>

ዛሬም እንደ ትናንቱ፥ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን! (ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ)

ዛሬም እንደ ትናንቱ፥ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!

 – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 

–   ለአንድ ደቂቃ በያለንበት ቆመን ለኢትዮጵያ አምላክ ምስጋና እንድናቀርብ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ!

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣

ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣

ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለችግሮች ያለመንበርከክ፣ በፈተና ሳይበገሩ የማለፍና እንቅፋቶችን ተሻግሮ ድል የማድረግ የክብር ስም ነው፡፡ ሀገራችን በታሪኳ ያለ ፈተና ያሳለፈቻቸው ዘመናት እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በብርቱ ልጆችዋ ጥረትና በፈጣሪ ቸርነት የሚገጥማትን የችግር ውርጅብኝ እየተቋቋማች እዚህ ደርሳለች፡፡ ዛሬም የሀገራችንን ብርቱ አቅም ሊገዳደር የመከራ ዶፍ በዙሪያችን ቢያስገመግም፤ እንደ ሐምሌ ክረምት በችግር ደመናቸው ሕይወታችንን ሊያጨልሙ የሚቋምጡ ኃይሎች ቢሰበሰቡም መጓዛችንን አናቆምም፡፡ በጽኑ ማንነታችንና በፈጣሪ እገዛ ለምንታመነው እኛ ሁሌም ከክረምቱ ባሻገር የሚመጣው ብሩህ ጸደይ ጎልቶ ይታየናል፤ ከጨለማው ማዶ ደማቅ ብርሃን እንዳለ እናውቃለን፡፡ የትናንቱን ጨለማ እንዳለፍነው ሁሉ÷ የዛሬውን ጽልመት የማንሻገርበት ምክንያት እንደሌለ እያመንን፣ ብርታትና ጥንካሬውን ለሚቸረን ፈጣሪ ዛሬም ምስጋና ከማቅረብ አንቦዝንም፡፡

አመስጋኝነት ያለፈውን ዘመን በአሸናፊነት፣ ያለንበትን ወቅት በዕድለኝነት፣ መጪውን ጊዜ ደግሞ በብሩህ ተስፋ እንድንመለከተው የሚያድርግ ታላቅ ኃይል አለው። በአንጻሩ አማራሪነትና ምስጋና ቢስነት የተሸናፊነትና የዕድለ ቢስነት ሥነ ልቡናን ይፈጥራል፡፡ ራሳችንንና ሌሎችን በአዎንታዊነትና በፍቅር መመልከት እንዳንችልም ያደርገናል። በምሬትና በምስጋና ቢስነት የተጠመደ ግለሰብም ሆነ ሕዝብ የጎደለው እንጂ በእጁ ያለው ጸጋ አይታየውም፡፡ የደረሰበት በደል እንጂ የተሰጠው ዕድል አይጎላለትም፡፡ የሚመጣው መከራ እንጂ ከፊቱ ያለው ደስታ በኅሊናው አይሳልም። አመስጋኝ ሰው በመከራውና በጭንቁ ውስጥ ድሉንና ዕድሉን ማየት የሚችል ነው፡፡ ከወጀቡና ከማዕበሉ ይልቅ የመርከቧን ጥንካሬ ያያል፡፡ ከፈተናና ከችግሩ ግዝፈት ይልቅ፣ ሁሉንም በአንድነትና በፈጣሪ ርዳታ ለማሸነፍ የሚቻል መሆኑን ያስባል፡፡

