አዳነች አበቤ ካቤኔ ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሯል፣ የኮሚኒኬሽን ኃላፊው ዮናስ ዘውዴ ሥልጣናቸውን ለቀዋል!!
ባልደራስ
የአዳነች አበቤ ካቢኔ አባል የሆኑት አቶ ዮናስ ዘወዴ በገዛ ፍቃዳቸው ኃላፊነታቸው ለቀዋል፡፡ አቶ ዮናስ ከቢሮ ከወጡ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ የቆዬ ቢሆንም፣ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቅ ስለነበር እስካሁን ተሸፋፍኖ ቆይቷል፡፡
የአዳነች አበቤ አስተዳደር አዲስ አበባ ከተማ በታሪኳ አይታው በማታውቀው ደረጃ በዘረኝነት አካሄዱ ይታወቃል፡፡ አቶ ዮናስ በአደባባይ ይህን ለመናገር ባይፈቅዱም፣ ውስጥ ውስጡን ግን ቅሬታቸው ከዚሁ እውነታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተዓማኒነት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡
የአዳነች አበቤ አስተዳደር አዲስ አበባን በኦሮሚያ እንዳለች አንድ ከተማ ለማድረግ የተግባር እንቅስቃሴዎች እያደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት በከተማዋ ባሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ መስቀል፣ ለኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር በከተማዋ እምብርት ነባር ነዋሪዎችን አፈናቅሎ ሰፋፊ ቦታዎችን መስጠት፣ በከተማዋ መስተዳደር ቁልፍ ቦታዎች ላይ የኦህዴድ ሰዎችን ማስቅመጥ፣ የከተማዋን ዲሞግራፊ ለመቀየር ከኦሮሚያ ክልል ብቻ የተፈናቀሉን በከተማዋ በማስፈር የዐማራ ብሔር የሆኑ ተፈናቀዮችን ግን በከተማዋ እንዳያርፉ እንኳን መከልከል፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎችን በከተማዋ ውስጥ ነዋሪነታቸው ላልተረጋገጠ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በማደል የአነስተኛና ጥቃቅን ብድር ቅድሚያ እንዲሰጣቸው በማድረግ፣ በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የገጠር ቀበሌዎች በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እንዲታጠቁ ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ጋር ተመሳጥሮ እየሰራ መሆኑ እስከ ካቤኔ አባላት ጭምር ክፍፍል ፈጥሯል፡፡
በዚህ ላይ ሰሞኑን በኮንደሚኒየም እጣ አወጣጥ ዙሪያ የለየለት አድልኦ የተደረገው እንቅስቃሴ ብሶቱን ይበልጥ አጋግሎታል፡፡
ከንቲባዋ ሥልጣን እንዲለቁ የሚሰሙ ድምጾች እየተበራከቱ ሲሆን፣ የሚመሩት ካቤኔ ተቀባይነቱ በእጅጉ በማሽቆልቆሉ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ሳይቀር እንደ ታከለ ኡማ እንደ ድንገት መነሳታቸው የማይቀር መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