>

“ይህ ትውልድ! ---“ (ፊልጶስ )

“ይህ ትውልድ! —“

(ፊልጶስ )


ትውልድ በዚህ ትውልድ ውስጥ አለ። የአንድ ሀገር ትውልድ እንደ ሰንሰለት የተሳሰረና የተያያዘ ነውና፤ ስልጣኔውም ሆነ ኋላ ቀርነቱ፣ ሀይማኖቱም ሆነ ባህሉ፣ ደግነቱም ሆነ ክፋቱ፣ ባለጸጋነቱም ሆነ ድህነቱ፤ በጠቅላይ የያ ትውልድ ማንነትና  የስራ ውጤት በዚህ ትውልድ ላይ ይወራረዳል፤ ይንጸባረቅል። ታዲያ እንደ ግዜው፣ እንደ ሀገራዊና እንደ አለም ሁናቴ፤ የትውልዱ ትስስርና ተጋቦ፤ በሂደት ውስጥ ደብዝዞ ወይም ጎልቶ ሊታይ ይችላል። አንዳንዴም በያ ትውልድ ያስከበር  የነበረው በዚህ ወይም በአዲሱ ትውልድ የሚያሳፈር ሊሆን ይችላል። 

በታደሉትሀገሮች ያሉ ትውልዶች ለሚመጣው ትውልድ ካለፈውና  ካ’ሉበት የተሻለ ነገር ለማስተላለፍና ለማውረስ ይጥራሉ፣ ይታገላሉ:: ሀላፊነት በተሞላበት መንገድ፤ ዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገውንም ትውልድ እያሰቡ ይሰራሉ።እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፤…..” ሳይሆን እኔ ከሞትኩ ትውልድና የሰው ልጅ የሚጠቀምበትና የሚተባበሩበትን መንገድ ሰርቼ ልለፍ ይላሉ። ጥላቻ ባለበት ፍቅር፣ በደል ባለበት ፍትህና ይቅርባይነት፣ መናናቅ ባለበት መከባበርና መተሳሰብ፣ በድህነት ፋንታ ባለጽግነትን እያሰፈኑ፤ የተጣመመውን እያቃኑ፣ የወደቀውን እያነሱ፣ ለሃሳብ ልዕልና፣ ለህዝብና ለአገር ቅድሚያ ሰተው፤ እንዲሁም  በጋራ ሀገር ላይ፣ የጋራ ሀላፊነት እንዲኖር ይሰብካሉ፣ ያሰተምራሉ። ለዚህም ሙሉ ግዜያቸውናንና እውቀታቸውን ብሎም ህይወታቸውን ለተቀደሰው ምግባር መሰዋት ያደርጋሉ።ባልታደሉትሀገሮች ደግሞ ትውልዶች ተቃራኒውን ይፈጽማሉ።  

አንድ ሀገር በአንድ ትውልድ ብቻ አንደማትገነባ ሁሉ፤ በአንድ ትውልድም አትፈርስም። በርግጥ መገንባት እንደ ማፍረስ ቀላል አይደለምና፤ ለዘመናት በብዙ የትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባች ሀገር በአጭር ግዜ ውስጥ በተውሰኑ ትውልዶች ልትፈራርስና የነበራት ሁሉ እንዳልነበራት ሊሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ እኛ ጥሩ ምሳሌ  ነን። 

እውነተኛ ፍትህና ነጻነት፣ ባለበትና በተገነባበት ማህበረሰብ ውስጥ፤ ትውልዱ ሁሉ እኩል ተጠቃሚ ሲሆን፤ እኩል ሀላፊነትም አለበት።እኔ ብቻ!የሚለው የሰው ልጅ እስከ አሁን ድረስ ያልተገራ ባህሪው አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ፍታዊ ህግ ቶ፤ ሁሉም ዜጋ ከህግ በታች ይተዳደርል። ይሁን እንጅ የተውሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖችተደራጅተውና አደራጅተውሀይልን መሥሪያ በማድረግ የአንድን ሀገር ትውልድ እጣፋንታ ሲቆጣጠሩና ሀገርንም የግላቸው የሚያደርጉበት ሁኔታ ብዙ ግዜ በአለማችን ተከስቷል። ስለዚህም ህግ ሳይሆን ሀይል መሥሪያ በሆነባቸው ሀገሮች የሚኖር ትውልድ በድህነት፣ በጎሰኝነት፣  በስደት፣ በውርደት፣ በፍርሀት፣ በድንቁርናና በፍትህ እጦት የሚሰቅይ ብቻ ሳይሆን፤  ለመጭው ትውልድም የሚያወርሰው ይህንኑ፤ የመሳሪያን ገዥነትናእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልን…” መርህ ነው። ይሁን እንጂ በያዝነው ዘመን ብዙ ሀገሮች ከሀይል አዙሪት ተላቀው በህግ የበላይነት የሚያምንና የሚተዳደር ትውልድ አላቸው።   

