>

የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ መሆን የለበትም (ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ መሆን የለበትም

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


የሱዳንና ግብጽ ወታደራዊ መንግስቶች፣ ትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት በሰሜን፣ የኦሮሞ ነጻነት ተዋጊዎች በምእራብ ኢትዮጵያ ዋነኛ ግባቸውና አላማቸው የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ማላላት ከሆነላቸውም ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደሆነ በብዙ ኢትዮጵያውያን የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ የሰፈረ መራር እውነት ነው፡፡ የሁለቱም ድርጅቶች የፕሮፓጋንዳ አታሺዮቻቸው፣ የፖለቲካ መሪዎቻቸውና  ወታደራዊ አዛዦቻቸው ሳይቀሩ በአደባባይ ይሄኑን መራር እውነት አርድተውናል፡፡ ከዚህ ባሻግር የታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ ለታለመለት አላማ እንዳይውል ( የግድቡን ስራ ለማዘግየት ሲሉ) የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይበጥሱት ቅጠል የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ለወደፊቱ  የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ ለሚደቅኑት አደጋ ወይም ለደቀኑት አደጋ አስተዋጾአቸው እጅጉን የሰፋ ነው፡፡

ለኢትዮጵያና ከ120 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ህዝቧ የሚከተሉት አደጋዎች አሳዛኝ ሁነቶች ናቸው፡-

 • በኢትዮጵያ ስር የሰደደው የጎሳ ፖለቲካና የውስጥ ጎሳ ፖላራላይዜሽን (Ethiopia’s internal ethnic polarization, ) 
 • በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የርስበርስ ጦርነት ( አሁንም ጦር አውርድ የሚሉ በዝተዋል፡፡)
 • በደቡብና ምእራብ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግዜ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በተለይም በአማራ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ልጆቻችን፣ እናቶቻችን እና አባቶቻችን ላይ ተፈጽሟል)
 • አለም አቀፍ መብቶችና ነጻነቶች መገፈፍ
 • የሌብነት መንሰራፋት 
 • ጉቦ
 • ምልጃ
 • የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት
 • የሸቀጦች ፣መድሃኒቶች፣ እህል ወዘተ ወዘተ ዋጋ ሰማይ መንካት (skyrocketing prices )
 • የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኤሊቶች በሰከነ መንፈስ፣ በሰለጠነ መንገድ ቁጭ ብለው የሀገሪቱን መሰረታዊ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ፣ እንዲሁም ልዩነቶቻቸውን መፍታት አለመቻላቸው ( ቢያንስ ቢያንስ ላለመስማማት፣ መስማማት በሚለው መርህ መስማማት አልቻሉም፡፡ )
 • አብዝሃው የፖለቲካ ኤሊቶች ለኢትዮጵያ አለመረጋጋት፣ ለተቋማት ድክመት መሰራተዊ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ተገንዝበው ገቢራዊ የሚሆን የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት አለመቻላቸው
 • የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የመንግስት ሃላፊነቶች ወይም ስራዎች ቅድሚያ ባለመስጠቱ ሀገሪቱን ለመጠነ ሰፊ ችግሮች ማጋለጡ
 • ሱዳንና ግብጽ በኢትዮጵያ ያለውን የውስጥ ፖለቲካ አለመረጋጋት ተገን አድርገው በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ እየገቡ መታየታቸው ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የግብጽና ሱዳን ዋነኛ አላማ በያዝነው የክረምት ወራት ለሶስተኛ ግዜ ወደ ታላቁ የአባይ ግድብ ውሃ እንዳይሞላ ማሰናከል ነው፡

