>
5:14 pm - Thursday April 20, 1713

ስለ ኢትዮጵያ - አቡነ ጴጥሮስ  ሐምሌ 22 ቀን 1928 ልክ በዛሬዋ እለት የሰማእትነት ጽዋን ጨለጡ...!!! (ዲ/ን መርሻ አለኸኝ)

ስለ ኢትዮጵያ – አቡነ ጴጥሮስ  ሐምሌ   22- ቀን 1928 ልክ በዛሬዋ እለት የሰማእትነት ጽዋን ጨለጡ…!!!

ዲ/ን መርሻ አለኸኝ

ሐምሌ   22- ቀን 1928 አባታችን  አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት  ከተቀበሉ ዛሬ ድፍን 80 ዓመት ሆናቸው ፤ ኢትዮጵያው ሰማዕት ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ በዓለ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ፋሺስት ጣሊያን እነ አቡነ ጴጥሮስንና ጎሬ ላይ ሰማዕት የሆኑትን እነ አቡነ ሚካኤልን ብቻ በሰማዕት የገደለ አይደለም! በ1928 ዓ.ም የጣሊያን ተዋጊ ወታደሮችን የሮሙ ጳጳስ ጦራቸውን ባርኮ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝቦች ያልወጋና ገዳማቶቻቸውን ያላፈረሰ አውግዣለሁ›› በማለት ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› ብሎ በሃይማኖታችንና በሀገራችን ላይ ነው ጦርነት ያወጀብን፡፡ በዚህም መሠረት ምን ያህል የገዳም አባቶቻችንና እናቶቻችን በጣሊያን ወታደሮች በግፍ በሰማዕትነት እንደተገደሉብን ቁጥራቸውን ቀጥሎ ተመልከት፡- አቡነ ጴጥሮስን ሐምሌ 22 ቀን 1929 ዓ.ም አ.አ ላይ በስምንት ጥይት ገደሏቸው፡፡ አቡነ ሚካኤልን ኅዳር 24 ቀን 1929 ዓ.ም ኢሉባቦር ጎሬ ላይ በግፍ ገደሏቸው፡፡ ታላቁን ሊቅ አቡነ ክፍሌን ታኅሣሥ 7 ቀን 1928 ዓ.ም ላይ ሲያወግዙት ስለነበር አንገታቸውን ሲሰይፋቸው ደም፣ ወተትና ውኃ ከአንገታቸው ፈሷል፡፡ ግንቦት 28 ቀን 1929 ዓ.ም ቁጥራቸው 662 የሆኑ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በግፍ ተጨፈጨፉ፡፡ ግንቦት 29 ቀን 1929 ዓ.ም ቅዳሴ ላይ እንዳሉ 43 የአቡነ ዜና ማርቆስ መነኮሳት ታረዱ፡፡ ደመናም ሸፈናቸው፡፡ ሰኔ 12 ቀን 1929 ዓ.ም በማስታኮት ላይ ያሉ የዝቋላ መኮሳት ብዛታቸው 211 መነኮሳት ተገድለዋል፡፡ ብዛታቸው 2116 የሆኑ የደብረ ዳሞ መነኮሳት ጥቅምት 17 ቀን 1929 ዓ.ም ታረዱ፡፡ ሰኔ 3 ቀን 1929 ዓ.ም 60 የምድረ ከብድ መነኮሳት ታርደዋል፡፡ 91 የሚሆኑ የአሰቦት መነኮሳት ሰኔ 15 ቀን 1929 ዓ.ም ታርደዋል፡፡ አንበሶች ከጫካ ወጥተው አልቅሰዋል፡፡ 143 የአዲስ ዓለም ካህናትና መነኮሳት ኅዳር 25 ቀን 1929 ዓ.ም ታረዱ፡፡ ብርሃንም ወረደ፡፡ የካቲት 12 ቀን ቀን 1929 ዓ.ም ብዛታቸው በውል የማይታወቅ ብዙ የአ.አ ነዋሪዎችን ሰብስቦ ፈጃቸው፡፡ መጋቢት 16 ቀን 1929 ዓ.ም 515 የማኅበረ ሥላሴ ገዳም መነኮሳትን ከላይ በቦንብ፣ ከታች በመትረየስ ፈጇቸው፡፡ መጋቢት 17 ቀን ቀን 1929 ዓ.ም ብዛታቸው በውል ያልታወቁ የደብረ ዓባይ ገዳም መነኮሳት ታረዱ፡፡ የመርጦ ለማርያምና የተድባበ ማርያም ካህናትና መነኮሳት ብዛታቸው 363 የሆኑ መነኮሳት ሚያዝያ 18 እና ሚያዝያ 20 ቀን 1929 ዓ.ም ታረዱ፡፡ የጎንደር ሊቃውንት እየተለቀሙ እንዲታሰሩ ከተደረገ በኋላ ሐምሌ 29 ቀን 1929 ዓ.ም ግመሾቹ ሲሰየፉ ግመሾቹን ደግሞ በግዞት ወሰዷቸው፡፡