የአክሱምና ቀደምት ሥልጣኔዎች፣ የላሊበላና በዙሪያው የነበሩ ምሥጢራዊ የኪነ ሕንጻ እምርታዎች፣ በሐረርና በዙሪያው አብቦ የነበረው የከተሜነት መነቃቃትና ዕድገት፣ በጊቤ ዙሪያ የነበሩ ንግድን ከግብርና ያጣመሩ ሥልጣኔዎች፤ በገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲን የማስተዋወቅ ጥረቶች፤ በወላይታ፣ በከምባታ፣ በሐላባ፣ በሐድያ፣ በዳውሮና ከፋ ዙሪያ የነበሩ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ አውሮፓ ድረስ የንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተመሠረተባቸው አስተዳደሮች፤ በጎንደር የተማከለ መንግሥታዊ አስተዳደር የመፍጠር ሙከራ፤ በአፋርና በሶማሊ የነበረው መረጃንና ማዕከላዊነትን መሠረት ያደረገው የአስተዳደር ሥርዓት፣ በጋምቤላ የነበረው ለሴቶች የተለየ የክብር ቦታ የሚሰጠው ሥልጣኔ፣ በቤኒሻንጉል የነበረው የሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪያዎች ልህቀት፤ እንዲህም በሌሎቹም አካባቢዎች ታይተው የነበሩትን ሥልጣኔዎች ወደ ኋላ ዞር ብለን በማየት ልንኮራባቸው የሚገቡ ሀብቶቻችን ናቸው። የምንኮራባቸውን ትናንቶች የሰጠንን የኢትዮጵያን አምላክ ማመስገን ያለብንም ለዚህ ነው፡፡

 

በውስጥ የነበሩ ዘመነ መሳፍንትን የመሰሉ መከፋፈሎችን፤ ከውጭ የመጡ የቅኝ ግዛት ጫናዎችን ሀገራችን በማይታይ ኃይል ተቋቁማቸዋለች፡፡ ታሪኳና ማንነቷ ሳይጠፋ፣ እንደ አድማስ ድንጋይ ጠንክራ ለዘመናት መቆየቷ ተአምር ሊባል የሚችል ነው። ዘመናዊቱ ኢትዮጵያ ከመበታተን ወደ አንድነት በተሰበሰብችበት ሂደት ውስጥም ጦርነቶችና ግጭቶች፣ ወረራዎችና የሥልጣን ሽኩቻዎች እልፍ ሆነው ተከሥተዋል፡፡ የሀገረ መንግሥት ግንባታው መልክ ይዞ ሳይጠናቀቅ፣ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ፈጣንና ተከታታይ ሥር ነቀል ለውጦች ሀገራችንን ገጥመዋታል፡፡ አብዮቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ ወረርሽኞች፣ ከፍተኛ ርሃቦች፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቀውሶች ጎርፍ ሆነው ቢግተለተሉም ኢትዮጵያን ነቀነቋት እንጂ አላፈረሷትም፡፡ በቅርብና በሩቅ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቿ በየጊዜው እየተነሡ ገዝግዘው ሊጥሏት ያላደረጉት ጥረት፣ ያልሸረቡት ደባ አልነበረም። ስሟን ጥላሸት ሊቀቡ ሞክረዋል፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ፍትሕን ደጋግመው ነፍገዋታል። ያላትን የባሕር በር አሳጥተው ሊያፍኗት ሞክረዋል። ከሆዷ የሚፈልቁትን ወንዞቿን እንዳትጠቀም ሊያደርጉ በተንኮል የተጠለፉ ውሎችንና በክፋት የተሸመኑ ስምምነቶችን አድርገዋል። በዚህ ሁሉ መሐል፣ ኢትዮጵያችን እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትና፣ በልጆቿ ጥረትና በፈጣሪዋ ፈቃድ ተጠብቃ እንደ ሀገር መቀጠል መቻሏ እጅግ ይደንቃል፡፡ ሀገራችን እነዚህን ሁሉ መከራዎች መሻገራን ስናስብ ለፈጣሪ ምስጋና እንድናቀርብ ምክንያት ይሆነናል፡፡