የዚህ ጽሁፍ ( አስተያየት) ዋነኛ አላማ ከሱዳን ጀርባ ግብጽ መኖሯን ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ እንደ ጨው ዘር በአለም ላይ ለተበተኑት ኢትዮጵያውያን ፣ እንዲሁም ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ማሳወቅ፣ ማንቃት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሱዳን ያዙኝ ልቀቁኝ ባይነት፣ ጠብ አጫሪነት፣ ኢትዮጵያን ድንበር ግዛት ያለምንም ከልካይ ተቆጣጥራ እርሻ ማሰረስ፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ተቋማት፣ ድልድዮች መስራት ወዘተ ወዘተ ጀርባ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ግብጽ መኖሯን የአሁኑ ትውልድ በቅጡ መረዳት አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ በጄኔራል አብዱል ፈታህ የሚመራው የሱዳን ጦር ሀይል በኢትዮጵያ ላይ ጠብ ጫሪነቱ፣ በግብጽ መሪ ጄኔራል አልሲሲ  እንደሚደገፍ   ይህንኑ ተብ ጫሪነት የኦነግና ወያኔ መሪዎችም መደገፋቸው ሚስጥር አይደለም፡፡ ግብራቸው ይናገራል፡፡ የቅንብሩ ምኞት የኢትዮጵያን ግዛት አንድነት ማናጋትና ኢትዮጵያን ባልካናይዝ ( መከፋፈል) ማድረግ ነው፡፡ The concert wishes to destabilize and balkanize Ethiopia. 

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ግጭት ፣ የትሮይ ፈረስ  (The Ethiopia-Sudan border conflict is a Trojan horse ) 

 

ኢትዮጵያና ሱዳን በመሃከላቸው 1600 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለው ድንበር የሚጋሩ ሲሆን፣ በመሃከላቸው የተዘረጋው እረጅም ድንበር በሁለቱም ሀገራት መሃከል ለብዙ አስርተ አመተታ የቆየ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን ይህንና በእውነት እና ፍትህ መሰረት ላይ ከተቆመ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት ሚከብድ ኤደለም፡፡ ሁለቱም ሀገሮች አሁንም መስራት የሚችል የድንበር አካላይ ኮሚሽን መመስረታቸው የታወቀ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እጅግ ለም የሆነውን ባለሶስት ማእዘን ቅርጽ ያለውን አል-ፋሽካን ጨምሮ በሌሎች አዋሳኞቻቸው የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መስማማት እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ በነገራችን ላይ አል-ፋሽካ ያለው ስፋት ወደ 260 ስኩዌር ኪሎሜትር እንደሚገመት ኤክሰፐርቶች ካቀረቡት ጥናት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን እጅግ ለም የሆነውን መሬት ሱዳን፣ ግብጽ እና ቀሪው የአረብ አለም በሱዳን ግዛት ውስጥ ይገኛል በማለት በአደባባይ ሲናገሩ መስማት ብርቅ አይደለም፡፡ 

ሆኖም ግን ይሁንና ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ቁምነገር ቢኖር የኢትዮጵያና ሱዳን ህዝብ ከንግድ፣ በባህል ልውውጥ፣ከአከባቢ ጸጥታ አማካኝነት የጋራ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አብዝሃው ሰላማዊ የሱዳን ህዝብ የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የግብጽ ትሮይ ፈረስ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዲከፍት አይፈቅዱም፡፡ አብዝሃው የሱዳን ህዝብ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1920 በጸደቀው ውል መሰረት የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ግጭት መፈታት ይችላል በማለት እንደሚያምኑ በተለያዩ የጥናት ወረቀቶች ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የሁለቱም ሀገራት ህዝብ ሰላምን ይሻል፡፡ ሰላምን ይፈልጋል፡፡ የድንበሩ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ምኞቱና ፍላጎቱ ነው፡፡ ጦርነት የገዢዎች ፍላጎት ነው፡፡ ለዚህም ነው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ጁን 30 2022 ከሱዳን ወታደራዊ አዛዦች በተቃረነ መልኩ ለሰላማዊ ትግል ነካርቱም፣ ኡምዱርማን ከተሞች በሚገኙ አደባባይ ላይ የወጡት፡፡ አንድ ሱዳናዊ የሰላማዊ ታጋይ ኢትዮጵያውያን እንደ ሱዳን ወንድሞቻቸው ሁሉ በህብረት ለሰላማዊ ትግል እንዲነሱ ጥሪውን በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ሲያቀርብ ታይቷል፡፡

