ታሪክን ወደ ሁዋላና ወደፊት
(በእውቀቱ ስዩም)
ያልተበረዘውን የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያነብ ሰው ፥ መጀመርያ የሚመጣለት ስሜት “ wtf ? ምን ጉድ ነው ?” የሚል ነው ፤ ለምሳሌ ነገስታት አንድ ልማድ ነበራቸው ፤ልክ ዙፋን ላይ ሲወጡ ልጆቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን ሰብስበው ከመዲናቸው ራቅ ያለ ማጎርያ ቦታ ያስቀምጧቸዋል፤ የማጎርያው መልክአምድር ለማምለጥ አይመችም፤ ከዚያም አልፎ፤ በንቁና አስፈሪ ዘበኞች ይጠበቃል፤ በአክሱም ዘመን ደብረዳሞ የልኡላን ማጎርያ ሆኖ አገልግሏል፤ የሸዋ ነገስታት በተራቸው ሲገዙ፤ ለዚህ ተግባር የመረጡት ቦታ፥ ወሎ ዛሬ ግሼን ማርያም የምትገኝበትን አምባ ነበር፤ የጎንደር ነገስታት በበኩላቸው ዘመዶቻቸውን “ወህኒ” ወደ ተባለ ስፍራ ማጋዝ ጀመሩ፤ ወህኒቤት የሚለውን ቃል የወረስነው ከዚህ ስፍራ ነው ፤ ወህኒ በመሰረቱ የፖለቲካ እስር ቤት ሲሆን ፥የመጀመርያው የፖለቲካ ወንጀል ከንጉስ መወለድ ነበር፤
ንጉሱ ድንገት ወራሹን ሳያሳውቅ በጦር ሜዳ ይገደላል እንበል፥ አንዱ የቤተመንግስት መኮንን ብድግ ይልና አንዱን ልኡል ከማጎርያ ቤት አውርዶ ዙፋን ላይ ያወጣዋል፤ ሌላው የጦር አዝማች ደግሞ የኔን ምርጫ ካላነገስኩ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ይነሳል፤ ባንጋሾች መካከል የሚደረገው ፉክክር መዲናይቱን ባንዴ ወደ ፍርስራሽ እና ያስከሬን ክምር ይቀይራታል::
የቀድሞ ሰዎች እንዲህ አይነቱን ብሄራዊ አደጋ ለመቀነስ የፈጠሩት “ዘዴ “ የንጉስን ሞት መሰወር ነበር ፤ የንጉስ ሞት ቀርቶ ህመሙ እንኳ ለህዘብ ይፋ አይደረግም፤ በዘመነ መሳፍነት ጊዜ ፥ የየጁው ራስ አሊ ሲሞት ፤ አንድ አሳባቂ ( የዘመኑ ፓፓራዚ) ወሬውን አሾለከው፤ ወድያው የረጋው አገር መላወስ ጀመረ፤ ጉዳዩ ያሳሰባት አንዲት አልቃሽ እንዲህ ብላ ገጠመች፥
“ እሻ እሻ ነው እንጂ የእስራኤልን ሞት
እንዲያልቅሰው አሊን ለምን ቀበሩት “
“ እሻ እሻ “ ማለት ዝም በሉ ጸጥ በሉ ማለት ነው ፤ በዘመኑ የንጉስ ወገን ነን የሚሉ ሰዎች ዘራቸውን ከሰለሞን ስለሚመዝዙ “ እስራኤል “ በሚል የወል ስም ይታወቃሉ፤
በግጥሙ መስመር ላይ ያለው ህብረቃል “ እንዲያልቅሰው “ የሚል ነው፤ ሰሙ “ እንዲህ አልቅሰው “ ሲሆን ወርቁ “ ሰው እንዲተላለቅ” የሚል ትርጉም አለው ፤
ባጭሩ አልቃሺቱ፥
“ ህዘብ እንዳይተላለቅ
የንጉስ ሞት ይደበቅ “ ማለት ነው የፈለገችው ፤
ከጥንት እስከዛሬ አገረ -መንግስታችን የሚቆመው ባንድ ሰው ትከሻ ላይ ነው ፤ መሪ ሲታመም አገር ይታመማል፤ መሪ ሲሞት አገር በጥቂቱ ይሞታል፤ ይህንን መለወጥ የሚቻለው እንዴት ነው? የማይሞቱ ተቋሞችን በመገንባት ፤ የማይታመሙ ህጎችን በመመስረት? ወይስ ሌላ መላ አለ?