>

ይድረስ ለ ጠቅላይ ሚኒስትር  ለዶ/ር አቢይ አህመድ  (ዶ/ር ኃይለመስቀል ተፈራ)

ይድረስ ለ ጠቅላይ ሚኒስትር  ለዶ/ር አቢይ አህመድ 

ዶ/ር ኃይለመስቀል ተፈራ


ጉዳዩ፤ በመቶ ሺዎች ቤት ቆጣቢ ዜጎች ህጋዊ መብት ላይ በአዲስ አበባ አስተዳደር ለተፈጸመ የማጭበርብር ወንጀል የቀረበ ጥያቄና ምክረ ሃሳብ፣

***

ሞራል እና ኃላፊነት የሰሞኑ የኮንዶሚኒዬም እጣ አወጣጥ ተጭበርብሯል የሚለውን ዜና ሰምቶ እንዳላልፍ ያስገድዱኛል፡፡ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የነበረ ጥርጣሬ ምስጋና ለባለቤቱና ለተጠቃሚው ዜጋ ይሁንና ሌብነቱ ተጋልጧል፡፡ይህ ምላሽ ቅን ከሆነ ወደ መፍትሄው አንድ እርምጃ  የሚያደርስ ነውና ይበል ያሰኛል፡

መንግስትን አምኖ ከሌለው ቆጥቦ በተስፋ የቤት ባለቤት ለመሆን ከሚጠብቀው ዜጋ መብት ላይ ረግጦ መረማመድ ተራ ወንጀል አይደለም፡፡ ታስቦበት የተፈጸመ ግዙፍ ወንጀል፡፡ እምነት ማጉደል ብቻውን የሚበቃው አይመስለኝም፡፡ የሙያ ስነምግባርም ተጥሷል፣ የጎላ ኢሰብአዊነትና ሌብነትም ይታያል፡፡ ችግሩን አስከፊ ያደረገው ከውጪ በመጡ ሌቦች ሳይሆን የውስጥ ሌቦች (Insiders) ድርጊቱን  በተደራጀ መንገድ መፈጸማቸው ነው፡፡ ልባችንን ያደማል፡፡

ገለጥ አድርገን ካየነው ሌቦቹ የማይገባቸውን  እንዲያውም ያልቆጠቡ ሰዎችን ጭምር  እጣ እንዲያገኙ አመቻችተዋል፡፡ ሆን ተብሎ የታቀደ የመረጃ ማፋለስም ተፈጽሟል፡፡አስተዳደሩ ምን እየሰራ ነበር የሚል ጥያቄ ይጠይቁልን፡፡ አዲስ አበባ ግዙፍ ከተማ በመሆኑ የፌዴራሉን መንግስት ቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ይፈልጋልና፡፡

እንደሚያውቁት የመኖሪያ ቤት ጉዳይ እንደ ተራ የሚታይ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ የመንግስት የቤት ፈላጊውን ፍላጎት ለማሟላት ያለው አቅም አናሳ መሆን በአንድ በኩል፤ የቤት ፈላጊው ሁኔታም በትክክለኛ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አለመሆን እና በቤት ልማቱ ላይ የተንሰራፋው ዙሪያ ገብ የሌብነት መረብ መደደር አሳሳቢ ሆኖ አለ፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር እንዝህላልነት ባዝንም ላሳዩት ቅንነት አድናቆት አለኝ፡፡ ቅንነት ከተጠያቂነት የማያስመልጥ ቢሆንም፡፡

ከዚህ ቀደም፣

በቤት ልማት ፕሮግራም ትግበራ ሂደት የቤት ማስተላለፍ ስራ ትከክለኛ የቤት ተጠቃሚዎችን  አጣርቶ፣  ለይቶ የማስተላለፍ ተግባር በተቀናጀና በጠራ መረጃ ላይ ተመስርቶ ሊስተናገድ የሚገባው አብይ ስራ ነው፡፡ የሚተላለፉ ቤቶችን በተመለከተም የተሟላና አስተማማኝ መረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት እና በዳታ ቤዝ  እንዲደገፍ መደረጉንም አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን ስራም ኢንሳ በኃላፊነት ወስዶ እንደሰራውም ጭምር፡፡