የጠብ ጫሪነቱ አጀማመር፣የተደበቀው የድንበር ግጭት

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 23 2020 የወያኔ ዘረኛ ቡድን የፈጸመውን የሀገር ክህደት ተከትሎ የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች በማንቀሳቀስ፣ ከባድ መሳሪያዎች የታጠቁ ወታደሮችን አሰማርቶ   የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሱዳን የአድርባይነት አቋም ግብጽን የልብ ልብ ስለሰጣት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ወራ እንድትይዝ ትረዳለች፡፡ በግዜው ሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ወረራ ስለተፈጸመባት የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የኢትዮጵያን ድንበር ለመውረር አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮለት እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶስትዮሹ ውይይት ( ማለትም በግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን መሃከል ) ሲካሄድ የቆየው ለግዜውም ቢሆን ቆሟል፡፡ የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ግብጽ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ችላ ያለ ቅድመ ሁኔታ በማቅረቧ ነው፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚዋን እንዳታሳድግ ደንቃራ መፍጠር የብዙ አመታት ፍላጎቷ እና ምኞቷ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የህዝቧን የኑሮ እድገት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ ግብጽ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ለአብነት ያህል 86 ፐርሰንት ለናይል ወንዝ ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም ሴራ በመጎንጎን ፣ ግብጽ ብቻ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት እንዳላት የግብጽ መሪዎች በየግዜው ሚነገሩት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካ ህብረት ተመልካችነት ሶስቱም ሀገራት ውይይት እንዲያደርጉ የተባበረችው አሜሪካ ለመርዳት ዝግጁ መሆኗ ይሰማል፡፡

ግብጽ አንዲት ጠብታ ውሃ ለተላቁ የናይል አታበረክትም ወይም አታዋጣም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ግብጽ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1929 እና ሱዳን ከታላቋ ብሪታንያ የቅኝ ግዛት ቀንበር ተለገላግላ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች ነጻነት በኋላ ማለትም 1959 ( እ.ኤ.አ. ) በተደረጉት የቅን ግዛት ስምምነቶች ብቻዬን በበላይነት የናይል ወንዝን እንድጠቀም ይፈቅድልኛል ብላ ታምናለች፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያና ሌሎች ለናይል ወንዝ ውሃ የሚያበርክቱ የጥቁር አፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ ግዜ ከዚህ ከቅኝ ገዢ ውል ለተደጋጋሚ ግዜ ባይተዋር እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግትር አቋም ያላት ግብጽ ለናይል ወንዝ ውሃ የሚያበረክቱት ኢትዮጵያና ሌሎች ጥቁር የአፍሪካ ሀገራት ከላይ በተጠቀሰው የቅኝ ገዢ እንግሊዝ ውል መሰረት መገዛት አለባቸው በማለት በየግዜው ታስጠነቅቃለች፡፡ ታስገድዳለች፡፡ ስለሆነም በምክንያታዊነት መሰረት ላይ ለመስማማት በታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ብቻ መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ የላይኛው እና የታችኛው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉ ታላቅ ጉባኤ በማካሄድ በናይል ወንዝ ላይ ሁሉም ሀገራት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው መስማማቱ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ይሄንኑ ጉዳይ ( የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት በናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሃዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ )  የአፍሪካ ህብረት ሃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ይመስለኛል፡፡

በአጭሩ ለማስቀመጥ በቅርብ ግዜ ውስጥ ሱዳን የምታሳየው ጸብ ጫሪነት ወይም ግጭቶች መሰረታዊ ምክንያቱ የድንበር ግጭት ብቻ አይደለም፡፡ የሱዳን ዋነኛ ፍላጎትና ምኞት የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ስራ ማስተጓጎል ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ጁን 22 2022 በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንደተከፈተ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቃ የድንበር መሬቶችን ተቆጣጥራለች፡፡ ሱዳን ይህን የእብሪት ድርጊት በመፈጸሟ የተነሳ አለም አቀፍ ህግን ጥሳለች፡፡ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችንም ችላ ብላለች፡፡ ከዚህ ባሻግር የድንበር አካባቢ ኢትዮጵያዊ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ፣ ንብረታቸው እንዲወድም እና እንዲዘረፍ ሱዳን ምክንያት ሆናለች፡፡ ሱዳን አካባቢውን ከመውረሯ ባሻግር ልክ እንደ የራሷ ሉአላዊ ግዛት በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን እየገነባች ትገኛለች፡፡ መንገድ፣ ድልድይ ወዘተ እየገነባች ትገኛለች፡፡ የአካባቢውን መልክአምድርና የህዝብ አሰፋፈርንም እየቀየረች ነው፡፡ ይህ በምንም አይነት ተቀባይነት ያለው ተግባር አይደለም፡፡

