዎቹን ለመተንበይ እንኳን በቂ ዕውቀትና ዝግጅት እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው ።

ዘርቶ ብቻ የሚታጨድ ከመሰለን ጉዳዩ አልገባንምና ያኔ ነገር ተበላሽቷል ።

በመስክ ላይ ቡቃያው አመርቂ መስሎን ይታያል ። 

በመጪው ዕድገት ደረጃው ምን እንደሚጠብቀው ግን መገመቱ አስቸጋሪ ነውና በኩራት አያስፈነጥዘንም ። መልካም ብናቅድም የወደፊት ምኞት ነውና አልጨበጥነውም ። መትጋቱ ግን ይቀጥላል ።

ሰብል ማምረት ሥራ ከመስክ እስከ ጎተራ ፣ ከገበያ እስከ ፍጆታ ተከታታይ ሥራዎች አሉትና ክትትሉ መዛነፍ የለበትም ። 

አድሐሪያንን ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን ! ኮሎኔል መንገስተ መንግሥቱ

የገበሬዎች አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኀበር ማልባ፣ ወልባ ፣ ወላንድ

የጦቢያ ሕዝብ በቀን ሦስቴ እንዲበላ እመኛለሁ ። አቶ መለስ ዜናዊ 

ከነ ግሎባል መለስ ፓኬጃቸው ።

ጦቢያ በቆሎ ወደ ውጪ ላከች ዜናው ተረጨ ።

ሰው ሰራሽ ዝናብ አዘነብን ፣ ስንዴ በመቶ ሺ ሄክታር በክላስተር እያመረትን ነው ። ስንዴ ኤክስፖርት ዶክተር ዐብይ

ግብርናው ሴክተር እንዲለማ መመኘታቸው መልካም ቢሆንም በዘመቻ ልማት ኢንታኔ ። 

ኖረንበትም ከራርመንበትም አየነዋ ።

ግብርናው እንዲለማና ተከታታይና በማይናወጥ ዕድገት እንዲታሰር የራሱ መንገድ አለውና ፖሊሲው ከመሬት ባለቤትነት ጀምሮ ለማንኛውም ልማት መሠረታዊና አጋዥ ነጥቦች ተደጋግፈው ካልተቃኙ ማነቆው አሁንም ያንቃል ።

ስንዴና ዋግ በሽታ ምንና ምን ናቸው ?

ሌላ ጊዜ ይጠብቁኝ ፡፡ ሰላም

 

 

Filed in: Amharic