እንግዲህ ቀዳሚው ጥያቄ የተሰበሰበውን የተመዝጋቢዎች መረጃ በወጉ አደራጅቶ እና በአይቲ ሲስተም አስደግፎ ለውሳኔ አሰጣጥ በሚያመች መልኩ መያዝ እና መጠበቁ እንዴት ነበር ብለንም እንጠይቃለን?  እኔ እንዳማስታውሰው በወቅቱ የጥበቃውን ስራ ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ መረጃው ተደራጅቶ በልዩ ሁኔታ 24/7 እንዲጠበቅ አድርገንም ነበር፡፡ መረጃዎችን በጥራት ሰብስቦና አደራጅቶ እንደዚሁም በአይቲ ሲስተም አስደግፎ ለውሳኔ እና ለዕጣ አወጣጥ በሚያመች መልኩ መያዝ ላይ ከአዲስ አበባ አመራሮች ጋር ከአንድ ዓመት በላይ ባደረግነው ጥናት እንደተግባባንም ትዝ ይለኛል፡፡

የእጣ ማውጫ ሲስተሙን ይበልጥ በማጠናከር ለዕጣ የሚቀርቡ ቤቶችን መረጃ ጭምር በማካተት ቤቶችን የማስተላለፍ ተግባር ላይ ማተኮር እንደሚገባ አጽንዖት የተሰጠበት ነበር፡፡ ስራ ላይ ያለው ሲስተም ቀደም ሲል የተከሰቱ ችግሮችን በተለይ የቤት ዋጋ ስሌትንና የስም ስህተትን በሚፈታና በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ የተቃኘ ሲስተም ሊዘረጋ እንደሚገባ፣ የተላለፉትን ቤቶችን መረጃም በሲስተሙ በማካተት የተሟላና የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ሲስተም ተጠንቶ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተጠቁሞም ነበር፡፡

በጥናቱ ወቅትም በቀጣይ ከሚኖረው በርካታ ግንባታ እና ተመዝግቦ ከሚጠባበቀው የህብረተሰብ ክፍል ብዛት አንፃር የቤት ማስተላለፉን ተግባር በሚገባ በተደራጀ የመረጃ ስርዓት ካልታገዘ ስራውን የበለጠ ውስብስብ ሊያደርገው እንደሚችል፣ ተቋሙ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ የመረጃ ማዕከል ሊኖረው እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቶ ነበር፡፡

የመረጃ ማዕከሉ የተለያዩ ሰርቨሮች፣ ኮምፒውተሮችና ለኔትወርክ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ተሟልተውለት እንዲሰራ እና ከክፍለ ከተሞች እና እንደ እንደአስፈላነቱ ከግንባታ ጽ/ቤቱና ከባንኮች ጋር ደረጃ በደረጃ በኔትወርክ ሊተሳሰር እንደሚገባ እና ግልጽ የሆነ የመረጃ ጥብቅነት ኦዲት ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም ከስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡

 

የተሰበሰበው የአንድ ሚልዮን ቤት ፈላጊዎች መረጃ በአይቲ ሲስተም ተደግፎ ማደራጀት እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስቀመጥ ቀዳሚው ተግባር በመሆኑ ጥሬ መረጃው በኢንፎርሜሽን መረጃ ደህንነት ኤጀንሲና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳታ ቤዝ ተከማችቶ ያለ መሆኑ አውቃለሁ፡፡