ሱዳን  ቋሚ መንገዶች፣የቴሌኮሚኒኬሽን መስመሮች፣የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ በአስደንጋጭ እና ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየዘረጋች ከመገኘቷ ባሻግር ከሌላ የሱዳን ክፍል ህዝቧን በማጓጓዝ በጉልበት በሃይል በያዘችው የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ እያሰፈረች ነው፡፡

በሃይል በሸፍጥ በተያዙ የኢትዮጵያ የድንበር መሬት ላይ ሱዳን ያቀደችውን የህዝብ አሰፋፈር ለማሳለጥ የሱዳን ጦር ሀይል የኢትዮጵያን የድንበር አስተዳደር መዋቅር አፍርሷል፣ የኢትዮጵያን የጦር ካምፕ አፍርሷል፣ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ለስደት ዳርጓል፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል፣ እህሎቻቸውን አውድመዋል፡፡ ሱዳን ይህን ወንጀል በመፈጸሟ የብይነ መንግስታቱን  ህግ ጥሳለች፣ለአፍሪካ ህብረት ህግም አልገዛም ባይነቷን አሳይታለች፡፡ ከዚህ ባሻግር በድንበር ይገባኛል ምክንያት ለሚነሱ ጭቅጭቆች ሰላማዊ መፍትሔ መኖር አለበት የሚለውን አለም አቀፍ ህግንም የጣሰ ነው፡፡

ስለሆነም የአፍሪካ ሀገራት የሱዳንን ጠብጫሪነት ማውገዝ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ሱዳን የአፍሪካ ህብረትን ህግ በመጣሷ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ህግ መንፈስ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ከራሳቸው ድንበር አልፈው የሌሎች ጎረቤቶቻቸውን ድንበር መድፈር ወይም መቆጣጠር የለባቸውም ይላል ፡፡ ( አንዱ ሀገር የሌላኛውን ሀገር ሉአላዊ ድንበር አቋርጦ መግባት አይችልም ፡፡) ስለሆነም ይህ ህግ ለሱዳንና ኢትዮጵያ የሚሰራ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ህግ ለተደጋጋሚ ግዜ ተገዢ ስትሆን፣ ሱዳን ግን ይህንኑ የአፍሪካ ህብረት ህግ በገሃድ፣ በአደባባይ ጥሳ ትገኛለች፡፡

የሱዳን ዋነኛ አላማ ምን ይሆን ?

በእኔ የግል አስተያየት መሰረት የሱዳን መሰረታዊ አላማ በሃይል፣ በጉልበትና ሸፍጥ ታክሎበት የተቆጣጠረችውን የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ህጋዊና ቋሚ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ በወልቃይት ምድር ላይ የተፈጸመውን ሸፍጥና ሴራ ያስታውሰኛል፡፡ በመጀመሪያና በቅድሚያ የወያኔ ጎሰኛ ቡድን የወልቃይት ምድርን በሃይል ተቆጣጠረ፡፡ አስከትሎም  ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የወልቃይት አማሮችን አስገደለ፣ የተረፉትን ደግሞ በማስገደድ ለስደት ዳረጋቸው፡፡ ይህን እኩይ ድርጊት ከፈጸመ በኋላ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች አስፍሯል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የህዝብ መገልገያ ተቋማትና መንገዶችን ከመገንባታቸው ባሻግር በጉልበት በሃይል የያዙትን የጎንደር አማራ መሬትን ምእራብ ትግራይ በማለት ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ ሱዳንም ብትሆን ተመሳሳይ ድርጊት ነው የፈጸመችው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ተመሳሳይ ጥቃትን መሸከም የሚችል ጀርባ የለውም፡፡ ( በአንድ በኩል ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ወራ መያዟ፣ በሌላ በኩል የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ወልቃይትን ዳግም ለመያዝ፣ ለመቆጣጠር የሚያደርገው የጦር ዝግጅትን ማለቴ ነው፡፡ )