ያለፉት አራትና አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተስፋና መከራ፣ አንድነትና ልዩነት፣ ዓለም አቀፋዊ አድናቆትና ውግዘት፣ እመርታና ጉተታ፣ ነጻነትና ግጭት ያስተናገድንበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ያገኘችበት ብቻ ሳይሆን ያጣችበትም ጊዜ ነው። ቀረ፣ ሊያበቃለት ነው የተባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን፣ ሙሌቱ ተገባድዶ ኃይልን ማመንጨት ጀምሯል። የድርቅና የጉስቁልና ምድር የተባለች ሀገር ቢልዮን ችግኞችን በመትከልና በየሥፍራው ፓርኮችን በማበጀት የምድረ ገነትነት ግስጋሤዋን ቀጥላለች። የህልውናዋ ዋስትና የምዕራባውያን ስንዴ እንደሆነ ሲያስቡ፣ ኢትዮጵያ ግን በጀመረችው የበጋ ስንዴና ሰፋፊ የእህልና የአትክልት እርሻዎቿ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ለመትረፍ ጫፍ ላይ ትገኛለች። በአንድ ወቅት የአፍሪካ የቆሻሻ መጣያ ለመባል የደረሰችው አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን መልክ ልትይዝ ዳር ዳር እያለች ነው፡፡ ያጋጠሙን ፈተናዎች ብዙ ውድ ዋጋዎች አስከፍለውናል፡፡ እነርሱን ባሰብናቸው ቁጥር ያመናል፡፡ ካጣነው በላይ ግን ያገኘነው ይበልጣል፡፡ መከራው አልገታንም፤ ፈተናው አላሸነፈንም፡፡ ለዚህም ለፈጣሪ ብዙ ምስጋና እናቀርባለን።

ውድ የሀገሬ ልጆች፣

ወንድም በወንድሙ ላይ የጨከነበትን፣ አብረን የኖርን ቀርቶ አብረን የዋልን በማይመስል መልኩ የተጋጨንባቸውን፣ በረባው ባልረባው የሰው ሕይወት የተቀጠፈባቸውን፣ ዒላማ እንጂ ዓላማ በሌላቸው ሰዎች የወገኖቻችን ደም በከንቱ የፈሰሰባቸውን ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ዞር ብለን ስናይ ልባችን በኀዘን ይሰበራል። እንደ ትውልድም ሐፍረት ይሰማናል፡፡ በሰሜኑና በምዕራቡ የሀገራችን ክፍሎች ጦርነቶችና ግጭቶች ያስከፈሉንን የሰው ሕይወትና የወደመውን የሀገር ሀብት ስናስብ ዓይኖቻችን ብቻ ሳይሆኑ ነፍሶቻችንም ያነባሉ። በአንድ ወቅት በምሥራቁና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ተከሥቶ የነበረው ጥፋት ያደረሰው ጉዳትና ሰቆቃም የሚረሳ አይደለም። እያነባንም ቢሆን ግን እናመሰግናለን፡፡ ከሆነብን የተደረገልን ይበልጣልና፡፡

አንገቷን ለመስበርና ወገቧን ለማጉበጥ የወረደባትን መዓት ሁሉ ችላ፣ ኀዘኗን በሆዷ፣ ፈተናዋን በክንዷ ተሸክማ አልፋ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም በጽናት መቀጠሏና አቅጣጫዋን ሳትስት በመንገዷ ላይ መገሥገሷ በርግጥ አስደናቂ ምሥጢር ነው። በጥፋት ውስጥ ልማትን፣ በኀዘን ውስጥ መጽናናትን፣ በችግር ውስጥ በረከትን፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን እያበራ የታደገንና ለሀገራችን ድጋፍና መከታ የሆነን የኢትዮጵያ አምላክ ነው፡፡ ይሄንን ጥላ ከለላ፣ አምባ መከታ፣ ጋሻ መሸሻ የሆነ አምላክ ማመስገን የኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነት ዜማ መሆን ይገባዋል፡፡

ለውጡ የመጣው የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ብቻ መሆኑን የተረዱ፣ በተለይ በዓባይና በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው አካላት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች የጥፋት ናዳቸውን ሲጎርፉት ነበር። ታላላቅ የምዕራባውያን ሚዲያዎችና ተቋማትም የመንግሥቶቻቸውን ዐቅም ተማምነው በሀገራችን ላይ ዘምተዋል። ኢኮኖሚዋንና ዓለም አቀፍ ገጽታዋን ለማጥፋት የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ፣ ወዳጆቻችንን እንዲርቁን በእጅ አዙር ጠፍረው ለመያዝ ሲሞክሩ ነበር። ዳሩ ግን የእነሱ ጥረትና ሙከራ ያንቀላፋውን ኢትዮጵያዊ አንድነትና ቁጣ ቀሰቀሰው እንጂ አልጣለውም፡፡ የዐድዋ ድልም በእኛ ዘመን ተደገመ፤ ያንዣበበው ሀገር የመበታተን ጥቁር ደመናም ተገፈፈ። ይህም የኢትዮጵያ አምላክ ምንጊዜም ከእኛ ጋር መሆኑን ያየንበት የዘመናችን ትንግርት ነበር፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ላይ የወረደውን ዓይነት ዓለም አቀፍ ጫናና ተጽዕኖ ብዙ ሀገራት መቋቋም ተስኗቸው ፈራርሰዋል። የኢትዮጵያ አምላክ ግን ለጠላቶቻችን ንክሻ አሳልፎ አልሰጠንም፡፡