ብዙ ጥንታዊና ገናና  ስልጣኔ ያላቸው አገሮች  በዓለማች ላይ ቢኖሩም በመሃል ግን ሥልጣኒያቸውና ግዛታቸው ፈርሶ በሌሎች አገሮች ቅኝ ግዛትና አስተዳደር  ውስጥ ውለዋል። ነገር ግን  እኛው ራሳችን፤ የራሳችን ታሪክ ”ተረት-ተረት” ለማለት ብንከጅልም፤ ግዛቷ ይጥበብ እንጅ፣ ገናናነቷ ይኮሥሥ እንጅ፣  ለሺ ዘመናት   ሥርወ-መንግስቷ ሳይቋረጥ በትውልዶች ቅብብል  ከዚህ የደረሰች አገር፤ እስከ ዚች ሰዓት ድረስ ያለች   ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያኖች ነን።  

ታዲያ በዓለማችን በአሳዛኙነቱ የሚጻፈው ታሪካችን  “እንዴት  የዛሬው ኢትዮጵያዊ ትውልድ   በማንኛውም የሰው ልጅና የአገራት መስፈርት ውስጥ የዓለም ጭራና ተመጽዋች ለመሆን በቃ?”  የሚል መጠይቅና መመራመሪያ ይሆናል።

 የዓለም ጭራና ተመጽዋች  ብቻ መሆን  አልበቃንም፤ ከብዙሃኑ ህዝብ ፍላጎትና እምነት ውጭ፤ ርስበርስ ተበላልተን እንድንጨራረስ የአገሪቱ ሃብት አሟጠን በልምና ጠምንጃ  ተራርደን አገር አልባ  ለመሆን ያለ የሌለ አቅማቸውን አይተጠቀምን  ነው።

ቅዱሱ መጸሃፍ  ” —-‘ርስ- በርሳችሁ በትበላሉ፤ ርስ-በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ::—” ብሎ መክሮን ነበር። እኛ ግን እንኳን ምክር መከራም ስላልመከረን ፤ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የእድገት ጎዳና ውጭ  በመውጣት የደሃ ወገናችን ሃብትና ንብረቱ አልበቃን ብሎ፤ በማንንቱ ካላጠፋነው ብለን፤ በየቀኑ የንጹሃን ደም  እንደ  ጅረት እናፈሳለን። በምድር ላይ የሰው ልጅ ሊፈጽመው ቀርቶ ያልሰመውን ግፍ በወገናችን ላይ እንፈጽማለን። ግን እስከመቼ??? 

በ’ውነቱ እስከ አሁን በተደረገው ጦርነትም ሆነ የዘር ማጽዳት ፍጅት ምን አተረፍን?? ርግጥ ነው አገራችን አሁን ካለችበት  አሳዛኝና ዘግናኝ ሁኔታ እንዳትደርስ ብዙ -ብዙ ተብሏል።  ብዙዎችም ኢትዮጵያዊያን መሰዋእት ከፍለዋል፡ እየከፈሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጅ ”ከድጥ ወደ ማጡ ” ገባን እንጅ  ጠብ ያለ ነገር የለም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል  የውሃ ሽታ ሆኖ፤ በገዥዎቻችንና በህዝብ መሃል ያለው ትግል የህልውና ሆኖ አረፈው።  በተለይም ባለፋት ዓመታት መምበሩን የተፍናጥጡት በኢትዮጵያዊያንና በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበዱ ብቻ ሳይሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያን ካላጠፋ እንደማይተኙ ላለፋት ሃምሳና ሰላሳ ዓመታት አስመስክረዋል።

ታዲያ ጥያቄው እንድንጠፋ የተፈረደብን  ኢትዮጵያዊያን  እንደ ‘’ሰጎን ጭንቅላታችን  አሸዋ ውስጥ ቀብረን’’  ተራችን  እየጠበቀ  ነው ወይስ   ካለፈው ትምህርት ወስደን ተደራጅተን መርህ ያለው ትግል በማድረግ ራሳችንና አገራችን ፤ ብሎም ወገናችን እንታደጋለን? 

እንደ እኔ እምነት  ጠላቶቻችን በቀደዱት ቦይ ሳንፈስ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነታችን ከመታገልና   ህልውናችን ከማስከበር ሌላ አማራጭ የለንም።

 

ከዚህ ላይ መሰመር ያለበት ጉዳይ አሁን ለደረስንበት የህልውና ጥያቄ  ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በማጥፋት ላይ ካሉት መመብሩን ከተፈናጠጡትም አሳራጆችና ጫካ ካሉት አራጆች ይልቅ ተጠያቂዎቹ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ  አባ ዮሃንስ የተባሉ የጥንት  ኢትዮጵያዊ  መምህር ናቸው

  ።  በተለያየ ግዜ በተለያየ መንገድ ቢተረክም ጭብጡ እንደሚከተለው ነው።

ከአስራ ሁለት እስከ አስራ አምስት ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ተሰባስበው ይጫዎታሉ። አባ ዮሃንስ  ወደ የሚጫዎቱት ልጆች ሲሄዱ ፤ ልጆቹ ጨዋታቸውን አቋርጡ። የእግዚአብሄርን  ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፤ አባ ልጆቹን በየተራ ስለ ትምህርታቸው ጠየቋቼው።