በድጋሚ ለማስታወስ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 2020 የወያኔ የጎሳ ቡድን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በከፈተ ማግስት አመቺ ግዜ አገኘሁ በማለት የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ ገብቷል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ወያኔ፣ ግብጽና ሱዳን አንድ ላይ በመነጋገር ኢትዮጵያ ላይ ጦር እንደሰበቁ ነው፡፡ ወያኔ በሀገር ላይ ክህደት አልፈጸመም የሚል ማናቸውም ግለሰብ ካለ  በግብጽ አይዞህ ባይነትና እርዳታ የሱዳን ወታደሮችና የትሮይ ፈረስ (the Trojan horse )  የሆነው ወያኔ የኢትዮጵያን ህለውና ለመፈታተን በየአቅጣጫው  በኢትዮጵያ ላይ የሚከፍቱትን ጦርነትና ግጭት መመርመር ይቻለዋል፡፡

የኢትዮ- ሱዳን የድንበር ግጭት በወፍ በረር ሲቃኝ

በኢትዮጵያ ድንበር ኮሚቴ ላይ የሰሩ ስመጥር ኢትዮጵያውያንና የስነምድር እና ዲፕሎማቲክ እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን  የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ግጭትን በተመለከተ በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ ካሰፈሩት  በመነሳት የሚከተሉት ድምዳሜዎች ላይ መድረስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ 

 1. ኢትዮጵያና ሱዳን በአል-ፋሽካ የድንበር መሬት ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት የሚያደርጉት የድንበር ጭቅጭቅ የሚመነጨው አጼ ምኒሊክና ቅኝ ገዢ ታላቋ ብሪታንያ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1902 ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ የመነጨ ነው፡፡ ( እ.ኤ.አ. 1902 ታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ትገዛት የነበረውን ሱዳንን በመወከል በሱዳንና ኢትዮጵያ መሃከል ያለውን የድንበር መስመር ለመወሰን ከኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አጼ ምንሊክ ጋር ውል ተፈራርማ ነበር፡፡ ይህ ውል የእንግሊዝ-ኢትዮጵያ ውል ተብሎ ይታወቃል፡፡ ( Anglo-Ethiopians Treaty) ) 

በአለም አቀፍ የባህል ህግ አሰራር መሰረት ሁለቱ ሀገራት ባቋቋሙት የጋራ ድንበር ኮሚሽን መሰረት ሁለቱም ወገኖች የጋራ ድንበር ማስመር ይቻላቸዋል፡፡ የጋራ ድንበር መስመሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱም ሀገራት ዜጎቻቸው በየትኛው የድንበር ክፍል መገኘት ወይም መኖር እንዳለባቸው ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ካለፈው መቶ አመት ( 100 ) አመት ጀምሮ አሁን ድረስ ገቢራዊ አልተደረገም፡፡ ( በአጭሩ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ወሰን፣ ሁለቱም ሀገራት በተስማሙት መሰረት ዛሬም አልተወሰነም፡፡ )

