>

ነገረ ቴዲ አፍሮ...! (ሞገስ ዘውዱ)

ነገረ ቴዲ አፍሮ…!

ሞገስ ዘውዱ


እኔ የጥበብ ሰው አይደለሁም። ነገር ግን ጥሩ መታዘብ፣ ስሜቴን መግለፅ እችላለሁ ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም፣ “ነገረ ቴዲ አፍሮ” ብዬ ለመጫር የምሞክረው ከጥበብ አንፃር ሳይሆን የግሌን ትዝብትና የረዥም ዓመታት ጥልቅ ስሜቴን ይሆናል።

ብላቴናው የመጀመሪያውን ዘፈን ይዞ ብቅ ሲል እኔ የ4ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ[1992ዓ:ም]። ያኔ ቤታችን ቴሌቭዥን የለም፣ ግን አንድ ቀይ ሞላላ ቴፕ አጎቴ ቤት ነበረች። እናም “ጉድ ሰራሽኝ” የሚለውን ዘፈኑን ስሰማ ቤተሰብ፣ ጎረቤትና ትምህርት  ቤት አካባቢ ካሉ ኹነቶች ጋር እያገናኘሁ እመለከታለሁ። ብላቴናው ” ጡር ሰርተሽ በፍቅር ገፍተሽ የኔን ገላ፣ ስትጠይኝ ጠላሁሽ ስትለምጂ ከሌላ” ሲል የግፍና የመከዳዳት ስሜት ምን እንደሚመስል ተረዳሁት። ያኔ ከፍቅር ውጪ በሌላ መልኩ አስፍቶ ለመተርጎም ለአቅመ-ፖለቲካ አልደረስኩም ነበር።

ቀጥሎ በሁለት ዓመት ልዩነት አቡጊዳን ይዞ ብቅ አለ። የኔም እውቀት ማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዓይነት( በተለይ ዋና ከተሞች) እና ከትምህርት በሬዲዮ አልዘለለም ነበር። ቢሆንም ትዝታው ግን አለ። አሁንም ካሴቱን የመግዛት አቅም ባይኖረኝም ዘፈኑን ግን በየ “ሻይ ቤት” ፊት ለፊት ሆኜ በመስማት ሙሉውን ሸምድጄው ለሌሎች እኩዮቼ በጅምላ አከፋፍል ነበር( ድምፁን ከጓደኞቼ፣ ግጥምና ዜማውን ከሸመደድኩት አዋጥቼ)። በዚያ አልበም ምን ያልተካተተ ማህበራዊ ጉዳይ አለ? ብሄራዊ ጀግንነት፣ የልጅነት ፍቅር፣ የፍቅር ሀሴት፣ ህመም እና ምስጢር፣ የሙዚቃ ህይወት፣ የሀገር ፍቅርና የህዝብ አንድነት፣ ናፍቆት፣ ወዘተ…

1997 ዓ:ም፣ ሰኔ ወር ደረሰ። ታሪካዊው ምርጫ ግንቦት ፯ ተደርጎ ውጥረት በነገሰበት ወቅት፣ ብላቴናው ምድሩን አናወጠው( በጥበብ ስራው)። እኔም የመጀመሪያ ካሴት ለመግዛት በቃሁ፣ ሰፈር ውስጥ ሽቆ ላይ ተሰማርቼ (ከጓደኛዬ ጋር ብሉኬት አምርተን)። አሁንም እውቀቴ ብዙ ባይጨምር ሙቀት ግን በክፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። አስቡት፣ ባለ ሁለት ጣቱ ቅንጅት ( የዛሬን አያድርገውና) ወጣቱን በአንድ ልብና እግር አቁሞ፣ የለውጥ ተስፋ በርግዶ፣ የኢትዮጵያ ፓርላማ በምሁራን ይታጨቃል፣ የእንግሊዝ ሀገር ዓይነት ፓርላማ ሁሉ በልቦናችን አስበን ባለንበት ወቅት ቴዲ በያይነቱ የሆነ አልበም፣ ግማሹ ትንቢት የሚመስሉ ዙፈኖች ይዞ ከተፍ አለ። እኔም በቀን ሶስት ግዜ የጥበብ ውሃ መጎንጨት ቅቋሚ ስራዬ ሆነ[ዝርዝሩን ክታች ይመለከቷል]።

አልጫው ሚሊንየም ሲመጣ “አበባ አየሁሽ፣ ምንም የለም” ብሎ ብቅ ሲል ትውልዱም አብሮ አስተጋባው። እኔም አሁን ለአቅመ-ፖለቲካ ደርሻለሁ!