የካቲት 18 ቀን 1929 ዓ.ም የአ.አ የካ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ካህናት አባቶች ተሰው፡፡ የካቲት 20 ቀን 1929 ዓ.ም በአ.አ ከተማ ያሉ በተለያዩ ገዳማት የሚገኙ ታላላቅ ሊቃውንት ተለቅመው እንዲሰበሰቡ ከተደረገና ከተደበደቡ በኋላ እጅና እግራቸውን አስረው እሳት አጉርሰዋቸዋል፡፡ ርዕሰ ደብር  አስተዳዳሪውን ጨምሮ የትግራይ ጮለቀት ሥላሴ አገልጋዮችን አስረው ‹‹በሮማ ካቶሊክ ታምናላችው ወይስ በረሃብ ትሞታላችሁ?›› እያሉ በረሃብ አሠቃይተዋቸዋል፡፡ እምቢ ቢሏቸው ጽኑ ግርፋት ገርፈው ከለቀቋቸው በኋላ በመኪና ገጭተው ገድለዋቸዋል፡፡ ካቶሊኮች ከቅባቶች ጋር ሆነው ሊቃውንቱን እነ እጨጌ ተክለ ሃይማኖትን እግራቸውን ከከብቶች ጭራ ጋር አስረው መሬት ለመሬት በመጎተት ገድለዋቸዋል፡፡ ( ምንጭ፡- ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን-ገጽ 88) ይሄ ሁሉ ግፍ በገዳማውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ላይ የተፈጸመብን በ1928 ዓ.ም የጣሊያን ተዋጊ ወታደሮችን የሮሙ ጳጳስ ጦራቸውን ባርኮ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝቦች ያልወጋና ገዳማቶቻቸውን ያላፈረሰ አውግዣለሁ›› በማለት ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› ብሎ በሃይማኖታችንና በሀገራችን ላይ ጦርነት ካወጀብን በኋላ ነው፡፡ በዚሁ ዓመት ፓትርያርክ አባ ማትያስ ‹‹የእኛና የሮም ካቶሊክ ልዩነታችን መጥበብ የሚችል ስለሆነ በጋራ ልማታዊ ሥራዎችን መሥራት አለብን…. እትት…›› እያሉ ቅብርጥሴ ሲሉብን የነበረው እንዲህ ዓይነት ግፍ ከሠራችብን ከሮም ካቶሊክ ቤ/ክ ጋር በልማት ሰበብ ሊያመሳስሉንና አንድ ሊያደርጉን አስበው ነው!!! ይህስ ቢቀር ምነው በዶግማው ጉዳይ ላይ ያለን እጅግ ግዙፍ የሆነው ልዩነታችን የት ደረሰ??? ለአምላካዊ ስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ከ451 ዓ.ም ጀምሮ ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ ነው ያለው›› ብላ ማመን ከጀመረች ከሮማ ካቶሊክ ጋር እንዴት ነው ልዩነታችን ጠባብ የሆነው??? ለማንኛውም ወደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ገድል እንመለስ፡- ኢትዮጵያዊው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ፡- የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት እንደሚሞቱ አስቀድመው መምህራቸው በትንቢት ነግረዋቸው ነበር፡፡

‹‹አለቃ ተጠምቀ›› የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው «ኀይለ ማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፣ አደራ›› ብለዋቸው ነበር፡፡ ይኸውም ትንቢት ደርሶ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ለማረፍ በቅተዋል፡፡ ብፁዕ አባታችን የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መመህር ኀይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በሸዋራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈጽመው መምህር ሆነዋል፡፡ የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር ሄደው ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ይመግቡ ወደነበሩት ወደ ሊቁ አካለ ወልድ ዘንድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በሚገባ አሒዱ፡፡ ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አምሐራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለ9 ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ፡፡ በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከዚያም መምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለ6 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለ3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ አ.አ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የንስሓ አባት ሆኑ፡፡

ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆቿ እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት ከዚህ በኋላ በሃይማኖታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ፡፡ ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባታችን ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ  ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ›› ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ፡፡  ብፁዕ አባታችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ቅድስት ሀገራችን በጸሎታቸው፣ ሕዝቡን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ቤተ ክርስቲያንን ያቃጥል ጀመር፡፡ በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኮሳት ተገደሉ፣ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎታቸው ሊዋጉት ተነሡ፡፡ አባታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አ.አ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሠላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል፡፡ በደብረ ሊባኖስ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ የነበረው የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር እና በሸንኮራ በኩል መሽጎ የነበረው የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር እንደሁም በምዕራብ ይመራ ከነበረው የእነ ደጃዝማች አባ ነፍሶ ጦር ሦስቱም በአንድ ጊዜ ወደ መሐል አ.አ በመግት አ.አ ላይ መሽጎ የነበረውን ፋሽስትን ለመውጋት ታቅዶ የነበረው ዕቅድ በመረጃ ክፍተት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀረ፡፡ በተለያየ ጊዜ መሐል አ.አ እየደረሱ ማለትም በመጀመሪያ የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር ለብቻው በኮተቤ አድጎ የካ ሚካኤል ላይ ሲድርስ ተመቶ ተመለሰ፤ ይሄኛው እንዳለቀ ቀጥሎ የእነ አባ ነፍሶ ጦር በባቡር ጣቢያ መጣሁ ቢልም በጠላት ጦር ድካሚ ተመቶ ተመለሰ፤ መጨረሻ ላይ የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር በእንጦጦ በኩል ቢመጣም እርሱም በጠላት ጦር ተመቶ ተመለሰ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሦስቱም የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደመጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኛው ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም ይልቁንም ‹‹ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ›› በማለት አባታችን ከአርበኞቹ ተነጥለው አ.አ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላዋ ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አባታችንን እንዳሰቡት ሊያነቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አባታችን ‹‹የሀገሬን ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል›› ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑና የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለሆነው ለራስ ኀይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡት፡፡

እርሱም ብፁዕ አባታችንን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አሳልፎ ሰጧቸው፡፡ ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት ኮርየሬ ዴላሴራ የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለው ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ በነበረ ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር፡-  ‹‹ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው ‹ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም››› ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአ.አ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ፡፡ ወደ ምሥራቅ አፍሪካው ዜና መዋዕል አዘጋጁ ወደ ፖጃሌ ዘገባ እንመለስና የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- ‹‹ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡

ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞቸ ሦሰት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው፤ መካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ‹ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል› የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም ‹ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፡- ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ» አሉ፡፡ ‹‹ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእክት አስተላለፉ፡- ‹አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፤ እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን› ብለው አወገዙ፡፡ ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍጥነት ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ እርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ፡፡ ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ፡፡ በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡ የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው፡፡  የሀገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒያ እውነተኛ ጳጳስ እንዲገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሑ ዐሥር ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ፡፡ ከገዳዮቹም አንዱ ‹ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ ‹ይህ ያንተ ሥራ ነው› ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ፡፡ ከመግደያውም ቦታ እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ፡፡ ከዚያም በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተ ጀመርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ወዲያው አዛዡ ‹ተኩስ!› በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቱዋቸው፡፡ ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ፡፡ ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በኋላ አንድ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡ ብፁዕነታቸው የተገደሉበት ቦታ መሐል አዲስ አበባ ላይ ዛሬ መታሰቢያ ሐውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው›› በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው ፖጃሌ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?›› ሲል በወቅቱ አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውውም የሚከተለውን ተናረዋል፡- ‹‹አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ፡፡

መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት፡፡ ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት፡፡ ወዲያው ወታደሮቸ በሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡ ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ፡፡ ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ‹በዚህ ቄስ መገደልኮ ሕዝቡ ተደስቷል› አለኝ፡፡ ‹እንዴት?› ብለው ‹አላየህም ሲያጨበጭብ?› አለኝ፡፡ ‹ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል› አልኩት፡፡ ‹እንዴት?› ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት፡፡ ‹ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ› ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ሰዓታቸውንም ጭምር አሳየኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተበስቷል፡፡ መስቀሉም ልክ በመሐሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል፡፡ የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንዲሁ ጥይት በስቶታል›› ብለው በወቅቱ የተመለከቱትን መስክረዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ) ብፁዕ አባታችን በአደባባይ በሕዝብ ፊት የሰማዕትነት ጽዋቸውን ሲቀበሉ ከሕዝቡ ጋር ሆና ትመለከት የነበረች አንዲት ከድጃ የምትባል እስላም ሴት ማንም ሰው ያላየውን ታላቅ ነገር እርሷ ተመልክታለች፤ ይኸውም አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ሲቀዳጁ ተመልክታ በዚያው እርሷም ‹‹የእኚህን አባት ሃይማኖት እከተላለሁ›› ብላ በመጠመቅ ክርስቲያን ሆናለች፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ ቀብራቸው በምሥጢር መፈጸሙን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምሥጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም ‹‹ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምሥጢር ቀበሯቸው›› ከሚል ከመላምት ያለፈ ነገር ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ‹‹ፉሪ ለቡ›› ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው ‹‹ሙኒሳ ጉብታ›› ላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ እየተነገረ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የአቡነ ጴጥሮስን ሥጋ በተመለከተ ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአ.አ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር መደረጉ በትንሣኤ መጽሔት ቁ.58 1978 ዓ.ም ላይ የተገለጠ ቢሆንም ነገር ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ቅዱሳን መላእክት የጻድቃንን በድን እያመጡ ወደሚያስቀምጡበትና በውስጡ የሚቀመጥ አስክሬን ወደማይፈርስበት አቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ገዳም መላእክት ወስደው እንዳስቀመጡትና በዚያም እንደታየ ይናገራሉ፡፡ ሰሜን ሸዋ ሚዳ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በአቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ውስጥ የቅዳሱኑ አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ የአንገት ክራቸው ራሱ ሳይበጠስ እንደዛው እንደነበሩ ስለሚገኝ ቦታውም እጅግ ትልቅ የቃልኪዳን ቦታ ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም በዚህ በጨረሻው ሀሳብ ይስማማል፡፡  ሰማያዊ ክብርን የሚያስገኝ አኩሪ ገድል በመፈጸም የቤተክርስቲያን ታላቅ አለኝታ አባትና መሪ የሆኑት የዘመናችንን ታላቅ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ትውልዱ የግድ ሊያስባቸውና ሊዘክራቸው ይገባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (united nations) አቡነ ዼጥሮስን “የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት” ወይም በፈረንጅኛው አፍ (MARTYR OF THE MILLENIUM) በሚል መጠሪያ ሰይሟቸዋል፡፡ ላልተነገረላቸውና ላልተዘመረላቸው ለእኚህ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያናችን ድንቅ አባት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 12 ቀን 1998 ዓ.ም እኚህን ሰማዕት ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ›› ተብለው እንዲጠሩ ወስኗል፡፡ በስማቸውም መቅደስ እንዲታነጽ ፈቅዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሠረት (ኢሳ 56፡4) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቁ በተወለዱበት ሥፍራ መታሰቢያ አቁማላቸዋለች፡፡ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በስማቸው የተሰየመው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና መታሰቢያ ሐውልታቸው ሲሠራ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ጭምር ለግንባታ የሚሆን አሸዋ ከመርዳት አንስቶ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ድንኳን እስከመትከል ተሳትፈዋል፡፡ በገንዘብም በጉልበትም ተባብረዋል፡፡ ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የአባታችንን እጅግ አኩሪ ታሪክ ሲያዘክራቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም በአ.አ መሐል ከተማ ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ የአቡነ ጴጥሮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡  + ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ሐምሌ 22 ቀን የታላቁ ሰማዕት የቅዱስ ፋሲለደስ ልጅ የሆነውና ምስክርነቱን በብዙ ሥቃይ የፈጸመው ሰማዕቱ ቅዱስ መቃርስ ዕረፍቱ ነው፡፡  + ከዕረፍቱ በኋላ ተገልጦ ብዙ ተአምራትን ያደረገው ሰማዕት ቅዱስ ለውንትዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡  + ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡  ቦታ ስላልበቃን ገድላቸውን በክፍል አንድ በዝርዝር እናየዋለን፡፡ ቀጣዩን ሊንክ ተጭነው ሙሉ ገድላቸውን ያንብቡ፡-  https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1124757474258320&id=905883512812385&_ft_=top_level_post_id.1124757474258320%3Atl_objid.1124757474258320%3Athid.905883512812385%3A306061129499414%3A2%3A0%3A1470034799%3A-2387279086886586054&__tn__=%2As  (ምንጭ፡- ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን-ዲ/ን መርሻ አለኸኝ 1996 ዓ.ም፣ የዳጋ ቅዱስ

Filed in: Amharic