ይህ በአይቲ ሲስተም ተደግፎ የተደራጀው መረጃ ተረክበው ደህንነቱ በጠበቀ መልኩ መያዝ ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩና የኤጄንሲው ነው፡፡ አሁን የሃላፊነት ለውጦች በመደረጋቸው እንደሰማነው ደግሞ ዋናው የማጭበርበር ድርጊቱን የፈጸመው ሳይንስና ኢኖቬሽን መስሪያቤት መሆኑ  ችግሩን ያከብደዋል፡፡ በዚህ እምነት ማጉደል ቅሌት የተነከረው ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በህግ ፊት ቀርቦ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የዲጂታል ወንጀሎች ህግ ማዕቀፍ ምናልባት  ካለን፡፡

ለማንኛውም ከዚህ በኋላም ቢሆን ያሉ ቤት ፈላጊ ጥሬ መረጃዎቹ በንክኪ ምክንያት የጥራት ችግር እንዳለባቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ስለሆነም ሁሉም ወደ ዕጣ ከመሄዱ በፊት መጣራት ይገባዋል እላለሁ፡፡ይህ ብቸኛው የመተማመኛ መንገድ ነው፡፡

መፍትሄ ሃሳብ፣

ይህ የማስተካከያ ሥራ የሚከተሉት ደረጃዎች እንዲኖሩት ቢደረግ የተጎጂዎችን ስሜት በተወሰነ መልኩ ያሽር ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

1)ወጣ የተባለው ዕጣ ፍትሃዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ክስተት በመፈጠሩ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ይደረግ፣

2)ቤት የሚገነባላቸው እስካሁን በትክክል እየቆጠቡ ያሉት የቤት ተመዝጋቢዎች በሙሉ ለዕጣ ከመቅረባቸው በፊት ስለአዲስ አበባ ነዋሪነታቸው የሚገልፅ መታወቂያ ወይም ብሄራዊ መታወቂያው የሚደርስ ከሆነም ብሄራዊ መታወቂያ እና የጣት አሻራ ሰጥተው ማንነታቸውን፣ የአዲስ አበባ ነዋሪነታቸውንና አድራሻቸውን ድጋሚ እንዲያረጋግጡ ማድረግ ፣ የመታወቂያው ኮፒና የጣት አሻራው ከተደራጀው የተመዝጋቢዎች የመረጃ ቋት ላይ ጨምሮ መያዝ፣ ከተቻለ የጣት አሻራ አሰጣጡ በገቢዎችና ጉምሩክ እንደተደረገው ኤሌክትሮኒካሊ/ባዮሜትሪክ/ በመውሰድ በቀጥታ ከተደራጀው የተመዝጋቢዎች መረጃ ቋት ውስጥ መጨመር፣ ይኸም ለዕጣ ለመቅረብ እንደ-ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ፡፡ በዚህም በርግጥም የሚታወቁ ትክክለኛ ተመዝጋቢዎች መሆናቸውን፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውን፣ እንደዚሁም ባልና ሚስት የተመዘገቡ አለመኖራቸውን (ከሚሰጡት አድራሻ በመነሳት) ማጣራት፡፡ ከዚህ በመነሳትም አስፈላጊው ማስተካከያ ማድረግ፡፡

3)በዚህ መልክ የተደራጀው የተመዝጋቢዎች መረጃ እየተደራጀ ካለው ካዳስተር ጋር በማመሳከር/በማናበብ ተመዝጋቢዎቹ ቤት ወይም መሬት የሌላቸው መሆኑን ማጣራት፣ ከዚህ መነሳትም አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ፣

4)ተመዝጋቢዎቹ ቀደም ሲል ከኮንዶሚኒየም ፕሮግራሙ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ እስካሁን ዕጣ ከወጣላቸው ተጠቃሚዎች ዝርዝር መረጃ ጋር ማመሳከር/ማናበብ፣

5)በዚህ ሂደት አልፈው ትክክለኛ ቤት ፈላጊና ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው መሆናቸው የተረጋገጡት ለዕጣ ማቅረብ (ሌሎች የሚጠበቅባቸውን ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላታቸውን ማረጋገጥ)፡፡