በ2001 ዓ:ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ብላቴናውን አገዛዙ አፍኖት ካለሁበት 500 ሜትር ርቀት ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ግቢ የችሎት ድራማ ነበር። እኛም ታደመናል፣ ስንወጣም “ቴዲ አፍሮ አይቀርም ታስሮ” እያልን ዘመርን( ዘመዶቻችን ግን አኩርፈዋል)። እናም ግቢ ውስጥ ሆነን ፍቅር የያዘውና ኑሮ የከበደው ተማሪ ሁሉ ( ባጠቃላይ ሆድ የባሰው ማለት ይሻላል) “ጉድ ያረገኝ ዓይኔ ነው አይቶሽ በክፉ ቀን…” በሚለው ዘፈን ሀዘን፣ ተማፅኖ፣ ቁጭት፣ ስጋትና ተስፋ እያደረገ( እኔን ጨምሮ) ቆየ። በዚህ እየቆዘምን እያለ 2004 ዓ:ም ላይ ጥቁር ሰው ከነ ግርማ ሞገሱ ብቅ አለ። አሁንም ሌላ አብዮት ፈነዳ። ገሚሱ ተደሰተ፣ የተወሰነው አደፈጠ፣ የተረፈው አግሮመረመ፣ ብሄርተኞች ክፉኛ ተቆጡ።

ከዚያ በኋላም ብሄራዊ መዝሙር የመሰለ ዘፈን በ2009 ዓ:ም “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን መቆያ ጀባ አለን። ኢትዮጵያ ስትታመም ” ሀገሬ መምጫሽ ናፈቀኝ” ሲል እነ ግብፅ ሲያፈሉ ደግሞ ጎራዴውን ስሎ ከፊት ተሰለፈ። የኢትዮጵያ ህመም በጣም ሲጠና ደግሞ ” እያመመው መጣ…” እያለ የብዙሀኑን ህመም አስተጋባ። ዳሰሳውን እዚህ ላይ ልግታና የቴዲ አበርክቶ( Legacies) ዋና ዋናዎችን አንስቼ ላብቃ።

፩: ፍቅር የተጠማውን ትውልድ መመገብ:-

ቴዲ በዘፈኖቹ ፍቅር የራበውን፣ ትካዜ ያጎበጠውን፣ ተስፋ የራቀውን ማህበረሰብ ሁሌም በዘፈኖቹ ቀና አደርጓቸዋል። “ሄዋን እንደ ዋዛ” ፣ “ፅጌረዳ”፣ ” እንደ ቢራቢሮ”፣” ለማን ልማሽ”፣ “ሰው ስጠኝ በልኬ”፣ ” ባሻው”፣ ” ደስ የሚል ስቃይ”፣ እና በመሰሳሰሉት ዘፈኖች ልብ ጠግኗል፣ ተስፋ አለምልሟል። ከዚህ መደብ ውስጥ ጎልቶ የሚታየኝ፣ ዘመን የማይሽረው ዘፈን “ሼመንደፈር” ነው። እንዴታ ” አንቺም በሀይማኖትሽ እኔም በሀይማኖቴ ፣ መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ፤ አዛንና ቅዳሴ አጥር ቢለያቸው፣ ፈጣሪ ከሰማይ በአንድነት ሰማቸው” የሚለውን የካድሬዎች ሳይሆን መሬት ላይ ያለችውና ለብዙ ዘመናት የኖረችን ኢትዮጵያ በአጭር ስንኝ ገለፀው። ደግሞ የምስራቅ ሰው እንደመሆኔ ለዚህ ዘፈን ትንሽ ባዳላም አትፍረዱብኝ።