 1. ታሪክ እንደሚያስተምረን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1972 ላይ አጼ ሀይለስላሴ ሱዳንን በይፋ ጎብኝተው የነበረው ወንድማዊ ወይም የወዳጅነት መንፈስ ያለው መፍትሔ ሰራሔ ለመፈለግ ( ለማግኘት0 ነበር፡፡ በግዜው ሱዳንና ኢትዮጵያ በሰከነ መንፈስ፣ በሰለጠነ መንገድ ሃሳብ ለሃሳብ ተለዋውጠው ነበር፡፡ ( ውይይት ) አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1974 የፈነዳው አብዮት የውይይቱን አቅጣጫ አስቀየረው፡፡ በኢትዮጵያና ሱዳን መሃከል በሰከነ መንፈስ ተጀምሮ የነበረው ውይይት ልክ የባቡር ሃዲዱን እንደሳተ ባቡር ሆኖ ቀረ፡፡ አጼ ሀይለስላሴ በአፍሪካም ሆነ በአለም ደረጃ የነበራቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በሱዳንና ኢትዮጵያ መሃከል ያለውን የድንበር ጭቅጭቅ በሰላም ለመፍታት የነበረው እድል መክኖ ቀረ፡፡ በሁለቱ ሀገራት መሃከል ያለውን ድንበር ለማስመር የሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ኮሚሽን እንዲቋቋም ሃሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ኮሚሽኑ በወረቀት ላይ ከመስፈሩ ውጭ መሬት ላይ አልታየም፡፡
 2. ከ1902ቱ ውል በተጻረረ መልኩ ታላቋ ብሪታንያ የራሷን ወታደራዊ ኦፊሰር ( ሜጀር ቻርልስ ደብሊው ጊዌይን ተብሎ ይጠራል ፡፡ ) ( Major Gwynn ) ስልጣን በመስጠት በኢትዮጵያና ሱዳን መሃከል ያለውን ድንበር እንዲያሰምር አድርጋለች፡፡ ይህ የእንግሊዝ ወታደራዊ ኦፊሰር ያለ ኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በእንግሊዝ ፈቃድ፣ የእንግሊዝን ፍላጎት ለማሟላት የሁለቱን ሀገራት ድንበር መለያ በራሱ ፍላጎትና እንደመሰለው ማስመሩን አንባቢው ልብ ሊል ይገባል፡፡ 
 3. ይህ የእንግሊዝ ወታደራዊ ኦፊሰር ለኢትዮጵያ እንዲወስንም ስልጣን ተሰጥቶት ነበር፡፡ ለታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ተገዢ ሱዳን በማዳላት ድንበሩን ያሰመረው በግድየለሽት፣ በግምት፣ ብቻውንና ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ ነበር፡፡ ስለሆነም በዚህ ሂደት እጅግ ትልቅ የድንበር መሬቷን እንድታጣ በግፍ ተፈርዶባታል፡፡ በውጤቱም በአንድ ወገን ብቻ የተሰመረውንና ለሱዳን የአንበሳውን ድርሻ እንድትወስድ የሚያስችላትን  የሁለቱ ሀገራት የድንበር መለያን ኢትዮጵያ ለዘመናት ሳትቀበለው ኖራለች፡፡ ( በሻለቃ ጌዌን አመሃኝነት የተሰመረውን የሁለቱን ሀገራት የድንበር መለያ መስመር የአጼ ሀይለስላሴም ሆነ የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም መንግስታት እንደማይቀበሉት በግልጽ መናገራቸውን ከታሪክ እንማራለን፡፡ ) ይህ ሱዳን በየግዜው ጠብ ጫሪ እንድትሆን፣ የኢትዮጵያን ድንበር ለመወረር የሚገፋፋት መሰረታዊ ምክንያት ነው፡፡ ሱዳን በህገ ወጥ መንገድ፣ በኋላ በር፣ ኢትዮጵያ ተዳክማለች ባለችበት ግዜ ሴራ በመጎንጎን  የራሷ ያልሆነውን የድንበር መሬት ከኢትዮጵያ ለመንጠቅ የዘመናት ፍላጎቷና ምኞቷ ነው፡፡
 4. ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት ( የአጼ ምንሊክና አጼ ሀይለስላሴ መንግስታት፣ የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም መንግስት ) ሱዳን የጌዌን መስመርን በማስረጃነት በማቅረብ    ይገባኛል የምትለውን የድንበር መሬት አልተቀበሉትም ነበር፡፡ የነበሩት ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት ምኞትና ፍላጎት የነበረው በመጀመሪያው በዋናው ስምምነት መሰረት፣ በታሪካዊና አስተዳደራዊ መሰረት፣ እንዲሁም በአለም አቀፍ ህግና ውል መሰረት ድንበሩ እንዲሰመር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህ ሳይደረግ መንግስታት ተለዋውጠዋል፡፡ ላለፉት ሰላሳ አመታት ኢትዮጵያን የገዛው ወያኔና ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ደግሞ የኢትጵያን ማእከላዊ መንግስት የተቆጣጠረው የዶክተር አብይ መንግስት አሁን ድረስ በሁለቱ ሀገራት መሃከል ስላለው የድንበር ውዝግብ በተመለከተ በግልጽ፣ በአደባባይ ለኢትዮጵያ ህዝብ አልተነገረውም፡፡
 5. ኢትዮጵያ ለአለም አቀፉ የፖለቲካ ማህበረሰብ፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአፍሪካው ህብረት  ድንበሯ ተከብሮ እንዲጠበቅ፣ በሌላ እብሪተኛ ሀገር ድንበሯ እንዳይደፈር ተከታታይ አቤቱታዋን ታሰማለች፡፡ 