 ከአንዱ ልጅ በስተቀር ሁሉም  እየተማሩ እንደሆነና እንዳዶቹ የዳዊት  ትምህርትን እንደጨረሱ፤ እንዳዶቹ ቅኔ  መቀኘትም እንደጅመሩ ነገሯቸው። አንደኛው ልጅ ግን ትምህርት ቤት እንዳልገባና ምንም እንዳልተማረ ነገራቸው።

 አባም በሁኔታው ተገርመው ፤ ” ልጄ! –ለምንድነው  ከሌሎቹ ተለይተህ  አንተ  ትምህርት ቤት ያልገባህው?” ሲሉ ጠየቁት። ልጁም ” የምበላው አልነበረኝምና ትምህርት ቤት አልገባሁም።” አላቸው።

አባ ዮሃንስም ” ታዲያ እስከ አሁን ምን እየበላህ  ኖርክና  ”ደደብ” ሆንክ?” አሉት ይባላል።

 

አሁን እኛም ”ኢትዩጵያ! ኢትዮጵያ! የምንል ትውልዶች መንደርተኞችና ጎሰኞች   ተደራጅተውና አደራጅተው ከብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብና ፍላጎት ውጭ  መመበሩን ይዘው፤ አገር ሲያፈርሱና የዘር ማጽዳት ሲያካሄዱ ፤ እስከዚች ሰዓት ድረስ  ምን እይደረግን ነው??  ለዚህም ነው አልበርተ አንስታይን ”ዓለም የምትጠፋው እኩይ ምግባር በሚፈጽሙ ሳይሆን ዝም ብለው በሚመለከቱ  ሰዎች ነው።” ያለው።

እስከ አሁን ድረስ እልፍ- አዕላፍ ግዜ  ሰበብ ቢደረድርም እንደ ከብት ከመታረድና የበይ ተመልካች ከመሆን አልዳንም። አድንምም።  

”ለምትፈለገው ነገር የማትታገል ከሆነ፤ ስለ አጣኽው ነገር አታልቅስ።” ይባላል። ባለፋት  ዓመታት ብዙ ነገሮችን አተናል።  ማጣት ብቻ አይደለም አሁን ጥያቂያችን የህልውና ሆኗል።  ታዲያ በዚህ ሁሉ መሃል   ያጣነውን ታገለን ማስመለስ አይደለም፤ ለወደፊቱም ሊደርስብን ከሚችለው ከመታገል ይልቅ   የለቅሶና የብሶት ፓለቲካን ትግል አድርገነዋል። ይህ ትውልድ እስከ አሁን ካሳለፈነው የለቅሶና የብሶት ፓለቲካ ጋር  መፋታታ አለበት።

ለቅሶ የሚወልደው ለቅሶን ነው፤ ትግል ደግሞ ትግልን ይወልዳል።  አሁን በየአቅጣጨው ያሉት ችግሮች በጣም አደገኛ ብቻ ስይሆኑ  ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ከመጡ ውለው አድረዋል። ትልቁና ዋናው  የአገራችን ችግር ደግሞ  ራሱ መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ነው። ታዲያ መንግሥት ነኝ የሚለው ገዥ ራሱም እየፈረስ መሆኑ ብቻ አይደለም  አገርና ህዝብ ይዞ እንዳይፈርስ ፤ ከልቅሶና ከብሶት የወጣ ተግባራዊ ትግል ያስፈልጋል።

 ገዥው ኃይል ኦነግ-ሸኔ በሚል  አራጅና ዘር አጽጅ  አሰማርቶ፡ ከቻልኩ ሁሉንም  ህዝብ እገዛለሁ፤ ካልቻልኩ ከወያኔ ጋር ተደራድሬ  ”ኦሮሚያን” ማንም አይወስድብኝም ብሎ በህዝብ ደምና ህይወት  የሚነግድ  የጎሳ ቡድን መሆኑን ደጋግሞ አረጋግጦልናል።  ስለዚህ ለወቅቱ የሚመጥን ትግል እንጅ በቅሶና በብሶት ወይም በአቤቱታ  ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ ተገንዝበን፤ ታገለን በማታገል   በውስጥም በውጭም  እንደራጅ።

የአሚሪካ መራሂ መንግስት የነበሩት ጄ. ኬኔዲ  በአንድ ንግግራቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር፤   

“’ትክክለኛውን መልስ እንጂ የሪፐብሊኩን መልስ ወይም ዲሞክራሲያዊ መልስ አንፈልግ። ዛሬ ሆነ ለወደፊቱ የራሳችንን ሃላፊነት እንውሰድ:;’’

እናም- ዛሬ ራሳችን ኃላፊነት ወሰደን ህልውናችን  እናስከብር። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ  አገርና ሥረዓተመንግሥት እንዲኖረን የሚያስፈልገውን መሰዋዕት ሁሉ ከፍለን በአሸናፊነት እንውጣ።  ምን ፈትናው ቢበዛ በመጨረሻ  እውነትና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ ነውና።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

ፊልጶስ E-mail: philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic