>

የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና ወጣቶች የስርቆት ድርጊት እና ከጀርባ ያሉ አሰማሪዎቻቸው (ከይኄይስ እውነቱ)

የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና ወጣቶች የስርቆት ድርጊት

እና ከጀርባ ያሉ አሰማሪዎቻቸው

ከይኄይስ እውነቱ

ይህ መጣጥፍ ስለ ጎዳና ተዳዳሪነት ችግርና ተግዳሮት መንሥኤና መፍትሄ ለማቅረብ ያለመ ምርምር የጎበኘው ወይም ጥናት-ቀመስ ጽሑፍ አይደለም፡፡ ባለቤት በሌላት በመዲናችን አዲስ አበባ የሚታይ አንድ ወቅታዊና አሳሳቢ ችግር በሚመለከት ተሐዝቦታችንን ለማካፈል እንጂ፡፡ 

አገር በወንጀል ሥርዓት የመገዛት፣ የኅብረተሰብና ተቋማቱ ማኅበራዊ ድቀት፣ በግልና በወል የግብረገብና የሥነ ምግባር ልሽቀት፣ የአገርና የኅብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ እንደ ተቋም (በምጣኔ ሀብት÷ በዕውቀት÷ በባህላዊና ሃይማኖታዊ እሤቶች ዐቅም) መናጋት፤ ልጆች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ወደ ጎዳና ሕይወት ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ቤተሰብን ስናነሣ ዐቅም ብቻ ሳይሆን የአስተዳደግ በደልም ለመንገድ ላይ ሕይወት መዳረጉ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ባዲስ አበባችን ጎዳናን መኖሪያቸው አድርገው በልመናና በስርቆት/ዝርፊያ ተሰማርተው የሚገኙ ወገኖች ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ የሠለጠኑት የወንጀል ሥርዓቶችና በዚሁ ሥርዓት ውስጥ ነፃነቱን አጥቶና መብቱ ተገፎ ጭቆናን ገንዘቡ አድርጎ የኖረው ማኅበረሰብ ውጤቶች ናቸው፡፡ የጎዳና ሕይወት ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች፣ ለአደገኛ ሱስ እና ለልዩ ልዩ በሽታዎች የሚያጋልጥ በመሆኑ በዚህ ሕይወት ውስጥ ውስጥ የሚገኙ አብዛኛው ወገኖቻችን የአካልም ሆነ የአእምሮ እንከን እንዳለባቸው ይገመታል፡፡ በተለይም በዚህ ሕይወት ውስጥ በለጋ ዕድሜአቸው ተገኝተው የሚጎለምሱ ወገኖች ለማኅበረሰብ ደኅንነት ምን ያህል አደጋ ሊደቅኑ እንደሚችሉ በማሰብ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ችግሩን ለማቃለል ከተቻለም ለማጥፋት ከወዲሁ መፍትሄውን ሊያስብበት ይገባል፡፡ በተለይም የሃይማኖት ተቋማት (እስከ ሕማማቸው) እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፡፡ እነዚህን ልጆች በተከታታይ የተሐድሶ መርሐ ግብርና የሃምሳ ሎሚን ብሂል ተጠቅመን ከዕዳና ሥጋትነት ወደ ሀብትነትና አምራች ዜግነት መቀየር ይቻላል፡፡ 

ዛሬ በአ.አ. ከተማ የትራፊክ መብራቶች ያሉባቸው ዐደባባዮችና አውራ ጎዳናዎችን ተከትለው ተሽከርካሪዎችን አበባ እንዳየ ንብ የሚወሩት ሕፃናትና ወጣቶች ከልመናው ይልቅ በትራፊክ መብራት የሚቆሙ ተሽከርካሪዎችን ክፍሎች እያወለቁ ላሰማሯቸው ‹ሌቦች› ማቀበል ዋነኛ የውሎአቸው መገለጫ ሆኗል፡፡ ዋናዎቹ የሕፃናቱ ‹አሰማሪዎች› ‹አብነት›  ተብሎ በሚታወቀው የከተማችን ክፍል ያገለገሉ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን ለመሸጥ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ የተሰጣቸው አብዛኛዎቹ ‹ነጋዴዎች› እና በፈቃዱ ተከልለው ስርቆትና ዝርፊያ ላይ የተሰማሩ ‹ሌቦች› ሲሆኑ፣ ቀድሞ ‹ሶማሌ ተራ› በሚባለው ቦታም  እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ አልፎ ተርፎም ንብረቱ የተሰረቀበት አሽከርካሪ ስልካቸው ተሰጥቶት የራሱን ንብረት ከነዚህ ‹ሌቦች› መልሶ መግዛቱ የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ በትራፊክ መብራት አካባቢ የሚደረጉት ስርቆቶች ዋና ሰለባዎች ባመዛኙ ሴቶች አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ይህ ጸሐፊ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች በመገኘት ሪፖርት ከተደረጉ ስርቆቶች ለመረዳት ችሏል፡፡ ስርቆቱ እየተፈጸመ ያለው በምሽት ብቻ ሳይሆን  በጠራራ ፀሐይ በቀን ጭምር ነው፡፡ 

ስርቆቱ ወይም ዝርፊያው በአብዛኛው የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ሜክሲኮ ዐደባባይ፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ስታድየም፣ ላጋር፣ መስቀል ዐደባባይ (በእስጢፋኖስና በቦሌ መስመር እና ባጠቃላይ ዙሪያውን) ተክለ ሃይማኖት ዐደባባይ፣ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል በቸርችል ጎዳና መስመር (ፖስታ ቤት አካባቢ) እነዚህ ከሞላ ጎደል መብራት ላይ ዓይናችን እያየ ስርቆት/ዝርፊያ የሚፈጸምባቸው ልዩ ቦታዎች ሲሆኑ፣ ተሽከርካሪውን አቁሞ የሚሄድ አሽከርካሪ በየትኛውም የከተማዋ ቦታዎች መኖሪያ ቤት በር ላይ ጭምር የተሽከርካሪ ክፍሎች ብቻ ሳይሆኑ ተሽከርካሪው ጭምር ይሰረቃል/ይዘረፋል። እንደሚታወቀው ዝርፊያ ኃይል፣ ዛቻና ማስፈራረትን ይጨምራል፡፡ ብዙውን ጊዜ ይህ የወንጀል ድርጊት የሚፈጸመው በተደራጁና የጎዳና ተዳዳሪ በሆኑም ሆነ ባልሆኑ ወሮበሎች ነው፡፡ 

ስርቆቱ ከተፈጸመባቸው ሴት አሽከርካሪ እኅቶቻችን እንደተረዳሁት የነዋሪውን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅና ከወንጀል ለመከላከል አገዛዙ ባሰማራቸው ‹ፖሊሶች› ተስፋ በመቁረጥ ስርቆቱን ሪፖርት ማድረግ ትተዋል፡፡ ሪፖርት ያደረጉትም ባብዛኛው መፍትሄ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ እኅቶቻችን ከተሽከርካሪዎቻቸው ወጥተው ሕፃናቱን እንከታተላለን ሲሉ በልጆቹ አደጋ የደረሰባቸውም አሉ፡፡

እነዚህ በልመናና በስርቆት የተሰማሩት ሕፃናት ባብዛኛው ዕድሜአቸው ከ9 እስከ 15 አካባቢ ሲሆን፣ ከዚህም ከፍ ያሉ ከ15-20 የሚሆኑም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በሕግ በወንጀል ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ በወጣት አጥፊነት የሚታዩትና የወንጀል ተጠያቂነት ያለባቸው፣ ሆኖም ባብዛኛው ክስ ሲሚመሠርትባቸው አይታይም፡፡ በነገራችን ላይ ልጆቹን በመክሰስና በቅጣት መልክ የሚወሰዱ የጥንቃቄ ርምጃዎች በሕግ የተደነገጉ ቢሆንም፤ ጎዳና ለወጡትና ወንጀል ለሚፈጽሙ ሕፃናትና ወጣቶች ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል እያልኩ አይደለም፡፡ 

ተሐዝቦቴን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው 3 አካላት አኳያ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ እነዚህም 1ኛ/ የስርቆቱ ተጠቂ አሽከርካሪዎች፤ 2ኛ/ ሌሎች አሽከርካሪዎች፤ እና 3ኛ/ ሕግ አስከባሪ ፖሊስ፡፡

1ኛ/ የስርቆቱ ተጠቂ አሽከርካሪዎች፤ እላይ እንደገለጽነው ሰለባዎቹ ባመዛኙ ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል አይችሉም፣ በቀላሉ እናስፈራራቸዋለን ብለው የሚያስቧቸው ሴት አሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ 

ሀ/ ድርጊቱ የሚፈጸመው የትራፊክ መብራት ተሽከርካሪዎችን ባቆመበት ጎዳና ላይ በመሆኑ ከተሽከርካሪ ወርዶ ልጆቹን ለመከላከል አመቺ ካለመሆኑም በላይ ይህን ለማድረግ የሞከሩ አሽከርካሪዎች ገሚሱን ለመከታተል ሲሞክሩ ሌሎቹ መኪናው ውስጥ በመግባት (በድንጋጤ በር ሳይቆልፉ በመውረድ) ገንዘብን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችን መስረቃቸው ተስተውሏል፡፡

ለ/ የስርቆቱ ተጠቂ በሆኑ አሽከርካሪዎች ዘንድ የታዘብነው ሌላ ጉዳይ ችግሩ መኖሩ የዐደባባይ ምሥጢር ሆኖ ሳለ (መፍትሄ እስኪበጅለት ድረስ) ከተሽከርካሪያቸው ደኅንነት ይልቅ ‹ውበት› ላይ በማተኮር አንዳንድ በቀላሉ ተፈተው ሊወሰዱ የሚችሉ (እንደ የኋላ ማሳያ መስታወት ወይም በተለምዶ ‹ስፖኪዮ› የምንለው) የተሽከርካሪ ክፍሎች ላይ የሚገጠሙ መከላከያዎችን ለማድረግ አለመፈልግ ነው፡፡ 

ሐ/ በፖሊስ የሚሰጠው መፍትሄ ምንም ይሁን ስርቆቱን ሪፖርት አለማድረግ፤ እና 

መ/ ሕፃናቱን ለስርቆት ካሰማሯቸው ዋና ‹ሌቦች› የተሰረቀውን የተሽከርካሪ ክፍል (መለዋወጫው ባገር ውስጥ አለመኖር አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል) መልሶ በመግዛት ስርቆትን ማበረታት ናቸው፡፡

2ኛ/ ስርቆት እየተፈጸመበት ካለው ተሽከርካሪ ጎን፣ ኋላና ፊት ያሉ አሽከርካሪዎች ኃላፊነት፤ ከትዝብታችን እጅጉን ያዘንበትና እንደ ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ውድቀት ላይ የመገኘታችን ምልክት ሆኖ ያየነው ሴቶች እኅቶቻችን በነዚህ ‹ውሪዎች› በጠራራ ፀሐይ የተሽከርካሪያቸው ክፍል እየተሰረቀባቸው መሆኑን እየተመለከቱ አብዛኛዎቹ ነግ በኔን ባለማሰብ ወይም ወንድ ስለሆንኩ አይደፍሩኝም በሚል ተልካሻ ምክንያት የጥሩንባ ድምጽ ሁሉ እየሰሙ እንዳልሰሙ መስለው ማለፍ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ይህንን ዳተኝነት አንኳር በሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች ብንመነዝረው ላገር ለወገን የኃላፊነት ስሜት አለመኖርን ብቻ ሳይሆን ለወገን ጥቃት ደንታ ቢስነትን ያመለክታል፡፡ እነዚህ ሕፃናትን ሀይ በማለት ሌላኛ ወገኑን ከስርቆት ማዳን የማይችል ዜጋ ስላገር ጥፋትና ስለ ሕዝብ ደኅንነት ይቆረቆራል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚለው በትንሹ ያልታመነን ማነው ለታላቅ ኃላፊነት የሚሾመው?

