>

አስፈፃሚው አካል ከሕግ አውጪውና የዳኝነት አካሉ እኩል መንግስት እንጂ የበለጠ መንግስት አይደለም! (ክርስቲያን ታደለ)

አስፈፃሚው አካል ከሕግ አውጪውና የዳኝነት አካሉ እኩል መንግስት እንጂ የበለጠ መንግስት አይደለም!

ክርስቲያን ታደለ

በሕግ ማስከበር ሽፋን ከአያያዝ ጀምሮ መብቶቻቸው የተጣሱና የተገደቡ ዜጎችን ሁኔታ በተመለከተ በእንደራሴዎች ምክርቤት ጭምር እስከመወያየትና የአቤቱታ ማመልከቻ አስገብተን ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች መመራቱን እናስታውሳለን።

ምክርቤቱም ከዚሁ ጋር በተያያዘ 2 ኮሚቴዎችን ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመላክ የማጣራት ሥራ ተሰርቷል። ምንም እንኳን የሁለቱም ኮሚቴዎች የተጠቃለለ ሪፖርት ደርሶን ውሳኔ ያረፈበት ባይሆንም የኮሚቴዎች አባላት ከሁለቱ ክልሎች አመራሮች ጋር በነበራቸው የማጠቃለያ ውይይት ላይ ያነሷቸውን ነጥቦችና በሚዲያ ያስተላለፏቸውን መልእክቶችን ስናስተውል ግን አበክረን ስንወተውት የነበረውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ያረጋገጠ ነበር።

ከባለፈው ስህተት በመማር ማስተካከያዎችን ማድረግ ሲገባ ዛሬም ድረስ ፍርድቤት ቀርበው በዋስትና ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ የተወሰነላቸውን ዜጎች፤ የፍርድ ቤት ውሳኔን አክብሮ ከእስር ከመልቀቅ አንፃር ግን ችግሮች ሆነው ቀጥለዋል። ፖሊስ በፍርድቤት የሚሰጥ ዋስትና የዜጎች ሕገመንግስታዊ መብት መሆኑን በውል ሊያጤን ይገባዋል። አስፈፃሚው አካል ሕግ አውጪውና የዳኝነት አካሉ እኩል መንግስትነታቸውን እየጎመዘዘውም ቢሆን ሊቀበለው ይገባል።

በዚህ ረገድ በተለይ በእነትኅትና በላይ [ቲና በላይን ጨምሮ የአሻራና ንስር ሚዲያ ጋዜጠኞ] ላይ ከአንድም ሦስቴ የተፈቀደን የዋስትና መብት አለማክበር ሕግን መጣስ ብቻ ሳይሆን ዜጎችን በኃይል ከሕግ ውጭ የመያዝ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተደርጎ የሚቆጠር ስለሆነ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስቸኳይ እርምት እንዲወስድ እጠይቃለሁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤትም በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰትን በዜጎች ላይ የሚፈፀም የሰብአዊ መብት ጥሰት በአንክሮ ተመልክቶ መሰል ጥሰት የሚፈጽሙ አመራሮችን ጠርቶ ሊጠይቅና እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል።

Filed in: Amharic