ስለ አማራ ሕዝብ ትግል አንዳንድ ነጥቦች…!!!
በሪሁን አዳነ
“… የጠላትን ጦር እየመሩ ያመጡት በበኩላቸውም እየተሰበሰቡ የጠላት መሣሪያ ላደረጉት ባንዳ የጦር አዝማች ሆነው የመጡት አባ ጆቢር አባዱላ የተባሉት ባላባት በ1928 ዓ.ም. መንግሥትን ከድተው አገራቸውንና ወገናቸውን ለመበቀል በክፉ መንፈስ ተመርተው የጀመሩት ይህ አድራጎታቸው አልበቃ ብሏቸው ጠላትን ይበልጥ ደስ ለማሰኘት ሲሉ በአውራጃው የሚገኙትን አማሮች በጭካኔ እየገደሉ ራሳቸውን ቆርጠው ያመጡላቸው ዘንድ በውስጣቸው ላለው ባንዳና ለተከታዮቻቸው ዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡
ይህንኑ ሰይጣናዊ ዐዋጅ በመከተል የአማሮችን ራስ ቆርጦ ለሚያመጣላቸው ሰው በእያንዳንዱ ጭንቅላት ሠላሳ ብር ሽልማት እሰጣለሁ ብለው የግፍ ድጋፍ የሆነ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም እንደዚህ ባላባት ልቡ በክፋትና በጭካኔ ከደነደነው ከአንዳንድ አረማዊ በቀር ይህን የግፍ ዐዋጅ መላው የጅማ ሕዝብ አልተቀበለውም፡፡ እንዲያውም ብዙዎች ርኅራኄ ያደረባቸው ያገሩ ሰዎች ለአማሮች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው አዝነው አደጋው እስኪያልፍ ድረስ በየቤታቸው ሸሽገው የግፍ ዐዋጅ ከተነገረባቸው ወገኖቻቸው የብዙዎችን ሕይወት ያዳኑ እንደነበሩ እርግጥ ነው፡፡ ለክፋት ተፈጥረው በክፋት ያደጉ አንዳንድ ርኅራኄ ቢሶች ግን ወንዶችንስ ይቅርና ሴቶችንም እንኳ ሳይመርጡ በጭካኔ እየገደሉ በዐሥር የሚቆጠሩ ራሶችን አምጥተው ለክፋት መሪያቸው ለባላባቱ ግዳይ ጥለው ዋጋቸውን ተቀብለው ሄደዋል መባልን ሰማን፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላም የሁላችንም ጠላቶች የሆኑት ጣልያኖች የተቆረጡትን ጭንቅላቶች ሲመለከቱ በውስጡ የአንገት ንቅሳት ያለበት ራስ ስለተገኘ፤ ሴቶችም በዚህ ዐዋጅ ምክንያት መገደላቸውን ተረድተው ከዚያ ቀን ጀምሮ በአገሩ ውስጥ የሚገኙት አማሮች እየተያዙ ወደ ጣልያኖች እንዲቀርቡ እንጂ ባንዳው በሥልጣኑ እንዳይገድላቸው፤ ገድሎ ቢገኝ ግን ስለአንድ አማራ አምስት ባንዳ የሚገደል መሆኑን አስታውቀው የበረታ ዐዋጅ ማስነገራቸውን ደግሞ እዚያው አጋሮ ሆነን ሰማን፡፡
በነዚያ ጊዜያት ውስጥ ጦራችን ይህ አሳዛኝና አሰቃቂ በደል መደረጉን ሲሰማ ምንም በግፉ ደሙ ቢፈላበትና ቁጣውም ህዋሳቱን ሁሉ ቢያንቀሳቅስበት ግፍ የተቀበሉትን የወንድሞቹን ደም የክፋት ምንጭ ከሆኑት ከዋናዎቹ ጠላቶቹ ለመክፈል አስቦ ጊዜው እስኪደርስ ጠበቀ እንጂ ትእዛዝ ተቀባይ ከሆኑት ወንድሞቹ (ከአገሬው ሕዝብ) ላይ ሰይፉን አልመዘዘም፡፡ ከንዱንም አላነሣም፡፡” ታደሰ ሜጫ፤ ጥቁር አንበሳ (የመጀመሪያ እትም፣ 1943 ዓ.ም. አሥመራ፤ ሁለተኛ እትም፣ 2004 ዓ.ም. አዲስ አበባ) ገጽ 77-78፡፡
ይህን ከላይ የቀረበውን የዓይን ምስክርነት የጻፉት የክስታኔ ጉራጌ ተወላጁ አቶ ታደሰ ሜጫ ናቸው፡፡ አቶ ሀዲስ ዓለማየሁም “ትዝታ” በተሰኘው ድንቅ የአርበኝነት ዘመን ትውስታ መጽሐፋቸው ስለዚህ ግፍ ጽፈዋል፡፡ ጣልያናዊው የታሪክ ምሁር አልበርቶ ስባቺ እና እንግሊዛው ምሁር ኢያን ካምቤልም እንዲሁ በስፋት ሄደውበታል፡፡
በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን የቆየና ታሪካዊ መሠረት ያለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ጋር ተያይዞ የመጣው ቅራኔ ዋነኛ ሰለባ ይኸው ሕዝብ ነው፡፡ በፋሽስቶች መጠነ-ሰፊ ውርጅብኝ ሲወርድበት የቆው የአማራ ሕዝብ በአፄ ኀይለሥላሴ ዘመንም የግፍ ሰለባ ነበር፡፡ የአፄ ኀይለሥላሴ መንግሥት አርበኞችን በግፍ ከመግደልም አልፎ ብዙ ግፍ ፈፅሞበታል፡፡ በኋላ በመጣው የነ ዋለልኝ አጥፊ ትርክት እና እሱን መሠረት አድርጎ በቀጠለው ሒደት ያለማቋረጥ የተቀጠቀጠውም ይኸው ሕዝብ ነው፡፡ ደርግም፣ ሻዕብያም፣ ወያኔም፣ ኦነግም … በአማራ ሕዝብ ላይ ያለማቋረጥ ዘምተዋል፡፡
ስለሆነም፣ ለአማራ ሕዝብ ነጻነት እታገላለሁ የሚል ማንኛውም አካል ይህንን የረዥም ዘመናት የቁልቁለት ዘመን (decline) መረዳት ይገባዋል፡፡ የቁልቁለት ጉዞው ለረዥም ዓመታት የቆየ በመሆኑ በአጭር ጊዜና በትንሽ ጥረት የሚሳካ ነገር አይኖርም፡፡ በቁጥርና በዓይነት ብዙ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ – በውጭም በአገር ቤትም፡፡ የፖለቲካ ትግል “ውድ” ስለሆነ ከፍተኛ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ የገንዘብና የጊዜ ብቻ ሳይሆን የሕይወት መሥዋዕት መክፈልም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም ልጆቿን በነጻነት፣ በእኩልነትና በዴሞክራሲ የምታስተናገድ ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ከሚታገሉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመግባባትና መከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነትን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አገር ቤት/ዲያስፖራ ሳይባል ሁሉም ለአንድ ዓላማ ቆሞ እንዲታገል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሁሉም በላይ፣ ትግሉ ረዥም ጊዜ የሚወስድ እና የጊዜ፣ የገንዘብና የሕይወት መሥዋዕት የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ እጅግ እጅግ መሠረታዊ ነው፡፡
ትናንት በመቶዎች በግፍ ይገደሉ የነበሩት ወገኖቻችን ዛሬ በሺሕዎች እየተጨፈጨፉ ነው፡፡ የምንገኝበትን አረንቋ በሚገባ ተንትነን መሠረት ያለው ሥራ ካልሠራን ነገ በዐሥር ሺሕዎችና ከዚያም በላይ ብዙዎች ያልቃሉ፡፡ ከስሜት ይልቅ ስሌትን አስቀድሞ፤ ውስጣዊ አንድነትን አጽንቶ እና ከሌሎች ወገኖችቻችን ጋር ኅብረት ፈጥሮ ለነጻነት፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ መታገል ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ አካላት የህልውና አደጋ ተጋርጦብን ሳለ ስለ ዴሞክራሲ ማውራት ቅንጦት ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡ ሆኖም በእኛ እምነት ዴሞክራሲ አንዱ የህልውና አደጋውን መቀልበሻ መንገድ ነው፡፡ ዴሞክራት ሳይሆኑ ሌሎችን ከጎን ማሰለፍ አይቻልም፡፡ እውነትም ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነጻነት፣ እኩልነትና ፍትሕ እንደሚታገሉ ሳያረጋግጡ የሌሎችን ወገኖች እምነት ማግኘትና ከእነሱ ጋር አብሮ መሥራት አይቻልም፡፡ ጠንካራ ኅብረት መመሥረት ባልተቻለበት ሁኔታ ደግሞ አሁን ያለውን አገር አፍራሽ ፌደሬሽን ማስተካከል እና በሌላ (የግልና የቡድን መብት የሚያስከብር) ፌደራላዊ ሥርዓት መተካት ፈጽሞ አይቻልም።