3ኛ/ ወንጀልን ለመከላከል፣ ተፈጽሞም ሲገኝ ሕግ ፊት ለማቅረብ/የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር በሕግ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የፖሊስ ኃይል፤ 

ሀ/ እንደሚታወቀው በወያኔና በወራሾቹ ኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዝ ዘመን አዲስ አበባ ከነዋሪዎቿ መካከል በተመረጡ ዜጎች እየተዳደረች አይደለችም፡፡ ይልቁንም ከ4 ዓመት ወዲህ ባለው የወንጀል ሥርዓት አ.አ. የወያኔ ሥሪት የሆነው ‹ኦሮሚያ› የሚባል የቅዠት አገር እንመሠርታለን የሚለው ግዛት አካል እንደሆነች በይፋ እየተነገረና በተግባርም እየተሠራ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በዚህም ምክንያት አ.አ. የራሷ የፖሊስ ኃይል የላትም፡፡ ኢትዮጵያና አዲሳቤ-ጠል የሆነው አገዛዝ ይህን አፍራሽ ዓላማ የሚያስፈጽሙ ላዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥላቻ ያላቸውን ቅጥረኞች፣ በቂ ትምህርትና ሥልጠና የሌላቸው፣ ካዲሳባ ውጭ በተለይም ‹ኦሮሚያ› ከሚለው አካባቢ ሰብስቦ ያሰማራቸው ኃይሎች ናቸው፡፡ በመሆኑም አማራጭ በማጣት ችግር ሲደርስበት ለማመልከት ከመሄድ በቀር አዲሳቤ ሕግ የሚያስከብርለት የፖሊስ ኃይል የለውም፡፡ በተቃራኒው ለደኅንነቱ ሥጋት ከሆኑት ኃይሎች አንዱ ይህ በወንጀል ሥርዓቱ ሳይፈልግ የተጫነበት ያዲስ አበባ ሳይሆን በሐሰት ስሙን የያዘ የጥፋት ኃይል ነው፡፡ 

ለ/ በ‹ሀ› የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አማራጭ በማጣትም አዲሳቤዎች ወደየ ፖሊስ ጣቢያው ጎራ ማለታቸው አይቀርም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ያነሣነውን ችግር ራሱን የአ.አ. ፖሊስ ብሎ የሰየመው ክፍል በሚገባ እንደሚያውቀው፤ አንዳንድ አባላቱም እንደሚናገሩት ልጆቹን ከከተማ ለማራቅ ቢሞክሩም ተመልሰው እንደሚመጡ፤  (በጥናት ያልታሰበበትና ዝግጅት ያልተደረገበት፣ የልጆቹንም ሰብአዊ መብት ያላገናዘበ ቦታ ላይ እነዚህን ልጆች እንደ ‹ቆሻሻ› ዘርግፎ መመለስ ምን ዓይነት መፍትሄ እንደሆነ እግዚአብሔር ይወቀው) ሰብስበው በየፖሊስ ጣቢያ እንዲቀመጡ ሲያደርጉ አለቆቻቸው ለልጆቹ የሚሆን ቀለብ የለንም በሚል ወዲያው እንደሚለቀቁ፤ ልጆቹን በመግረፍ ከስርቆት ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ቢሞክሩም የሕፃናትን ሰብአዊ መብት የሚጋፋ ነው ተብለው መቅጣት እንዳልቻሉ፣ ለበላዮቻቸውም ቢያመለክቱም መፍትሄ እንዳላገኙና ከዐቅማቸው በላይ መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ 

    እዚህ ላይ አንድ የዐደባባይ ምሥጢር ልንገራችሁ፤ ዜጎችም ትእይንቱን ከብበን ከማዳነቅ ውጭ ኃላፊነት የማንወስድበት ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

    ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው የፖሊስ ኃይል ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ተይዞ ሊያመልጥ የሞከረ ተጠርጣሪ ላይ ሊወሰድ የሚችል ተመጣጣኝ የኃይል ርምጃ ሳይሆን፣ በወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ፖሊስ እጅ ሲገባ ሰብአዊ መብትን በሚጋፋ መልኩ እየደበደቡ፣ እየቀጠቀጡና እያዳፉ መውሰድ የተለመደ ተግባር ሆኗል፤ የፖሊስ ተግባር በወንጀል የተጠረጠረን ሰው ሕግ ፊት ማቅረብ /እስከዚያም በቊጥጥር ሥር ማቆየት/ እንጂ ሕግን በራሱ እጅ ወስዶ ተጠርጣሪውን ጥፋተኛና ወንጀለኛ ነው ብሎ ደምድሞ ስቃይ የተሞላበት ቅጣት የሚፈጽም ግለሰብ ከመነሻው እንዴት ሕግ አስከባሪ ፖሊስ መሆን ይችላል? ባለፉት 31 ዓመታት ‹የፖሊስ ሠራዊት› በሚል ስም በማዕከልም ሆነ በየክፍላተ ሀገሩ የተደራጀው ኃይል ‹ፖሊስ› ስለመሆኑ፣ መሠረታዊውን ሥልጠና ስለማግኘቱ፣ ዓላማውና ተልእኮው ምን እንደሆነ በጨረፍታም የተረዳ አይመስልም፡፡ ለዚህም ዋና ምስክሩ ተግባሩ ነው፡፡ በየፖሊስ ጣቢያውና ውኅኒ ቤቶች ሲፈጸም የነበረውና እየተፈጸመም ያለው አረመኔያዊ ድርጊት ‹ፖሊሶች› ነን በሚሉ አመራሮችና ተራ አባላት ነው፡፡ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ብልሽት አንዱ መገለጫም ፖሊስ እንደ ተቋም ሁለንተናዊ ውድቀት የደረሰበት መሆኑ ነው፡፡ ለዳኝነቱ ሥርዓት አልታዘዝ ያለ ‹ፖሊስ› ወንጀለኛ ነው፡፡ ወንጀለኛ ደግሞ  ጥፋተኞችን ሊያርም ሊያስተካከል አይችልም፡፡ እነዚህና ሌሎችም የዚህ ጽሑፍ ጉዳዮች ያልሆኑ ውድቀቶችን ደምረን ነው ሥርዓቱን የወንጀል ለማለት የምንገደደው፡፡

ሐ/ በሌላ በኩል የውጭ መንግሥታት ለስብሰባም ሆነ ይፋዊ ለሆነ ሥራ ሲመጡ ሕፃናቱን ከተማ ‹ያቆሽሻሉ› ተብለው የፖለቲካ ድጋፍ በማግኘት (ሰብአዊ መብት የሚባለው ሁሉ አፈር ድቤ በልቶ) ከከተማ አውጥተው እንደሚወረውሯቸው የተናገሩ አባላት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ልጆቹን አሠማርተው የወንጀል ፍሬ ተጠቃሚ የሆኑት ‹ዋና ሌቦችም› ሆኑ የሕፃናቱንና ወጣት አጥፊዎችን ድርጊት ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት ጥናት ላይ ተመርኩዞ የሚወሰድ ተግባራዊ ርምጃ ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ለማንኛውም ስርቆቱም ቀጥሏል፤ ሕፃናቱን የሚጠቀሙባቸው ከጀርባ ያሉት ‹ሌቦችም› በወንጀል ድርጊታቸው ቀጥለዋል፤ አዲስ አበቤም ከወንጀል የሚከላከለው ፖሊስ የለውም፡፡

መልእክቴ ባጭሩ የሚከተለው ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የሚገኘው የወንጀል ሥርዓት ለፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መፈልፈያ ከሚሆኑ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚውና ዐቢዩ ነው፡፡ የመንግሥት ባሕርይ በሌለውና ለዜጎቹ ደኅንነትና ላገር ህልውና ሥጋት ከሆነ የዱርዬዎች አገዛዝ ሕግና ሥርዓትን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ‹‹የሕግ ማስከበር›› ትርጕም ዜጎችን በነገዳቸውና በሚከተሉት ሃይማኖት ምክንያት የጅምላ ጭፍጨፋ ማድረግ ወይም በትክክለኛ ስሙ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸም መሆኑን በአማራው ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ባለው ግፍና ሰቆቃ እስኪታክተን ታዝበናል፡፡ አዲስ አበባችን ደግሞ የዚህ የወንጀል ሥርዓት ዋና ዒላማ መሆኗን መዘንጋት የለብንም፡፡ ችግሩ የአጠቃላዩ አገራዊ ቀውስ ፍንካች ቢሆንም፤ አዲስ አበቤ ሆይ! ነዋሪ ወገንህ በወንጀል ጥቃት ሲደርስበት ዓይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ መሆን በራስ ሲደርስ ሰሚ አልባ ጩኸት እንዳይሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንና ኅብረታችንን እናጠንክር ለማለት ነው፡፡

Filed in: Amharic