ተንገዳግደን እንድንቆም፣ ሸብርክ ብለን እንድንጸና፣ ደክመን እንድንበረታ ዐቅምና ብርታት ሆኖናል፡፡ ይሄው ዛሬም ኢትዮጵያ ዓለምን እያስደነቀችም እየታዘበችም ቀጥላለች፡፡ መጪውን ዘመን በዚህ ክንደ ብርቱ መከታዋ ላይ ሆና ለመሻገር በተስፋ አርቃ ትመለከታለች። በታሪክ የሰማነውን የኢትዮጵያን ጽናት በዓይናችን ላሳየን፤ በኛም ዘመን ታሪክ ለሠራልን፣ ለኢትዮጵያ ፈጣሪ ለኢትዮጵያ አምላክ ምስጋና ይድረሰው።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ በዘመናት መካከል ካገጠሙት ችግሮች በላይ ቆሞ በልዕልና የሚያሸበርቅ ሀገር ማነው? የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ብዝኃነትን ከአንድነት ጋር አገናዝበው ለረጅም ዘመን የዘለቁ ሀገራትስ ስንት ናቸው? በከርሰ ምድራቸውና በገጸ ምድራቸው ላይ በሀብት የተሞሉ፣ አየርና ውኃቸው የተባረከላቸው፣ የልብ ጀግንነትንና የአእምሮ ብሩህነትን በጥምረት የታደሉ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ስንት ናቸው? ሁሉም ዓይነት የጥቁር ሕዝቦች መልክና ገጽታ እንደ ፈርጥ ተሠራጭተው የሚያብረቀርቁባት ሀገር ከኢትዮጵያ ሌላ ማናት? በነጻነትና በሉዓላዊነት የአፍሪካ ተምሳሌት የሆነችስ ሀገር ከኢትዮጵያ ሌላ ከወዴት ይገኛል? ከጥንት እስከ ዛሬ የሌሎች ሀገር ስደተኞችንና መጻተኞችን በሀገራቸው እንደራሳቸው ልጆች ያስተናገዱ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትስ እነማን ናቸው?

የውስጥ ፈተናውንና የውጪ ጫናውን ተቋቍመው በዓለም የስፖርት መድረክ ላይ በድል ላይ ድል የሚቀዳጁ ኢትዮጵያውያን አይደሉምን በስፖርት አደባባይ የእናት ሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ፣ ድል ባደረጉበት ሜዳ ላይ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ፈጣሪያቸውን የሚያመስግኑ ኢትዮጵያውያን አይደሉምን? በርጋታ ካሰብንና በጥሞና በረከታችንን ከቆጠርን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ከምሬት ይልቅ አመስጋኞች ልንሆንባቸው የሚገቡ እጅግ ብዙ ሌሎች ምክንያቶችና መንሥኤዎች አሉን። ለዚህም ነው ልቡናችን በተረዳቸውም ሆነ አስበን ባልደረስንባቸው ብዙ ጉዳዮች ላይ ቆመን ፈጣሪን ልናመስግንና ልናከብር የሚገባን።

የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች የከፍታዋ መሰላሎችና የእመርታዋ ድልድዮች እንጂ የውድቀቷ መቃብሮችና የመደናቀፊያ መሰናክሎች አይሆኑም። እነዚህ ሁሉ የክፋት ኃይላት የሚረባረቡብን፣ መጪውን ብሩህ ዘመን አይተው እንጂ ተስፋ ቢስ ድሆች መሆናችን አስጨንቋቸው አይደለም፡፡ በወርቅ የተሞላ ቤት እንጂ ባዶ ቤት የጠላትን ልብ አይስብምና፡፡ ቢያንስ ለጠላቶቻችንና በጎአችንን ለማይመኙ አካላት የታያቸው ዐቅማችንና እንደ ሀገር ያለን ዕምቅ ሀብት ለእኛም ሊታየን ይገባል። ምክንያቱም ወደ ፊትና ወደ ከፍታ በፍጥነት የመውጫ መንገዱ አመስጋኝነትና ያለንን በጎ ነገር በአድናቆትና በክብር ለመቀበል መቻል ነው። ባለፈችበት ወጣ ገባ መንገድ ሁሉ ሀገራችንን ጠብቋታልና ቸር አምላክ ዛሬም ምስጋና ይግባው።

ከከርሰ ምድሩ እስከ ጠፈሩ፣ ከእምነቱ እስከ ታሪካዊ ሀብቱ፣ ከአየር ንብረቱ እስከ ባህል ብዝኃነቱ፣ ከጀግንነቱ እስከ ነጻነት ወዳድነቱ፣ ፈጣሪ የለገሠንን የተከማቸ ረቂቅ ብልጽግና በማሰብ እናመስግነው። እርስ በርስም ከመጠላላትና ከመጋጨት ወጥተን አንዳችን ሌላችንን ማድነቅና ማመስገን ባህላችን ይሁን፡፡ ባልፈውና በጎደለው እያማረርንና ብሶት እያወራን መጪውን ትውልድ አናድክመው። ይልቁንም አንዳችን ሌላችንን፤ የዛሬዎቹ የትናንቶቹን፣ እናመስግን፡፡ ከሁሉም በላይና በፊት ደግሞ በዘመናት መካከል የረዳንን ፈጣሪ ቆም ብለን እናመስግን። ወዳጆቻችን ሲለወጡ፣ አጋዦቻችን ፊታቸውን ሲያዞሩ፣ ጎረቤቶቻችን ባዳ ሲሆኑ አይተናል፡፡ የማይለወጠው የኢትዮጵያ ኃይል፣ ረድኤት፣ ጋሻና መከታ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡

በዓመቱ ካሉት 365 ቀናት አንዲቷን ቀን ምስጋናችንን በጋራ ለፈጣሪ ለማቅረብና ውለታውን ለማሰብ ብንወስን የሚበዛ አይመስለኝም፡፡ ከቀኑስ ለአንዲት ደቂቃ ያህል የምናደርገውን ሁሉ አስቀምጠን በያለንበት ቆም ብለን፣ የፈጣሪን ውለታና ቸርነቱን አስበን፣ የኢትዮጵያን አምላክ ማመስገን አለብን፡፡ መጪውን ዓመትና ዘመን በምሬትና በብሶት፣ በጥላቻና በቂም፣ በበቀልና በቁርሾ ከምንቀበለው ይልቅ፣ በአድናቆትና በምስጋና፣ በመረዳዳትና በይቅርታ ልንቀበለው ይገባል፡፡

የጽንፈ ዓለም ሁሉ ፈጣሪና የመልካምነት ሁሉ ምንጭ የሆነውን ፈጣሪ እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ፣ እንደ መሪና እንደ ዜጎች፣ በየቋንቋችንና በየእምነታችን ከልባችን እናመስግነው። ከክፉ ወረርሽኝ ጠብቆናል፣ ከአንበጣ መንጋ ታድጎናል፤ ድርቅ መቅሰፍት እንዳይሆን ከበር ቆሞልናል፤ ከቅርብና ከሩቅ የተነሣብንን የማፈራረስ አደጋ ቀልብሶልናል፤ የጀመርናቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶችና የታላቁን ግድብ የውኃ ሙሌት እውን እንዲሆን ረድቶናል፤ ሀገራችንና ሕዝባችንን ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ በምሥጢራዊ አሠራሩ ጠብቆልናል፡፡ ክብር ምስጋን ለእርሱ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን ብለን፣ ለአንድ ደቂቃ በያለንበት ቆመን ለኢትዮጵያ አምላክ ምስጋና እንድናቀርብ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሀምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም.

Filed in: Amharic