>
5:26 pm - Tuesday September 15, 6020

ከታጋቹ አንደበት  (ጌጥዬ ያለው)

ከታጋቹ አንደበት

ጌጥዬ ያለው


ወራሪው ኦሕዴድ-ብልፅግና #በአማሮች ላይ የሚያደርሰው አፈና እና እገታ ቀጥሏል። የአማራ ወጣቶች ማሕበር – አዲስ አበባ፤ ሸዋ ቅርንጫፍ የአደረጃጀት ዘርፍ ሓላፊና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድሜ ወጣት #ሰለሞን ልመንህ ለ11 ቀናት በጨለማ ቤት ታግቶ አድራሻው ጠፍቶን ከቆየ በኋላ ተፈቷል። ሰሎሞን ስለሁኔታው እንዲህ ይለናል፦

አዲስ አበባ፤ ሐና ማርያም አንድ ሕንፃ ውስጥ ነበርኩ። ስድስት ሰዎች መጡና በተቀመጥኩበት ከበቡኝ። አንደኛው ጠረንጴዛ ላይ የነበረ ስልኬን አነሳ። ሌሎች ተባብረው ክንድና  ክንዴን በመያዝ ከተቀመጥኩበት አንጠልጥለው ክፍት ሆኖ ሲጠብቅ ወደ ነበረው ቪ8  መኪና ውስጥ አስገቡኝ። እንዳስገቡኝ አንደኛው ዓይኔ ስር በቡጤ መታኝ። ሌላኛው ደግሞ ሽጉጥ ደቀነብኝና እንዳትንቀሳቀስ እያለ አስፈራራኝ። ከዚያም ዓይኔን በጭምብል ሸፍነው መኪናውን ነዱት። በዚህ መሀል ደብድበውኝ ስለነበር ስወራጭ ጭብሉን ፈትቼው ስታዲዮም አካባቢ መሆኔን  አየሁት። መልሰው አሰሩትና ጉዞ ቀጠልን። ከደቂቃዎች በኋላ ራሴን ጨለማ ቤት ውስጥ አገኘሁት። ይህ ቤት የት እንደሆነ አላውቅም። የባቡርና የአምቡላስ ድምፅ ይሰማኝ ነበር። ብቻ ወደ ጦርኃይሎች ይመስለኛል።

ዓይኔን ሸፍነው ምግብ በስሃን ይሰጡኛል። ወደ መፀዳጃ ቤት ስሄድም ዓይኔን ሸፍነው ረጅም ፎቅ በደረጃ ያስወጡኛል፤ ስመለስ በሌላ ደረጃ ቀይረው ያመጡኛል። በዚህ ሁኔታ አስር ቀን ቆይቼ በ11ኛው ዕለት ምሽት 4 ሰዓት ጎተራ፤ ቀለበት መንገድ ላይ ዓይኔን ሸፍነው ጥለውኝ ሄዱ። “አንተን አስረን አለቀልብም። ከድርጊትህ ባትቆጠብ እንገድልሀለን” ብለውኛል።

በጨለማው ቤት ስሰብት ሌላም ታፋኝ እንዳለ ኮቴ ሰምቻለሁ። በመርዝ ይገድሉኛል በሚል ስጋት እስከ ስድስት ቀን ድረስ ምግብ ያልበላ እንዳለም ሰምቻለሁ።

ዓይኔን እንደተሸፈንኩ የመርማሪዎች አለቃ ይመጣና ጉልበቴን መትቶ “አንድ ሳታስቀር ንገራቸው” ብሎኝ ይሄዳል። እርሱን ተከትለው መርማሪዎች ይመጡና አራት ጥያቄዎችን ደጋግመው ይጠይቁኛል። እነርሱም፦

1. የአማራ ወጣቶች ማሕበር ከባልደራስ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

2. የሚያበረታቷችሁ የመንግሥት ባለሥልጣናት እነማን ናቸው?

3. ከውጭ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግላችሁ ማን ነው?

4. የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለምን ታደራጃላችሁ? የሚሉ ናቸው።

ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ አፍነው ካሰነበቱኝ በኋላ ሲለቁኝም ወጣቶችን እንዳላደራጅ አስጠንቅቀውኛል። ማሕበራችን እንደማንኛውም ሲቪክ ድርጅት ከባልደራስ ጋርም ሆነ ከግለሰቦች ጋር ሕጋዊ ግንኙነቶች ማድረጉን እንደሚቀጥል፤ ሕጋዊ አደረጃጀቱንም እንደማያቋርጥ ነግሬያቸዋለሁ።

መነኩሴ አባቴ ከገጠር መጥቶ እኔን ፍለጋ በየፖሊስ ጣቢያው ሲንከራተት ነው የሰነበተው። የእርሱ ጫና ይመስለኛል ያስፈታኝ።

ይሄ ግፍ ማብቃት አለበት!

Filed in: Amharic