6)ፍትሃዊ የሆነ እና ከማንኛውም ንክኪና ተንኮል የጸዳ የቤት እጣ ኮድ እንዲዘጋጅ እና ስራ ላይ እንዲውል እና አፈጻጸሙንም ኦዲት ሊያድርግ የሚችል ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም፣

7)የዕጣ አወጣጡ ልክ እንደአሁኑ በይፋ እንዲፈፀም ማድረግ፡፡ ኢንሳ በቅርቡ ያዘጋጀውን የሎተሪ ሲስተም አስተማማኝቱን በሙከራ በማረጋገጥ ሲታመንበት ተግባራዊ በማድረግ፡፡ የዕጣው ውጤት ጊዜያዊ እንደሆነ ማሳወቅ፡፡ የዕጣው ውጤት የሚፀናው ተጨማሪ ማጣራት ከተደረገ በኋላ ይሆናል፡፡ ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞችም አሁንም እንደሚደረገው ዝርዝራቸውን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ለህዝብ ይፋ በማድረግ (በጋዜጣ፣ በህዝብ ማስታወቂያ፣ በዌብሳይት፣ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥንና፣ በወረዳ ላሉ ባለድርሻ አካላት ማሳወቅ፣ በሁሉም ወረዳዎች የማስታወቂያ ሰሌዳ ዝርዝሩን መለጠፍ) ጥቆማና ግብረ-መልስ መቀበል፡፡ የሚመጣ ጥቆማ ካለ ማጣራት፣ ማረጋገጥና ማስተካከል፤ ከሌለ ውጤቱን ማፅደቅ፡፡

8)ልክ እንደ ተመዝጋቢው መረጃ ሁሉ ለዕጣ የሚቀርቡ መረጃዎችም የጥራት ችግር እንዳለባቸው ታይቷል፡፡ ስለሆነም በቀጣይ የቤቶቹን ዝርዝር መረጃዎች የሚሰበሰቡበትና የሚረጋገጡበት አስተማማኝ አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ የእያንዳንዱ ሳይትና ቤት መረጃ በሳይት ጭምር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ፕሮጀክት ፅ/ቤቱ ለዕጣ የሚቀርቡ ቤቶችን ሲያስረክብ መረጃውን ያዘጋ፣

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

የተፈጸመው ወንጀል የኮምፒውተር እና ሳይበር ወንጀል ባህሪ ያለው በመሆኑ የዜጎች እና የሀገር ደህንነት ለአደጋ መጋለጡን ያሳያል፡፡ የእጣ ማውጫ ሲስተሙ ላይ የተሰራው ሙስና ደግሞ ከወንጀልም በላይ የሆነ የከፋ ወንጀል ነው፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ አስተዳደር ራሱ ያለ እጣ በውሳኔ ቤት እያከፋፈለ መሆኑ በህዝቡ ወስጥ ጥርጣሬን እንደጫረ አለ፡ በዚህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ከፕሮግራሙ ውጭ ማደሉና መሸጡ በህዝቡ ውስጥም የፈጠረው ቅሬታ እንዳለ እያወቀ ማለፉም ትክክል ባለመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ሙያቸውን ተጠቅመው ፍትሃዊነትን ያዛቡ፣ መተማመን እንዳይኖር  የሰሩ፣ የሞራል እና የፋይናንስ ጉዳት ያደረሱ፣ በሃሳብም ሆነ በተግባር የተሳተፉ ግለሰቦችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢኖቬሽንና ሳይንስ ሚኒስቴር፣ ተቋማቶች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግና ስህተቱን እንዲታረም ያደርጉ ዘንድ  በእኔና በሌሎች ከ200 ሺህ በላይ በሚሆኑ ቤት ተመዝግበው እየቆጠቡ በሚጠባበቁ ዜጎች ስም እጠይቃለሁ፡፡

ከሰላምታ ጋር

Filed in: Amharic