>

ግራ በገባው ሕገ መንግስት ግራ የምትጋባ ሀገር፤ ክልልም - ሀገርም...!!! ( ያሬድ ሀይለማርያም)

ግራ በገባው ሕገ መንግስት ግራ የምትጋባ ሀገር፤ ክልልም – ሀገርም…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ክልል ብቻ ሳይሆን አገር የመሆንም መብት የሚፈቅድ ሕገ-መንግስት ይዞ የወላይታን፣ የጉራጌን እና የሌሎች ሕዝቦችን ክልል የመሆን ጥያቄ መግፋት ትክክል አይሆንም። ጥያቄያቸው በሕጉ አግባብ መልስ ሊያገኝ ይገባል። አለያም ሕገ-መንግስቱን እና የአገሪቱን አወቃቀር በአፋጣኝ ትኩረት ሰጥቶት እንደገና ይከለስ።

ጥያቄያቸው በቂ ሕገ-መንግስታዊ መሠረት ያለው እና የመብት ጥያቄም ነው። የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 እንዲህ ይነበባል፤ “በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱት ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው።” በማለት ይደነግጋል።

ለእኔ ከስር ከመሠረቱ ችግሩ የሚጀምረው ከሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 8 እና አንቀጽ 39(5) ነው። አንቀጽ 8 ማነው ብሔር፣ ማነው ብሔረሰብ፣ ማነው ሕዝቦች የሚለውን በግልጽ ሳያስቀምጥ እና መስፈርቱ ምን እንደሆነም ሳያብራራ በጥቅሉ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ብሎ ያልፋል። በተለይም አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 5 እንዲሁ “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ” ማለት ብሎ የወል የሆነ እና ግልጽ ያልሆነ አንዳቸው ከሌላቸው በምን እንደሚለዩና መስፈርቱም ምን እንደሆነ የማይገልጽ ትርጉም ሰጥቶ ያልፋል። በመሰረቱ ብሔርና ብሔረሰቦች የሚሉት ቃላቶች ግራ የሚያጋቡና ትክክለኛ የቃላቶቹን ትርጓሚ በሳተ መልኩ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ ሥራ ላይ የዋሉ ናቸው። ለእኔ ሁሉንም “ሕዝብ” የሚለው ቃል ይገልጻቸዋል። አማራም ሕዝብ ነው፣ ኦሮሞም ሕዝብ ነው፣ ጉራጌም ሕዝብ ነው፣ ሲዳማም ሕዝብ ነው፣ ወላይታም ሕዝብ ነው፣ ኮንሶም ሕዝብ ነው፣  ሌሎቹም እንዲሁ። በሕዝብ ቁጥር ብዛት እየሰፈሩ እገሌ ብሔር ነው፣ እገሌ ብሔረሰብ ነው፣ እገሌ ሕዝብ ነው እያሉ ቃል እየለያዩ መስፈሪያ ማስቀመጥ በሕዝቦች መካከል የመብት መበላለጥን ብቻ ሳይሆን የዜግነት ደረጃንም ይፈጥራል። አንዱ ሕዝብ በማንነቱና በቁጥሩ ክልል ሆኖ የሚያጣጥመው መብትና ጥቅም ካለ እና አነስተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ደግሞ ያንን መብትና ጥቅም የማያገኝ ከሆነ የዜግነት ደረጃ ፈጠርን ማለት ነው።

ስለዚህ፤ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሲዳማ፣ አፋር፣ ሶማሌ ክልል ከሆኑ ሌሎቹ ሕዝቦች የክልልነት ጥያቄ ሲያነሱ ለምን ግራ ይገባናል? ክልል መሆን ምን ጥቅም አለው? የለውም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር እዚህ ከተደረሰ በኋላ ፋይዳ የለውም። ጥቅም ከሌለው ሁሉም ክልሎች ይፍረሱና አገሪቱ በሌላ አይነት ፌደራሊዝም ትዋቀር። በሕገ መንግስት የተረጋገጠን መብት መከልከል ግን አላስፈላጊ የፖለቲካ ውጥረትን ይፈጥራል።

ሕገ-መንግስቱና የፌደራል አወቃቀሩ ቶሎ ይሻሻል፤ ካልሆነም የሁሉም ሕዝቦች ክልል የመሆን ጥያቄ በአግባቡ ይስተናገድ።

Filed in: Amharic