በሀገር መሃከል የሚሰመር የድንበር ዋነኛ አላማ የሀገራትን ሉአላዊነት ለማክበር እንደሆነ መሰመር አለበት፡፡ በሁለት ሀገራት መሃከል የሚገኝ ደንበር በአንደኛው ሀገር ፍላጎት ብቻ የሚሰመር ወይም የሚከለል ከሆነ ለግጭት የሚጋብዝ ነው፡፡ በሱዳንና ኢትዮጵያ መሃከል የሚገኘው ድንበር በሱዳን ፍላጎት ብቻ የሚሰመር ከሆነ ሰላምን አያስገኝም፡፡

 1. ማላቂያ የሌለው፣ ቀጣይነት ያለው የሱዳን ጠብ ጫሪነት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ድንበት ዘልቆ በመግባት ወረራ በመፈጸሟ የድንበር አካባቢ ኢትዮጵያዊ ነዋሪዎችን ህይወት አናግታለች፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በኢትየዮጵያና ሱዳን ወንድማማቾች መሃከልም ደም መፋሰስን የሚያስከትል ነው፡፡ ጸጥታና አለመረጋጋት በአፍሪካው ቀንድ እንዲቀሰቀስ ያስችላል፡፡
 2. የሱዳን እብሪት፣የኢትዮጵያን የኢትዮጵያን የድንበር መሬት በሃይል መቆጣጠር፣ ለብቻዋ፣ ያለ ኢትዮጵያ ይሁንታ  የሁለቱን ሀገራት መለያ ድንበር ማስመሯ ፣ በሃይል በጉልበት በያዘችው የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ቋሚ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን መገንባቷ ህገወጥና እጅግ አደገኛ ድርጊት ነው፡፡ ይህ የሱዳን እብሪት የኢትዮጵያን የድንበር ግዛት፣ ብሐየራዊ ጸጥታን ችላ ያለ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የህብረተሰቡን የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምንም የሚጎዳ ነው፡፡ የ 120 ሚሊዮን የሚጠጋውን ኢትዮጵያዊ ዜጎችን የምግብ፣ ዘይት እና የስራ እድልንም ጭምር መብትን የገፈፈም ነው፡፡
 3. በነገራችን ላይ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት፣የተባበረችው አሜሪካ እና ሌሎች ከአመት በፊት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር በሃይል ስትቆጣጠር ዝምታን መርጠዋል፡፡ ሱዳንን አልወቀሷትም፡፡ ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር በርካታ ማእቀቦችን በሩሲያ ላይ የጣሉት ሀያልን ሱዳንን በዝምታ መመልከታቸው ፍትሃዊ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያንና በውጭው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተባበረችው አሜሪካ የሚመራውን አለም አቀፍ ስርአት ላይ እምነታቸው እየተሟጠጠ ነው፡፡ የአለሙ ሲስተም ጠላትን ለመቅጫ ጓደኛ ወይም ወዳጅ የሚሉትን ለመሸለም የቆመ ይመስላል፡፡
 4. የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የተባበረችው አሜሪካ እና የአውሮፓው ህብረት በትግራይ ተከስቶ በነበረው ድርቅና ጠኔ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ተጥሷል በሚል ወቀሳ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የምእራቡ አለም በሩሲያ ላይ ማእቀብ ለመጣል፣ ዩክሬንን ለመርዳት ፈጣን ነው፡፡ ለዩክሬን በ10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን አቀብለዋል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ብቻዋን ወደ 10 ቢሊዮን የሚገመት የአሜሪካ ዶላር ለዩክሬን በእርዳታ ለግሳለች፡፡