፪: የአገርና ህዝብ አንድነት፣ ፍቅርና ይቅርታ:-

“ጃ ያስተሰርያል” ፣ “ዳህላክ ላይ ልስራ ቤቴን” ፣”ወደ ሀገር ቤት “፣ ” አልሄድ አለ እግሬ”፣ “ኮርኩማ አፍሪካ”፣ እና ሌሎች ዘፈኖች የሀገር ፍቅርና የህዝብ አንድነት ላይ ሰርቷል። በተለይ ” ይያያዝ እጃችሁ በልዩነታችሁ፣ አለበለዚያማ በምን ያስታውቃል እኛን መውደዳችሁ” ብሎ ዛሬ ስለሚወራው ብሄራዊ ምክክርና እርቅ አስቀድሞ ባጅቷል። የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም ልደት ተንብዮ በጥቂቱን ቢሆን በህይወት እያለ ፍቅር ሁሌም እንደሚያሸንፍ አይቷል።

 

የትናንቱን፣ የዛሬውንና የወደፊቱን ትውልድ በጥበብ ስራ ለማስተሳሰር ሞክሯል። “ግርማዊነቶ”፣ ” የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ”፣ “አፄ ቴዎድሮስ”፣ ” ጥቁር ሰው”፣ ወዘተ…

፫: ከፖለቲካ ትግልና ማህበራዊ ፍትህ ረገድ:-

አፋኙን አገዛዝ እንደ ቴዲ ፊትለፊት የተጋፈጠ የጥበብ ሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ያለ አይመስለኝም። ዝና፣ ሀብት፣ ቤተሰብ ሳይል የበሰበሰውን ስርዓት ተጋፍጦ፣ በዘፈንና ግጥም ስራዎቹ ወጣቱን ለትግል አነሳስቷል። መቼም “ጃ ያስተሰርያል” ብሎ በድፍረት መዝፈን ቀርቶ በየመንደሩ ማንሾካሾክ በማይቻልበት ዘመን ” አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?” ብሎ የማይደፈረውን በገሀድ ደረመሰው። በዚያው አልበሙ “ኡኡታዬ አልሰማ አለ” ብሎ ከትውልድ ጋር ተነጋገረ። እንዲያውም አንተ ዙፋን ላይ ብትሰየምም ግፍ ስለማታይ ” በማየት ስለማትበልጠኝ ና መነፅሬን ለውጠኝ” እያለ ፎከረ።  ወደ ደቡብ ዓይኑን ዞር ሲያደርግ ግፍ አየ፣ እሱም አለ: “ሀይዞህ ዶርዜ”! አገዛዙ ያን ሁሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ወጣት ላይ ግፍ ሲያደርስ “አናኛቱ” [እኔን ይብላኝ] በማለት ህመሙን ተጋራው። በአገዛዙ ታስሮ ዋጋ ከፈለ፣ ግን አልሸሸም! ሌላም ጨምሩበት። እስከ ዛሬው እለት ድረስ ይሄው የህዝብን ህመም እኩል እያታመመ አለ። የጥበብ ሰው መሆን ትርጉሙ ይሄ ነው።

፬: የወደፊት ተስፋ ምን ይሆን!?

ቴዲ “ይራቅ ችግር ከምድርሽ፣ መሉ ይሁን ሌማትሽ” እያለ ተስፋ ቢያደርግም  በየመሀሉ ነገሮች ሲደፈርሱ “አገሬ መምጫሽ ናፈቀኝ” የሚለውን ትካዜ፣ ቁጭት እና ተስፋ አሸክሞናል። እኔም ሀገሬ መምጫሽ መቼ ይሆን? በአንቺ እቅፍ ውስጥ ሆነን ሳለ መቼ ይሆን አንቺነትሽ የሚሰማን? እያልኩ እሰናበታለሁ።

መልካም ልደት ብላቴናው💚💛❤

Filed in: Amharic