ሃያላኑ መንግስታት የአለምን ኢኮኖሚ እንደ መሳሪያ በመጠቀም በየአካባቢው ጦርነት እንዲቀፈቀፍ በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ከማድረጋቸው ባሻግር፣ የገንዘብ ግሽፈት እንዲከሰት ፣የምግብ ፣ በአለም ላይ የነዳጅ እና የምግብ ዘይት እጥረትም እንዲከሰት በማድረግ ሀገራትን ያስጨንቃሉ፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ የምእራቡ አለም ሱዳን ወረራዋን ብተገፋበት ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት ወያኔን በመርዳት ሃይል እንዲያገኝ ለሌላ ዙር ጦርነት እንዲዘጋጅ  ዛሬም ከመርዳት የሚታቀቡ አይደሉም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ጦርነት ከተቃሰቀሰ ማለቴ ነው፡፡ የሚጎዱት ንጹሃን ዜጎች ናቸው፡፡ በጦርነቱ መሃከል ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ይደቃል፡፡ ጸጥታው የበለጠ ይደፈርሳል፡፡

መደምደሚያ

የእኔ ምክረ ሃሳብ

በሱዳንና ኢትዮጵያ መሃከል የሚከፈት ጦርነት ሁለቱንም በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ የባሰ ምስቅልቅል ውስጥ ትገባለች፡፡ የሱዳን ህዝብ እና የኢትዮጵ ህዝብ ለዲሞክራሲ መስፍን ሰላማዊ ትግላቸውን ማጠናከር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሁለቱም ሀገራት ዴሞክራሲ ስር ከሰደደ ሁለቱም ሀገራት ለገጠማቸው የድንበር ይገባኛል ፍጥጫ ወይም ግጭት መፍትሔው ይቀላል ነው፡፡ ሱዳንና ኢትዮጵያ ሃያላቸውን በማስተባበር፣ መንፈሳቸውን በማጠንከር የሁለቱን ሀገራት የጋራ ድንበር ኮሚቴዎችን ማንበሩ አማራጭ የለውም፡፡ ይህ የሁለቱ ሀገራት ጥምር የድንበር ኮሚቴ ስራውን ማከናወን እንዲችል ከተፈለገ ግን ሱዳን በሃይል፣ በጉልበት ከያዘችው የኢትዮጵያ የድንበር መሬት ለቃ መውጣት አለባት፣ ከመሬታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ደግሞ ወደ ቀደመው መኖሪያቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ሱዳን ከጠብ ጫሪነቷ እንድትቆጠብ፣ ሱዳን የግብጽ ትሮይ ፈረስ ከመሆን እንድትቆጠብ የምእራባውያኑ እገዛ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ትግል ማካሄድ ይጠበቅባታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካው ህብረት የሱዳንን ጠብ ጫሪነት መገሰጽ ቢያቅተው፣ ሁለቱም ሀገራት ( ሱዳንና ኢትዮጵያ ) የጋራ የድንበር ኮሚሽን እንዲያቆሙ እገዛ ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያ እና ቀሪው የአፍሪካ ክፍል ግብጽ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል ፣ በኢትዮጵያ የእጅ አዙር ጦርነት ለመከፍት ስትል የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ታቆም ዘንድ ውተወታቸውን ማካሄድ አለባቸው የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ሁሉ በጠረቤዛ ዙሪያ ላይ ተቀምጠው ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ስምምነት ላይ ለመድረስ  በሰለጠነ መንገድ መነጋገር አለባቸው የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው ፡፡ ሰላም፡፡

 

Filed in: Amharic